የእለት ዜና

በአዲስ አበባ አምስት ሺሕ ሰዎች ያለ አግባብ የሴፍቲኔት ድጋፍ ሲደረግላቸው እንደነበር ተገለጸ

Views: 177

አንድ ሺሕ 972ቱ በሞቱ ሰዎች የተጠቀሙ ናቸው

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሴፍቲኔት ቀጥታ ድጋፍ ፕሮግራም 4 ሺሕ 996 ሰዎች ያለ አግባብ ሲጠቀሙ መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። ከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር፣ በቀጥታ ድጋፍ ፕሮግራም ያለ አግባብ ተጠቃሚ የሆኑ 3 ሺሕ 24 እና በሞት የተለዩ ነገር ግን አገልገሎት የሚሰበሰብባቸው 1972 በአጠቃላይ 4 ሺሕ 996 ሰዎች መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ አበባ እሸቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቢሮው በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ መሥራት ለማይችሉ ዜጎች ከዓለም ባንክ በሚቀርብለት የገንዘብ ድጋፍ የቀጥታ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተረጅዎችን ለይቶ ተጠቃሚ ያደርጋል። ይሁን እንጅ በተለያዩ የአሠራር ከፍተቶች በቀጥታ ድጋፍ ለማግኘት ከሚያስፈልገው መስፈርት ውጭ ሆነው አገልግሎቱን ሲያገኙ የነበሩ ሰዎችን ቢሮው ማግኙቱን ጠቁሟል።

ዓለም ባንክ የቀጥታ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ለማድረግ ካስቀመጠው መስፈርት ውጭ ወይም ያለ አግባብ ሲጠቁሙ የተገኙ ሰዎች ከፕሮግራሙ ማስወጣቱንና በምትካቸው ሌሎች መስፈርቱን የሚያሟሉ ዜጎች የድጋፍ ተጠቃሚ እንድሆኑ መድረጉን አበባ ጠቁመዋል።
ቢሮው ያለ አግባብ ሲጠቀሙ ያገኛቸውን ሰዎች ከድጋፉ እንዲወጡ በማድረግ እስካሁን አራት ሺሕ 800 አዲስ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መደረጋቸው ተገልጿል። አዲስ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የሆኑት ዜጎች ችግራቸው ተለይቶ በተጠባባቂ መዝገብ ላይ የሰፈሩ ሲሆኑ፣ የመጀመሪያ ክፍያቸው የሆነውን የግንቦት ወር ድጋፍ ማግኘት ችለዋል ተብሏል።

ያለ አግባብ የቀጥታ ድጋፉን ሲያገኙ የነበሩ ሰዎች የተገኙት በተለያየ ምክንያት መሆኑን አበባ ጠቁመዋል። ከምክንያቶቹ መካከል የቀጥታ ድጋፍ ተረጅ ሆነው እራሳቸውን ችለው ከቤተሰብ የወጡ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጥተው ክፍለ አገር የሚኖሩ፣ ከተማ አስተዳደሩ በሚያስተዳድራቸው መርጃ ተቋማት ገብተው ድጋፉ ሲያገኙ የነበሩ፣ 18 ዓመት ሞልቷቸው የቀጥታ ድጋፍ ሲጠቀሙ የነበሩ የቤተሰብ አባላት፣ የት እንደሚኖሩ አድራሻቸው የማይታወቅና በሞት የተለዩ ሰዎች መሆናቸውን አበባ ገልጸዋል። ዓለም ባንክ የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ለሆነና መሥራት ለማይችሉ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች የሚያደርገው የቀጥታ ድጋፍ በመስፈርት ነው። ከመስፈርቶቹ መካከል በአንድ የቀጥታ ድጋፉ ተጠቃሚ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ እድሚያቸው ከ18 ዓመት በላይ የቤተሰቡ አባላት የቀጥታ ድጋፉ ተጠቃሚ መሆን አይችሉም። እንዲሁም የቀጥታ ድጋፉ ተጠቃሚ የሆነ ሰው ከሞተ ድጋፉ የሚደረገው ለሦስት ወራት ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ቀድሞ የነበረው መስፈርት ለአንድ ዓመት ነበር።

መንግሥት አረጋውያንን ለመደገፍና ለመንከባከብ ፖሊሲ ቀርፆ እየሰራ ነው ያሉት፣ አበባ እሸቴ የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ በሴፍቲኔት ፕሮግራም በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ከሆኑ 66 ሺሕ በላይ ዜጎች ውስጥ አብዛኛው አረጋውያን መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዓለም ባንክ በሚገኘው የሴፍቲኔት ፕሮግራም በቀጥታ ድጋፍ የሚያገኙ አዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች በወር በአንድ ቤተሰብ 360 ብር የሚከፈላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የነበረው ድጋፍ በአንድ ቤተሰብ ለአንድ ወር 300 ብር እንደነበር አበባ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com