የእለት ዜና

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአትክልት ዘሮች ማምረቻ ተቋም ወደሥራ መግባቱ ተገለጸ

Views: 136

‹ቢ ኤስ ኤፍ› የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የአትክልት ዘሮች ማምረቻ ተቋም በመገንባት ወደስራ መግባቱ ተገለጸ። ድርጅቱ ይህን ተቋም የገነባው በአማራ ክልል በወሰደው 15 ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን፣ 416 ሚሊዮን ብር ወይንም 8 ሚሊዮን ዩሮ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ተቋሙ ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ ማወቅ ተችሏል። ቢ ኤስ ኤፍ የአካባቢውን ማሕበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ካለበት ኃላፊነት በመነሳት በዓለም ዙሪያ ያሉ ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተቋም እንደገነባ ታውቋል።

በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ከፍተኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአትክልት ዘሮች የሚያመርት ተቋም መገንባቱ ነው የተገለጸው። ተቋሙ በዋናነት ለበርበሬ፣ ለቲማቲም እና ኮሽም የሚሆኑ ዘሮችን ዓመቱን ሙሉ ማምረት እንደሚችል ታውቋል። ‹‹ይህንን ተቋም ለመገንባት 8 ሚሊየን ዩሮ ኢንቨስት የተደረገው በአለም ዙሪያ ደንበኞችን ለማገልገል፣ ተጨማሪ የአቅርቦት አስተማማኝነት ለመፍጠር ነው›› ሲሉ የቢ ኤስ ኤፍ የአትክልት ዘሮች ንግድ ምክትል ፕሬዝዳንት ቪሴንቴ ናቫሮ ለአዲስ ማለዳ በላኩት መግለጫ ጠቅሰዋል።

ቪሴንቴ አክለውም ‹‹ ዘላቂ የምግብ ዘሮች ምርት ለእኛ አስፈላጊ ስለሆነ እኛም የበኩላችንን መወጣት እንፈልጋለን። ለዚያም ነው በዚህ አዲስ ተቋም በጣም የምንኮራበት ነው ብለዋል።›› ‹‹እርጥበትን የሚቆጣጠር፣ ማሞቂያና መስኖን ጨምሮ የአየር ንብረት ቁጥጥርን ሙሉ በሙሉ በራሱ ስር የሚያከናውን የመጀመሪያ የሆነውን የዘር ማምረቻ ጣቢያ መገንባታችን በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ አድርጎናል›› ብለዋል። 15 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ተቋሙ ተጨማሪ ኹለት ሄክታር መሬት ደግሞ ለዘመናዊ ቤቶች እና የዘር ልማት ማምረቻ የሚውል ቦታ እንደሚኖረውም ተገልጿል።

በዚህ አዲስ ተቋም ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 60 የሚጠጉ ቋሚ ሠራተኞች እየሠሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም ቢ ኤስ ኤፍ ከ100 ለሚበልጡ ሠራተኞች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተነግሯል። አብዛኛዎቹ የሥራ አድል የተፈጠረላቸው ሰዎች በአካባቢው የሚኖሩ እና ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውም ታውቋል። በኢትዮጵያ የተገነባው ይህ የመጀመሪያው የዘር ማምረቻ ጣቢያ ለዘላቂ የግብርና ሥራዎች አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ትልቅ ስኬት መሆኑን፣ እንዲሁም ዘር ለሚወስዱ ደንበኞች በተሻለ ሁኔታ እንዲያገለግል ከማስቻሉም በላይ የአፍሪካን የገበያ ሁኔታ ያጠናክራል ሲሉ በአፍሪካ የገበያ ጥናት ኃለፊ ጁሊያና ሆስከን ወርኔክ ጠቁመዋል።

ጣቢያው አካባቢያዊ ጤናን እና ደህንነትን የሚያስጠብቅ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር ዘላቂ የግብርና ልማት ለማካሄድ ያስችላል ተብሏል። እንደዚህ አይነት ተቋም መገንባቱ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ እና በዋናነት ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለማመንጨት ያገለግላል ተብሏል።
በተጨማሪም ተቋሙ የራሱ የሆነ የፍሳሽ ውኃ ማጣሪያ ጣቢያ ስላለው የሚያመነጨው ቆሻሻ ሁሉ በቦታው ላይ እንደገና ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል መሆኑ ተገልጿል። ቢ ኤስ ኤፍ በአካባቢው ላይ የተለያዩ ማሕበራዊ ኃላፊነቶች በመውሰድ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ከእነዚህም ሥራዎች መካከል ዘርን ለኢትዮጵያ አነስተኛ አርሶ አደሮች ከማድረስ ባሻገር፣ በአካባቢው ለደን ልማት እና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ሥራ የሚሰራ ድርጅት መሆኑ ለአዲስ ማለዳ ከተላኩት መረጃዎች ማወቅ ተችሏል።

ድርጅቱ በጣቢያው ዙሪያ ላሉት ማሕበረሰብ ንጹህ የመጠጥ ውኃ በማቅረብ፣ አዳዲስ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት እና ኢንቨስት በማድረግ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚነትን እያሰፋ ይገኛል። ቢ ኤስ ኤፍ በፍጥነት እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ብዛት መሰረት በማድረግ ቀጣይነት ያለው የግብርና እና ጤናማ አካባቢዎችን የማልማት ሥራ የሚሠራ ሲሆን ከአርሶ አደሮች እና ከግብርና ባለሙያዎች ጋር አብሮ በመሥራት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ጥረት የሚያደርግ ተቋም መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ተቋሙ ዘሮችን እና ባህሪያቸውን፣ የኬሚካል እና ባዮሎጂካል የሰብል ጥበቃ፣ የአፈር አያያዝ፣ የእጽዋት ጤና እና ዲጂታል እርሻዎችን ለማስፋፋት ኢንቨስት በማድረግ የሚሰራ ተቋም ነው። ቢ ኤስ ኤፍ ዘላቂ የኬምስትሪ ውጤትን የሚፈጥር፤ ከ100ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት እና ኬሚካሎች፣ ቁሳቁሶች፣ የኢንዱስትሪ መፍትሄዎች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ አልሚ ምግብ እና የእርሻ እንክብካቤ የሚያሳድግ መሆኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com