የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ማንቂያ ደወል!

Views: 132

መንግሥት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ወታደራዊ ሕግ የማስከበር እርምጃ ከጀመረ አንስቶ በህወሓት ደጋፊዎች ጠንሳሽነት ምዕራባውያኑ ከመንግሥት በተቃራኒው እንዲቆሙ ተደርገዋል፡፡ የግድቡን ኹለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ልናከናውን ጥቂት ጊዜ ሲቀር አሜሪካ በውስጥ ጉዳያችን በመግባት ማዕቀብ መጣሏ አይዘነጋም፡፡ ከማዕቀቡ ጋር በተገናኘ ምን መደረግ እንዳለበት ታዬ ብርሃኑ(ዶ/ር) ሃሳባቸውን እንዲህ አስፍረዋል፡፡

የረጅም ጊዜ የነጻነት እና የሥልጣኔ ታሪክ ባለቤት፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ ብሎም ለሠላም እና ለወዳጅነት የቆመች ለምለሚቷ አገራችን እያልን የምንዘምርላት ኢትዮጵያን ስሟን አንስተን አንጠግበውም። ሰንደቅ ዓላማዋ በሠላሙም፣ በጦር ሜዳውም፣ በስፖርት ዓለሙም የፍቅር ጮራ የሚፈነጥቀው፣ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር የዘረጋችው፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ስሟ ገኖ የሚገኘው አገራችን ከውስጥና ከውጭ ቡርቦራ፣ ወረራ፣ ትንኩሳና ክህደት ተላቃ አታውቅም። አገራችን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ለተደጋጋሚ የውጭ ደባ እና ወረራ የተጋለጠችው የርስበርስ ጦርነት ሲኖር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በማይናወጥ አቋሙ በአንድነቱ ጸንቶ ባይቆይ እና መራራ መስዋዕትነት ባይከፍል ኖሮ የአገሩን ህልውና ባጣ ነበር።

የሰሞኑ ዓብይ ክስተት አሜሪካ በአገራችን የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ችግርና ከግድቡ ጋር በተገናኘ በኢኮኖሚ እና በጸጥታ ጉዳይ የምታደርገውን ትብብር ትታ ዕቀባ ማድረጓና በተወሰኑ የአመራር አባላት ላይ የጉዞ ዕገዳ መወሰኗ ነው። ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ አሳዝኗል። በአገር ውስጥና በውጭ የተቃውሞ ሰልፎችን አስከትሏል። ውሳኔው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳዘነው በሚያሳድረው ተጽዕኖ ሳይሆን በዋናነት በአንድ የሰለጠነ፣ኃያል እና ወዳጅ አገር የተወሰደ በመሆኑ ነው። ይህ አይነቱ ውሳኔ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካና በአውሮፓ አንዲተገበር በህውሓት ቀንበር ውስጥ በነበሩበት ረጅም ጊዜያት የታገሉለት ጉዳይ ነው። ህውሓት በፈጸማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ኢትዮጵያውያን ለኢሕአዴግ መንግሥት የሚሰጠው ዕርዳታ እንዲቆም፣ የጉዞ ገደብ እንዲደረግ፣ አመራሮቹ የዘረፉት ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አቅርበዋል። መሪዎቹ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ሲመላለሱ ይደርስባቸው የነበረው ተቃውሞ ምነው ባልመጣን ያሰኛቸው ነበር።የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ ያቀረባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘገባዎችም ጉልህ ምስክሮች ናቸው። ይሁንና ውሳኔው ለሚገባው ሳይሆን ለማይገባው መዋሉ ትክክል አይደለም።

በሕዝብ ግፊት ከመንበረ ሥልጣኑ የተወገደው ህውሓት፣ በራሱ ሙሉ ተሳትፎ በድምጽ ብልጫ ቦታውን ለቆ በኩርፊያና በማንአለበኝነት በትግራይ መሽጎ በመንግሥት፣ በሕዝብ እና በአገር ያደረሰው ግፍና መከራ ለአሜሪካ ስውር አይደለም። ህውሓት መሰል ዓላማ ካላቸው ጋር ያካሄደው ጎሣ ተኮር ደባ፣ ሴራና ድርጊት ለጆሮ የሚቀፍ ነው። በራሱ ወገን በብሔራዊ ጦር ላይ የወሰደው ዘግናኝ የግፍ እርምጃ፣ በባህር ዳር፣በጎንደር እና በሉዓላዊት አገር ዋና ከተማ አስመራ ላይ ያስወነጨፈው ሮኬት በምንም መመዘኛ ከሕግ ተጠያቂነት አያድነውም። በዚህም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ ማስከበር እርምጃ በቡድኑ ላይ መውሰዱ አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ አይደለም። ከዚህ አኳያ የአሜሪካ መንግሥት የወሰደው ውሳኔ፣ የኹለቱን አገሮች የረጅም ጊዜ የወዳጅነት ግንኙነት እና አሜሪካ በዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆዎች መከበር ያላትን ግንባር ቀደም ሚናዋን የሚመጥን አይደለም። ውሳኔው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚደፍር፣ የተባበሩት መንግሥታትን እና የአፍሪካ ሕብረትን አንድ አገር በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርሆዎችን የሚጻረር ነው።

ከውጭ ግንኙነት አንጻር፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ሠላም ፈጥረው ጠላትን በጋራ ለመከላከል የሚያደርጉት ትብብር ለቀጣናው ሠላምና ጸጥታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ከኢትዮጵያ መንግሥት የጣልቃ ገብነት ችግር ባልተነሳበት ሁኔታ የአሜሪካ መንግሥት የኹለቱን መንግሥታት ሉዓላዊነት በሚነካ መልኩ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ መፈለጉ ተገቢ አይደለም። ኹለቱ አገሮች በሕዝቦቻቸው መልካም ፈቃድ እንኳንስ መተባበር፣ በፌዴሬሽን ወይም በኮንፌዴሬሽን ብሎም በውህደት መገናኘት ሉዓላዊ መብታቸው ነው። የኤርትራ መንግሥት በግፍ ራቁታቸውን ተባረው ደንበር አቋርጠው አገሩ የገቡትን ተሳዳጅ የኢትዮጵያ የጦር አባላት አልብሶ፣ አብልቶና አጠጥቶ ወንድማዊ እና ሰብዓዊ ምግባሩን ከማሳየቱም በተጨማሪ ከተማው አስመራ በሮኬት ሲመታ ለኢትዮጵያ ክብርና የአካባቢውን ችግር ላለማባባስ ሲል ምላሽ አለመስጠቱ እሰየው የሚያሰኝ ነው። ለዚህ ሁሉ በጎ ድርጊት ሙገሣው ቀርቶ ጣልቃ መግባቱ ባላስፈለገ።

የኢሕአዴግ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት እና ከአፍሪካ ሕብረት ዕውቅና በፊት በብቸኝነት ጦሩን ሶማሊያ ሲያዘምት ስትራቴጂያዊ አጋሬ ተባለ እንጂ ጦሩን ከሶማሊያ እንዲያውጣ አልተጠየቀም። በዚህ ወቅት እንኳ ሱዳን የኢትዮጵያን ደንበር አልፋ ስትወር አልተወገዘችም። በአባይ ግድባችን ምክንያት ከልክ ባለፈ የሚተናኮሱንን ግብጽና ሱዳን አደብ እንዲገዙ ከመምከርና በአፍሪካ ሕብረት በኩል ማሸማገሉ እንዲቀጥል በጎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አድሏዊ አቋም ማሳየቱም አግባብነት የለውም።

ውስጣዊ ጉዳይ
የአሜሪካ መንግሥት የህወሓትን የከፋፋይ ፖሊሰን በሚያንጸባርቅ መልኩ የአማራ ልዩ ኃይል ከትግራይ ይውጣ ማለቱ አስደንጋጭ ነው። በአገሪቷ ያሉ ሁሉም ማሕበረሰቦች ወያኔ እንደሚለው ሳይሆን በደም የተሳሰሩ የአንድ እናት ልጆች ናቸው። መንግሥት በአገሩ ውስጥ ማንኛውንም አይነት ማሕበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አሠራር የመፍጠር እና ተግባራዊ የማድረግ ሉዓላዊ ሥልጣኑ ነው።

መንግሥት ቢያሻው የአንዱን አካባቢ ልዩ ጥበቃ ወደሌላ የመውሰድ ወይም የመከላከያ ኃይሉ አካል የማድረግ እና በማናቸውም አገራዊ ግዴታ የማሰለፍ ሥልጣን አለው። ይህ ሥልጣኑ የሚመነጨው ከሕዝቡና አገራዊ ሕጎች በመሆኑ የውጭ ኃይሎች መመሪያ አስፈጻሚ መሆን አይጠበቅበትም። ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተገናኘ የአሜሪካ መንግሥት በአገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዳሳሰበው፣ ችግሩ እየተራዘመ ከሄደ አገራዊ ቀውሱ ወደ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ብሎም ዓለምአቀፋዊ ቀውስነት ሊሸጋገር እንደሚችል ሥጋት ማሳደሩ ተገቢ ነው። ይሁንና በትግራይና በተቀሩት የአገራችን ክፍሎች ለዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ምንጭ የሆነውንና መንግሥት በሽብርተኝነት ፈርጆ የሕግ የማስከበር ሥራ የሚያካሂድበትን ህውሓትን ትቶ ሕግ የማስከበር ተግባሩን በሠላማዊ ድርድር ሰበብ ለማደናቀፍ መሞከር ተገቢ አይደለም። ሠላማዊ ድርድሩ ተጠልቶ ሳይሆን ተሞክሮ ባለመቻሉ እንጂ። በሌላ በኩል፣ ሰብዓዊ መብት በአንድ አካባቢ አሳሳቢ በሌላው አካባቢ ደግሞ የተዘነጋ መሆንም ሚዛናዊነትን ያሳጣል። በየትኛውም ዓለም ይሁን የአንድ አሜሪካዊ ጥቃት የሚያንገበግበው፣ በእራሱ ላይ የመጣ ሽብርተኛን እንዴት ተከታትሎ እርምጃ እንደሚወስድ የሚታወቀው የአሜሪካ መንግሥት የሌሎችን ህመም እንደራሱ አለማየቱ አሳዛኝ ነው።

መቆርቆር እና ዕርዳታ
መንግሥታት ለየራሳቸው ሕዝቦች እንደሚቆረቆሩ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥትም ለአገሩ ሕዝብ ከማንም በበለጠ እንጂ ባነሰ ደረጃ አይደለም የሚቆረቆረው። በቅድሚያ ከራሱ ቆርሶ መስጠት ግዴታው ሲሆን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ከውጭ ከቀረበለት ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ዕርዳታን ማቅረብ የሚችል ነው። የሚፈለገው ዕርዳታው እንጂ አድራሽና አከፋፋይ አይደለም።

ከመንግሥት የሚጠበቅ – የማንቂያ ደወልን መስማት
በአገራችን ለአንድነት የሚበጅ በርካታ ተከታታይና ተደጋጋሚ የማንቂያ ደወሎች ተሰምተዋል። የሰሞኑ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ትልቅ የማንቂያ ደወል ሊሆነን ይገባል። የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ሕብረት ተመሳሳይ አዝማሚያ፣ የግብጽና የሱዳን የጥፋት ጥምረት፣ የሱዳን ወረራ፣ የአፍሪካ ወንድም አገር ኬኒያ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ያላት አሉታዊ አቋም እና በአገር ውስጥ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ ሁሉም ሲደመሩ ከፖለቲካዊ ሥርዓታችን እና ችግሮቻችንን ለመቅረፍ ካለን ድክመት የመነጩ መሆናቸውን ሁሌም ማመን ያስፈልጋል።
በህወሓት እና በሌሎች አገር ጠል ወገኖች አፋጣኝና ቆራጥ እርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ እየተወሳሰበ ነው። አሁኑ የሚታዩ ውስብስብ ችግሮች እንዲሁ በቀላሉ በአንድነት ስሜታዊ አባባሎች ጋጋታ እና በታሪክ ትረካ ብቻ መፍትሄ አያገኙም። ዛሬ የጎሣ ልዩነት ፖለቲካ ጦዞ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ጎሣዊነት ከብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የመገንጠል መብት አባዜ ጋር የተጣመረበት ወቅት ላይ በመሆናችን ለውጭ ኃይሎች ቡርቦራና ወረራ ተጋልጠናል።

ግልጽ የማንቂያ ደወል!
መንግሥትን ፈጣንና ቁርጠኛ ውሳኔ እንዳይወሰድ ጠርንፎ የያዘው የኢሕአዴግ የከፋፋይ ሕገ-መንግሥት መሆኑ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። ለአሁኑ የወዳጅ አገሮች ተጽዕኖ መጠናክር ምክንያት በአንድ በኩል የዲፕሎማሲ ሥርዓታችን ደካማነት ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ እያለን የዲፕሎማሲ ጥንካሬን ማምጣትም እጅጉን ይከብዳል። በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በዓለም ጤና ድርጅት፣ በዓለም ባንክ ፣ በዓለም የገንዘብ ድርጅት እና በተለያዩ የዓለም አቀፍ መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ በመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ ቦታ ላይ ያሉት የህወሓት አባላት እና ሌሎችም በህወሓት የፖለቲካ ሥርዓት የተገዙ ጠባብ ጎሠኞች መሆናቸው የሚታወቅ ነው። በየኤምባሲዎቻችንም ያሉ መሪዎች እና ዲፕሎማቶች በጎሣ መነጽር የተመረጡ ነባርና ቱባ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ናቸው። እነዚህ ከአፋዊ ኢትዮጵያዊነት ያልዘለሉ አካላት ለውጭ መንግሥታት ሆነ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርኩስ ሴራቸውን ለማራመድ የተመቻቹ ናቸው። አንዳንዶችም በአሜሪካና በአውሮፓ “የኢትዮጵያ ትውደም!” ቅስቀሳ አደራጆች ሆነው ተገኝተዋል። በአገር ውስጥም ከመንግሥታቸው ይልቅ ለውጭ አለቆቻቸው አቤቱታ አቅራቢዎች ሆነዋል። በእነዚህ አካላትና በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቀጥረው የሚሠሩ ተወካይ ጋዜጠኞች እና በማኅበራዊ ድረገፆች የተጠመዱ ተሟጋቾች ግልጽና ስውር ደባ ያራምዳሉ። ከአገር በተዘረፈ ገንዘብ የተገዙ ቅጥረኛ ወሬ ነዥዎች በአገራችን ላይ ቀውስ እንዲፈጠር ተግተው ይሠራሉ። በዚህም ዲፕሎማሲው ፈተና ላይ ወድቋል። አሜሪካም ሆነች ሌሎች እውነታውን ቢያውቁም በመንግሥት ደረጃ ዝምታው በመሥፈኑና በዲፕሎማሲ መስኩ መደረግ ያለበትን ያህል ባለመደረጉ በአገራችን ላይ ለተፈጠረው የውጭ ጣልቃ ገብነት አስተዋጽኦ አድርጓል። ለዚህ መፍትሄው የራስን ያልተቀናጀና ደካማ ሥራ አምኖ፣ የችግራችን ቁልፍ የሆነውን የፖለቲካ ሥርዓት ማስተካከል ነው።

ለውጥ ጊዜ ይወስዳል የሚልን አባዜ ትቶ በቁርጠኝነት የተሳሳቱ ወዳጆችን ወደ ማሳመኑ የተጠናከረ ሥራና የፖለቲካ ሥርዓቱን ወደ ማስተካከሉ መግባት የግድ ይላል። አለበለዚያ በደሙና በአጥንቱ፣ በሙሉ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ያለውን የመከላከያ ኃይላችንን፣ የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊታችንን፣ የልዩ ኃይሎችን እና የሌሎች ታጋዮቻችንን ተጋድሎ ዋጋ ማሳጣት ይሆንብናል። በተጨማሪም በመርህ ከኢትዮጵያ ጋር የቆሙ መንግሥታትን ማሳፈርና ወደ ማንፈልገው ቀለበት እንዲገቡ ማድረግ እንዳይሆን በጥበብ፣ በጥንቃቄና በብርታት መሥራት ያሻል።

ለማንቂያ ደወሉ ምላሽ
የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ በሰብዓዊ መብት፣ በጤና እና በግብርና ያለውን ዕርዳታና ትብብር ስለማያቋርጥ ይህን በቀና መልኩ ወስዶ ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ሕብረት የሚጎድልን ከሌላ በመፈለግ የተሻለና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴን በወጉ ማስኬድ ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ግን አገራችን በዕርዳታ የትም አትደርስም። ይልቁንስ የአደጉ አገሮችን የልማት ልምድ መውሰድ ይበጃል። የአገራችንን መወረር መቀልበስ እና ዓመታትን በለፋንበት የግድብ ሥራ ማለቂያ ላይ የሚደረግን ተጽዕኖ በብርታት መቋቋም ያሻል። አሁንም ለጥቃታችን መንስዔ የሆነውን የጎሣ ፖለቲካ በቶሎ ማስወገድ የግድ ይላል። በጥቂቶች የተዘራን መርዝ ማጥፋት ነገ ሳይሆን ዛሬ መደረግ አለበት። ስለሆነም ትልቁ ነገር በአዳዲስ አጀንዳዎች ባለመደናበር የራስን የቤት ሥራ እየሠሩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን በአግባቡ ማስኬድ አስፈላጊ ነው።

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ትግል ፍሬያማ ማድረግ የሚቻለው የውስጥ ችግራችንን በማስወገድ፣ ጎን ለጎንም በኩርፊያ ሳይሆን በጥበብና በአገራዊ ኩራት የተሳሳቱትን ከስህተት መንገዳቸው እንዲመለሱ በማድረግ ነው። የአገራችን የማንቂያ ደወል የሚሆነው አንድነትን ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን እውነተኛ አንድነትን ማምጣት እና ለአንድነታችን ጠር የሆነውን የጎሣ ፖለቲካን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ነው። የባዕዳንን መርዝ ውጦ አገር ማዳን አይቻልም። የማንቂያ ደወሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኤርትራውያን ወንድሞቻችንም ጭምር ነው።

ታዬ ብርሃኑ(ዶ/ር) በኢሜል አድራሻቸው
tayeberhanu27@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com