የእለት ዜና

የኹለት ዙር ምርጫ ጉዳይ

Views: 137

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታ የመጨረሻው የምርጫ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርደ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ሁኔታ የምርጫ ሂደቱ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ከመደበኛ አከባቢዎች አኩል መሄድ አልቻለም። ከጸጥታ ችግር በተጨማሪም በደምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ላይ ቦርዱ ችግር እንደገጠመው መገለጹ የሚታወስ ነው። በዚህም ቦርዱ ምርጫውን በአንድ ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል መወሰኑን ተከትሎ፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር እንዲካሄድ ወስኖ እየሰራ ነው። በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው ዙር ምርጫ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14/2013 የሚካሄድ ሲሆን፣ ኹለተኛው ዙር ምርጫ ደግሞ ጳጉሜ 1/2013 እንደሚካሄድ ቦርዱ ውሳኔ አሳልፏል።

በመሆኑም ቦርዱ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ለማካሄድ በሁኔታዎች መገደዱን ተከትሎ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከሚደረግበት ሰኔ 14/2013 በተጨማሪ ኹለተኛ ዙር የምርጫ ቀን አስፈልጎታል። በዚሁ መሰረት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኹለተኛ ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1/2013 እንደሚካሄድ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ከትግራይ ክልል ውጭ በተመሳሳይ ጊዜ ለማድረግ አቅዶ ሲሰራ ቢቆይም፣ በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ በጸጥታ ምክንያት የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን በተገቢው ሁኔታ ባለመሰራታቸው ኹለተኛ ዙር ምርጫ ማካሄድ አስፈልጓል። ይሁን እንጅ በኹለት ዙር በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የትግራይ ክልል አልተካተተም።

በዚህም የደምጽ መስጫ ወረቀት ችግር በገጠመባቸው የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ማሳተም በማስፈለጉ ተጨማሪ የምርጫ ክልሎች ለኹለተኛ ዙር ማሸጋገርና፣ በተለይ በሶማሌ ክልል ቦርዱ በገጠመው የኅትመት ችግር የክልልና የክልሉ የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ሙሉ በሙሉ በኹለተኛው ዙር እንዲሆን ቦርዱ ወስኗል። የድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ችግር ባጋጠመባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ኅትመት ማስፈለጉን ቦርዱ መገልጹ የሚታወስ ነው። የድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ኅትመት ያስፈለገባቸው የምርጫ ክልሎች በአፋር ክልል ስድስት ምርጫ ክልሎች፣ በአማራ ክልል ኹለት ምርጫ ክልሎች፣ በጋምቤላ ክልል አንድ ምርጫ ክልል፣ በሶማሌ ክልል አስራሁለት ምርጫ ክልሎች እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል አስር ምርጫ ክልሎች መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

በሐረሪ ክልል በክልሉ መንግሥት በኩል በቦርዱ ላይ በቀረበው ክስ መሰረት ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ለማስፈጸም ቦርዱ ተጨማሪ ጊዜና ኅትመት ስላስፈለገው ምርጫው በኹለተኛው ዙር እንዲካሄድ ተወስኗል። በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የማይካሄድባቸውን ሶማሌ ክልል፣ የሐረር ክልልና በሌሎች ክልሎች ተቆርጠው የቀሩ አካባቢዎችን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤት ደረጃ የሚካሄደው ምርጫ በኹለት ዙር ወደ ጳጉሜ 1/2013 ተዘዋውሯል። ወደ ጳጉሜ አንድ የተሸጋገሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በአማራ ክልል 10 ፣ በአፋር ክልል 2፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ 4፣ በኦሮሚያ ክልል 7፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል 16 ፣ በሐረር ክልል 2 ሲሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ምርጫ በማይደረግበት ሶማሌ ክልል 23 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊታችን ሰኞ በሚደረገው ምርጫ አይካፈሉም።
በአጠቃላይ በሰኔ 14/2013 ምርጫ ተቆርጠው የቀሩና ኹለተኛው ዙር ምርጫ ማለትም ጳጉሜ 1 የሚካሄድባቸው በጥቅሉ 64 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ናቸው።

በክልል ደረጃ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የማይካተቱና ለኹለተኛው ዙር ምርጫ የተዘዋወሩ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ በተዛወረው ሶማሌ ክልል 72 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል 22 ፣ በኦሮሚያ ክልል 7 ፣ በሐረር ክልል 3 ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 13፣ አፋር ክልል 7 የክልል፣ አማራ ክልል 9 ሲሆኑ፣ በጥቅሉ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የማይካሄድባቸው 197 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በሲዳማ ክልልና በጋምቤላ ክልል ቀድሞ ሰኔ 14/2013 ይካሄዳሉ የተባሉ ምርጫዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚካሄዱ ቦርዱ አስታውቋል። በጋምቤላ ክልል ድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ኅትመት ቢያስፈልግም በክልሉ ክረምት ከገባ ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን በመገንዘብ ችግሩ ተስተካክሎ ምርጫው እንዲካሄድ ውሳኔ ተሰጥቶበታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫ ወንበሮች ያሉት ሲሆን፣ የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተለያዩ ክልሎች መቀመጫ የሆኑ 64 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ወንበሮች የማይካተቱ ሲሆን፣ በሰኔ 14ቱም ይሁን በኹለተኛው ዙር ጳጉሜ 1 በሚካሄደው ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 መቀመጫዎች ያሉት የትግራይ ክልል አልተካተተም። በመሆኑም 547 መቀመጫዎች ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኹለት ዙር ምርጫ ከተካሄደ በኋላ በትግራይ ክልል ምርጫ አለመደረጉን ተከትሎ የትግራይ ክልል መቀመጫ 38 ወንበሮች ክፍት ይሆናሉ።

በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ማለትም የሰኔ 14 ምርጫ በ673 ምርጫ ክልሎችና 44 ሺሕ 372 ምርጫ ጣቢያች የሚካሄድ ሲሆን፣ በኹለተኛው ዙር ጳጉሜ አንድ ይካሄዳሉ ተብለው ቀጠሮ የተያዘላቸው ምርጫ ክልሎች 27 መሆናቸውን ቦርዱ ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ በስድስተኛው አጠቀላይ ምርጫ 37 ሚሊዮን 400 ሺሕ መራጮች ለመምረጥ ተመዝገበዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ አብሮ ለማካሄድ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል። ሕዝበ ውሳኔው ቀደም ሲል ከሰኔ 14 ምርጫ ጋር አብሮ እንዲካሄድ ውሳኔ የተሰጠው ቢሆንም፣ የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ ከሰኔ 14 ወደ ጳጉሜ 1/2013 እንዲሸጋገር ቦርዱ ባለፈው ሳምንት ውሳኔ አሳልፏል።

የደቡብ ምዕራብ ከጳጉሜ አንዱ ምርጫ ጋር ጎን ለጎን ውዝበ ውሳኔ የሚሰጥባቸው የከፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን፣ ቤነች ሸኮ ዞን፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የሸካ ዞንና የኮንታ ልዩ ወረዳ አስተዳደር ሲሆኑ፣ ሕዝበ ውሳኔው ወደ ጳጉሜ አንድ የተሸጋገረው ዞኖች ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ለጥያቄዎቹ ምላሽ መስጠት በማስፈለጉ ነው ተብሏል። ቦርዱ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1/2013 ለማካሄድ ያቀደ ቢሆንም በጸጥታ ችግር ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተስተጓጎሉ አከባቢዎች መንግሥት የጸጥታ ችግሩን በፍጥነት እንድሻሻልና አስቻይ ሁኔታዎች እንድፈጠሩ ካላደረገ ከኹለተኛው ዙር ምርጫ ላይካሄድ እንደሚችል የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ጠቁመዋል።

በመሆኑም መንግሥት በተለይ በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን ያለውን የጸጥታ ችግር አስተካክሎ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታው መመለስ ካልቻለ በኹለተኛው ዙር ምርጫ ለማካሄድ እንደማይቻልም ሰብሳቢዋ አክለው ገልጸዋል። በመሆኑም መንግሥት ከወዲሁ መሥራት የሚጠበቅበትን ሥራ በትኩረት ሰርቶ የጸጥታ ሁኔታዎችን በማስተካከል አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል። በተጨማሪም የጸጥታ ተቋማትና አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ በመወጣት የጸጥታ ችግሮችን ለማሻሻል እንዲረባረቡ ስብሳቢዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በኹለት ዙር ካካሄደ በኋላ፣ በ2014 በመስከረም ወር በምርጫው አሸናፊ ሆኖ የተገኘው አዲስ መንግሥት እንደሚመሰርት ብርቱካን ጠቁመዋል። ምርጫው በኹለት ዙር ቢደረግም የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ በምርጫ ማግስት ይፋ የሚደረግ ሲሆን፣ አጠቃላይ የመጀመሪያው ዙር ጊዜያዊ ውጤት በቦርዱ በኩል ምርጫው በተካሄደ አስር ቀናት ውስጥ የሚገለጽ ይሆናል። የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ውጤት ይፋ ቢደረግም መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን የመጨረሻ ውጤት ለማወቅ ጳጉሜ አንድ የሚደረገውን የኹለተኛ ዙር ምርጫ ውጤት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ብርቱካን ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com