የእለት ዜና

ሱዳንና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት!

Views: 175

በቅርቡ በኢትዮዽያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ከተከሰቱ ዲፕሎማሲያዊ መንገራገጮች ውስጥ አንዱ ከ አሜሪካ መንግሥት ጋር የተገባው እሰጥ አገባ ነው፡፡ የኢትዮዽያ መንግሥት በአገር ውስጥ የሕግ ማስከበር ተግባሬ የአሜሪካ መንግሥት በሰብአዊ መብት ጥስትና በእርዳታ አቅርቦት ስም ጣልቃ አየገባ ነው፡፡ ይህም በአገር ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው ፡፡ የተጣለውም ማዕቀብ ተገቢ ያልሆነና የአገራቱን የረዥም ጊዜ መልካም ግንኙነት ግምት ውስጥ ያላስገባነው ነው ሲል ተደምጧል፡፡ ይህን ተግባር ከሉዓላዊነት ጋር ማስተሳሰሩ እና በሰሜኑ የአገራችንን ክፍል የተፈጸመውን የሱዳንን ወረራ በቀላሉ ማየቱ፣ ሰፊ መሬት በሱዳን ጦር መያዙንና የሱዳን ግዛት መደረጉን የሚቃወም ሰልፍ አለመጥራቱና ተግባራዊ ምላሽ አለመስጠቱ በብልጽግና ፓርቲ የሚዘወረው የኢትዮዽያ መንግሥት ስለ ሉዓላዊነት ያለው አረዳድ የተዛባ ነው ሲሉ ግዛቸው አበበ በጽሁፋቸው ይሞግታሉ፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄዱ ጸረ-አሜሪካ ሰልፎች ሉዓላዊነታችንን አናስነካም የሚሉ ነበሩ። ከአሜሪካ መንግሥት ጋር መካረር መፈጠሩን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቃል አቀባዩ በኩል በሉዓላዊነታችን አንደራደርም ሲል ተሰምቷል። የኦሮምያና የአማራ ክልል ብልጽግና ኃላፊዎችና የክልሎቹ መሪዎችም ሉዓላዊነታችን በምንም እንደማይለወጥ ሲናገሩ ተሰምተዋል። ለመሆኑ የህወሓት/ኢሕአዴግን ሕገ-መንግስት መገንጠልን ከሚፈቅደው አንቀጹ ጋር አቅፎ የሚወዘወዘው ብልጽግና የሉዓላዊነት ጥልቅ ትርጉምና ከፍተኛ ክብር ገብቶታልን?
በአሜሪካ የተሰነዘረውን የባለሥልጣናት ላይ ያተኮረ የቪዛ ዕገዳ ሉዓላዊነትን እንደ መገዳደር አድርጎ ተቃውሞውን ያሰማውና ሰልፎችን የጠራው የብልጽግና ቡድን የሱዳንን ወረራ በቀላሉ ማየቱ፣ ሰፊ መሬት በሱዳን ጦር መያዙንና የሱዳን ግዛት መደረጉን የሚቃወም ሰልፍ አለመጥራቱ፣ የሱዳን ድፍረት እንደቀጠለና በግብጾች ግፊት ትንኮሳው ማቆሚያ ሊያጣ እንደሚችል የሚጠቁሙ እንቅስቃሴዎችን በቸልታ መመልከቱ በእርግጥ ሉዓላዊነት ማለት ለብልጽግና ቡድን ምን ማለት ነው ብሎ ለመጠየቅ በር የሚከፍት ነው?

የሱዳን መንግስት ‘መሬቴን ከኢትዮጵያ በጉልበቴ አስመልሻለሁ’ ብሎ በሚፎክርበት ጊዜ ከጠቅላይ ሚንስትሩ እና ከውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጀምሮ ካድሬውና ጋዜጠኛው የሱዳን መንሥስት ሳይሆን አንዳንድ ሱዳናዊ ቡድኖች ናቸው ትንኮሳ የሚያካሂዱብኝ እያለ ራሱን ሲያታልል የከረመው ብልጽግና፣ የሱዳን መንግስት የሕዳሴው ግድብ ያረፈበት ቤኒሻንጉል ሊመለስልኝ የሚገባ ግዛቴ ነው የሚል መግለጫ በውጭ ጉዳይ ቢሮው በኩል መስጠቱን ተከትሎ የሱዳን መንግስት አልወረረኝም ማለቱን የተወው ቢሆንም፣ ወረራውን ለመቀልበስም ሆነ የሱዳን ጦር ከያዘው መሬት እየተነሳ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰውን ጥቃትና የሚያካሂደውን ዘረፋ ለማስቆም ሲጥር አልታየም።

እዚህ ላይ ሊወሳ የሚገባው አንድ ነጥብ አለ። የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያን እንደ ስስ ዒላማ አድርጎ እያያት ነው። ሉዓላዊነቷን የሚሽር ሕገ-መንግስት የተጫነባትን ኢትዮጵያን፣ በዘር መከፋፈልንና የክልል ሉዓላዊነትን ትኩረት እየሰጡ አገሪቱን ችላ የሚሉ የክልልና የፌደራል ፖለቲከኞች የሚጨፍሩባትን ኢትዮጵያን፣ በጸረ-ኢትዮጵያዊነት ለመነሳሳትና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማጥቃት የቋመጡ ብዙ ግለሰቦች በልጅነት አቅፋ እንድትኖር የተፈረደባትን ኢትዮጵያን፣ አጥቅቶ መሬቷን ለመውሰድ ከዚህ ጊዜ የተሻለ ጊዜ እንደማያገኝ ያመነ ይመስላል፤ግብጾችም እንደዚው።

የሱዳን ጦር ‘የናይል ዘብ’ በሚል ስያሜ ከግብጽ ጦር ጋር የምድር እና የአየር ጦርነት ልምምድ እያካሄደ ነው። በአማራና በቤኒሻንጉል ክልሎች በሱዳን መንግስት እንደ ሰለጠኑና እንደ ታጠቁ በሚነገርላቸውና ግድያወችንና ውድመቶችን በሚያካሂዱ ቡድኖች እየተበጠበጡ ነው። እነዚህ ታጣቂወች በቤኒሻንጉል አንድን ወረዳ ለመቆጣጠር እስከ መሞከርና የጎንደር ከተማን በተለያዩ አቅጣጫዎች በመክበብ እስከ ማሸበር የደረሰ እንቅስቃሴወችን ማድረጋቸው በቀላሉ ሊታይ የማይገባው ጸረ-ሉዓላዊነት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህን መሰሉ የቅጥረኞች ዘመቻ ከዓመታት በፊት የግብጽ መሪ አልሲሲ ‘አንድም የግብጽ ጥይት ሳይተኮስ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርሳቸው በማጋጨት አገሪቱን ችግር ውስጥ መዝፈቅ ይቻላል’ ሲል ያሰማው ዛቻ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። የግብጽ ጦር አንድ እግሩን ሱዳን ላይ ተክሎ ነገር ፍለጋ ከጀመረ መሰነባበቱ፣ ሱዳንን በግልጽ ወደ ጦርነት ከመገፋፋት አልፎ ሱዳን ተነካችብኝ የሚል ሰበብ ደርድሮ የጦርነቱ ቀጥተኛ ተካፋይ ለመሆን ማቆብቆቡም ከማንም የተሰወረ አይደለም።

የሱዳን መንግስት ክረምቱ ከመግባቱ በፊት በወረራ ወደ ያዘው የኢትዮጵያ ምድር የሚያመራ መንገድና ድልድዮችን እየገነባ፣ በወረራ በያዘው መሬት ላይም አንዱን አካባቢ ከሌላው ጋር የሚያገናኙ መንግዶችን እየሰራ መሆኑ በአካባቢው ባለሥልጣናት እየተነገረ ነው። ይህ የተፋጠነ የመንገድና የድልድዮች ግንባታ፣ የሱዳን መንግስት ለወረራ የያዘው ጦሩ የአካባቢውን ለም መሬት በከፍተኛ ሁኔታ አጨቅይቶ መንቀሳቀስ እንዳይችል የሚያደርገው የዝናብ ወር ሲመጣ ጦሩ እርዳታ ሲያስፈልገው በቀላሉ እንዲመጣለት እየሰራ፣ ጦሩ ተቆርጦ ከበባ ውስጥ እንዳይገባ ለመከላከል ዝግጅት እያደረገ፣ በወረራ በያዘው ምድር ላይ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ጥበቃ ለማድረግና አጥቂ ጦር ከመጣበት ለመከላከል እየተሰናዳ መሆኑን የሚረጋግጥ ነው። ይህን መሰሉ እንቅስቀሴ የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን መሬት ለቅቆ የመውጣት ምንም ዓይነት ሃሳብ የሌለው መሆኑን የሚያሳይ ነው።

የብልጽግና መንግስት ይህን ወረራ እስከ መቼ ዝም ብሎ እንደሚያየውና ለምን ዝምታን እንደመረጠ ግልጽ አይደለም። በይፋ የተነገረ ነገር ባይኖርም ብዙው የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ ጦርነትና በኮማንድ ፖስት ስም በየቦታው ስለተወጠረ በአንድ ግንባር ላይ ትኩረት ለማድረግ በሚያስችለው ሁኔታ ውስጥ ያለውንና ካስፈለገው ሙሉ ኃይሉን በዚሁ ግንባር አሰልፎ ሙሉ ጦርነት ማካሄድ የሚችለውን የሱዳንን ጦር ለጊዜው በዝምታ ማየት ተገቢ መስሎ በመታየቱ የግዴታ ውዴታ አድርጎት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ነገር ግን የአባይን ግድብ በውኃ መሞላቱን ለመቃወም ወይም ቤኒሻንጉልን ልውረር የሚል ሱዳናዊ ቅዠት ተወልዶ ወይም በሱዳን ወታደራዊ መንግስት ላይ የሚደረገው የግብጾች ወይም የኃያላኑ ገፊ ጫና አይሎ መጠነ ሰፊ ጦርነት ሊከተል አይችልም ብሎ ተማምኖ መቀመጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል።

ሱዳኖች በወረራ በያዙት አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ለብዙ ዘመናት በተለይ ደግሞ በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የሱዳኖችን ጦር ሲመክት የኖረ መሆኑ ይታወቃል። የአሁኑ የሱዳኖች ድፍረት ለዚህ ሕዝብ የከበደው የሱዳን ጦር በርቀት ሊመቱ የሚችሉ መሳሪያዎችን በመጠቀሙና ብረት ለበስ ተሽከርካሪወችን ጭምር በመጠቀሙ መሆኑ ይነገራል። ስለዚህ የአካባቢውን ሚሊሻዎችና አካባቢውን የሚጠብቀውን ልዩ ኃይል፣ ዒላማን በርቀት የሚያጠቁ መሳሪያዎችን፣ የጸረ-ታንክና ጸረ-ብረት ለበስ ሚሳይሎችንና ፈንጅዎችን አጠቃቀም በሚመለከት ተገቢውን ስልጠና በመስጠት፣ ስልጠናውን ተከትሎም ብቁና ውጤታማ ለሆኑት መሳሪያዎቹን በማስታጠቅ የሱዳኖችን ግስጋሴና ትንኮሳ መግታት ተገቢ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ይህን መሰሉን ስልጠናና ከፍተኛ የተኩስ ዓቅም ያላቸው መሳሪያዎችን የማስታጠቁ ስራ በቤኒሻንጉል አካባቢም ጭምር ቢታሰብበት ተገቢ ሊሆን ይችላል። በተከታታይ በየአቅጣጫው በአገሪቱ ላይ የሚሰነዘሩ ዛቻወች እየበዙ ነው። የዚህ ሰሞን ተረኛ አስፈራሪና ዛቻ ሰንዛሪ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የሆነው ኔቶ መሆኑ እየተወራ ነው። ኔቶን ያህል ግዙፍ ጦረኛ እና ብልጽግናን የመሰለ ዝርክርክ ቡድን ግብግብ ሲገጥሙ ኢትዮጵያ ምን ትሆን ይሆን? ሁሉም ለአገሩ ዘብ የሚቆምበት ወቅት የደረሰ ይመስላል። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ከሚታየው ውስብስብ መከፋፈልና ውጥንቅጡ ከበዛው ችግር እንጻር ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በአንድነት ማሰለፍና የሚመጣውን ጠላት ሁሉ መመከቱ በቀላሉ የሚሳካ ነውን?

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ፈተና እየተጋረጠበት ያለው ከሱዳን፣ ከግብጽና ከምዕራባውያኑ ብቻ አይደለም። ከብልጽግና ልፍስፍስነትና ደካማነት በተጨማሪ ለውጭ ኃይሎች መሳሪያ ለመሆን ያቆበቆቡና ከአሁኑ ለማንኛውም የውጭ ኃይል አጨብጫቢ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ነን ባዮችም ሌሎች ፈተናዎች እየሆኑ ነው። እነዚህ በአሜሪካና በአውሮፓ መሽገው ብልጽግናን እንቃወማለን ከሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች አልፎ በአዲስ አበባ ፎቆች ላይ መሸገው ወሬ የሚያሰራጩ የመደበኛና የዩትዩብ ሚዲያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን ቻይናንና ሰሜን ኮርያን ሲዘረጥጡ ወሬውን እንደወረደ ተቀብለው በሚያስተጋቡበት መንፈስ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስተጋቡትን ወሬ እንዳለ ተቀብለው እያስተጋቡት ነው። እነሱ ወደ ትግራይ ወርደው የትግራይ ሕዝብ የሚደርስበትን ችግር አይተውና ሕዝቡ ከወዲያና ከወዲህ የሚደርስበትን ዱላ እያዩ ሕዝቡ ከሰቆቃና ከመከራ የሚላቀቅበትን፣ የወዲያና የወዲህ ግፈኞች የሚጋለጡበትን ሥራ ከመሥራት ይልቅ ከወደ አሜሪካና አውሮፓ የሚመጣ ወሬን እንዳለ እየተቀበሉ ሚዛኑን የሳተ ወሬ እየነዙ ነው።

እነዚህ ኢትዮጵያዊ ነን ባይ ሚዲያዎች የኤርትራ ወታደሮች፣ የኢትዮጵያ ጦር፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አደረሱት የሚባለውን በደል ምዕራባውያኑ በቀመሙት መንገድ ሲያስተጋቡ የህወሓት ፈዳይኖች የሚያካሂዷቸውንና በአንዳንድ ሚዲያወች ላይ እንደ ህወሓታዊ የድል ወሬ በግልጽ የሚስተጋቡ የከተማ ውስጥ ግድያዎችና አፈናዎች የምዕራባውኑ መገናኛ ብዙኃንና ፖለቲከኞች ምንም እንደ ወንጀል ስላልቆጠሩት በአሜሪካና በአውሮፓ የመሸጉት ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ ነን ባዮችም ሆኑ በአዲስ አበባ ፎቆች ላይ የመሸጉት መሰሎቻቸው ከፍርድ ቤት ውጭ የሚካሄደውን ይህን የህወሓት የግፍ እርምጃ ተችተውት አያውቁም። የትግራይን ሕዝብ መግደል የለብህም ተብሎ ሊነገረውና ተጋሩወችን አኔ በፈለኩት መንገድ ብቻ አስብ ብለህ ማፈን የለብህም ተብሎ ሊነገረው የሚገባው የትኛውም ጉልበተኛና አምባገነን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በአዲስ አበባ ፎቆች ላይ መሽገው ብልጽግናን በመቃዎም ሽፋን ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ወሬዎችን ከሚያሰራጩት ግለሰቦች ብዙዎቹ በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድም ሆነ በጎጠኝነት ህወሓትን ሲያገለግሉና በአገርና በሕዝብ ላይ በጠላትነት ዘምተው የነበሩ መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው። በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን በከፍተኛ ሹመት ላይ ሆነው የስርዓቱን የግፍ ዘመቻ ሲያራምዱ የነበሩ፣ በመንግሥትና በፓርቲ እንዲሁም በግል ሚዲያነት ስም በሚሰሩ የኅትመትና የስርጭት ሚዲያወች ውስጥ በቅጥረኛት ተሰግሰገው፣ አንዳንዶቹም የሚዲያወች ባለቤት ሆነው የስርዓቱን የግፍ እርምጃወች ሲሸፋፍኑ የነበሩ፣ የስርዓቱን የግፍ ሰለባዎች አሸባሪዎችና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የተነሱ ወንበዴዎች እያሉ ሲዘልፉና ለአምባገነንነት ሲጨፍሩ የነበሩ ጋዜጠኞች አሁን ለትግራይ ሕዝብ አሳቢና ተቆርቋሪዎች መስለው ቀንና ለሊት አስመሳይ ጩኸቶችን እያስተጋቡ ነው። እነዚህ ግለሰቦች ለትግራይ ሕዝብ አሳቢ መስለው የሚታዩ የቀበሮ ባህታውያን ናቸው።

ምዕራባውያኑ በምዕራብ ትግራይ ደረሰ ስለሚሉት ግፍና መፈናቀል ባሻቸው መንገድ የራሳቸውን ግብ ለማራመድ በሚያስችል መልኩ እያጣመሙ ወሬ ሲነዙበት የቀበሮ ባህታውያኑም ይህ ምዕራብ ትግራይ የሚባል ቦታ በ1984 ዓም ወደ ትግራይ የተካተተና ከአማራ ምድር ማለትም ከጎንደርና ከወሎ የተዘረፈ መሬት መሆኑን ያላወቁ መስለው የምዕራባውያኑን ወሬ በቀጥታ ተቀብለው ያስተጋቡታል። ምዕራባውያኑ ከምዕራብ ትግራይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤የዘር ማጽዳት ተፈጽሟል እያሉ ሲያወሩ የቀበሮ ባህታውያኑም ህወሓት ከበረኸናት ዘመኑ ጀምሮ እስከ 1980 ዓም የመጨረሻ ዓመታት ከወልቃይት፣ ከቃፍቲያ፣ ከጠገዴ፣ ከጠለምት፣ ከራያና ከመሳሰሉት የተዘረፉ ቦታወች በገፍ ያባረራቸውንና ያሳደዳቸውን፣ የጨፈጨፋቸውንና አስሮ አድራሻቸውን ያጠፋቸውን በመቶ ሽሕዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ረስተው እንደ ምዕራባውያኑ ይዘፍናሉ።

ለነዚህ የቀበሮ ባህታውያን አቶ ጌታቸው ረዳ ከየካቲት 1968 ኣም ጀምሮ በህወሓት ማንፌስቶ ላይ በግልጽ የሰፈረውንና የ45 ዓመታት ዕድሜ ያለውን የአማራ ጠላትነት በበረሀ ውስጥ ሆነው “አማራ ሒሳቡን ያወራርዳል” በሚል በጅምላ ሲዝቱበት ነበር። ከሚሊዮነር የቢራ ፋብሪካነት ባለቤትነት ወደ በረኸኛነት ራሳቸውን የቀየሩት የቀድሞው ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ “…ዐቢይና ኢሳያስ የአማራ አገዛዝን መልሰው ለማጣት ህወሓትን አጠቁ…..” በማለት ዐማራውን ተጠያቂ በማስመሰል የጥላቻ ዒላማ ሲያደርጉት፣ የቀበሮ ባህታውያኑ እንደ ተገቢ ዛቻ አድርገው ተቀብለውታል። ህወሓታውያኑ ሌላ የገዘፈ ማይ-ካድራዊ እልቂትን ለመፈጸም እየተዘጋጁ መሆኑን እያወቁና ዕድሜ ልኩን ጥላቻ በመዝራት የኖረው ፓርቲ ገና ከአሁኑ ለሌላ የጥላቻ ዘመን እየተዘጋጀ መሆኑን እያዩም የቀበሮ ባህታውያኑ ከበሮ ከመደለቅ አልተቆጠቡም።

በዚህ መካከል ደግሞ አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ፖለቲከኞች አስገራሚና አጠያያቂ አቋም ይዘው እየታዩ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል። አንዳንዶቹ በአሜሪካ ዕርዳታ ወይም በአሜሪካ መንግስት የሚካሄድ የመንግስት ግልበጣን ተከትሎ ሥልጣን አገኛለሁ የሚል ቅዠት ሰንቀው፣ ሌሎቹ በግርግሩ ዕድሜ ጠገብ አገር የማፍረስና ክልል የመገንጠል ሱሴን አረካለሁ ብለው፣ የቀሩት ደግሞ እነ አሜሪካ ብልጽግናን ይቀጡልኛል፤ ይበቀሉልኛል ብለው በማሰብ ብቻ በአሜሪካና በምዕራባዊ አጋሮቿ የተወሰደውንና ለወደፊት ሊወሰድ ለታቀደው እርምጃ ሁሉ ሲያጨበጭቡ ይታያሉ። እነዚህ ዕድሜ ጠገብ ፖለቲከኞች በሚዲያዎች ውስጥ ለመሸጉት የቀበሮ ባህታውያን ጥሩ ወሬ ማወፈሪያዎችና በሽሚያ ለእንግድነት የሚቀርቡ ደንበኞች ሆነው እየታዩ ነው።

በእርግጥ ከቀበሮ ባህታውኑ ብዙዎቹ ከህወሓት ስልጣን ማጣት ጋር አብረው ያጡትን ጥቅም ለማስቀጠል እየዳከሩ ነው። ቀድሞውንም ቢሆን ተጨነቀውለት ለማያውቁት ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ አስበው የሚሠሩት አንዳችም ሥራ የለም።
የቀበሮ ባህታውያኑ ግብጽ ከአሜሪካ የጦር መሳሪያዎችን ስትገዛ፣ ግብጽና ሱዳን የጋራ የጦር ልምምድ ሲያደርጉ፣ የግብጽ ወታደራዊ ባለስልጣናት ሱዳን ሲገቡና በመሳሰሉት አጋጣሚወች ደስታቸውን በሚያጋልጥ መልኩ የቡረቃ ዜናዎችን ሰርተዋል። የቀበሮ ባህታውያኑ የአሜሪካ መንግስት ማስጠንቀቂያ መሰንዘሩንና ማዕቀብ ማድረጉን ተከትሎ የተፈጠረባቸውን የአሜሪካን ጦር በኢትዮጵያ ምድር ሲወር የማየት ምኞት እና የአሜሪካ ቦምብና ሚሳይል በኢትዮጵያ ምድር ሲፈነዳ የመስማት ጉጉት ሰሞኑን ኔቶ በተዘዋዋሪ መንገድ እርምጃ ስለ መውሰድ መናገሩን ተከትሎ ኔቶ ኢትዮጵያን ሊወርር ነው ወደሚል ከበሮ ድለቃ አሳድገውታል። የአሜሪካ መንግስት በቅጥረኞቹ አማካይነት ስለሚያስገድላቸው ሰዎች፣ በአሜሪካ በቦምብ ሊጋዩ ስለሚችሉ ቦታዎችና በሚሳኤልም ወደ ዶግ አመድነት ስለሚቀየሩ ተቋማት ብዙ ግምቶችን ሲሰነዝሩም እየሰማን ነው። የቀበሮ ባህታውያኑ አዲሰ አበባ ላይ እዚያ እዚህ ቦምብና ሚሳይል ሲፈነዳ እነሱ በአዲሰ አበባ ፎቆች ላይ ሆነው እንደሚዘፍኑና በውጭ ያሉትም በቴሌቪዥን መስኮቶች አዚህና እዚያ እሳት ሲንቦገቦግና ጭስ ሲትጎለጎል ለማየት መናፈቃቸውን ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል። በውጭ ያሉት እልቂትንና ውድመትን እንደ ፊልም ለመኮምኮም ቢዘጋጁ አይገርምም። የአዲስ አበባወቹ ግን ስለ ‘ፍንጣሪዎች’ እና ስላልተገመቱ ጥቃቶች አለማሰባቸው፣ አቅጣጫቸውን ስለሚስቱ ቦምቦችና በሚሳይሎች አለመጨነቃቸው የሚገርም ነው። ጦርነት ባህሌ ነው ብሎ የጨፈረና ያስጨፈረ ቡድን የፈረንጅ ያለህ ባይ ሆኖና ፈረንጆች እንዲደርሱልኝ ንገሩልኝ ብሎ ወትዋች ሆኖ በሚታይበት በዚህ ጊዜ እኔ ደህና ብሎ መኮፈስ ከየት የመጣ ነው?

ግዛቸው አበበ በኢሜል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com