የእለት ዜና

ምርጫ ቦርድ የማያውቃቸው ጣቢያዎች የፈጠሩት ስጋት

Views: 141

የኢትዮጵያን መፃኢ አድል ለመወሰን ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እሙን ነው። ለዚህም አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ደጋፊዎቻቸው እና የሕብረተሰቡ ካለፉቱ አምስት ምርጫዎች ይህ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ብለው ተስፋን ሰንቀው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ከሰሞኑ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ 79 የምርጫ ጣቢያዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደተመሠረቱ የተነገረው ዜና ሲሰማ፣ የምርጫው ፍትሃዊነት ላይ ጥያቄን በሚያጭር መልኩ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሯል። ጉዳዩን የአዲስ ማለዳው ወንድማገኝ ኃይሉ በስፋት ተመልክቶታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጨረሻው የዘውዳዊ ሥርአት ጀምሮ በተለያየ ጊዜ ምርጫዎች ተደርገዋል። በአፄ ኃይለስላሴ እና በደርግ ዘመን የተደረጉ ምርጫዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲደራጁ በማይፈቀድበት ምህዳር ውስጥ የተከናወኑ እንደነበሩ ይነገራል። በ1987 ዓ.ም የጸደቀውና አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግስት ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውቅና ሰጥቷል ከተባለ በኋላ በየአምስት ዓመት ልዩነት አምስት ምርጫዎች ተደርገዋል። በአንጻራዊነት ከ1997ቱ በስተቀር በአንዳቸውም ከገዢው ግንባር እና አጋሮቹ በስተቀር፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው አማራጮቻቸውን የማስተማር ዕድል ያገኙበት፣ ዜጎች በነጻነት ያለምንም ፍርሃት የሚመሯቸውን የመረጡበት ወይንም በመረጡት እንዲተዳደሩ የተቻለባቸው አልነበሩም።

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተደረጉ ምርጫዎች ለይስሙላ እና በጉልበት ኃይል የተያዘን ሥልጣን ቅቡልነት ለማላበስ ከመሆን አልፈው፣ እውነተኛ የሕዝብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር የተደረጉ እንዳልነበሩም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲናገሩ ይደመጣል። የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የሚደረገው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት ከተደረጉ ምርጫዎች በተለየ መልኩ ብቸኛ የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው አጠቃላይ ስምምነት አለ። ቀጣዩ ምርጫ፣ በሕዝብ እና የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲያስተዳድር ሥልጣን በሚሰጠው መንግሥት የሚባል ተቋም መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሥልጣን በሕዝብ ይሁንታ ብቻ የሚገኝ እንዲሆን መሠረት የሚጣልበት እነዲሆን ይጠበቃል።

የኢትዮጵያን መጻኢ እድል የሚወስነው ይህ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጠንካራ እና ዘላቂ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉትን አሳሳቢ የሰላም መደፍረስ ችግሮችን ከምንጮቻቸው ለማድረቅ የሚያስችል መሆን ሲችል እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። በረጅም ጊዜ እይታ የተቃኙ እርምጃዎችን መውሰድ ጨምሮ በአገር እና በሕዝብ ላይ ሲፈፀም የኖረውን ውስብስብ የአስተዳደር በደል፣ ስር የሰደደ ኢ-ፍትሃዊ አሰራር እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መሰረታዊ በሆነ መልኩ በመቀየር፣ እንደ አገር በፊታችን የተደቀነውን አስከፊ የህልውና አደጋን ለማስወገድ ብቸኛው አማራጭ ይህ ከፊታችን ሰኞ የሚደረግ ምርጫ እንደሆነ ብዙኃኑ አምነው የተስፋ አይኖቻቸውን ጥለውበታል።

በመሆኑም በዚህ ምርጫ ከነባራዊው የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች በመነሳት፣ በቅድሚያ በመላው ኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዳለበትም ይታመናል። ይህን ለማድረግም ሁሉም ዜጋ እና የማኅበረሰብ ክፍል በተረጋጋ ሁኔታ፣ በንቃት እና በስፋት በምርጫው መሳተፉ ፍጹም አስፈላጊ ነው። በኢትዮጵያ ዘላቂ ዋስትና ያለው ሰላም እና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማህበራዊ እድገት እንዲፋጠን፣ በሕግ የበላይነት እና በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት መሥራት ያስፈልጋል።

ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ እየተፈጠረ ያለው የዲሞክራሲ መድረክ ለሕዝቦች አብሮነት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብ እና ሕገ-መንግስታዊ መብቶች መከበር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማስቻል በሚደረገው አገራዊ ንቅናቄ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የኢትዮጵያን መጻኢ አድል ለመወሰን ፍትሀዊ እና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እሙን ነው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ጠንካራ መደላድል ላይ ማስቀመጥ የምንችለው ቀጣዩን ምርጫ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ ስንችል ብቻ ነው። ለዚህም አብዛኞቹ በሚባል ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ደጋፊዎቻቸው እና የህብረተሰቡ ክፍል ካለፉቱ አምስት ምርጫዎች ይህ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ብለው ተስፋን ሰንቀው በመጠባበቅ ላይም ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ከሰሞኑን ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ 79 የምርጫ ጣቢያዎች እንደተመሠረቱ የተነገረው ዜና ሲሰማ ደግሞ እንድያውም እንድያው የሆነው የምርጫው ፍትሃዊነት ላይ ጥያቄን በሚያጭር መልኩ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሯል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደር ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑ አንድ ዕጩ ተወዳዳሪ (የጥሞና ወቅት እንደመሆኑ ማንነታቸውን ከመግለፅ ተቆጥበናል) ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ እንደተመሠረቱ ስለተነገሩ የምርጫ ጣቢያዎች አስመልክቶ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ይህ በመንግስት እርከን ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች እጅ አለበት።

ሕገ-ወጥ የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱባቸው አከባቢዎች ላይ የሚገኙ የቀበሌ አመራሮች ካልከፈቱዋቸው በስተቀር ሌላ ተጻራሪ ኃይል ነው የከፈታቸው ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ነው የተናገሩት። እነዚህ ተከፈቱ የተባሉትን የምርጫ ጣቢያዎች ከታች ያሉ ኃይሎች እንዲፈጽሙት ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነም ሳይናገሩ አላለፉም። ይህም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት እየተስተዋለ እንደመጣ አመላካች መሆኑን በመጥቀስ፣ በምርጫው ፍትሃዊነት ላይ ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል። ከ ምርጫ ቦርዱ እውቅና ውጪ ከ 70 በላይ ሕገ-ወጥ የምርጫ ጣቢያዎችን የከፈቱትን አካላት ቦርዱ በሕግ እንዲጠይቅልን እንፈልጋለን ሲሉም አመልክተዋል።

ይህ ካልሆነ ግን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በመዘናጋቱ፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ እና በእንዝህላልነቱ የተፈጸመ ሕገ-ወጥ ድርጊት በመሆኑ ያስጠይቀዋል ብለዋል። ይህ ደግሞ መራጩ ሕዝብ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ፍትሃዊነት ላይ ያላቸውን አምነት ሊሸረሽር እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፣ ጉዳዩ ሪፖርት በማድረግ ብቻ የሚታለፍ አይደለም ብለዋል። መንግሥት በአገሪቱ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄዳል በሚልበት በዚህ ጊዜ፣ ይህን መሰል እኩይ ተግባር ሲፈጸም ማየት እጅጉን እንደሚያም አንስተዋል። ከዚህ በላይ ምርጫን የሚያዛንፍ ተግባር የለምም ብለዋል።

ይህም ሕዝቡ ድምጽ ባልሰጠበት ሁኔታ ድምጽ ተሰጥቷል በማለት ኮሮጆን በመሙላት ነጥብ ለማስቆጠር የተደረገ ስለሆነ፣ ጉዳዩ በሚገባ ሊጣራ እና አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል። እርምጃ መወሰድ እና አለመወሰዱንም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ እንዲያደርግልንም እንጠይቃለን ብለዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደር የሌላ ፓርቲ የምርጫ ስትራቴጂ እና ማኔጅመንት ኮሚቴ አባል የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች የምርጫ ጣቢያዎችን በየቦታው የሚያቋቁመው መንግስት እንደነበር እና አሁን ደግሞ በአዲሱ አሰራር እና ቀድሞ በነበሩ ምርጫዎች የገለልተኝነት ጥያቄ ተፈጥሮ ስለነበር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን እንዲወሰድው ተደርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም በሕገ-ወጥ መልኩ ከቦርዱ እውቅና ውጪ ስለተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ ሪፖርት ማድረጉ በበጎ የሚወሰድ እንደሆነ አንስተዋል።

ከዚህ ባሻገር የመንግስት ጣልቃ ገብነት አሁንም ድረስ እየተስተዋለ እንደሆነ ማሳያ ነው ያሉ ሲሆን፣ አሁን ላይ ተከፈቱ ከተባሉት 79 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ 71 የሚሆኑት በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው በአካባቢው የሚገኙ ካድሬዎች ከዚህ ቀደም በለመዱት አካሄድ ሕገ-ወጥ ጣቢያዎችን ከፍተው እንዲንቀሳቀሱ አድርገዋል ብለዋል። አክለውም ሕገ-ወጥ ጣቢያዎች እንደተከፈቱ መታወቁ እና ይህን ተከትሎም ከዚህ በኋላ በሕገ-ወጥ መንገድ የተከፈተ የምርጫ ጣቢያ ከሌለ፣ እንዲሁም የተከፈቱትም ተዘግተዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ከተደረሰ በምርጫው እና በፓርቲዎች ላይ ሊፈጥር የሚችል አሉታዊ ተጽእኖ አይኖርም ሲሉም ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

አያይዘውም ምርጫ ቦርድ አዲስ የዘረጋውን አሠራር፣ በተለይም የምርጫ ውጤት ይፋ በሚደረግበት ወቅት ውጤቱ የየትኛው ምርጫ ጣቢያ ውጤት ነው የሚለውን የልየታ ሥራ በሚሰራው የሲስተም ኮድ በመጠቀም፣ ምርጫው ተዓማኒ እንዲሆን ሥራውን አጠናክሮ በመሥራት ገለልተኝነቱን ማስመስከር እንዳለበት አሳስበዋል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አገራችንን ሰላሟን እና አንድነቷን አስጠብቆ መቀጠል የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ከቻልን እንደሆነ ግልጽ ነው።
የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ጠንካራ መደላድል ላይ ማስቀመጥ የምንችለው ደግሞ ቀጣዩን ምርጫ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ ስንችል ብቻ ነው ብለዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ልዩ ልዩ የመረጃ ሰዎች እና ከፍተኛ አመራሮች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ ውስጥ ሠርገው እየገቡ፣ ከቦርዱ እውቅና ውጪ የሚያደራጁት ምርጫ ጣቢ ያለ አግባብ ድምጽ ለመሰብሰብ የሚደረግ ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው የሚሉት ደግሞ የሌላ አገር አቀፍ ፓርቲ ዋና ጸኃፊ የሆኑ ዕጩ ናቸው። ድርጊቱ በምርጫው ላይ ያለንን መተማመን የሚገድብና ውስጠ-ዴሞክራሲ እንዳይሰፍን ተግዳሮት የሚሆን ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ደቡብ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎች ከተከፈቱት ሕገ- ወጥ ጣቢያዎች ባሻገር ትርፍ እጩዎች ተመዝግበዋል ሲሉም ተደምጠዋል።

ይህም በምርጫ ውጤት ላይ ያለ ውድድር የሚገኝ ቁጥር በመሆኑ ውጤቱ ላይ ልዩነትን ሊያሰፋ እንደሚችልም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ይህ ክስተት ከመፈጠሩም በፊት፣ በተለይ አዲስ አበባ ላይ፣ ይህ እንደሚሆን እንደ ፓርቲያቸው ስጋት እና ጥርጣሬ እንደነበር ገልጸው፣ ጉዳዩ የሚያሳዝን እና የሚያስተዛዝብ ነው ሲሉ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ በምርጫ ቦርድ በክፋት እና ሆን ተብሎ የተደረገ ባይሆንም፣ በክትትል እና ቁጥጥር ላይ የልምድ ማነስ ችግር ይስተዋላልም ብለዋል። ይህን ክስተት ወይንም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውጪ በሕገ-ወጥ መንገድ ተከፍተዋል የተባሉ የምርጫ ጣቢያዎችን አስመልክቶ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ የሕግ ባለሙያዎችን አነጋግራለች።

የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት፣ ካርዶችን ማሳተምና መበተን፣ እንዲሁም አጠቃላይ የምርጫ ጉዳዮችን በተመለከተ ኃላፊነት ያለው የምርጫ ቦርድ ብቻ እንደሆነ በምርጫ አዋጅ ላይ መቀመጡን አንስተዋል። በምርጫ አዋጅ አንቀጽ 157 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ከቦርዱ እውቅና ውጪ የምርጫ ጣቢያዎችን የከፈተ፣ ካርድ ያሳተመ እና የበተነ፣ እንዲሁም የምርጫ ሂደቱን ያስተጓጎለ በብር ከ 30 እስከ 50 ሺሕ የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት የገለጹት የሕግ ባለሙያው፣ በወንጀል ድርጊታቸው የሦስት አመት የእስር ቅጣት እንደሚበየንባቸው በግልጽ መቀመጡን በመጥቀስ አስረድተዋል።

ሌላኛው ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ማንኛቸውንም የምርጫ ሂደቶችን የተመለከቱ ጉዳዮችን የማስፈጸም ብቸኛው ኃላፊነት የምርጫ ቦርድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ ውጪ ገዢው ፓርቲን ጨምሮ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት፣ ካርድ ማሳተም እና መበተን በሕግ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል አብራርተዋል። ይህንን የወንጀል ድርጊት ማነው የፈጸመው፣ የምርጫ ጣቢያዎችንስ ማነው የከፈተው? እንዴትስ ሊሆን ቻለ? የሚለውን በማጣራት ተከታትሎ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፍርድ ቤት እርምጃ ማስወሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ይህ ድርጊት በመንግሥት አካላት ትብበር፣ ቅንጅት አና አየዞህ ባይነት የተፈጸመ መሆኑን ያነሱት ጥጋቡ፣ የዚህ አይነት ድርጊት ባህል እና ልምድ ሆኖ እንዳይቀር ምርጫ ቦርዱ ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ አንድ ድምጽ የምርጫ ውጤትን በመቀየር ረገድ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ገልጸው፣ ይህን መሰሉ የወንጀል ድርጊት ደግሞ የምርጫውን ተዓማኒነትን ጥያቄ ውስጥ ይከታል ብለዋል። ጉዳዩን በማስመልከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ እንደተመሠረቱ ከገለፃቸው 79 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ71 የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች ስድስተኛው አጠቃላይ የመጀመሪያው ምርጫ በሚደረግበት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. መርሃ ግብር ድምጽ እንደማይሰጡ ነው ያስታወቀው።

እነዚህ ጣቢያዎች በሙሉ የሚገኙት በደቡብ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን እንደሆነም ነው ቦርዱ የገለጸው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ባሳለፍነው ሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ እነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ለድምጽ መስጫ በተያዘው ኹለተኛ መርሃ ግብር ወቅት ድምጽ ይሰጣሉ ብለዋል። ይኼ የሚሆንበትም ምክንያት ያለቦርዱ ዕውቅና የተከፈቱት የምርጫ ጣቢያዎች የመዘገቧቸው መራጮች ነዋሪ መሆናቸው መረጋገጥ ስለሚኖርበትና ተጨማሪ ማጣሪያ ማድረጉ ጊዜ ስለሚጠይቅ እንደሆነም ሶልያና ተናግረዋል።

ምንም እንኳን እነዚህን የምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ ባያውቃቸውም የተመዘገቡት መራጮች ግን ይኼ መረጃ ስለሌላቸውና የመምረጥ መብታቸው መከበር ስለሚኖርበት፣ ተጨማሪ ማጣሪያ ከተደረገ በኋላ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምጽ እንዲሰጡ ይደረጋል ተብሏል። በጠቅላላው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካለው 547 መቀመጫዎች መካከል 59 መቀመጫዎች በሚያስመርጡ የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምጽ አይሰጡም ተብሏል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለው አሳሳቢ የሰላም መደፍረስ የተጀመረውን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ንቅናቄ ወደ ኋላ እንዳይመልሰው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። ተቋማዊ እና ቀጣይነት ባለው የአደረጃጀት መድረክ አማካይነት እየተወያዩ የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ማስቻል ፍጹም አስፈላጊ መሆኑንም ያምናሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት በተሞላበት አካሄድ የአገርን ብሔራዊ ደህንነት፣ የዜጎችን ነፃነት እና መሰረታዊ መብት በዘላቂነት ማስጠበቅ በይደር የሚቆይ አይደለም። በአገራችን የፊታችን ሰኞ የሚደረገውን ብሔራዊ እና የአካባቢ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ብሎም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የሁሉንም አስትዋጽኦ እና ትኩረት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ደጋፊዎቻቸው የዜጎችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት እና ግዴታዎችን ባከበረ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com