የእለት ዜና

እስቲ ይለፍ ሲባል የነበረ ምርጫ

Views: 131

በብዙ መልኩ በተለያየ ስሜት ሲጠበቅ የነበረው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ተከናውኗል። እርግጥ ነው! ጉዳይ አለኝ ከሚለው አካል ኹሉ የሚነሱ ብዙ መግለጫዎች፣ ይፋ የተደረገውን ውጤት መነሻ የሚያደርጉ ሙግትና ክርክሮች፣ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚቀጥሉ የምርጫ ሂደቶች ገና መንገድ ላይ ናቸው። ያም ሆኖ ግን እንደተባለው በተለያየ ስሜት ሲጠበቅ የነበረውን ዋናውና አንዱን የምርጫ ክፍል ተሻግረናል።

ታድያ ምርጫው እንደምን ነበር? የምርጫ ካርዳቸውን ሌሊት ይዘው ወጥተው፣ ውለው አምሽተው፣ ድምጻቸውን ሰጥተው ሌሊት ወደየቤታቸው የገቡ ሰዎች ድካሙ ቀላል እንዳልሆነ መጥቀሳቸው አይቀርም። ከአንዳንድ የተጓተቱ ሂደቶች የቀጠለ እንግልትም፣ ከአየሩ ጸባይና ከሰልፍ ርዝመት የተከተለ ድካምና የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ካለመረዳት የመጣ ግራ መጋባትም የተሰማቸው ሰዎች ነበሩ።

እንዲያም ሆኖ አለፈ! የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደገሰው ድግስ ‹ኧረ ወጥ ጨምሩ! ኧረ ሌማቱ ባዶ ሊሆን ነው! ኧረ እዚህ ጋር ጨው ያንሳል!› ቢባልበትም፣ አሳላፊዎቹ ያለእረፍት እየባተሉ የጎደለውን ለማሟላት ደፋ ቀና ሲሉ ታይተዋል።
እያፈረሱ መሥራት ቀርቶ የተጀመረውን ጥሩ ጅምር ማስቀጠል ከተቻለ፣ ይህኛው የ2013 ምርጫ ቦርድ አዳጊ የሚባልና በቀጣዩ ምርጫ እንከኖችን በፍጹም ቀንሶ የሚገኝ ተቋም እንደሚሆን እሙን ነው። የድምጽ መስጫ ወረቀቶች አለመዳረስ እና የአስፈጻሚዎች በቶሎ በቦታቸው ላይ አለመገኘት ለምሳሌ ጥቂቶቹ ናቸው።

የምርጫ አስፈጻሚዎች ድካምና ልፋታቸውን ሳንዘነጋ፣ አንዳንዶች ግን ሥልጠና፣ ለተመደቡለት ሥራ ታማኝነትና ቀና መሆን እንዲዋሃዳቸው ሥልጠናዎችና ትምህርቶች ከዓመት ቀድሞ ቢሰጥ ያሰኛል። ብርቱ የምርጫ አስፈጻሚዎችና ጠንካራ ታዛቢዎች ባሉባቸው ቦታዎች መጭበርበሮችን መከታተልና መቀነስ አስቸጋሪ ስለማይሆን።

በድምሩ ለወደፊት ብዙ ትምህርት ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራት በእርግጥ ተስተውለዋል። በተለይም የመራጮች ጽናትና የድምጽን ዋጋ መረዳት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ማልደው ተሰልፈው እስከ እኩለ ቀንና ከዛም በላይ ያመሹ፣ አመሻሽ ላይ በተከፈቱ ጣቢያዎች ጠብቀው ድምጽ የሰጡ ጥቂት አይደሉም።

በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ይልቁንም በፌስቡክ ብዙዎች የቆሙባቸውን ሰልፎች ርዝመት፣ የቆዩበትን ሰዓትና የታዘቡትን ሲያሰፍሩ ነበር። ልጅ ያዘሉ እናቶች፣ ከዘራና መቋሚያ የተመረኮዙ አረጋውያን፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ሰብሰብ ያሉ ወጣቶች፣ ባለሥልጣናትና የመንግሥት የተለያየ ሥራ ኃላፊዎች፣ ምስላቸውን ብዙዎች ሲጋሩት ከነበሩት መካከል ይገኛሉ።

ለሁሉም ግን ‹ቆይ ምርጫው ይለፍና› እያልን ብዙዎቻችን ለይደር ያቆየናቸውን እቅዶች መከወኛ ግድ የሚል ጊዜ መጥቷል፤ ምርጫው በደኅና አልፏል። ደግሞ ‹ኧረ ቆይ ውጤቱ ሁሉ ጨርሶ ይሰማ!› የምንል ካልሆንን በቀር፣ ከዚህ በኋላ ይህኛውን ምርጫ ድኅረ ሂደቱንም ጨራርሶ ጓዙን ጠቅልሎ መሸኘት ብቻ ነው የቀረው። ከዚህ በኋላም ሁሉም በሰላም እንደሚጠናቀቅ ተስፋ እናደርጋለን።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com