የእለት ዜና

ቀጣዩ ምዕራፍ ተስፋ እና አደራ

Views: 105

6ተኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቁን ተከትሎ በውጤቱ መሠረት መንግሥት የሚሆን አካል የሚጠበቅበት ብዙ ነገር አለ። ከምርጫ በፊት የተገባ ቃልን በማክበር፣ እንዲሁም የሕዝብን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሻሻል ካለባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የአገር ሰላምና አንድነትን ማስጠበቅ ዋናው መሆኑ እሙን ነው። ላለፉት 30 አመታት የተበላሸውን ታሪካችንን ለማደስና የእርስበርስ ልዩነታችንን ለማስተካከል የሕገ መንግስቱ መሻሻል ዋና ጉዳይ መሆኑን ታዬ ብርሃኑ (ዶ/ር) በጽሁፋቸው እንዲህ አስቀምጠውታል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለአገራችን ታሪካዊ የምርጫ ቀን ሁና አልፋለች። ታሪካዊነቷ ምርጫ በመካሄዱ አይደለም። ምርጫው ካለፉት የምርጫ ጊዜያት እጅጉን የተለየ በመሆኑም አይደለም። ታሪካዊነቷ የተዋጣለት ዲሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ እና ፍትሃዊ ምርጫ በመካሄዱ አይደለም። ለታሪካዊነቷ መገለጫ ከሆኑት ክስተቶች ዋነኞቹን ለመጥቀስ ያህል፡-

  • በአገራችን በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫው በመላ አገሪቱ ያለመካሄዱ፣
  • የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አደረገ እንደተባለው ለመምረጥ ሕጋዊ መብት ያለው 50 ሚሊዮን ሕዝብ ቢሆንም ለምርጫ የተመዘገበው 37 ሚሊየን መሆኑ፣
  • ምርጫው በጸጥታና በአንዳንድ የአፈጻጸም ግድፈቶች ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ለሌላ ጊዜ – ለጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም መተላለፉ፣
  • ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ምርጫው በኮቪድ ወረረሽኝ ምክንያት የተላለፈ ቢሆንም አማራጭ የለምና ኮቪድን እየታገሉ ምርጫ የግድ መሆኑ፣
  • ምርጫው ካልተካሄደ በማለት ይወተውቱ የነበሩ አንዳንድ ፖለቲከኞች ምርጫውን ለማካሄድ ቁርጥ ሲሆን ደግሞ የከረረ ተቃውሞ ያሰሙበት ሁኔታ መስተዋሉ፣
  • የውጭ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ምርጫው እንዳይካሄድ ለማድረግ እና አገራችን ወደ ዲሞክራሲ እና ልማት የምታደርገውን ጉዞ ለማደናቀፍ የተረባረቡበት ወቅት መሆኑ እና
  • የፖለቲካ እስረኞች እስር ቤት ታጉረው ለውድድር እንዲቀርቡ መደረጉ ናቸው።

ከላይ እንደተጠቀሰው ከዓመት በፊት በኮቪድ ምክንያት ምርጫ መተላለፉ ይታወቃል። ኮቪድ አሁንም አለ። መቼ እንደሚወገድ አልታወቀም። ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይቀርም እንዲሉ ኮቪድን አንደ አመጣጡ መቋቋም የግድ ሆነ። ከኮቪድ በፊት ጀምሮ ለሦስት አስር ዓመታት ሲያናውጠን የቆየው የእርስ በርስ ችግራችን ተባብሶ ይገኛል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የውጭ ጠላቶቻችን የተፈጠረላቸውን አጋጣሚ ተጠቅመው የፕሮፓጋንዳ፣ የኢኮኖሚ ዕቀባ እና የማስፈራሪያ ዘመቻ እያደረጉ ነው። የአካባቢ ጠላቶቻችንን እና ጸረ-ኢትዮጵያ ወገኖቻችንን እያደፋፈሩ ነው። ለነገሩ የእርስ በርስ ችግር ጠንሳሾች እና ፈጣሪዎች በዋናነት የውጭ ኃይሎች አይደሉምን!

በዚህ የውስጥና የውጭ ውጥረት ሆኖ ምርጫ መደረጉ የኢትዮጵያ ሕዝብን ብሩህ ተስፋ፣ ትዕግሥት እና ቆራጥነት የሚያረጋግጥ ነው። ለሰላም እና ለአንድነት ያለውን ጽኑ ዕምነትና አቋም የሚያሳይ ነው። በየትኛውም መስፈርት ሕዝብ ተወካዮቹን መምረጡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመጓዙ ጉልህ ማሳያ ነው። በዚህ አጣብቂኝ ወቅት ሕዝብ የመንግሥትን ሥልጣን የሚይዙ ተወካዮቹን መምረጡ የሚደነቅ እና የሚበረታታ ተግባር ነው። ግን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የአለቆቻቸውን የውስጥ እስትንፋስ በመተንፈስ ኢትዮጵያ ጠልነታቸውን አሳይተውናል።

ለጠላት ደስ አይበለውና ቅድመ ምርጫ ዝግጅቱ ተጠናቆ ምርጫው ከእንዳንድ ተግዳሮቶቹ ጋር በሰላም መጠናቀቁ በራሱ ትልቅ አገራዊ ውጤት ነው። ቀጣዩ ሥራ የምርጫውን ውጤት ማሳወቅ ነው። ሌላው ምርጫ ባልተካሄደባቸው እና እንደገና ምርጫ እንዲካሄድባቸው በተወሰኑባቸው ቦታዎች ምርጫውን ማካሄድ ይሆናል። በአሁኑ ምርጫም ሆነ በሚቀጥለው የሚገኝን ተገቢ ውጤት መቀበልና ማክበር የኹሉም ተወዳዳሪዎች አገራዊ ግዴታ ነው። በመሆኑም የምርጫ የክንውን ሂደቶች ተጠናቀው አሸናፊው ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች ይፋ ከሆነ/ኑ በኋላ የሚቀረው ትልቁና ዋናው ቀጣዩ የሥራ ምዕራፍ የሕዝብን ተስፋና አደራ ተቀብሎ መንቀሳቀስ ነው።

ቀጣዩ ምዕራፍ
ዲሞክራሲያዊ መብት በምርጫ አያቆምም። ሂደቱ ቀጣይ እና ፈታኝ ነው። የመጀመሪያው በአግባቡ እና ካለአንዳች ሕጋዊ ጥሰት በተገኘ ውጤት የመንግሥትን ሥልጣን የሚረከብ ፓርቲ የሕዝብን ተስፋና አደራ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እና በቆራጥነት መነሳት ይኖርበታል። ቀደምት፣ ነጻ እና በቅኝ ግዛት ያልወደቀች ኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት በቅኝ ገዥዎች የከፋፍለህ ግዛ ስውር ደባ ተጠልፋለች። በቅኝ ገዥዎች የከፋፍለህ ዘይቤ ሲማቅቁ የኖሩ የዓለም አገራት ነጻነታቸውን በአንድነት ሲያጣጥሙ የአንድነት ተምሳሌቷ ኢትዮጵያ በልዩነት ቋንቋ ተዘፍቃ በዘግናኝ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ጥቁር በጥቁር ላይ የዘረኝነት ፖሊሲን በማራመድ የአገር መዘባበቻ ሆናለች።

ጥንካሬዋን፣ ዕድገቷን እና ልማቷን ማየት የማይሹ ምቀኞች እና ጠላቶች አንገት መቁረስ አልበቃቸውም። በሕገ መንግሥት የተከለችውን ልዩነት ተጠቅመው ለደረት፣ እጅ እና እግር ቆረጣ ተዘጋጅተዋል። ዛሬም እንደትናንቱ ለማስፈጸሚያነት የጎሣ ክፍፍሉን እያጦዙ ነው። ልማትን ለማደናቀፍ ግድባችንን እንዳናጠናቅቅ ደባ እየፈጸሙብን ነው። በሱዳን ሉዓላዊነት ተደፍሯል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ይበልጥ ያንገፈገፈው የሩቅ ጠላቱ ሳይሆን አስፈጻሚው የራሱ ወገን ነው። ከጣሊያን በባሰ የተዘራው የከፋፋይ ትርክት ሕገ መንግሥታዊ ሆኗል። የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የዕውቀት፣ የልምድ ድርቀትን የተከናነበው ሕገ መንግሥት አገራችንን በዓለም የሌለ ልዩና ብቸኛ የጎሣ ፌዴራሊዝም ሥርዓት መሥራች አድርጓታል። ውጤቱም አሳዛኝ፣ አሰቃቂ እና ዘግናኝ ነው። ወገን በወገኑ የጨከነበት፣ በማንነት የግፍ ግድያ፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ የንብረት ዘረፋ እና ውደመት የተፈራረቁባት አገር ሁናለች። የመገንጠል መብት ያላንዳች ገደብ የተሰጠባት ከዓለም ብቸኛ አገር ነች። ለመገንጠል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሌላውን ማፈናቀል፣ ግዛትን ማስፋት፣ የዜግነት መብትን ማሳጣት፣ የባለአገር ታሪክ መፈብረክ እና ጥላቻን ማባባስ የሰርክ ሥራ ሆኗል።

ያልነበረን እና የሌለ ልዩነትን በማናፈስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም እንዳይኖርና ወደልማቱ እንዳያተኩር ተደርጓል። በልጆቹ የሥራ እጦት ምክንያት ይቆዝማል። ሳይደግስ አይጣላም ያሰኝ እንደሁ ግራ ያጋባል። አብዛኛው ሕዝብ በስደተኛ ልጆቹ ባይረዳ ኖሮ እንዴት ይኮን ነበር አስኝቷል። የልጅ ስደትን ሰርግና ምላሽ አስመስሏል። በድህነቱ ላይ የአገሩ በሱዳን መደፈር እና የሌሎች ጣልቃገብነት አንገቱን አስቀርቅሮታል።ለአገር መጥፋት የሚደረግ እቡያዊ ጀብዱና ውጤቱ አሳፍሮታል። በአገሩ ሰላም ዕጦት መንግሥትንና ዕኩይ ዓላማ የሚያራምዱትን መውቀስ ሰልችቶታል። ፈጣሪውን ማማረር ብሎም መለመን ምርጫውን ካደረገ ከራርሟል።

ከዚህ ሁሉ ጣጣ እና መከራ ለመላቀቅ ዛሬም የማያልቅበትን ተስፋ ሰንቋል። ወይ አገሬ! እያለ ተኝቶና በዕውኑም የሚያልመውን ለማየት እየጓጓ ይኖራል። በህልም የታጀበችው ተስፋ እውን እንድትሆን ምርጫን ብቸኛ አማራጭ አድርጓል። የምርጫው ተሳትፎም ይኸው ነው። ለአገሩ ሰላምና ደህንነት፣ ለሕዝቡ አንድነትና ዕድገት የሚያመጣለት መሪ ናፍቆታል። ይህን ያህል ደግሞ በተመራጩ እውነተኛነት ሙሉ በሙሉ ተማምኖ አይደለም። ለተስፋው ሂደት ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል በሚል እምነት እንጂ።

በዚህ አገራዊ ምርጫ ማንም ምንም ይሁን ለሥልጣን የሚበቃ አካል የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትን ማሟላት ይጠበቅበታል። ምርጫው የተስፋ መግለጫ እና የአደራ መልዕክት ነው። ተስፋው የሕዝብ አንድነት፣ ሰላም፣ ደህንነት እና ዕድገት ዕውን መሆን ነው። ተስፋው በአደራነት ለመጪው መንግሥት የተላለፈበት የመራጭ አደራ ነው። ይህን አደራ ለመወጣት መንግሥትን የሚመሠርት አካል መነሻው እና መድረሻው አንድ እና አንድ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አክብሮ አደራውን ለመወጣት በታማኝነት፣ በታታሪነት እና በቆራጥነት መሥራት ነው።

በሥልጣን ተሳክሮ ልዩነትን ማራገብ መቆም አለበት። ስካሩ ካስፈለገም የሕዝብን ፍላጎት፣ ጥቅም እና የአገር ሉዓላዊነትን ማስከበር ሊሆን ይገባል። የውስጥ እና የውጭ ተግዳሮቶችንና ችግሮችን መቋቋም እና ማስወገድ የሚቻለው ልዩ ተዓምር በመሥራት አይደለም። በተዓምርነት እንውሰደው ካልንም አገሪቷን ከዚህ ሰቆቃ እና አጣብቂኝ መዘፈቅ ምክንያት የሆነውን ሕገ መንግሥት መለወጥ ነው። ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ትውፊት ገደል የከተተ በኋላቀር ጎሣዊ ፖለቲካ አስተሳሰብ የተተበተበ ነው። ያለውን ሕገ መንግሥት አቅፎ ዲፕሎማሲያችንን አጠናክረን ጠላቶቻችንን እናሳምናለን፤ እናንበረክካለን እና ጠንክረን በመሥራት አኪኖሚያችንን እናስመነድጋለን ማለቱ ከንቱ ፉከራ ነው።

ካለአንድነት ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና አይኖርም። የጥቁር ሕዝብ ዘረኝነት አያምርም። የኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ ለመንደር አውራነት ዕድል በሚፈልጉ ደካማ ወገኖቻችን እንደጠለሸ መቀጠል የለበትም። መፍትሄያችን በደም፣ በታሪክ በማሕበረሰባዊ ትስስር የተቆራኘን ሕዝብ በቋንቋ እና ሴቶችን – እናቶችን- በናቀ መልኩ የተዘረጋን የማንነት ፍረጃን አስወግዶ ኢትዮጵያዊነትን ማንገስ ነው።

ለኢትዮጵያችን የጎሣ ፖለቲካ አይመጥናትም። የእስከዛሬው ውጤት በቂ ማስረጃ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ እና አደራም ይህን ሰንካላና ውል የለሽ ሕገ መንግሥት መለወጥ ነው። ስለሆነም፤ የአዲሱ መንግሥት ቀዳሚ ሥራ በሕገ መንግሥቱ ላይ ሊሆን ይገባል። የቀጣዩ ኹለተኛ ምዕራፍ ትኩረታችን በእዚህ እና በእዚህ ዙሪያ ቢሆን ይበጃል።

ታዬ ብርሃኑ(ዶ/ር) በኢሜል አድራሻቸው
tayeberhanu27@gmail.com
ማግኘት ይችላሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com