የእለት ዜና

ሀሰተኛ መረጃ በምርጫው ላይ ስጋት ደቅኗል

Views: 132

ለአገር ህልውና እና ለዜጎች አብሮነት የሚሰሩ የበየነ መረብ መገናኛ ብዙሃን የመኖራቸውን ያህል ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ጥቅማቸውን ብቻ የሚያሳድዱ መኖራቸውም በየጊዜ ይነገራል። በተለይም በበዙ የአገር ውስጥ እና የውጭ ጫናዎች ተከባ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከአንድ ሳምንት በኋላ ለምታደርገው አገራዊ ምርጫ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ስጋት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎባታል። ይሁን እንጂ እውነተኛ፣ የተጣሩ እና ትክክለኛ መረጃዎች መራጮች ስለተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎች፣ ስለ ቅድመ ምርጫ፣ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ክንውኖች እና ወዘተ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ ዜጎች በዕውቀትና በነጻ ፍቃዳቸው ላይ ተመስርተው ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ይረዳሉ።

በአንጻሩ ደግሞ ሀሰተኛ መረጃዎች ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዳያሳልፉ ተግዳሮት በመሆን እንዲሁም በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ሂደቶች እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የጀመሩትን ጉዞ እንደሚያውኩ አያጠራጥርም። ከዚህም አልፎ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በማህበረሰቦች መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬ እንዲሰፋ በማድረግ ለግጭት በር እንደሚከፍትም እሙን ነው። የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በምርጫው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የመንግስት አካላት፣ ሚዲያዎች እና መረጃ አጣሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች የራሳቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።
ከኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ማደግ እና ከማህበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሀሰተኛ የሆኑ እና ሆን ተብሎ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት በበርካታ አገራት ቀውሶች እንዲፈጠሩ አድርገዋል።

እንዲህ ያሉ ችግሮች ታዲያ በተለያዩ አገራት ላይ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ቀወሶችን ከማስከተል አልፎ ለግጭት እና ለጉዳት መንስኤ እየሆኑ መጥተዋል። ኢትዮጵያም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ አገራት ግንባር ቀደም ስትሆን በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ሳቢያ የተቀሰቀሱ ግጭቶች እና ጥቃቶች ለሰዎች ህይወት መጥፋት እና ለንብረት ውድመት መንስኤ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። በተለይ በዚህ የምርጫ ወቅት በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ሳቢያ ህብረተሰቡ እንዳይረበሽ እና ወዳልተፈለገ እርምጃ እንዳይገባ ነው ምሁራን ስጋታቸውን የሚልገጹት። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ እና የድህረ ምርጫ ክንውኖችን በግልጽ፣ በዝርዝር እና በወቅቱ ለዜጎች እንዲደርሱ በማድረግ እንዲሁም ለጋዜጠኞች እና ለመረጃ አጣሪዎች በሩን በመክፈት ሀሰተኛ መርጃ የሚያሰራጩ አካላትን ተጽዕኖ ለመቀነስ ራሱን ማዘጋጅት እንደሚጠበቅበት ከዚህ ቀደም በርካታ ፓርቲዎች ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

በተለይም የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የሚያንቀሳቅሱ የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን የጋዜጠኝነት ሙያ መርሆችን በላቀ አግባብ በመተግበር ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ለማድረስ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዲሁም መረጃ የሚያጣሩ ባለሙያዎችን በመመደብ እና በማሰልጠን ሀሰተኛ መረጃ በምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው የሚሉ የበዙ ድምጾች ሲደመጡ ከርሟል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደር የአንድ ፓርቲ ኃላፊ የምርጫን ውጤት ቀድሞ የመግለጽ፣ ሀሰተኛ መረጃ መፈብረክ እና ማሰራጨት እንዲሁም አንዱ የሌላኛውን ፓርቲ ስም የማጠልሸት ተግባር በየጊዜው እንደሚፈጸም አንስተዋል። ከምርጫ ውጤት ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ትስስር ገጾች (SOCIAL MIDEA) አማካኝነት ዛሬ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ አደጋዎች ነገ እንደማይደገሙ ምንም አይነት ማረጋገጫ እና ዋስትና የለንም በማለት ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

አክለውም ፓርቲያችን በተደጋጋሚ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ከፍተኛ የሆነ የስም ማጠልሸት ከሚካሄድባቸው ፓርቲዎች አንዱ ነው ብለዋል። በተለይም ያልተባሉ ንግግሮችን ከቪዲዮ ላይ ቆርጠው አውጥተው በመለጠፍ እና የፓርቲውን እና የአመራሮችን ስም የማጥፋት ድርጊት ተፈጽሟል ብለዋል። በሌላ በኩል አንዳንድ ፓርቲዎች በተደራጀ መልኩ መሬት ላይ የሌላቸውን ድጋፍ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ስም በማጥፋት፣ የሌላውን ፓርቲ አሳንሶ ማሳየት እና የራሳቸውን በማጉላት ተመራጭ ለመሆን የሚፈልጉ ጠርዝ የረገጡ አቀንቃኞች የፓርቲያችንን ስም በተደጋጋሚ አጉድፈዋል ሲሉም ተደምጠዋል።

ምንም እንኳ እነዚህን የመሳሰሉ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በትእግስት ብናልፍም ጉዳዩ ስር የሰደደ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በቀጣዩ ምርጫም ስጋት አለን ብለዋል። አያይዘውም ከምርጫ ቦርድ ቀድመው አሸናፊው እኔ ነኝ በማለት ውጤት መግለጽም ማህበረሰቡን ወዳልተፈለገ ግጭት እና አለመረጋጋት እንዳያስገባ የሚመለከታቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና አካላት በጥንቃቄ ሊሰሩበት እንደሚገባም ጠቁመዋል። የፓርቲያቸው አባላቱ እና ደጋፊዎች የሌሎችን ፓርቲዎች ስም ከማጉደፍ፣ ከማንቋሸሽ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን እንዳያሰራጩ በቂ ስልጠና እና ምክክር አድርጓል ብለዋል።

በምርጫ እና ድህረ ምርጫ ወቅት የመሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች እንድያውም እንድያው የሆነውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል አያጠያይቅም የሚሉት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደር የሌላ ፓርቲ ኃላፊ ናቸው።
የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ አስከፊው እና አደጋኛ የሆነው የሀሰተኛ መረጃ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ለዚህም የርዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ማሳያ ነው ብለዋል። በሌላም በኩል በ1997ቱ ምርጫ ላይ ትክክለኛ ባልሆነ ጥናት ይሄኛው ፓርቲ አሸንፏል በሚል የተለቀቀው የሀሰት መረጃ ለግጭት መዳረጉን እንደ ማሳያ አንስተዋል።

ስለሆነም በቀጣዩ ምርጫ ላይ ሀሰተኛ መረጃን ከማሰራጨት ባለፈ አንደኛው የሌላኛውን ፓርቲ ስም የሚያጎድፉ አካላትን ጨምሮ መንግስት በህግ ሊጠይቅ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል። በተለይም ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚነዙ የሀሰት ትርክቶችን መከላከል ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ጠቅሰው ህብረተሰቡም በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁ መረጃዎችን እንደወረደ ከመቀበል ይልቅ ማጣራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ማህበራዊ ሚዲያዎች በበዙበት በዚህ ዘመን መረጃዎች ያለተጠያቂነት በዘፈቀደ ሲሰራጩ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሚዲያ ግንዛቤያቸው አነስተኛ የሆነ ህዝብ ባለባቸው አገራት በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎች የተለያዩ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶችን አስከትለው አልፈዋል።

ኢትዮጵያ በውስጥ እና በውጭ ሀይሎች በተወጠረችበት በአሁን ሰዓት በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች የአገሪቱን የወደፊት ቁመና እንዲጣመም ሊያደርጉ የሚችሉ ስለመሆናቸው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በጅማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት መምህሩ ጌታቸው ጥላሁን ዶ/ር በኢትዮጵያ ምርጫን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች አጀንዳ በሆነበት በአሁን ሰአት የማህበራዊ ሚዲያው ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ነው ይላሉ። በተለይም በምርጫ ወቅት በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአደጉ እና በሰለጠኑ አገራትም ጭምር በርካታ ተጽእኖዎችን እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።

በቂ የሚዲያ ግንዛቤ የሌላቸው ማህበረሰብ በሞላባት ኢትዮጵያ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃዎችን በመፍብረክ (content fabricate) በማድረግ የሚያደናግሩ እየበዙ መጥተዋል። እኛ እና እነሱ የሚሉ ጽንፍ የያዙ ሀሳቦች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተንጸባረቁ ነው የሚሉት መምህሩ ሚዲያዎች ሀሰተኛ ትርክቶችን በመፈብረክ እና ግጭት አባባሽ ሚናን በመወጣት አገሪቱን የበለጠ ፈተና ውስጥ እየከተቷት ነው ይላሉ። ስለሆነም አገርን ለማስቀጠል ሀላፊነት በተሞላበት መልኩ መረጃን ማዘጋጀት እና ማሰራጨት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብዋል።
አሁን ላይ የማህበራዊ ሚዲያውን ለመቆጣጠርም ሀላፊነት ለመውሰድም እንደማይመች ገልጸው በተለይም ግን በምርጫ ወቅት ፖለቲካ ፓርቲዎች በስነ ምግባር በመገዛት የሚሰጡት የመረጃ ፍሰት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ባለፉት ሶስት አመታት በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኢንተርኔት መረቦችን ተጠቅሞ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ የሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን ለመከላከል እና ለመቆታጠር ባለፈው አመት 1185/2012 የሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አዋጅ መውጣቱ ይታወቃል። ይህንን የሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አዋጅን በማስፈጸም ሂደት ታዲያ መዘናጋቶች መኖራቸውን ነው የተለያዩ አካላት የሚገልጹት። በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሶሽዮሎጂ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ትንግርቱ ገብረ ጻዲቅ እንዳሉት በተለይ አሁን አገሪቱ የምትገኝበት ወሳኝ እና እጣ ፈንታዋን በቀጣይ የሚወስነው ምርጫ በሚካሄድበት እና በርካታ እቅዶችን መተግበር በጀመረችበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት አገርን ወደ ጥፋት የሚወስዱ ፓርቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን መንግስት በፍጹም ሊታገስ አይገባም ብለዋል።

አክለውም አገርን እና በአገር ላይ ክህደት ለመፈጸም ወይንም ከሌሎች አካለት አጀንዳዎችን ተቀብለው ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩ ሄሎች እንዳሉ ጠቁመው ጉዳዩ ለድርድር የሚቀርብ ባለመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል። የፖለቲካ፣ የብሄር እና ሌሎች አጀንዳዎችን በማንሳት ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የሀሰት ትርክትን በመንዛት የሚያራግቡ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እና በተጠንቀቅ የዜጎችን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲዊ መብቶችን በማይነካ መልኩ አገሪቷ የራሷን ሰላም ለማስጠበቅ ልትሰራ ይገባል ብለዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት መመህሩ ሰለሞን ሙሉ በበኩላቸው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጽፉ ሰዎች በጎ አላማ ያላቸው እንዳሉ ሁሉ የተለየ አላማ ያነገቡ እንዳሉም መለየት ያስፈልጋል ይላሉ።

በምርጫ እና ድህረ ምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩ ተወዳዳሪዎች የድምጽ ብልጫ ለማግኘት እና ለማሸነፍ ሲሉ ሀሰተኛ መረጃን ሊያሰራጩ ስለሚችሉ ጥብቅ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸው ፓርቲዎችም ሀላፊነት በተሞላ መልኩ መረጃዎችን ማጋራት ይኖርባቸዋል ሲሉም ጠቁመዋል። በምርጫ እና ድህረ ምርጫ ወቅት ሊፈጠር የሚችል የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖን ለመቀነስ ህብረተሰቡ እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ከታማኝ ምንጮች ብቻ መውሰድ እንዳለባቸውም አመልክተዋል። የሲቪክ ማህበራት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ዜጎች ስለሚዲያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ፣ማስተማር እና ራሳቸውን በማዘጋጀት ሀሰተኛ መረጃ በምርጫው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተግዳሮት በመቀነስ በጎ ሚና መጫዎት እንዳለባቸው እሙን ነው።

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሯቸውን የሚረዱ በቂ ባለሙያዎችን በመቅጠር የክትትል እና የእርምት ተግባራቸውን በማሳለጥ፣ ሪፖርት ለሚደረጉ ይዘቶች፣ አካውንቶች እና ገጾች ፈጣን ግብረመልስ በመስጠት እንዲሁም የፓርቲዎችን፣ የእጩ ተወዳዳሪዎችን፣ የሚዲያዎችን፣ የጋዜጠኞችን እና የምርጫ አስፈጻሚዎችን አካውንቶችና ገጾች እውቅና በመስጠት (verify) በማድረግ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ለሀሰተኛ መረጃ አሰራጮች ምቹ እንዳይሆኑ በማድረግ መጭው ምርጫ በአንጻራዊነት ጤናማ እንዲሆን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት ታምራት ደጀኔ በበኩላቸው በኢንተርኔት መረብ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ አካላትን ህጋዊ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ውጪ ለህግ አልገዛ ብለው በአገር እና በህዝብ ላይ አደጋ ለማድረስ እና የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ተጠቅመው ሀሰተኛ መረጃን የሚያሰራጩ አካላትን በህግ ለመጠየቅ እየተሰራ ነው ብለዋል። ባለስልጣኑ የበየነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ወደ ህጋዊ አሰራር ለማስገባት እየንቀሳቀሰ መሆኑንን ገልጸው በቅርቡም የበየነ መረብ መገናኛ ብዙሃን እንዲመዘገቡ ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ 30 የሚሆኑ መመዝገባቸውን አመልክተዋል።

ለተመዘገቡ የበየነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ከለላ ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል። ማህበረሰቡ የሀሰተኛ መረጃን እና የጥላቻ ንግግሮችን በተለያዩ ማህበራዊ ድረ- ገጾች ሲሰማ መረጃውን ተቀብሎ በፍጥነት ወደ ጥፋት ከማምራቱ በፊት ስለመረጃው ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይኖርበታል ያሉት ታምራት የመንግስት አካላትም ችግር ተፈጥሮበታል ተብሎ በሚነሱ አከባቢዎች ትክክለኛ መረጃዎችን በማስረጃ ለመንግስት እና ለመገናኛ ብዙሃን በገልጽ ማሳየት እና ተገቢውን መረጃ በማድረስ ህብረተሰቡ በሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ዘመቻዎች እንዳይጠለፍ መስራት ይገባቸዋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ምንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በህጋዊ መንገድ ለተመዘገቡ መገናኛ ብዙሃን መረጃ ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀው የበየነ መረብ ተጠቃሚ ዜጎችም ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ገጾችን ባለመከተል እና መልእክቶቻቸውን ባለማጋራት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል። የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር መንግስታት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እውነተኛ መረጃዎችን በፍጥነት ለህዝብ ማድረስ እንዲችል ከምንም በላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም። ማሕበራዊ ሚዲያ በመጪው ምርጫ ላይ ሊኖረው የሚችለውንም አሉታዊ ጫና በመረዳት በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግስት እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ሃይሎች እንዲሁም ፊደል የቆጠረው ህብረተሰብ በሃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባው ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com