የእለት ዜና

የቅስቀሳ ፖስተሮች ስለምርጫው ምን ይናገራሉ? ክፍል 2

Views: 97

የምርጫ ቅስቀሳ ከሚካሄድባቸው መንገዶች መካከል የተፎካካሪ ፓርቲ የቅስቀሳ ፖስተሮችና ባነሮች በዘንድሮው ምርጫ ትልቁን ቦታ እየያዙ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበዙ ስለመጡት ፖስተሮች ይዘት እንዲሁም በየአደባባዩ ስለተሰቀሉ ባነሮች ተመሳሳይነት ከአላማቸው ጋር በማነጻጸር ግዛቸው አበበ ያስተዋለውን ቀጣይ ክፍል እንዲህ ያስነብበናል፡፡

ክፍል 2
የአንድን ግለሰብ ፎቶ በየቦታው በመገተር ወደ ምርጫ የገባው ሦሥተኛ ፓርቲ ባልደራስ ነው። ባልደራስ የአቶ እስክንድር ነጋን ፎቶ በየፖስተሩና በየባነሩ ለጥፎ እያሳየ ነው። ባልደራስ የተጠቀመበት የአቶ እስክንድር ምስል እጁ ለቦክስ የተጨበጠ መስሎ የተንጠራራበት ነው። አቶ እስክንድር ነጋ ወደ እስር ቤት ከመግባታው በፊት በየቦታው ሲገኙና በየመንገዱ ሲያልፉ ለሚያጨበጭቡላቸው ደጋፊዎቻቸው ምላሽ የሚሰጡት ለቡጢ የተዘጋጀ የመሰለና የተጨበጠ እጃቸውን በማወዛወዝ ነው። የአቶ እስክንድር የተጨበጠ እጅ የፓርቲው አርማና የምርጫ ምልክት መደረጉንም ብዙዎች ይገምታሉ። ብዙዎቹ የባልደራስ ሰዎች አቶ እስክንድር ነጋን ታላቁ እስክንድር ብለው ሲጠሩ ይሰማሉና የሰዎቹ ግምት ትክክለኛ ይመስላል።

አቶ እስክንድር ነጋ ባልደራስ የሚባለውን ስብስብ የመሰረቱትና ኢትዮጲስ የምትባል ጋዜጣ ማሳተም የጀመሩት ከእስር ቤት እንደወጡ ብዙም ሳይቆዩ ነው። አቶ እስክንድር የሰዎችን ሕሊና አቁስሎ፣ መንፈስን አዳሽቆና አካልንም አጎሳቁሎ ከሚለቀው ወይም ከሚገድለው ከሕወሐት ‘ማረሚያ ቤት’ የወጡ ሰው ናቸውና ጋዜጣዋንና ባልደራስን ኢሕአዴጋውያኑን መዝለፊያና የብቀላቸው ማራመጃ አድርገው ተጠቅመውባቸዋል። አቶ እስክንድር በስነ-ልቦና እና በስነ-አዕምሮ ባለሙያ መንፈሳዊ ማሳጅ ሳይደረግላቸው ወደ ፖለቲካው ዓለም መግባታቸው ባልፈረጠመ ጡንቻና ባልዳበረ አካላዊ ቁመና ወደ ፕሮፌሽናል ቦክስ ውድድር የገቡ ሰው አስመስሏቸዋል። አቶ እስክንድር ነጋ ገና ከእስር ቤት እንደወጡ አክራሪ ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን ዘላፊ ሆነው ከለውጡ መሪወች በተጻራሪ አቅጣጫ ስለቆሙ በብዙዎች ደጋፊወቻቸው ዘንድ እንደ አዋቂና እንደ ነብይ አስቆጥሯቸዋል። የአሁኑ ውድቀት እንደሚመጣ አስቀድመው ስላወቁ ግትር የሆነ የመቃወም አቋም እንዲይዙ አድርጓቸዋል ሲሉ ያሞካሿቸዋል። ነገር ግን ይህን መሰሉ አክራሪና ብልጠት የጎደለው አቋማቸው በመጀመሪያ ጋዜጣቸውን አንባቢ አሳጥቶ ከሚወዱትና ጥሩ ልምድ ካዳበሩበት የጋዜጣ ንግድ ሲያሰናብታቸው፣ ቀጥሎ ደግሞ እሳቸውን ለእስር ቤት አብቅቷቸዋል። ፓርቲያቸው በአብዛኛው በተወሰነ የዕድሜ ክልል በታጠሩ አባላት መሞላቱም ሌላው የውድቀት ምልክት ነው። ባልደራስ የወጣት ማሕበር እንዲሆን የታሰበበት ስብስብ አይደለምና።

አቶ እስክንድር ነጋ ሕገ-ወጥ የተባሉ ቤቶችና መጠለያወች በፈረሱ ቁጥር በየቦታው እየተገኙ አሳቢና ተቆርቋሪ መሆናቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። ነገር ግን አቶ እስክንድር ቤት ሰርተው ለምስኪኖች ማደል ባይጠበቅባቸውም፣ ሕገ-ወጥ ቤቶችና መጠለያወች በየቦታው ሲሰሩ ሕግን ለማስከበር ሳይንቀሳቀሱ ወይም ሰዎች ሕግን እንዳይጥሱ ለመምከር ምንም ዓይነት ሙከራ ሲደርጉ አልታዩምና እንቅስቃሴዎቻቸው አስመሳይ ድራማዎችና እሳቸው የአአ መሪ ቢሆኑ በጸጥታ ኃይላቸው ራሳቸው የሚያስፈጽሙትን ድርጊት ለታይታ ሲሉ እየተቃወሙት መሆኑን ብዙዎች ገምተዋል። አቶ እስክንድር ነጋ የፈራረሱ ቤቶችንና መጠለያዎችን ከጎበኙ በኋላ ‘ለፈረንጆች እንናገራለን’ ሲሉ የተሰሙበት ጊዜ አለ። የአቶ እስክንድር ነጋ ሌላው ደካማ ጎን በፈረንጆች ከልክ ባለፈ መጠን የሚመኩ ሰው መሆናቸው ነው። የሕወሐት/ኢሕአዴግን መቶ-በ-መቶ የምርጫ ድል የተቀበሉትን፣ እሳቸውን የመሳሰሉ ስርዓትን ከመቃወም ያለፈ ድርጊት ያልፈጸሙትን ሰዎች በማሰርና በማሳደድ ከሚታወቀው የሕወሐት/ኢሕአዴግ መንግስት ጋር ሲሞዳሞዱ የምናውቃቸውን ፈርንጆችን፣ ነገሮችን ሁሉ ከራሳቸው ጥቅም አንጻር የሚያዩትን ፈረንጆችን መከታ ማድረግ ተገቢነት ያለው አይደለም።

አቶ እስንድር ነጋ የአንድ ወቅት ፋሽን የነበረውን ለምስኪን ሰዎች ዘይትና ዱቄት እየተሸከሙ የማደል ስራ እየሰሩ ተመሳሳዩን ስራ ሲሰሩ ከነበሩት ከጠቅላይ ሚ/ሩና ከባለቤታቸው ጋር፣ በወቅቱ የአአ ምክትል ከንቲባ ከነበሩት ከአቶ ታከሉ ዑማ ጋር ፉክክር ገጥመው ታይተዋል።

አቶ እስክንድር ነጋ በሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን ወደ እስር ቤት ከመግባታቸው በፊት የተለያዩ ጋዜጦችን በባለቤትነት እያሳተሙ የነበሩ እንጅ ፖለቲከኛ ነበሩ የሚያስብል እንቅስቃሴ አልነበራቸውም። አቶ እክንድር ነጋ አንድ ጋዜጣ ወይም መጽሔትን ዕለታዊ ወይም በየሁለትና በየሦሥት ቀን እያሳተሙ ተገቢ በሆነ መንገድ የሚዲያ ስራ ከመስራት ይልቅ በየሳምንቱ ሦሥት ዓይነት ጋዜጦችን (አስኳል፣ ምኒሊክና አስኳል) እያሉ እያሳተሙ፣ አንዱን ዜና ወይም አንዱን ዘገባ በተለያየ አርእስትና በተለያየ መንገድ ሁለቴና ሦሥቴ ለንባብ እያበቁ በሚዲያ የነገዱ ሰው ናቸው የሚሏቸው ጥቂቶች አይደሉም። እናም አቶ እስክንድር ታላቅ ነጋዴ ናቸው ወይስ ታላቅ ፖለቲከኛ ብሎ ለመጠየቅ የግድ የሚል አቋም ያላቸው ሰው ናቸው።

አቶ አስክንድር ባልደራስን ሲመሰርቱት የሲቪክ ማሕበር ይሁን ዕድር መሰል ስብስብ ግልጽ ያልነበረ፣ በፖለቲካ ፓርቲነት ሳይመዘግብ የተወሰነ ጊዜን የቆየና ብዙዎችን ያወዛገበ መሆኑ ሊታወስ ይገባል። ስለዚህ አቶ እስክንድር እንደ ታላቅ ፖለቲከኛ እንደ ታላቅ የፖለቲካ ድርጅት መሪ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ መሪነት የካበተ ልምድን፣ ተግባራዊ ተሞክሮንና በትዕግስት የታጀበ ብልሃትን የሚጠይቅ ነው። እጅን በየደረሱበት እንደ ሰነፍ ገበሬ ጅራፍ ማወናጨፍ፣ ዘለፋና ቁጣን የዘወትር ስራ ማድረግ እንኳን ለብልጽግና/ኢሕአዴግ ስርዓት በዳበረ ዲሞክራሲ ውስጥ ለሚኖሩ ፓርቲወች ግንኙነትም የሚበጅ አይደለም። አቶ እስክንድርና አንዳንድ ባልደረቦቻቸው ሚዲያ ላይ ሲቀርቡና በስብሰባወች መድረክ ላይ ሲገኙ ከግጥሚያው በፊት ለቃለ ምልልስ አብረው የቀረቡ ቦክሰኞችን ነው የሚመስሉት።

ቦክሰኞች ለቃለ ምልልስ መቅረባቸውንና የድብድቡ ጊዜ ገና መሆኑን እያወቁ በቃላት ከመዛዛት ቡጢ እስከ መሰነዛዘር ይደርሳሉ፣ ለያዥ ለገናዥ እስኪያስቸግሩ አፍንጫውን ካልሰበርኩት ብለው የተገኙበትን ቦታ ትርምስምሱን ያወጡታል። አቶ እስክንድርና አንዳንድ ባልደራሶችም እንደዚሁ ናቸው። አቶ እስክንድር ነጋ የካራማራን ድል ለማክበር በሚል ምክንያት በድላችን ሃውልት በተገኙበት አንድ አጋጣሚ ከአቶ እስክንድር አጋሮች እንዱ ከፖሊስ ጋር ለመደባደብ መጋበዙና የፖሊሱን እንገት አንቆ ካልደበደብኩት ማለቱ የሚረሳ አይደለም። ብዙዎቹ የአቶ እስክንድር ነጋ አጋሮች ሚዲያ ላይ ሲቀርቡም ጭምር ከረር ያለ ቃል ማሰማታቸውና የተቀሰረ ዕጣታቸውን ዛቻ የሚሰነዝሩ ይመስል እያወዛወዙ መታየታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። አንዳንድ የቴሌቪዥንና የዩቲዩብ ሚዲያዎች አንድን ብሄር በጅምላ ለማሳደብ ማንን መጥራት እንዳለባቸው በሚገባ አውቀው ጥሪ ያረጉ ነበረ። ከነዚህ ተመራጭ ስሜታዊና አጉል በሆነ ድፍረት በማንም ላይ ያሻቸውን ከሚናገሩ ሰዎች መካከል አቶ እስክንድር ነጋና አርቲስት ሃጫሉ ይገኙበታል። አርቲስት ሃጫሉ ወንጀል በተፈጸመበት ዕለት ዋዜማ ላይ እና አቶ እስክንድር ነጋ ኢሬቻ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት በመሰሪ ሚዲያወች ላይ ሲጋበዙ ተገኝተው የተናገሯቸው ነገሮች ለዚህ አብነቶች ናቸው።

አቶ እስክንድር ነጋ ዘወትር ጨብጠው የሚያወዛውዙትን እጃቸውን በማንም ላይ ሳያሳርፉ እጃቸውን ይዘው ወደ ማረፊያ ቤት ገብተዋል። እጃቸውን ግን በየጎዳናውና በየአደባባዩ ከሚታየው ምስላቸው ጋር፣ የፓርቲው ዓርማና የምርጫ ምልክት ማሳወቂያ ሆኖ እየታየ ነው።
ግዛቸው አበበ በኢሜል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com