የእለት ዜና

የቤት ለቤት ጤና ክብካቤ አገልግሎት – ምን አዲስ?

Views: 133

‹‹እናቴ ከዛሬ ነገ ትድንልኝ ይሆናል በሚል ተስፋ እየጠበቅን ነው።›› ይላል የአዲስ ማለዳ ባለታሪክ የሆነው ወጣት። ሥሙ እንዲጠቀስ አይፈልግ እንጂ የእናቱን ጤና በሚመለከት ያለውን ሁኔታ ነግሮናል።
ወላጅ እናቱ በዘውዲቱ ሆስፒታል ሕክምናቸውን መከታተል ከጀመሩ ከስድስት ወራት በላይ ዘልቋል። ትንሽና ቀላል በሚመስል የመውደቅ አጋጣሚ ሕመም የጀመራቸው እናቱ፣ የቀዶ ጥገና ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የተረዱት በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር። ታድያ በዘውዲቱ ሆስፒታል አስፈላጊውን የቀዶ ጥገና ሕክምና አግኝተዋል።

ሆኖም ግን በፍጥነት ሊያገግሙ አልቻሉም። ከአጠገባቸው ሆኖ በተገጠመላቸው ትቦ በኩል ፈቃሽ ምግብ የሚሰጥ፣ ሰውነታቸውን የሚያጸዳና ንጽህናቸውን የሚጠብቅ፣ ከአጠገባቸው ሆኖ ክትትል የሚያደርግ ሰው አስፈላጊ ሆነ። ይህ ታድያ በሆስፒታል እያሉ ብዙ አላስቸገራቸውም፣ ችግር ቢፈጠር ቶሎ የሕክምና ባለሞያዎችንና ነርሶችን ለመጥራት አመቺ ነበር።

ሆኖም የጤናቸው ሁኔታ ባለበት ሲቆይና መሻሻል ባለማሳየቱ ሆስፒታሉ ወደ ቤታቸው ሄደው እንክብካቤ እንዲደረግላቸውና ለክትትል በሚሰጣቸው ቀጠሮ እንዲመጡ ያዟቸዋል። ይልቁንም በሕመማቸው ላይ የኮቪድ 19 ቢጨመር ከባድ እንደሚሆንና በሆስፒታሉ መቆየታውም ለወረርሽኙ ያጋልጣቸው ይሆናል በሚል ስጋትም ጭምር ነበር።

ባለታሪኩ ለቤተሰቡ ብቸኛ የገቢ ምንጭ መሆኑ እንዲሁም ታናናሽ እህቶቹም ገና በትምህርት ላይ መሆናቸው አሳስቦታል። ‹‹ቋሚ መኖሪያችን ከአዲስ አበባ ውጪ ነው። ታናናሾች እህቶቼን ሳይቀር የምትንከባከብ የነበረች እናታችንን ቤት ውስጥ ጤና አጥታ ስትውል የሚንከባከባት እንደማናገኝ አውቀን ነበር። አጣብቂኝ ውስጥ ነበርኩ።›› ይላል።

በአጋጣሚ በሕክምና ዘርፍ የሚሠራ የቅርብ ጓደኛው ቆይቶም ቢሆን ወላጅ እናቱን በቤት ውስጥ መንከባከብና ተገቢው ክትትል እንዲደረግላቸው ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ፣ በሳምንት ልዩነት እየሄደ እየጎበኛቸው እንደሆነ ይናገራል። ‹‹ጓደኛዬ ስላለ ቢያንስ አንድ ያሳስበኝ የነበረ ጉዳይ ቀለለልኝ፤ እርሱ ባይኖር ኖሮ ግን ምን ይውጠኝ እንደነበር አላውቅም።›› ሲል ለአዲስ ማለዳ ሐሳቡን ገልጿል።
የቤት ውስጥ ጤና ክብካቤ

ሩቅ የሚባል ጊዜ አይደለም፤ በኢትዮጵያ የቤት ለቤት የጤና ክብካቤ አገልግሎት ከተጀመረ። ዘመድ አዝማድ ለችግር ጊዜ አለሁ ማለቱ በተመለደባትና መተጋገዝ ወግ በሆነባት አገር ኢትዮጵያ፣ አንዳንዴ የቤት ውስጥ ተንከባካቢና አስታማሚ ወጥቶ መፈለግ ግድ ላይል ይችላል።

‹‹ዛሬ እኔ አድራለሁ፣ እኔ ምግብ አመጣለሁ፣ አጥሚቱን እኔ እሠራለሁ…›› እያለ የሚሞግት ወዳጅ ዘመድ በየሆስፒታሉ ማየት የተለመደ ነው። ሕመምተኛ ወደ ቤቱ ሲገባም የሚበላውን የሚጠጣውን ሸክፎ፣ ‹የቤት ምግብ እሺ ብሎ አይበላም፤ ባይሆን ሠርቼ ላምጣ› እያሉ የበሰለ ምግብ መውሰድና ማስታመም የቆየና የኖረ ባህል ነው።

ነገር ግን ደግሞ የጤና ባለሞያን እገዛ የሚፈልግ ሕመምተኛ አለ። ያም ብቻ ሳይሆን ዘመድና ወዳጅም በየራሱ ሩጫ እየተጠመደ ከእለት እለት እግሩ እየቀነሰ መሄዱ አይቀርም። ይሄኔ ነው የቤት ለቤት ጤና ክብካቤ አገልግሎት አስፈላጊነት ግልጥ ብሎ የሚታየው።

ይህ አሠራርና አገልግሎት በአገራችን የተለመደ አይሁን እንጂ ሠለጠኑ በሚባሉ አገራት ቤተኛ ጉዳይ ነው። አገልግሎቱም ሰፊ ሲሆን፣ ሕመምና ጉዳትን ጨምሮ ከእርጅና ጋር በተያያዘ ለሚያስፈልጉ እገዛዎችም የሚጠቅም አገልግሎት ነው።

‹አንኮታ› የተሰኘ ጤና ነክ ጉዳዮችን የሚያስነብብ ድረገጽ እንዳሰረፈው፣ ሳንጠቅስ በማናልፋት አገር በአሜሪካ የቤት ውስጥ የጤና ክብካቤ አገልግሎት ኢንዱስትሪ ደረጃ የተመዘገበ መሆኑን ይጠቅሳል። በየዓመቱም 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕሙማንን 600 መሚሊዮን የሚደርስ የጤና ክብካቤ ጉብኝት እንደሚደረግላቸው ይጠቅሳል። በአሜሪካም ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ከ35 ሺሕ በላይ ናቸው ብሏል።

‹ኬርቮያንት› የተባለ ሌላ ድረገጽ ይህንኑ የቤት ውስጥ ጤና ክብካቤን በሚመለከት ባለንበት የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2021 ያደረገውን ምልከታ ተከትሎ ያሰባሰበውን ነጥብ አስፍሯል። በዚህም የቤት ውስጥ የጤና ክብካቤ አገልግሎት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የበለጠ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ነው ይላል። ቴክኖሎጂም ይህን አገልግሎት እያገዘው መሆኑን ጠቅሷል።

ዓለማቀፉ የፋይናንስ ትብብር (IFC) በበኩሉ በጠቅላላው የአፍሪካን የጤና ክብካቤ በሚመለከት ያለውን ነጥብ ያነሳል። ይኸውም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በዓለማችን እጅግ መጥፎ የሚባል የጤና ክብካቤ ያለባቸው ናቸው ይላል። ለዚህም ማሳያው የዓለም ጤናድርጅት በዓመት ለአንድ ሰው ለጤና አገልግሎት ሊውል ይገባል ብሎ ያስቀመጠው የገንዘብ መጠን (ከ34-40 ዶላር) ነው።
እናም በአፍሪካ ተገቢውን የጤና ክብካቤ አገልግሎት ለመስጠት የግድ መዋዕ ነዋያቸውን በዘርፉ የሚያፈስሱ ባለሀብቶች ሊኖሩ ይገባል ባይ ነው፤ ትብብሩ።

በማያያዝ በአፍሪካ የጤና ክብካቤ አገልግሎት ላይ የግሉ ዘርፍ ሃምሳ በመቶ የሚጠጋ ድርሻ እንዳለው ተጠቅሷል። አሁንም ከመንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ እንደ ዘገባው ገለጻ። ከዚህም መካከል አንደኛው የቤት ለቤት የጤና ክብካቤ አገልግሎትን በተመጣጣኝ ክፍያና ጥራት ባለው አገልግሎት ማሳደግ የሚለው ነው። ይህም ለብዙዎች የሥራ እድልን የሚፈጥር ከመሆኑ በተጓዳኝ የጤና አገልግሎቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ያስችላል።

ምን አዲስ?
ይህን ጉዳይ እንድናነሳ ግድ ያለን ባሳለፍነው ሳምንት ግንቦት 28 ቀን 2013 በፓናሮማ ሆቴል የተሳተፍንበት አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። መግለጫው ‹ኸልፐርስ› የተሰኘ የቤት ለቤት ማስታመም አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት አዲስ መተግበሪያ ማስተዋወቁን የተመለከተ ነው።

ላለፉት አምስት ዓመታት የቤት ለቤት ሕክምናና ማስታመም አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ይኸው ኸልፐርስ የተሰኘ የቤት ለቤት ማስታመም አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የቤት ለቤት ሕክምና የሞባይል መተግበሪያ ነው ያስተዋወቀው። ድርጅቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ መተግበሪያው በምን መንገድ እንደሚሠራ አስተዋውቋል።

በመግለጫው ላይ ስለመተግበሪያው ገለፃ ያደረጉት በድርጅቱ የሥልጠና ክፍል ኃላፊ ዶክተር በኃይሉ አበራ፤ መተግበሪያው አስቀድሞ ለመመዝገብ እንጂ አገልግሎቱን ሲሰጥ የኢንተርኔት ቀጥታ ግንኙነትን በግድ የማይጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል። መተግበሪያው ድርጅቱ በዋናነት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማገዝ እንደሚውልም ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት የቤት ለቤት ማስታመም፣ የአረጋውያን ክብካቤ፣ በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን መስጠት፣ የደም፣ ስኳር እና ካንሰር ሕሙማን ክትትል፣ ግነዛ፣ በአፋቸው መመገብ ለማይችሉ የመመገቢያ ትቦ ማስገባትና መቀየርና የመሳሰሉ አገልግሎቶች በድርጅቱ ይሰጣሉ።

ኃይሉ አያይዘው ያነሱት ነጥብ ሜዲካል ቱሪዝምን ነው። ሜዲካል ቱሪዝም የሚሠሩ ድርጅቶች ሕሙማንን ሕክምና ወደሚያገኙበት አገር ማድረስና መከታተል ትልቅ ኃላፊነቱ ሲሆን፣ ለእነዚህ ድርጅቶች አብረው የሚሄዱ አስታማሚ ነርሶችን በማዘጋጀትና አብሮ በመላክ በጋራ እንደሚሠሩና ሊሠሩ እንደሚችሉ ነው የገለጹት። እንዲሁም ድርጅቱ ከወሊድ በኋላ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ክብካቤን በቤት ለቤት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ሆስፒታል ውስጥ አስታማሚን ተክቶ የሚሠራ ባለሙያ መመደብን ጨምሮ የግብዓትና ቁሳቁስ ማከፋፈል ሥራን ይሠራልም ብለዋል፤ ድርጅቱ።
መተግበሪያው ታድያ ለታማሚዎች ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሞያዎች ለሥራ የሚያመለክቱበት አውድን ያካተተ መሆኑም ተጠቅሷል። በዚህም ባለሞያዎች የሥራ ልምዳቸውን (ከ0 ዓመት ጀምሮ)፣ የትምህርት ደረጃና የብቃት ምዘና ማረጋገጫ እንዲሁም ተያያዥ ማስረጃዎችን በዚህ የመተግበሪያ አካል በሆነ ማፈንጠሪያ በኩል ሊያስገቡ ይችላሉ።

በመግለጫው የተገኙት የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የአዳዲስ ሥራና ፕሮጀክቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዓለምፀሐይ ደርሶልኝ ባደረጉት ንግግር፣ ኮሚሽኑ አዳዲስ አስተሳሰብ ማምጣት፣ በቅንጅት መሥራትና ወደ ተግባር መለወጥ የሚሉት ነጥቦች መሠረት መርህ አድርጎ እንደሚይዝ አንስተዋል።

ኸልፐርስ የቤት ለቤት የማስታመም አገልግሎትም እንደ ድርጅት ከሚያገኘው ጥቅም በተጓዳኝ ለሕክምና ባለሞያዎች የሥራ ዕድል መፍጠርና ችግር በመፍታት ይልቁንም በማስታመም የሚንገላቱና አስታማሚ የሌላቸውን በማገዝ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

‹‹ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ብቻ አይደለችም።›› ያሉት ዓለምፀሐይ፣ አገልግሎቱ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተደራሽ ሲሆን ብዙዎችንም በየዘርፉ ሊያነቃቃ የሚችል ደወል ነው ብለዋል። እንዲሁም አስፈላጊ በሆነ ሁኔታ ሁሉ ኮሚሽኑ ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ጋር ባለው ትብብር ውስጥ ለማገዝና ከድርጅቱ ጋር አብሮ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል። ለዘላቂነትና ለጥራት፣ የጤና አገልግሎቱን ወደፊት በማራመድ እንዲተጉም አበረታተዋል።

የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አበራ ጉልላት በበኩላቸው፤ ድርጅቱ መነሻውን አዲስ አበባ ያድርግ እንጂ የማስፋፋትና በክልሎችም የመድረስ እቅድ አለው ብለዋል። አያይዘውም ድርጅቱ ልምድ ያላቸውም ሆነ ተመርቀው እውቅና (COC) ያገኙ አመልካች የጤና ባለሞያዎችን በማሠልጠን ወደ ሥራ እንደሚያስገባ ጠቅሰዋል።

እንዲህ እንደ ኸልፐርስ ያሉ ጥቂት ድርጅቶች በዚህ በጤና ዘርፍ የቤት ለቤት ጤና ክብካቤ ወይም ማስታመም አገልግሎት በመስጠት ላይ ተሰማርተዋል። ይህ ለራሳቸው ሊያስገኛቸው ከሚችል ጥቅም ባለፈ ለተገልጋዮችና አስፈላጊ ክብካቤ ለማግኘት ሲረዳ፤ እንደ አገር የጤናው ዘርፍን ጫና በመቀነስና የሥራ እድልን በመፍጠር ቀላል የማይባል ሚና እንዳለው ይታመናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com