የእለት ዜና

በአማራ ክልል በኹለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከገቡ 1447 ፕሮጀክቶች ሥራ የጀመሩት 225 ናቸው

Views: 168

በአማራ ክልል በመሠረተ ልማት ችግር በክልሉ የሚገኙ ኹለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የገቡ 1447 ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ሥራ መጀመር የቻሉት 225 ብቻ መሆናቸው ተገለጸ። በክልል መሠረተ ልማትና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች በሁለገብ ኢንዱስትሪ ወስጥ ከገቡት 1147 ውስጥ ወደ ሥራ ያልገቡ 1222 ፕሮጀክቶች ያሉበት ሁኔታ ግንባታቸው አልቆ በመሰረተ ልማት ችግር (በመብራት፣ በውኃና በመንገድ) ሥራ መጀመር ያልቻሉ፣ በቅድመ ግንባታ ላይ እያሉ ችግር የገጠማቸውና በግንባታ ላይ እያሉ መጠናቀቅ ሳይችሉ የቀሩ ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ ላለመግባታቸው ዋነኛ ምክንያት በመንግሥት እና በአልሚ ባለሀብቶች ችግር መሆኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይሄነው አለሙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደገለጹት ከሆነ፣ በዋናነት ፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ ያልገቡት በመንግሥት ችግር መሆኑን ጠቁመዋል። በመንግሥት በኩል ከሚታዩት ችግሮች መካከል ትክክለኛ ለማልማት የሚያስችል አቅም ያለው ባለሀብት ለይቶ አለማሰማራት፤ በኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሀብቶች እንደ ማበረታቻነት የሚያገለግሉ የብድርና የውጭ ምንዛሬ በታቀደው ልክ ማቅረብ አለመቻል፣ የኃይል አቅርቦት አለመኖርና በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ጠንካራ ክትትልና ግምገማ አለማድረግ የሚሉት ናቸው ብለዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ አለመግባት በኹለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ምክንያት በአልሚ ባለሀብቶች በኩል የሚስተዋል ችግር ሲሆን፣ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲጠይቁ የተጋነነና የውሸት ንድፈ ሃሳብ አንዱ በባለሀብቶች በኩል የሚታይ ችግር መሆኑን ይሄነው ጠቁመዋል። በተከታይነት የተቀመጠው የባለሀብቶች ችግር የተፈቀደ ማበረታቻን ለተፈቀደበት ዋና አላማ አለማዋል፣ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የተቀበሉትን መሬት በተለያዩ መንገዶች ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍና የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግሮች በባለሀብቶች በኩል የሚታዩ ለፕሮጀክቶች ወደ ሥራ አለመግባት ዋና ዋና ምክንያች መሆናቸው ተመላክቷል።

በክልሉ የሚታውን ችግር ለመፍታት የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የችግሮቹን መነሻ መሰረት በማድረግ አሠራሮቹን ለማስተካከል እየሠራ መሆኑን ይሄነው ጠቁመዋል። በዚህም በባለሀብቶች በኩል የሚታየውን የተጋነነ ወይም ውሸት ንድፈ ሃሳብ ለማስቀረት ከዚህ በፊት ሲጠየቅ የነበረው የባለሀብቶች ስደስት ወር የባንክ ዝውውር ወደ ሦስት ወር መሻሻሉን ጠቁመዋል። ይህ የሆነብት ምክንያት ባለሀብቶች ለፕሮጀክት መነሻ የሚያቀርቡት የባንክ ገንዘብ ዝውውር ሆን ተብሎ የሌለውን ያለ ለማሰመሰል ሲደረግ የነበረ ሙከራ መገኘቱን ተከትሎ ነው።

እንዲሁም ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲጠይቁ ያቀረቡትን ንድፈ ሃሳብ ተቀብሎ መሬት ከማስረከብ ይልቅ፣ ትክክለኛ ለማልማት አቅምና ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የማጣራት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል። ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈቃድ ሲጠይቁ 30 በመቶ የራሳቸውን ሀብት ይዘው ከመንግሥት 70 በመቶ ብድር እንደሚያገኙ የጠቆሙት ይሄነው፣ ክልሉ አቅም ሳይኖራቸው ፈቃድ የሚወሰውዱ ባለሀብቶችን ለማስቀረት የፕሮጀክቱን 10 በመቶ ገንዘብ በዝግ አካውንት ገቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ አሰራር መጀመሩን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በመሰረተ ልማት አቅርቦት ምከንያት ወደ ሥራ ያልገቡ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ለማስገባትና ችግሩን ለመፍታት በበጀት ዓመቱ 100 ሚሊዮን ብር በጅቶ እየሰራ መሆኑን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይሄነው አለሙ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። በዚህም በ2013 ባለፉት ዘጠን ወራት ውስጥ ቢሮው 110 የመንገድ፣179 የመብራት፣169 የውኃ፣ 126 የሊዝ ፋይናንንስና 137 የፕሮጀክት ፋይናንስ ችግሮችን እንደፈታ ተጠቁሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com