የእለት ዜና

በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ተባለ

Views: 124

በቤት ለቤት አሰሳ ብዙዎች ተይዘዋል

የሳዑዲ አረቢያ ፖሊስ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያንን በአሰሳ መያዙን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንግልት እና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በአገሪቱ በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ ገብተው እየሰሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በአሰሳ አድኖ በመያዝ ከአገሪቱ እያስወጣ መሆኑንም ነው ያነሱት። በጉዳዩ ላይ ቃል አቀባዩ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም ረገድ በጅዳ እና ሪያድ ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶች ተገኝቶ የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ሊፈጠር ከሚችለው ችግር ዜጎችን ለመታደግ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ወደ አገር የመመለስ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በፖሊስ አሰሳ ተይዘው እንግልት እና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ መንግስት ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ ነው ብለዋል። የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን እያስወጣ ያለው ከሕዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ ለግብጽ ውግንና ይዞ ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና አመልክተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎቹ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሰነድ ማሳደስ ካልቻሉ ያላቸው ዕድል አገር መልቀቅ መሆኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ ወደ አገር ቤት ለመመለስም ከኢምባሲዎች የይለፍ ደብዳቤ ማግኘት አለባቸው ብለዋል።

በዚያው የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ለኢትዮጵያውያን ፓስፖርትና ሌሎች ሰነዶችን እያደሰና የይለፍ ደብዳቤ እየሰጠ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። ሆኖም በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኘው ኢምባሲና የቆንፅላ ፅህፈት ቤት የሚገሄዱት ችግር ሲያጋጥማቸው በመሆኑ ለዜጎች ትክክለኛውን ጥበቃና ክትትል ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኗል ነው ያሉት። በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከአካባቢው ማሕበረሰቦች ጋር በመሆን ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ መሥራቱን እንደሚቀጥል አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል።

የሳዑዲ ፖሊስ የውጭ አገር ዜጎች ይበረክቱባቸዋል ባላቸው ሆቴሎች፣ ሱቆችና የግንባታ ሥፍራዎች አሰሳውን እያካሄደ ይገኛል። በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት የመመለስ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም አግባብነት ያላቸው የፌዴራል ተቋማት የተሳተፉበት ኮሚቴ ከተለያዩ አገራት በርካታ ዜጎችን የመመለስ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም። በሳዑዲ የሚገኙ ቀሪ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚቻልበት መንገድ ላይ በልዩ ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ተፈላጊው ሂደት ተጠናቆም እነዚህ ችግሮች በቅርቡ መፍትሄ የሚያገኙ ይሆናል ብለዋል። በሳዑዲ እየታደኑ የሚያዙት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሙቀት ባለው አዳራሽ ውስጥ በርካታ ሆነው በመታጨቃቸው ለከፍተኛ ችግርና ስቃይ መጋለጣቸው ታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com