የእለት ዜና

የኮቪድ ክትባት ሥርጭት በአፍሪካ

Views: 77

በአፍሪካ የክትባቱን ሥርጭት ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። የዚህ እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም ለሁሉም የሰው ልጅ ህይወቶች እኩል ዋጋ በመስጠት የአፍሪካን ምጣኔ ሀብት በፍጥነት ከችግር እንዲወጣ ማገዝ ነው። በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ኮቪድ-19 ክትባት ልማትና ተደራሽነት ዕቅድ የአፍሪካን ሕዝብ 60% ወይም 750 ሚሊዮን አፍሪካውያንን፣ ከተቻለ አጠቃላይ የአፍሪካ ጎልማሶችን፣ የኮቪድ 19 ክትባትን እንደ አውሮጳውያን የቀን አቆጣጠር ከ2022 መገባደጃ በፊት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ነገር ግን፣ እስካሁን በአህጉር ደረጃ ቢያንስ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ማግኘት የቻለው ከጠቅላላው ሕዝብ ከ 2% በታች ነው።

ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በአጠቃላይ 1.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ህይወትና የኑሮ ደረጃን መታደግ የሚችል፣ እንዲሁም የተጎዳውን የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብት በፍጥነት ከችግር እንዲላቀቅ የሚያደርግና በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር የትብብር ስምምነት ከአፍሪካ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ጋር መፈራረሙን አዲስ ማለዳ የደረሳት መረጃ ያሳያል።

“ህይወትንና የኑሮ ደረጃን የመታደግ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ቃል የተደረሰው ስምምነት ከ50 ሚሊዮን በላይ ክትባቶችን ማሰራጨት፣ በአህጉሪቷ ለሚኖሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን ማዳረስ፣ የኮቪድ 19 ክትባት በአፍሪካ ለማምረት የሚያስችል መሰረት መጣልና የአፍሪካን ሲዲሲ ማጠናከር የመሳሰሉ ሥራዎችን ያቀፈ እቅስቃሴ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ የደረሰው መረጃ ያሳያል።

የተፈረመው አዲሱ አጋርነት በዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ክትባት ልማት (COVAX) ፣ የአፍሪካ የኮቪድ 19 ክትባት ፍለጋ ቡድን እና በዓለም ዙሪያ ለአፍሪካ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ የሚሰሩ አካላትን የእስከዛሬ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል ስምምነት ነው።

ለአፍሪካ የቀረበው የኮቪድ-19 ክትባት መጠኑ በጣም ዝቅተኛ ነገር ግን የመግዣ፣ የማጓጓዣና ክትባቱን የማስፈጸሚያ ዋጋው ደግሞ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ‹‹ኹሉን-ዓቀፍ ተደራሽነት ያለው የክትባት ስርጭት ሥርዓትን ማረጋገጥ እና አፍሪካ የራሷን ክትባት እንድታመርት አቅሟን ማሳደግ ለአፍሪካ መልካም ሥራ ብቻ ሳይሆን ከወርርሽኙ ለመውጣትና የወደፊቱን የጤና ዋስትና ለማረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ ነው›› ሲሉ የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ጆን ንኬን ጋሶንግ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

“ይህ ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር የተደረገው ሥምምነት በአፍሪካ አዲስ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ጉልህ እርምጃ ነው፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ትልቅ ዓላማ ያለውን ይህን ታሪካዊ እንቅስቃሴ ቢቀላቀሉ በደስታ እንቀበላለን” ብለዋል።

አፍሪካ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በ2020 ከ25 ዓመታት በኋላ ትልቅ የኢኮኖሚ ችግር ተጋርጦባታል። የአፍሪካ ልማት ባንክ የአህጉሪቱ የኹለት አስርት ዓመታት የድህነት ቅነሳ ትግሏ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት በመስተጓጎሉ 39 ሚሊዮን አፍሪካውያንን በ2021 ወደ ከፋ ድህነት ሊገቡ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል። ከፍተኛ የክትባት ዘመቻ በማድረግ የአህጉሪቷን ምጣኔ ሀብት ዳግም እንዲያንሰራራ ማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው።

የአፍሪካ ሲዲሲ የትብብር ማዕቀፍ (PACT) በአህጉሪቱ ውስጥ ከ47 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ ምርመራዎች ማድረግ ችሏል። በዓለማችን ለኮቪድ 19 ምክንያት የሆነው SARS-CoV-2 ቫይረስ እስካሁን 170 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን ፣ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ነፍሶችን ነጥቋል። በአፍሪካ የተመዘገበ የኮቪድ ተጠቂዎች ቁጥር ከ4.8 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን የሟቾቹም አህዝ ከ130ሺህ ዘሏል።
ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር የተደረገው ስምምነት በአራት ቁልፍ አቅጣጫዎች ላይ ያተኩራል።

የመጀመሪያው የኮቪድ 19 ክትባትን ግዢን የተመለከተ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት ቢያንስ ለ 50 ሚሊዮን ሕዝብ ውጤታማና አስተማማኝ ክትባት በመስጠት በአህጉሪቱ ውስጥ ያለውን የክትባት ሽፍን ሰፊ ልዩነት ማጥበብ ነው።

ሁለተኛው የአፍሪካ የኮቪድ 19 ክትባትን ማበልፀግ ነው። የአፍሪካ ሲዲሲ የአባል አገራትን ጤና ሚኒስትሮችንና አጋር አካላትን ያማክራል። ትክክለኛ ፍላጎትን በመለየትና በማሳወቅ ይህ ተነሳሽነት ውጤታማ የክትባት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል። ይህም የክትባቱ ግዢና ትራንስፖርት፣ አስፈላጊ ግብዓቶችንና ተጨማሪ ድጋፎች፣ እንዲሁም አገራዊ ሎጀስቲኮች፣ የኮቪድ ክትባት መስጫ ማዕከላትን ማሳደግና የክትባቱን ሽፋን ከፍ ማድረግ ያካትታል። ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ማሕበረሰቡን አሳታፊና የኮቪድ 19 ክትባትን ለማሳደግ ማስተዋወቅ፣ እንዲሁም ክትባቱን ለመውሰድ ያለውን ቸልተኝነት መግታት፤ የክትባቱንት አወሳሰድ ጥንቃቄ መከታተል፣ መገምገምና የማስተማር ሥራን መምራት፤ የዘረ-መል ሂደትን በመከተል የሚኖረውን ተለዋዋጭ ሁኔታ መለየትና ማወቅ፤ ለብሔራዊ የክትባት መርሃ-ግብር ቴክኒካዊ ድጋፎችን መስጠት ይገኙበታል።

በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ በአፍሪካ የኮቪድ 19 ክትባትን የማምረት ሂደትን ማስፋፋት ነው። ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሺኝ አፍሪካ ክትባትን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን ለውስጣዊ ፍጆታ የማምረት አቅምን ለማጠናከር አስችሏል። አፍሪካ የኮቪድ 19 ክትባት ለማምረት መካከለኛ የተካነ የሰው ኃይል ማብቃት እንዲሁም የላብራቶሪ ምርመራ ማድረግን ያካትታል። በአራተኛ የተቀመጠው የአፍሪካን ሲዲሲ ማጠናከር ነው። የአፍሪካ ሲዲሲ በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት የአህጉሪቷ ሕብረተሰባዊ የጤና ፍላጎትን ለማሟላት የተቋቋመ ቴክኒካዊ ተቋም ነው። ይህ እንቅስቃሴ የአፍሪካ ሲዲሲ በአህጉሩ የትኛውም ክፍል ያለን አቅምና ታሪካዊ የሀብት እንዲቆጣጠር፣ ቀጠናዊ የክትባት ልምዶች እንዲያሳደግ፣ ለወደፊቱ የጤና ቀውስ እንዲዘጋጀ እና የሕብረተሰብ ጤና ማሻሻያን መምራት እንዲችል ያግዘዋል። በእያንዳንዱ አገር ሁለገብ የሆኑ አርቲስቶችንና አካባቢያዊ አጋራትን በማስተባበር የአፍሪካ ሲዲሲ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ ይሠራል።የጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር መሥራቱ ተገለጸ

የጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎቶችን ለማጠናከርና ወደሥራ ያልተመለሱ የጤና ተቋማትን ለመመለስ ከኤጀንሲዎች፣ከትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እና ከሰብዓዊና የልማት አጋሮች ጋር የሚያከናውኗቸዉ ሥራዎች እንዳሉ ተገለጸ፡፡ በክልሉ በአጠቃላይ ከሚገኙት ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች በአሁኑ ወቅት 46.5% የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
በየጤና ተቋማቱ መድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያ ለሟሟላት በተደረገው ጥረት የጤና ሚኒስቴር ከመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እንዲሁም ከሌሎች ተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ግምቱ ከብር 3.8 ሚሊዮን በላይ የመድኃኒትና የግብአት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና ኤጀንሲዎች ለተለያዩ የፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል በድምሩ ብር 2 ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡
በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት በነጻ እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህን ሥራ ለማጠናከርም ቀደም ብለው ከነበሩት በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ 80 ሐኪሞች፤25 ነርሶች እንዲሁም 15 አዋላጅ ነርሶች (በድምሩ 120 የጤና ባለሙያዎች) ቅጥር በጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ተከናውኖ በሁሉም የተፈናቃይ ማዕከላት በመመደብ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ከፍተኛ የተፈናቃይ ቁጥር ባለበት 17 መጠለያ መለስተኛ ክሊኒክ እንዲቋቋም ተደርጓል። ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን አስፈላጊውን ህክምናና ድጋፍ መስጠት እንዲቻል በድምሩ 57 የአእምሮ ጤናና የሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች በስድስት ከተሞች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com