የእለት ዜና

የጥብቅና አገልግሎት አሠጣጥ አዋጁ የአካል ጉዳተኞችን ያካተተ አይደለም ተባለ

Views: 148

የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳዳር ረቂቅ አዋጅ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የሚሰሩ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ አይደለም ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሙያዎች ተናግሩ። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ማጽደቁ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ለፍትሕ ልዕልና የሚሰሩ የአካል ጉዳተኛ ጠበቆችን አካታች፣ አሳታፊ እና የሚያበረታታ እንዲሆን ሀሳብ ብናቀርብም ድምጻችን ሳይሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ቀርቷል ያሉን ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ ናቸው።

አካል ጉዳተኞች በዘርፉ በቁጥር በርካታ በመሆናቸው ወደ ዘርፉ በማምጣት እና የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በማድረግ ረገድ የሚያበረታታ ሥራ አልተሠራም ያሉት ጠበቃው፣ አዋጁ ላይ በአዎንታዊ መልኩ የሚያበረታታ ሥርአት አልተቀመጠም ብለዋል።
ጠበቃው አያይዘውም ከዚህ ችግር ባሻገር የአዋጁ አፈጻጸም ላይ ችግር ሊኖር እንደሚችልም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ይሁንና በአዎንታዊ መልኩ ከሚነሱት ውስጥ የጥብቅና አገልግሎት አሰጣጥ እና የጠበቆች ማኅበር መቋቋሙ እንደ መልካም አጋጣሚም አንስተዋል።

ሌላኛው የሕግ ባለሙያ ካፒታል ክብሬ በበኩላቸው፣ በአዋጁ ላይ ከጸደቁት በአመዛኙ ከዚህ በፊት የነበሩ ሁኔታዎች እንደቀጠሉ ገልጸው፣ በዚህም በዋነኛነት አካል ጉዳተኞች የጥብቅና አገልግሎትን እንዲያሳልጡ የሚደግፍ ሥርአት አልተዘረጋም በማለት ከላይ የተነሳውን ሀሳብ ተጋርተዋል። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ የከረመው የጠበቆች ማኅበር፣ ከበርካታ አመታት ውትወታ በኋላ አሁን ላይ መቋቋሙ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።ይህም የሕግ እና የፍትሕ ሥርአቱ እንዲሳለጥ ይረዳል ብለዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን፣ በአዋጁ ላይ የተነሳውን የአካታችነት ጥያቄ በተመለከተ ሲመልሱ ከ130 በላይ ጠበቆችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ በማሳተፍ አስተያየታቸውን ተቀብለን ነው አዋጁን ያጸደቅነው ብለዋል።
አያይዘውም ለጠበቆች ፈቃድ የመስጠት እና የመከልከል ሥራን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይሠራ እንደነበር ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ ይህ ሥልጣን አዲስ የተቋቋመው የጠበቆች ማኅበር እንደሆነም አመልክተዋል። አክለውም ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው ከተመራ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ከአስረጂዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገበትና በቂ ግብዓትም የተገኘበት መሆኑን ኃላፊው ለአዲስ ማለደ አስረድተዋል።

የጥብቅና ፍቃድ አሠጣጥና አሥተዳደር አገልግሎት ላይ ሰፊ የሕግ፣ የአሠራር፣ በአንዳንድ ጠበቆች ላይ የብቃትና የስነ-ምግባር ችግሮች እየተስተዋሉ መምጣቱን አወል አብራርተዋል። አያዘውም የጥብቅና ፍቃዱ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑ አገልግሎቱ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳያድግና የሙያ ነጻነቱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎቱ እንዳይሰጥ አድርጎ ነበር ተብሏል። በረቂቅ አዋጁም አንዳንድ አንቀጾችን ሙሉ በሙሉ በሌሎች አንቀጾች ከመተካት ጀምሮ በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ነው የጠቆሙት።

ከዚህ ባሻገር የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሠጣጥና አሥተዳዳር አዋጅ የአገሪቱን ዜጎች ፍትሕ የማግኘት እና የሕግ የበላይነት በማረጋገጡ ሂደት ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች የሚኖራቸው ድርሻ የጎላ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ፣ የጠበቆችን ብቃትና የሥነ ምግባር ችግር የሚፈታ፣ መብትና ነጻነት የሚያስጠብቅ፣ የተገልጋዮችን መብት የሚያስከብር ነው ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com