የእለት ዜና

ግጥምን በጃዝ የኪነጥበብ ምሽት መቀዛቀዝና መነቃቃት

የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የሚቀርቡበት ግጥምን በጃዝ የተሰኘዉ የመድረክ የኪነ-ጥበብ ፕሮግራም፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ የተወሰነ መነቃቃት እንዳሳየ የብራና የኪነ-ጥበብ ዋና አዘጋጅ በፍቃዱ አባይነህ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳም ከተለያዩ የኪነ-ጥበብ መድረኩ ዋና አዘጋጆች ጋር ቆይታ አድርጋለች። ከኮሮና በፊት ሰዎች በነጻነት የመዝናኛ ቦታዎች ይገቡ ነበር ፤ያሉን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የሬድዮ ዝግጅት ዋና አዘጋጅና የሰምና ወርቅ ባለቤት ጌታቸዉ አለሙ ናቸዉ። ከወረርሽኙ በፊት ግጥምን በጃዝ የተሰኘውን የኪነ ጥበብ መድረክ የሚያዘጋጁ 27 የነበሩ ቢሆንም፣ በተለያዩ ችግሮች የጥበብ ሥራዎቹን መስራት ማቆማቸዉን የሰምና ወርቅ የግጥም ምሽት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸዉ አለሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አንድ ኪነ ጥበብ ተሰርቶ እስኪቀርብ ከ 20 ሰዉ በላይ ይሳተፍበታል ። ይህም የኢኮኖሚያዊ አቅማቸዉንም ስለሚፈታተን ብዙ የኪነ ጥበብ መድረክ አዘጋጆች ማቆማቸዉን የብራና ኪነጥበብ ምሽት አዘጋጁ በፍቃዱ ይናገራል። አሁን ላይ ችግሩን ተቋቁመዉ በቋሚነት የሚሰሩ አራት የሚሆኑ የግጥምን በጃዝ አዘጋጆች እንዳሉ ተገለፀ ሲሆን፣ ጦብያ ግጥምን በጃዝ፣ ብራና የኪነጥበብ ዝግጅት ፣ ሰምና ወርቅ የኪነ ጥበብ ምሽት ናቸዉ።

ሥራዉን በቀዳሚነት በመጀመርና አስር አመቱን ያሥቆጠረዉ በምስራቅ ተረፈ የሚዘጋጀዉ ጦብያ ጃዝ ነዉ። ሌሎች የግጥምን በጃዝ የኪነ ጥበብ መድረክ አዘጋጆች ጦቢያ ሥራቸዉን ለመጀመር ምሳሌ እንደሆናቸዉ ይናገራሉ። ከሰላም ሚኒስቴር ፍቃድ በማዉጣትና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን የመከላከል ሥርዓቶችን በጠበቀ መልኩ ወደ ሥራዉ መመለሳቸዉን ጋዜጠኛ በፍቃዱ አስታዉቋል። አንድ አዳራሽ ወይም ሆቴል ሊይዝ ከሚችለዉ የሰዉ መጠን አንድ ሶስተኛዉን ብቻ ማስተናገድ እንዲችሉ ነዉ የተፈቀደላቸው። ለምሳሌ አንድ አዳራሽ 1000 ሰዉ የመቻል አቅም ቢኖረዉ፣ በወረርሽኙ ምክንያት ግን ከ300 እስከ 350 ሰዎች ብቻ ማስተናገድ እንደሚችል ነዉ።

ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ከ1000-1200 የመግቢያ ቲኬቶችን መሸጥ ይችሉ ነበር። ዝግጅቶቹም በብሔራዊ ቴአትር ከመሆናቸዉም ባሻገር ብዙ ጊዜ ታዳሚዎች ቦታ ሞልቶባቸው ይመለሱ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከወረርሽኑ መከሰት በኋላ ወደ 300 የመግቢያ ትኬቶች እንደሚያሳትሙ የኪነ-ጥበብ መድረክ ዋና አዘጋጆች ይናገራሉ። ከዚህ በላይ እንዳያሣትሙ የሚቆጣጠሩ የሰላም እና ጤና ሚኒስቴር አሉ። ከእነዚህም በተጨማሪ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችና አዳራሾች ከተፈቀደዉ ቁጥር ዉጪ እንደማይፈቅዱ ተመላክቷል።

ታዳሚዎች ወደ ዝግጅቱ ሲገቡ የኮቪድ 19 የመከላከል ሕግን በጠበቀ መልኩ ነዉ። የወንበሮች አቀማመጥ ጨምሮ ርቀት እንዲኖራቸዉ እተተደረገ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ባደረገቸዉ ዳሰሳ ተገንዝባለች። የአንድ ትኬት ዋጋ 100 ብር የነበረ ሲሆን፣ በአንድ መድረክ የትኬት ሽያጭ 300 ወይም 350 ብር እንዲሆን ምክንያቱ የወረርሽኙ ተጽእኖ እንደሆነ ታዉቋል። የታዳሚዎች ቁጥር ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ መቀነሱ ደግሞ ለኪነ-ጥበብ መድረክ አዘጋጆቹ ኪሳራ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። አብዛኞቹ ግጥምን በጃዝ አዘጋጆች የመድረክ የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸዉ ትኩረት የሚያደርጉት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ነዉ።

አንድነት፣ መቻቻል፣ መከባበር እና ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ማዳበር ላይ የተመለከቱ የጥበብ ሥራዎች በመድረኮቹ እንደሚቀርቡ አዘጋጆቹ ይናገራሉ። ወቅቱ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን የሚሸረሽሩ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል ። የዝግጅቶቹ ዓላማ ሕዝቡ ወደ አገራዊ አንድነት እንዲመጣ፣ ሰላምን እንዲያዉቅ፣ እንዲሰብክ፣እንዲረዳ፣ እንዲተባበርና አብሮ የመኖር እሴቶቹን እንዲያዳብር የሚረዱ ሥራዎችን ኪነ-ጥበቡ እያዝናና የሚያሥተምርበት የጥበብ መድረክ መሆኑን አዘጋጆቹ ይገልጻሉ። በዚህ ረገድም ይህ የኪነጥበብ መድረክ ትልቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለን እናስባለን ሲሉ የመድረኩ አዘጋጆች ይናገራሉ። በየመድረኩም ሕዝቡን ለማስተማር እና ለማዝናናት ግጥሞች፣ ወጎች፣ ዲስኩሮች፣ መነባንቦች፣ ሙዚቃዎች ለታዳሚያን እየቀረቡ እንደሚገኝ ጋዜጠኛ በፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።

በሌላ በኩል ወደ ተለያዩ ክፍለ አገሮች እየሄድን የኪነ-ጥበብ ሥራዎቹን እንድናቀርብላቸዉ ጥያቄዎቻቸዉን በኢሜል፣ በፌስ ቡክ፣ በስልክ እና በተለያዩ መንገዶች ያቀርባሉ። ጥያቄ ይኑር እንጂ ሄደን ስንሞክረዉ የተሳታፊዉ ቁጥር ያን ያክል አይደለም ይላሉ የመድረኩ አዘጋጆች። ብዙ ሕዝብ በሚገኝባቸዉ ትላልቅ ከተሞች በፕሮግራሙ አዘጋጆችና በየከተሞቹ በሚገኙ ተወላጆች ተሞክሮ አለመሳካቱን የብራና ኪነ ጥበብ አዘጋጁ ይገልጸል። ለአብነትም በደሴ፣ በአዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በሰመራ፣ በጅማ፣ በድሬደዋና ሐረር ከመጻሕፍት  ርቃዎች ጋር በማያያዝ ለማቅረብ ተሞክሮ ወረርሽኑ እና የገንዘብ አቅም እንቅፋት እንደሆነበት የሰምና ወርቅ አዘጋጁ ለጋዜጣ ክፍላችን ገልጿል።

ማንም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ሲንቀሳቀስ በዘርና በኃይማኖት የታጠረ እንዳይሆን በኪነ ጥበቡ እንደሚያስተምሩ ይናገራሉ። ማሕበረሰቡም ከእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ እንዲወጣ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል። አሁን ባለዉ ሁኔታ የኪነጥበብ መድረኮቹ አዲስ አበባ ላይ በዋናነት እየሰሩ እንደሚገኙ ይታወቃል። በተለያዩ ክፍል አገሮች እየሄዱ እንዳይሰሩ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቅሱት ሌሎች ምክንያቶች ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ፣ የአዘጋጆቹ የኢኮኖሚ አቅም ማነስ ናቸዉ። በቀጣይም የተለያዩ መነቃቃቶችን በየክፍለ አገሮቹ በመፍጠር የተሻለ ለመስራት ሃሳብ እንዳላቸዉ የኪነ ጥበብ አዘጋጆቹ አስቀምጠዋል።

እነዚህ የጥበብ መድረኮች የኢኮኖሚ አቅማቸዉን የሚገነቡት ከትኬት ሽያጭ እና አልፎ አልፎ ከሚደግፏቸዉ ስፖንሰሮች ነዉ። ለኹሉም ሙያተኛ ቢከፈል የሚገኘዉ ገቢ በቂ አለመሆኑም ተገልጻል። በሙያቸዉ በበጎ ፍቃደኝነት የሚያገለግሉ የጥበብ ባለሙያዎች መኖራቸዉ ያለባቸዉን የገንዘብ እጥረት እንደሚቀርፍላቸው ይናገራሉ። በአንድ የኪነጥበብ መድረክ ከ60 እስከ 70 ሺህ ብር ለሆቴል ኪራይ፣ ለባንድ፣ ለሳዉንድ ሲሰተም፣ ለባነር፣ ለትኬት ህኅትመት፣ ለሽያጭ ሰራተኞች ክፍያ ፣ለእንግዶች ክፍያና ለሌሎችም ነገሮች ወጪ እንደሚደርጉ ለማወቅ ተችሏል።

አብዛኞቹ አዘጋጆች እንደሚገልጹት ዋነኛ ዓላማቸዉ ትርፍ ማግኘት ሳይሆን ማሕበረሰብን በኪነ-ጥበቡ ማንቃት እና ማስተማር ነዉ ይላሉ። ይህንን በጎ አስተሳሰብ አውቆ የሚደግፋቸዉ አካል ቢያገኙ ከዚህ በላይ ይበልጥ የማሕበረሰቡ ንቃተ ህሊና ላይ መሥራት እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። መንግሥት እና የተለያዩ የሚመለከታቸዉ የግል ተቋማት ይህን የኪነ-ጥበብ መድረክ እንዲያግዙ ጥያቄ ቢቀርብላቸዉም፣ በጀት የለንም የሚል ምላሽ እንደሚሰጧቸዉ ሰምተናል። በሌላ በኩል፣ የተለያዩ ሚዲያዎች ስራዎቻቸዉን በመቅረጽ እና ለሕዝቡ በማስተላለፍ አብረዉ እየሰሩ መሆኑ ተጠቁሟል። በተለይም የግል የቴሌቭዥን፣ የሬድዮ ፣የኅትመት እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከጎናችን በመሆን ዝግጅቶቻችን ያስተላለፋሉ ሲሉ ይገልጻሉ።

የመንግስት ሚድያዎች በብዛት ሲጋብዟቸዉ ባይገኙላቸውም ኢዜአ እና ዋልታ እንደሚተባበሯቸው ተናግረዋል ። በአጠቃላይ ሚዲያዉ ባይኖር የኪነ ጥበብ ዝግጅቱ በሕዝቡ ዘንድ ተረስቶ መቀጠል አይችሉም ነበር። ኹሉም የግልም ሆኑ የመንግሥት ሚዲያዎች በመዝናኛ ዝግጅቶቻቸዉ የመድረክ የኪነ ጥበብ ሲራዎችን ቢያቀርቡ ሕዝቡን ያስተምሩባቸዋል የሚል ጥቆማ ሰጥተዋል። በተለይም መንግሥት ይህን የኪነ ጥበብ ዝግጅት ድጋፍ ቢያደርግለት ከዚህ በተሻለ መልኩ ለኹሉም አካባቢዎች ማዳረስ ይቻላል ብለዋል። የጥበብ መድረኩ ለየትኛዉም ድርጅት ወግኖ የሚሰራ ሳይሆን፣ የሚስማማንንም ሆነ የማይስማማንን ሃሳብ ለታዳሚዎች በማድረስ እና እንዲያደምጡ ማስቻል እና ተሳታፊዎች የተመቻቸዉን ሃሳብ የመዉሰድ ያልፈለጉትን ደግሞ የመተዉ እድል እንዲፈጠርላቸዉ እና ሃሳብ እንዲሸራሸር ነዉ ይላሉ የጥበብ መድረኩ ባለቤቶች።

አብዛኞቹ የኪነ ጥበብ መድረክ አዘጋጆች በኪሳራ እንደሚሰሩ በፍቃዱ አባይነህ ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል። ጥበብ ከለላ የለዉም፤አጋዥ የለዉም ይላል የሰምና ወርቅ የግጥም ምሽት አዘጋጁ ጋዜጠኛ ጌታቸዉ። በኪነ ጥበብ መድረኩ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ኮርኳሪ፣ አሰላሳይ ሃሳብ ጠያቂ ፣ አልፎ አልፎም ራስን ወቃሽ አይነት ናቸዉ። ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነትን ለሚያደምጡ መድረኩ ይበልጥ እድል ይሰጣል። ለሚነሱ ሃሳቦችም ጥበብን፣ ባህልን፣ ታሪክን፣ ፍልስፍናን፣ እና ንባብን የሚወዱ ሰዎች የኪነ-ጥበብ ምሽቱ ቤተሰብ ናቸዉ።

በተለያየ አካባቢ ያለዉን ማህበረስብ ለማየት ሙከራ ማድረጋቸዉን ይናገራሉ። አራት ኪሎ አካባቢ ጥበብ እና ንባብ በደንብ የሚሸራሸርበት አካባቢ ነዉ። ቅርስ ጥናት ፣ሙዚየም፣ ስፖርት እና ሌሎችም ታሪካዊ ነገሮች በአካባቢዉ ይንጸባረቃሉ። ይህም ተሞክሮ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋፈት እነዚህ መድረኮች የሚጠበቅባቸወን ሚና እንዲወጡ እየሞከርን ነዉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አዉግተዋል። ለዚህም ማሳየዉ የአራት ኪሎን መንፈስ በብሔራዊ ቴአትር ፣በኢትዮጵያ ሆቴል፣ በዋቢ ሸበሌ፣ በራስ እና በኤልያና ሆቴል አካባቢዎች የኪነ ጥበቡ ማዕከል በማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። አካባቢዎቹ ለትራንስፖርት ለሁሉም አካባቢዎች ምቹ ከመሆናቸዉ አንጻር መመረጣቸዉን አስታዉቀዋል። በአዲሱ ገበያ አካባቢም የሚገኝ ከግጥምን በጃዝ ቀጥሎ ሀዋዝ የሚባል በርካታ ወጣቶች የሚሳተፉበት የጥበብ መድረክ መኖሩን ጋዜጠኛ ጌታቸዉ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቋል።

ደራሲዎች፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ወጣት ገጣሚዎችን ከሚወዱዋቸዉ የጥበብ ቤተሰቦች ጋር የማገናኘት ስራ እየሰሩ እንደሆነ የሰምና ወርቅ አዘጋጅ ጌታቸዉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረዉ ቆይታ ገልጻል። ምሁራን ሃሳባቸዉን እንዲገልጹ መድረኩ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል። ምሁራን የታሪክ ፣ የፖለቲካ ፣የፍልስፍና፣ የኃይማኖት፣የጥበብ ሰዎች መድረኮቻቸዉን በቁም ነገር እንደሚያዋዙላቸዉ ይገልጻሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com