የእለት ዜና

የኮሮና ወረርሽኝ የተረሳበት የደምጽ አሰጣጥ

Views: 138

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረውን 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ማድረጉ ይታወሳል። በወቅቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በገለልተኛ ተቋማት አማካይነት ይህ ወረርሽኝ እየተስፋፋ መሄዱ ተገምግሞና በወቅቱ ምርጫ ማካሄድ ከባድ መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሶ ሂደቱ እንዲራዘም መደረጉ የሚታወቅ ነው።

ይህ ምርጫው እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዘንድሮው ዓመት የምርጫ ወቅት ተረስቶ የተስተዋለበት ሁኔታ ታይቷል። ኮቪድ 19 በምርጫ ሥራዎች እና በምርጫ አፈጻጸሙ ላይ ያደረገው ተጽእኖ በግልጽ ሲታይ ቆይቷል። አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ እና ደብረ ብርሃን የሚገኙ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ባደረገችው ዳሰሳ አብዛኛው የሚባለው የሕብረተሰብ ክፍል የኮቪድ 19 መተላለፊያ መንገዶችን አውቆ ጥንቃቄ ሲያደርግ አላስተዋለችም። በዚህም መሰረት ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያ አካባቢዎች አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ፣ ማክስ አለማድረግ፣ ቁሳቁሶችን በጋራ የመጠቀም እንዲሁም በአንድ ቦታ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው መገኘት አዲስ ማለዳ በሰፊው ታዝባለች። በተለይ ደብረ ብረሃን ተገኝታ ያደረገችው ምልከታ ማሕበረሰቡ ዘንድ የነበረው የኮቪድ19 ፍረሃት ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ከፍተኛ መዘናጋት የተስተዋለበትን ሁነት ነበር።

ኮቪድ 19 ሊኖረው የሚችለው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ፣ ማኅበራዊ ውጥረቶችን እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ሊጨምር ይችላል። በዚህም የተነሳ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ያለመረጋጋት ስጋቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ኮቪድ 19 ስርጭት መከላከል ጋር የተያያዙ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ እና በአንድ አካባቢ የሚሰበሰቡ ሰዎች ቁጥር ላይ ገደብ ማድረግን የመሳሰሉ እርምጃዎች የምርጫ ሥራዎች በተከናወኑበት ጊዜ ላይ ተፈጻሚ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የአካል ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ከአልኮል የተሰሩ የእጅ ማጽጃዎች፣ የፀረ-ተህዋሲ ርጭት ማድረግ የመሳሰሉት በመራጮችም ሆነ በአስፈጻሚዎች በኩል እንደሚፈለገው መጠን ሲተገበሩ አልታየም።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ አደረኩት ባለው ዳሰሳ መሰረት፣ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በሕዝቡም ሆነ አስፈጻሚዎች በኩል የጥንቃቄ ጉድለቶች መታየታቸውን አስታውቋል። በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ የሚኖረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጥንቃቄ መተግበር ሲገባው ይህ ሳይሆን ቀርቷል። የኅብረቱ ታዛቢዎች በምርጫ ሂደቱ የድምጽ አሰጣጥ መመሪያዎች መከበርን፣ በድምጽ አሰጣጡ ወቅት የኮቪድ 19 መመሪያዎች መከተልን እንዲሁም የመራጮችን ጥንቃቄ በጣቢያው ተገኝተው ታዝበዋል።

በዚህም መሰረት ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ 20 በመቶ ያህሉ የሚሆኑት የኅብረቱ ታዛቢዎች በተኙባቸው ጣቢያዎች የነበሩት 53 በመቶ ያህሉ ሰልፎች አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ እንዳልተዋቀሩ ገልጸዋል። በምርጫ ቦርድ መምሪያ መሰረት ታዛቢዎች በኮቪድ 19 ምክንያት እስካልሆነ ድረስ በምርጫ ጣቢያው በመገኘት ሙሉ የምርጫ ሂደቱን የመታዘብ መብት እንዳለቸው ተደንግጓል። በዚህ መሰረት በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት 94 በመቶ ማለትም 1975 የሚሆኑ የኅብረቱ ታዛቢዎች፣ የምርጫ ሂደቱን ያለገደብ መታዘብ መቻላቸውን የተሰበሰበው መረጃ ያሳያል።

ይሁንእንጂ ከኮቪድ 19 መመሪያ ጋር ባልተያያዙ ምክንያቶች 12 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች በድምጽ አሰጣጡ ወቅት የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲቆዩ አልተፈቀደላቸውም። ከዚህ በተጨማሪ 119 የሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የኅብረቱ ታዛቢዎች በኮቪድ 19 መመሪያ ምክንያት የምርጫ ጣቢያዎቹን ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውን ተናግረዋል። በኅብረቱ ኹሉም እውቅና የተሰጣቸው ታዛቢዎች በምርጫው ሂደት እንዲካፈሉ የሚጠብቅ ቢሆንም፣ በምርጫ ጣቢያዎች አወቃቀር ምክንያት እንዲሁም ኮቪድ 19ን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከድምጽ መስጫ ጣቢያው እንዲለቁ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ይታወቃል።

በተለያዩ አለማት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የምርጫ ሂደት መከናወኑ ይታወሳል። የቅርብ ጊዜ ትውስታ ከሆነው መካከል የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርን ለመምረጥ የተካሄደው ምርጫ አንዱ ነበር። በዚህ ምርጫ ላይ የኮቪድ 19 ጥንቃቄ ሲደረግ ብዙም ባይስተዋልም የቁሳቁስ መገልገያዎችንና አጠቃቀም በተመለከተ በአንጻራዊነት ከኢትዮጵያ የተሻለ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ታይቷል። በተጨማሪም የኮቪድ 19 የተከሰተ ዓመት ላይ ተካሂዶ የነበረውን የአሜሪካን ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ማስታወስ ይቻላል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ አንፃር ቀጣይ በቀጥታ ከምርጫ ጋር የተገናኙ የአሠራር እቅዶችን ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል።

ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት የሚወሰዱ እርምጃዎች በምርጫ አፈጻጸም ሂደት ተግዳሮት እንደፈጠሩ ይታወቃል። በአገራችን ተግዳሮቶቹ ከፍተኛ የሆኑበት ምክንያት የምርጫ ሂደቱ ዋና ዋና ሥራዎችን በተለይም የመራጮች ምዝገባ፣ የዕጩ ምዝገባ እንዲሁም ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በአነስተኛ የቴክኖሎጂ እገዛ እንዲከናወኑ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል። የምርጫ ሥራው ስፋት፣ ካሉት የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች እንዲሁም የደህንነት እና የልማት ሁኔታዎች ዝቅተኝነት አንጻር ሲታይ፣ በሌሎች አገሮች እየተተገበሩ ያሉ በበይነ-መርበ (ኦንላይን) መራጮችን መመዝገብ፣ በፖስታ ድምፅ የመስጠት እና የኤሌክትሮኒክ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት የመሳሰሉት ተግባራት ሊከናወኑ አልቻሉም።

በአጠቃላይ ድምፅ የመስጫው ቀን የተስተዋለው የጥንቃቄ ጉድለት እየቀነሰ ላለው የኮቪድ19 ወረርሽኝ ስርጭት እንቀፋት ሊሆን ስለሚችል ስርጭቱ በምርጫው ሂደት እንዳይጨምርና ወደፊት የባሰ ደረጃ ላይ እንዳደረስ ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት መደረግ ይገባዋል። ጳጉሜ 1 ለሚካሄደውም ቀጣዩ ምርጫ ያለፈው ጉድለት ትምህርት ተወስዶበት የጎደለው መስተካከል ይገባዋል።ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com