የእለት ዜና

በሱማሌ ነዳጅ መኖሩ አልተደረሰበትም ተባለ

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ከዛሬ ሦስት አመት በፊት ተገኝቷል የተባለውን ነዳጅ ለማረጋገጥ ገና ፍለጋ ላይ መሆኑን የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ከሦስት አመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ የድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርት እንደምትጀምርና ይህ ደግሞ በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የሥራ አጥነት፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍና ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት እንደሚረዳት መግለጻቸው ይታወሳል። የተፈጥሮ ሀብቱ መገኘት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኢኮኖሚ በመሰረታዊነት ሊቀይር የሚችል ዕድል እንዳለውም ብዙ ተብሎለታል።

ይሁንና የዚህ የተፈጥሮ ሀብት መገኘትን ለማረጋገጥ ተጨማሪ የምርመራ እና የማፈላለግ ሥራን ለመሥራት የተለያዩ ድርጅቶች ፈቃድ ወስደው ሥራ መጀመራቸውን ነው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የገለጸልን። አዲስ ማለዳ የነዳጁ ማዕድን ያለበትን ዝርዝር ሁኔታ ለማጣራት ባደረገችው ሙከራ ጉዳዩን የማጣራት ሂደት ላይ እንዳለ የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ ተገኘ የተባለው ነዳጅ በምን ያህል ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ እና አዋጭነቱን ለማወቅ ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልጋል ብሏል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ መሰል ሌሎች አገራት የተፈጥሮ ሀብቱን ማግኘታቸውን ተከትሎ ያጋጠሟቸውን አገራዊ ውጥንቅጦችና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮቻቸውን መፍታት መቻላቸው ይታወቃል።

ነገር ግን፣ ይህ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የተፈጥሮ ሀብት መገኘቱን እና አለመገኘቱን ለማወቅ ገና ተጨባጭ ሁኔታ ላይ መድረስ አለመቻሉን ለመስማት ችለናል። ተጨማሪ ምርመራ እና ፍለጋ ለማድረግ የተሰማሩ ድርጅቶችም እስካሁን ምንም አይነት ውጤት ላይ እንዳልደረሱ ተሰምቷል። በተለይ ደግሞ የተፈጥሮ ሃብቱ ተገኘ በተባለበት ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለውን የነዳጅ እጥረት ችግርን ከምንጩ ሊያደርቅ እንደሚችል እና የኢትዮጵያን እድገትና ልማት ሊያፋጥን እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተሰንቆ እንደነበር ይታወሳል።

በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት የነዳጅ መገኘትን ተከትለው የሚከሰቱትን ሁነቶችን በተመለከተ “the three R’s” (Renter states, Rent-seeking and Repression) ብለው በሚጠሯቸው አበይት የሆኑ ሁነቶች ሳቢያ አስቀድመው ሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ገንብተው ያልጨረሱ አገራት ይህን የተፈጥሮ ሀብት ማግኘታቸው አገራዊ አደጋዎችን ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ማስገንዘባቸውንም መረጃዎች አመላክተዋል። ተገኝቷል ተብሎ ብዙ የተነገረለት ይህ ነዳጅ ወይንም የተፈጥሮ ሀብት መጨረሻ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አሁንም ጊዜ ይፈታዋል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!