የእለት ዜና

የ“አሻራ” አተካራ

Views: 270

“አሻራ” በሚል ርዕስ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መፀሐፍ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተዘጋጅቶ ለህትመት መብቃቱ የቃላት አተካራ ፈጥሮ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን በፊትም ሆነ በኋላ መጻህፍትን በራሳቸውና በብዕር ስም አውጥተው ለገበያ ቢያቀርቡም የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ያሳተመው አካል ማንነት ነው። ከ2010 የስልጣን ዘመናቸው ጀምሮ ያደረጉትን የመድረክ ንግግር በመጸሐፍ መልክ ያወጣው የመንግስት የሚዲያ ተቋም ገለልተኛ መሆን ሲጠበቅበት፣ ምርጫ በተቃረበ ሰሞን የአንድ ተወዳዳሪ አመራርን ንግግር በመፀሓፍ መልክ በሕዝብ ሓብት ማሳተሙ መነጋገሪያ ሆኗል።

የህትመቱ አትራፊነትና አዋጭነተ ወይም የመታተሙ ጠቀሜታ ሳይሆን፣ በዚህ ወቅት የማንን ታሪክ ማን ለማስተዋወቅ ሞከረ የሚለው ነበር የመከራከሪያው ጭብጥ። የመንግስት የሚዲያ ተቋም እንደመሆኑ ከፖለቲካ ተፅእኖ ገለልተኛ ሁኖ ሁሉንም ያማከለ ፍትሓዊ ስራ ይሰራል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ይህን የምርጫ ቅስቀሳ የመሰለ ተግባር መፈጸሙ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የኢዜማው አመራር አንዷለም አራጌ፣ የባልደራሱ እስክነድር ነጋና የልደቱ አያሌው መፅሐፎች ለህትመት ሲበቁ ለማስተዋወቅ እንኳን ያልሞከረው ይህ ተቋም፣ ስልጣን ላይ ያለን መሪ ለማሞካሸት ንግግሮቹን መርጦ ማውጣቱ ብዙዎችን አስገርሟል። ለወደፊቱ የሌሎችን በተመሳሳይ ያስተዋውቅ ይሆን ብለው እንደማያደርገው እያወቁ በማህበራዊ ሚዲያ ለማሳጣት የሞከሩ ነበሩ።

እንደማንኛውም ሚዲያ ገለልተኛ ሆኖ መዘገቡን ትቶ ይህን ማድረጉን የተቹ ግለሰቦች መጸሐፉ ላይ የወጣው ሙሉ ንግግራቸው እንደማይሆን ገምተዋል። ለወደፊት ሲነበብ ከአንድ ንግግር ላይ ተመርጦ የወጣ ካለ የመቀስቀስ አላማ እንዳለው በራሱ ያስረዳል ብለዋል። በተቃራኒው ይህ አይነት የማዳነቅ ስራ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመንም የተፈጸመ ስለሆነ አይገርምም የሚሉ ተደምጠዋል። ሌሎች ደግሞ ይህ ተግባር ከአመታት በፊት ተፈፅሞ ቢሆን አይደንቀንም በማለት ተቋሙ እንዳልተለወጠ አመላካች ነው ይላሉ።

የፕሬስ ድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መጸሐፉን ያሳተሙት ለቀጣይ ትውልድ ትምህርት እንዲሆን ታስቦ መሆኑን ቢናገሩም፣ በትምህርት ሚኒስቴር ስራ ገቡበት ከሚል ትችት አላዳነም። የንግግራቸው አስተማሪነት የታመነበት አሁን ምርጫ ሲድርስ ይሁን አይሁን ባያብራሩም በመመረቂያ ፕሮግራሙ ላይ ስለሚዛናዊነታቸው ለመናገር ሞክረዋል። ከማን ጋር አመዛዝነዋቸው እንደሆነ ሳይናገሩ በድርጅቱ የታተሙ ሌሎች መፃሕፍት መኖራቸውን ርዕሳቸውን ሳይናገሩ በደምሳሳው ማሳወቃቸው ትዝብት ላይ እንደጣላቸው የተናገሩ አሉ።

የሚዲያ ተቋሙን ተግባር የተመለከቱ ከቀድሞ አመለካከቱ አለመላቀቁን በማንሳት ወገንተኝነቱን ለመሸፋፈን ሳይሞክር በይፋ ማውጣቱ አስገርሟቸዋል። የድረጅቱ ኃላፊ ምርጫው ፍትሓዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እንወጣለን ቢሉም ፍትሐዊነት እንዲህ ነው ወይ በሚል አስተችቷቸዋል። ተቋሙ 80 አመት ሆኖኛል እያለ የአዲስ ዘመንን ታሪክ ያላግባብ ከሚሻማ የራሱን ታሪክ ቅድሚያ ማሳወቅ ይጠበቅበት ነበር በማለት የወቀሱትም አሉ። ያም ተባለ ይህ የሚዲያ ተቋም እንደመሆኑ ከግራና ከቀኝ ተባለውን ሰምቶ እንደዳኛ ባይፈርድም፣ ለውሳኔው የሚሆንን ያልተዛባ መረጃን አጠናቅሮ እንዲያቀርብ ይጠበቃል። ነገር ግን አሁን እንዳደረገው የአንድ ተመራጭን ንግግር አሳትሞ እያሞካሸ አስመርቆ ሌሎችን ማግለሉ ፍትሓዊ ሊያስብለው ቀርቶ የሚዲያ ተቋም አያስብለውም። ምርቃቱ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነኑኝ” ከሚለው ብሂል ሊማሩ እንደሚገባ በርካቶች ይስማማሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com