የእለት ዜና

በቆዳ ዘርፍ የውጪ ንግድ ከታቀደው 53 በመቶ ብቻ መገኘቱ ተገለጸ

Views: 154

በቆዳ ዘርፍ ከውጪ ንግድ 36.3 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 19.4 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱ ተገለጸ። ይህ ደግሞ የዕቀዱን 53.4 በመቶ ብቻ ማሳካት እንደተቻለ ነው የተገለጸው። በዚህ 2013 ዓመት የ10 ወር አፈጻጸም ከዚህ በፊት ከነበረው የውጪ ንግድ ገቢ ያነሰ ሆኖ የተመዘገበው ዓለምን አስጨንቆ በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክኝያት ነው ሲሉ የኢንሰቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርሃኑ ሰርጄቦ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የውጪ ምንዛሬ እጥረት እና የግብዓት በበቂ ሁኔታ አለማግኘት ዘርፉን እንዲዳከም ካደረጉት ችግሮች መካከል አንዱ ነው ሲሉ ብርሃኑ ጠቁመዋል። በቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የ10 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ግንቦት 10 የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህም ኢትዮጵያ ከቆዳ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አለመሆኑ ተጠቁሟል። ለዚህም ደግሞ እንደ ተቋም የሚሠሩ ሥራዎች ኤክስፖርትን ያማከሉ እንዲሆኑ መደረግ አለበት ተብሏል። እንደ ሪፖርቱ ገለጻ ከሆነ ሆዳቻንና ሆራ፣ ጆርጅ ሹ፣ ባህር ዳር፣ ዛንግ፣ ባቱ፣ ኮልባና ፋሪዳ ያሉ የቆዳ ፋብሪካዎች ከእቅዳቸው 50 በመቶ በላይ አምርተዋል።

እንደ ፍሬንድሺፕ፣ ኤሊኮ፣ ዩናይትድ ቫሳን፣ ድሬ፣ ሼባ፣ ሞጆ፣ ኢስት አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ቆዳ ያሉት የቆዳ ፋብሪካዎች ደግሞ ከእቅዳቸው ከ50 በመቶ በታች አስመዝግበዋል ተብሏል። በተጨማሪም አዲስ አበባ ፣ገላን እና ዋልያ ምንም የውጪ ንግድ ያላስመዘገቡ ፋብሪካዎች እንደሆኑ በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጫማ አምራች ኩባንያዎች ከውጪ ንግድ የሚያኙት ገቢ 17.43 ሚሊዮን ዶላር እቅድ ተይዞ 3.86 ሚሊዮን ዶላር ማሳካት ተችሏል ተብሏል። የዚህን እቅድ 22.1 በመቶውን ማሳካት የተቻለው 462 ሺህ ጥንድ ጫማ ኤክስፖርት በማድረግ መሆኑ ለአዲስ ማለዳ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

ሁዋጂያን፣ ዮባንግና ጆርጅ ሹ በድምሩ 5.7 ሚሊዮን ዶላር ማለትም 43 በመቶ ከአጠቃላይ ኤክስፖርት ዕቅድ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን፣ በኮቪድ ምክንያት የምርትና ኤክስፖርት ሥራ በማቆማቸው ለአፈጻጸም ጉድለቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አሳድሯል ተብሏል። በቆዳ አልባሳትና እቃዎች ዘርፍ 6.9 ሚሊየን ዶላር ማለትም 51 በመቶ የተገኘ ሲሆን፣ ፓንግኩክ ባግ ማኑፋክቸሪንግ ፣ፒሲኢ ቬንቸር፣ ጆርጅ ሹ፣ ኤፍ አይ ኤፍ፣ ፍሬንድሺፕ ከፍተኛውን የኤክስፖርት ድርሻ መያዛቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። ለቆዳና ሌጦ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከተለያዩ አካላት ትኩረት አለመሰጠቱ አነስተኛ አፈጻጸም እንዲኖር መንስኤ ሆኗል ሲሉ ብርሃኑ አንስተዋል።

ለቆዳው ዘርፍ ትኩረት ያለመስጠት የሚለው ጉዳይ በዋናነት ከባንከ፣ ከጉምሩክ፣ ከሎጂስቲክ እና ከመብራት ኃይል አገልግሎቶች ጋር ይገናኛል። እነዚህ ተቋማት ማለትም ገንዘብ ከማበደር አንጻር፣ የመብራት መቆራረጥ ከመቀነስ እና የውጭ ንግዱን ከማቀላጠፍ አንጻር ተባባሪ በመሆን ዘርፉን ሊደግፉ እንደሚገባ ነው ብርሃኑ የገለጹት። የአምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በአግባቡ የውጪ ምንዛሬ እና ለሥራ የሚሆን መንቀሳቀሻ ብድር እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው የሚሉት ብርሃኑ፣ የግብዓት ማለትም የኬሚካል፣ የጨው እና የቆዳ አቅርቦት ችግር መቅረፍ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የቆዳ ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የቆዳና ሌጦ ፋብሪካዎች በከፍተኛ መጠን እንዲያመርቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ፋብሪካዎች በከፍተኛ መጠን የሚያመርቱ ከሆነ ቆዳ የሚያገኙበትን መንገድ ተመጣጣኝ ማድረግ ይገባዋል ያሉ ሲሆን፣ ቆዳ አቅራቢዎች ቆዳዎችን ሰብስበው ከ70 እስከ 80 ብር እየሸጡ ነው ብለዋል። ፋብሪካዎች የመግዛት አቅማቸው እስከ 50 ብር መሆኑ የሚታወቅ ስለሆነ ከዛ በላይ ገዝተው እንዲያመርቱ ማድረግ ከባድ መሆኑን ነው ያነሱት። አሁን ባለው ሁኔታ የተጣለ ቆዳ የሌለ ሲሆን፣ ነገር ግን የሚመጡት ቆዳዎችም በውድ እየተሸጡ ነው ሲሉ ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ብርሃኑ እንደገለጹት እንደ አገር ያሉብንን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት ለውጪ ንግድ ትልቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸው፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ በቀሩት ጥቂት ጊዜያት ፋብሪካዎች ያሉባቸው ችግሮች ተቀርፈው የውጪ ንግድ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ኹሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com