የእለት ዜና

‹ምረጡን› ነው ‹አትምረጡን›?

Views: 109

6ኛው የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ እንቅፋቶቹን ሁሉ ተሻግሮ ለክንውን ቀርቧል። የዛሬ አምስት ዓመት፣ የዛሬ ዓመት፣ የዛሬ ወር፣ የዛሬ ሳምንት እያለ ‹ከነገ ወዲያ› ላይ ደርሷል። ፍጻሜውንም ያሳምረው! ብዙዎች ታድያ ይህን ምርጫ እንደ ዘመን መለወጫ እያዩት ይመስል ነበር። እቅዶቻቸውንና ሐሳባቸውን ተስፋቸውን ሁሉ በይደር ‹ከምርጫው በኋላ› ብለው አቆይተዋል። ‹‹ምን ልትሠራ አሰብክ?›› ሲባል፤ ‹‹ቆይ ይሄ ምርጫ ይለፍና…!›› ብሎ የሚነሳ ‹‹ምን ለማድረግ ወሰንሽ?›› ስትባል፤ ‹‹ምርጫው ካለፈ በኋላ…›› ብላ የምትጀምር ጥቂት አይደሉም።

‹‹ይህ ምርጫ አልፎ የሚሆነውን ዐይቼ!›› የሚል ስጋትም፣ ጉጉትም ያዘለ ንግግር የሚናገሩም ጥቂት አይደሉም። የቅስቀሳ ድምጽ ሲሰሙ፣ የምርቃት ዜና ሲበራከት፣ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሁሉ የፖለቲከኞችን ሙግት ሲያቀርቡ፣ ግድግዳና ድልድዩች፣ መንገዶች ሁሉ በ‹ምረጡኝ› ባነሮች ሲጥለቀለቁ፣ የምርጫ ቦርድ እንደ አፍላኛ ወዳጅ ማልዶ ‹ካርድ አውጡ! ምረጡ!› እያለ ሲያስታውስ ሲቀሰቅስ፣ ነገር ሁሉ ከምርጫና ፖለቲካ አንጻር ሲተነተን…ብቻ ምኑ ቅጡ! አንዳንዶች ‹‹እንደው ይህ ምርጫ አልፎ ዐይቼ!›› ማለታቸው አልቀረም። ምርጫው አልፎ ለማየት የሚጓጉ ሰዎች ሁሉ ታድያ የሚመርጡት ፓርቲ አሸናፊ ሆኖ የማየት ፍላጎት ኖሯቸው አይደለም። ይልቁንም የአደባባይ ላይ የምርጫ ቅስቀሳው ያሰለቻቸው ደግሞ አሉ። ‹‹እውነት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲመረጡ ነው ወይስ እንዳይመረጡ ነው የሚፈልጉት?›› ብለው የጠየቁም አልጠፉ፤ መንገድ ዘግቶ ምረጡኝ ትርጉም አይሰጥማ! ማንን ነው ተቀስቃሹ?

እንደውም ጉዳዩን እንደ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ሚዛን ያደረጉት ነበሩ። ‹‹እገሌ ፓርቲ መንገድ ካልዘጋ የአደባባይ ቅስቀሳ ያደረገ አይመስለውም። ቅስቀሳ መራጭን እያንገላቱ ነው ወይ?›› በማለት ይጠይቁና በመራጩ ደካማ ጎን ለመግባት ይሞክራሉ። ‹‹እኛ ግን መንገድ አንዘጋም!›› ዓይነት መሆኑ ነው። በእርግጥ ሲሆን ምረጠኝ ያሉትን ጋብዞና አዝናንቶ፣ አቀማጥሎ ጎንበስ ቀና ብሎ አስተናግዶ ነው። ወትሮም ያላማረበት የመንገዱ ነገር ግን በብሶት ላይ ብሶት ይወልዳል እንጂ ሌላ ትርፍ የለውም። ‹‹ከአሁኑ መንገድ ከዘጋችሁማ ብንመርጣችሁ ምን ልትዘጉ ነው!›› ያሉም አልጠፉ። እንግዲህ መልካም አስተዳደር ከመልካም ቅስቀሳና አካሄድ ያስታውቃል ብለው ይሆናል፤ ገና ከምጣዱ እንደሚያስታውቅ አጥጋቢ እንጀራ።

ነገሩ እርግጥም አግባብ አይደለም። በምርጫ ቅስቀሳ ምክንያት መንገዶች ተዘጋግተው ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ብዙዎች በእግራቸው ረጅም መንገድ እንዲሄዱ ተገደዋል። አንዳንዶቹም መንገድ ፍለጋ እንደሰለሜ ጭፈራ ባልበላ አንጀት ሲጠማዘዙ ውለዋል፡፡ ሠራተኞች፣ ተማሪዎችና ባለጉዳዮች መንገድ ላይ እንዲጉላሉ ሆነዋል። ነገሩ የዚህ ነገር መልዕክትና ትምህርቱ የሰርክ አይደለም። እንደው ግን ነገሩ ማስተዛዘቡ አልቀረም። በእርግጥ! ጊዜም እየሮጠ ነው። ቀጣዩ 7ኛ አገራዊ ምርጫ ሩቅ አይደለም።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com