የእለት ዜና

ምርጫ እና የሕዝቡ ዝግጅት

Views: 125

ኢትዮጵያ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ያቀደችው በ2012 ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሺኝ እንዳይካሄድ ምክንያት ሆኖ ነበር። ከዚያም በኋላ ምርጫው ለመጨረሻ ጊዜ ግንቦት 28 / 2013 ይካሄዳል ተብሎ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዝግጅት አልጨረስኩም በማለቱ ወደ ሰኔ 14 መቀየሩ የሚታወስ ነው። ምርጫ ለመወዳደር ዝግጁ ነን ሲሉ ከነበሩ ከ110 በላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አሁን ላይ ከግማሽ በታች የሚሆኑት ብቻ በምርጫው ውድድር ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲዎች በምርጫው የመሳተፍ አቋም ላይ አንገኝም ሲሉም ቆይተዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ደግሞ በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ በመመስረት ጫና ሲያሳድር መቆየቱ ይታወሳል። ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ እና የፖለቲካ ግለቱ ሲጨምር እንዲህ ያሉ ወቀሳዎች ጨምረው ታይተው ነበር። ቦርዱም በፈተና እያለፈ መሆኑ እየተስተዋለ ነው።

ባለፈው ሰኔ 9/2013 ኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጨረሻ ቅስቀሳ ያደረጉበት ጊዜ ነበር። በዕለቱ ገዢው ፓርቲን ጨምሮ፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ምርጫ ቦርድ ሕዝቡ እንዲመርጥ ጥሪ ሲያቀርቡ ውለዋል። በኢትዮጵያ በሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ይወስዳሉ ብሉ ምርጫ ቦርድ ካቀዳው 50 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 37.4 ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ ካርድ መውሰዱ ይታወቃል። እንደ ማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ መሰረት ከሆነ በኢትዮጵያ ከ110 ሚሊየን ሕዝብ በላይ ይገኛል ተብሎ ይገምታል።

ከእዚህ ሕዝብ ውስጥ ግማሽ እንኳን የማይሞላ ቁጥር የምርጫ ካርድ መውሰዱ ሕዝቡ ምርጫ ላይ ያለውን መተማመን ማጣቱ ማሳያ ነው ሊባል ይችላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ መጪው ሰኞ ሰኔ 14 ለሚደረገው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ማሕበረሰብ መኖሩም መዘንጋት የለበትም። ሰኔ 14 ምርጫ ከሚደረግባቸው ቦታዎች መካከል አዲስ አበባ፣ ድሬደዋ፣ አፋር፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሲዳማ፣ እና ኦሮሚያ ይገኙበታል። ሰኔ 14 እና ጳጉሜ 1 ለሚደረገው ምርጫ በጠቅላላ 50ሺ የምርጫ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ሰኔ 14 ለሚደረገው ምርጫ 44,372 ምርጫ ጣቢያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ከምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአገራችን ለሚደረገው ምርጫ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል። ከዝግጅቶቹ መካከል ለምርጫ ቅስቀሳ እና ለምርጫ የሚያስፈልጉ እንደ ወረቀት እና ድምጽ መስጫ ሳጥን የመሳሰሉ ግብአቶችን ማሟላት ይጠቀሳል። ለዚህ የሚያገለግል ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የ40 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱ አይዘነጋም። ይህና ሌሎች የተለያዩ የዓለም አገራት የሰጧቸው የገንዘብ ብድሮችና ድጋፎች ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ዕጩዎቻቸው ብዛት ሲከፋፈል ቆይቷል። ይህ ሂደት ምርጫ ቦርድ ፍተሐዊ መሆኑን ያሳየበት አንዱ ተግባር ነው። በርግጥ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገንዘቡ በጊዜው ስላልደረሳቸው ቅሬታ ሲያነሱ መቆየታቸው አይዘነጋም።

ከዚህም ባለፈ ምርጫ ቦርድ ግልጽ መረጃዎች በማድረስ እና የገጠሙትን ፈተናዎች በመቋቋም ለመጨረሻው የድምጽ መስጫ ቀን ተቃርቧል። የፊታችን ሰኞ ለሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በምርጫ ቦርድ፣ በገዢው ፓርቲ፣ በሕዝቡ እና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅቶች ተጠናቀዋል። አዲስ ማለዳ በሕዝቡ በኩል ያለውን የምርጫ ዝግጅት በተመለከተ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግራለች።

መሐመድ ከድር የ29 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ በንግድ ሥራ ይተዳደራል።
መጪው 6ኛው አገራዊ ምርጫ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስጋት ካሳደረባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው። መሐመድ የምርጫ ካርድ የወሰደው ያለውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በመመልከት ሲሆን፣ ምርጫው በርካታ ተቃዋሚዎችን ያሳተፈ በመሆኑ ፍትሐዊ እንደሚሆን ተስፋ በማድረግም ጭምር ነው።
‹‹እኔ የምፈልገው መንግሥት ሰላም የሚያሰፍን፣ የሥራ እድሎችን የሚያመቻች፣ እንዲሁም ከኹሉም በላይ ደግሞ በጣም መቆጣጠር ያቃተንን ኢኮኖሚ የሚያረጋጋ ነው›› ሲል መሐመድ ለአዲስ ማለዳ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ምርጫውን በሚመለከት ምንም አይነት የቴሌቪዥን የክርክር መድረኮችን አልተመለከትኩም ያለው መሐመድ፣ ነገር ግን ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ መንገዶች በድምጽ የሚያስተላልፉትን መልዕክት ለማዳመጥ ችያለሁ ብሏል።
‹‹እኔ የምመርጠው ሰላማዊ መንግሥት ያላት አገር እንድትፈጠር ስለምፈልግ ነው። በዚህ ለውጥ ደግሞ የኔ ድምጽ መስጠት አስተዋጽኦ ስላለው ነው›› ብሏል።
ኹለት ልጆቹን የሚያስተዳድረው ከሚያገኘው የንግድ ገቢ መሆኑን የነገረን ሲሆን፣ የሚሸጣቸው የቤት ዕቃዎች በሚፈለገው መልኩ ገበያ ስለሌላቸው ተጨማሪ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ነግሮናል።
“እኔ ያለሁበት ሁኔታ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ስለሆነ፣ ተጨማሪ ሥራ እየሠራሁ ነው ልጆቼን የማስተዳድረው። ይህን ደግሞ የፈጠረው እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት ነው። ስለዚህ ተመርጦ የሚሾመው መንግሥት ማንም ይሁን ማን ኑሮውን ማረጋጋት ከቻለ ለኔ ብቁ ነው” ሲል መሐመድ ያክላል።
‹‹አሁን የሚታየው የምርጫ ቅስቀሳ እና የምርጫ ቦርድ ግልጽ መረጃዎችን ማቅረብ ከመንግስት ለውጥ በኋላ የመጣ በመሆኑ መነቃቃት ፈጥሮብኛል›› ሲልም ይናገራል። አይይዞም ‹‹የምርጫ ካርድ ወስጄ፣ ድምጼን የምሰጥበትን ቀን እየጠበቅኩ ነው›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹ለቀጣይ አምስት ዓመት ለአገራችን የሚጠቅማትን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለው›› በማለት ሀሳቡን ደምድàል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሂደት በጣም ግልጽነት በተሞላበት መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝ እየታየ ነው። ከምርጫ 97 በኋላ በሂደቱ ፍትሐዊ እና ግልጽ የሚባል ምርጫ ሲካሄድ የዘንድሮው ተጠቃሽ ነው።
ሙሉቀን ደጀኔ የተለያዩ የማስታወቂያ ሥራዎችና ሁነቶች አዘጋጅ በመሆን ላለፉት 8 ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል።
6ኛው አገራዊ ምርጫ ለእሱ ትልቅ የሥራ እድል እንደፈጠረለት ይናገራል።
ሙሉቀን ለሚሠራቸው የመኪና ኪራይ እና የድምጽ ማጉሊያ (ሞንታርቦ) ኪራይ ሥራዎች ወቅቱ መልካም የሚባል የንግድ በር እንደከፈተለት ይናገራል።
የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ የሚከራዩትን መኪና፣ ሞንታርቦ በተጨማሪም የሚሰበሰቡበትን ድንኳን በማከራየት ፕሮግራሞችን እየሰራ ቆይቷል።
‹‹እኔ የምመርጠው አገር ሰላም የሚያደርግ፣ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩትን የሚያበረታታ እና የብርን ዋጋ ከፍ ማድረግ የሚችልን ነው›› ሲል ሙሉቀን ይናገራል።
ወደፊት አገራችንን የሚመራው መንግሥት፣ ለንግድ ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የብድር አገልግሎትና የኢንቨስትመንት መሬት የሚያመቻች ብሎም ከውጭ በምናስገባቸው ምርቶች ላይ ቀረጥ የሚቀነስ እንዲሆን ፍላጎት እንዳለው ይናገራል።
የምርጫ ሂደቱን በተመለከተ ‹‹የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁኑ ገዢው ፓርቲ በመገናኛ ብዙኃን ርዕዮታቸውን እያስተላለፉ ቢሆንም፣ የመከታተል እድል ገጥሞኝ አያውቅም። ነገር ግን፣ አልፎ አልፎ ማኅበራዊ ድረ-ገጽ ላይ የሚለቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመወዳደሪያ ምልክት እና አንዳንድ መረጃዎችን እከታተላለሁ›› ሲል ሙሉቀን ገልጿል።
ከምርጫው የምጠብቀው ግልጽነት ነው። ከምርጫ 97 በኋላ እስከዛሬ ድረስ 99 በመቶ ገዢው ፓርቲ አሸናፊ እንደሆነ ስንሰማ ቆይተናል። በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ኢሕአዴግ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፌያለሁ ባለ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ፀረ-መንግሥት አመፆች መቀስቀሳቸው ይታወሳል።
‹‹አሁን ያለው ምርጫ ቦርድ እየሰራቸው ባሉት ግልጽ ተግባራት፣ በቀጣይ የሚገዛንን መንግሥት በግልጽነት እናውቀዋለን የሚል ተስፋ አለኝ›› ሲል ሙሉቀን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።
ኃይሉ ጸጋዬ የ21 ዓመት ወጣት ነው። አዲስ ማለዳ የሊስትሮ ሥራውን እየሠራ አግኝታዋለች።
ኃይሉ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምርጫው የሚያሳስበው ሆኖ አላገኘነውም። እንደውም የዕለት ጉርሱን ለማግኘት የሚለፋ እንጂ የሚሾመው መንግሥት ለሱ ምንም ግድ እንደማይሰጠው ገልጾልናል።
‹‹የምርጫ ካርድ አልወሰድኩም። ምክንያቱም የቀበሌ መታወቂያ የለኝም። ቢኖረኝም ኖሮ አልወስድም። ከላይ ያለ መንግሥት ማንም ይሁን ማን እኔ ኑሮዬን ማሸነፍ ነው የምፈልገው›› ሲል ኃይሉ ይናገራል።
ኃይሉ እንደሚለው ከሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ቢቀያየር የኑሮ ውድነቱን የማያሻሽል እና ሥራ የማይፈጥር ከሆነ ምን አስጨንቆኝ እመርጣለሁ ይላል።
ለምርጫ ቅስቀሳ በየመንገዱ ሲዞሩ አይቼ አውቃለሁ። ግን እኔን ምንም አይመስለኝም። ምክንያቱም መምረጥ አልፈልግም ሲል ኃይሉ ይናገራል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕዝብ ልክ እንደ መልኩ የተለያየ አስተሳሰብ አለው። ከላይ ያቀረብናቸው አስተያየቶች አዲስ ማለዳ ሀሳብ ከሰበሰበችባቸው በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ተመርጠው የቀረቡ አስተያየቶች ናቸው።
ደረጀ ወ/ገብርኤል ይባላሉ። ከ50 ዓመት በላይ በመምህርነት ሙያ ሲያገለግሉ ቆይተው አሁን ጡረተኛ ናቸው።
ደረጀ ወጣት በነበሩበት ዘመን የነበረው የትምህርት ሥርዓት እና አሁን ያለው እጅግ የተለያዩ ናቸው።
‹‹እኔ የምመርጠው የትምህርት ሥርዓቱን የሚያስተካክል፣ ለነዋሪዎች የቤት አቅርቦት የሚያመቻች፣ የሥራ እድል መፍጠር የሚችል፣ የኑሮ ውድነትን በጣም የሚያረጋጋ እና አገር ሰላም የሚያደርግ ነው›› ሲሉ ደረጀ ይናገራሉ።
የትምህርት ሥርዓት ሲባል አስተማሪዎችን ከማብቃት ነው የሚጀምረው የሚሉት ደረጀ፣ ብቁ ዜጋ እንዲፈጠር ብቃት ያለው መምህር ያስፈልጋል ይላሉ።
ደረጀ እንደሚሉት ከሆነ፣ ‹‹ምርጫ ቅስቀሳ በተመለከተ ብዙውን ጊዜ ቤት ውስጥ ስለምሆን አልፎ አልፎ በየሰፈሩ በድምጽ ማጉሊያ የሚያደርጉትን ቅስቀሳ ሰምቻለው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚደርጉትን ቅስቀሳ በብዛት ተመልክቻለው። በጣም ጥቂት ከሚባሉ ፓርቲዎች በስተቀር አብዛኛዎቹ የራሳቸው የሆነ ርዕዮተ አለም የሌላቸው እና ማኒፌስቶ ያላቀረቡ ሆነው አግኝቻቸዋለው›› ብለዋል።
‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ለአገር የሚጠቅም ነገር ይዟል ብዬ ያሰብኩት ፓርቲ አለ። ግልጽ የሆነ ርዕዮተ አለም ባይኖረውም ባለው ነባራዊ ሁኔታ የምመርጠውን አስቤያለሁ›› ሲሉ ደረጀ ይገልጻሉ።
‹‹ከምርጫው የምጠብቀው ፍትሃዊነት እና ግልጽነትን ነው። ያሉትን የምክርቤት መቀመጫዎች ትክክለኛና ግልጽ በሆነ ቁጥር ማን እንዳሸነፈ እንደሚገለጽ ተስፋ አለኝ›› ሲሉም ይገልጻሉ።
ከሁሉም በላይ ይላሉ ደረጀ፣ ‹‹በየአካባቢው የምንሰማው የሰው ሞት እና መፈናቀል ከምርጫው በኋላ እንደሚቆም ትልቅ ተስፋ አለኝ።›› በርግጥ የምርጫ ማግስት ብጥብጥ ወይም ደግሞ የሰላም እጦት ሊፈጠር እንደሚችል ይታወቃል። ነገር ግን መንግሥትም፣ ሕዝቡም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ምርጫ ፍትሐዊ የመንግሥት ሽግግር የምናደርግበት መንገድ መሆኑን መረዳት አለባቸው። በእስራኤል የተደረገውን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በአገራችንም እንዲሆን ማድረግ የሁላችንም ድርሻ ነው። ከምርጫ በኋላ ሕዝብ ለሕዝብ ማጋጨት፣ ማፈናቀል፣ ሰው መግደል እና ሌላ የፖለቲካ ጥቅም መፈለግ ለአገርም እንደማይጠቅም ነው ደረጀ ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት።
በየትኛውም መለኪያ ቢሆን ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በተለይም በ2002 እና 2007 ከተካሄዱት ምርጫዎች የተሻለ ሆኖ ይካሄዳል። መለኪያው መሆን ያለበት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርአቱ እና ሕጎች የሚጠይቁት መመዘኛዎች መሟላታቸው ነው ብለዋል።

ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com