የእለት ዜና

አንዳንድ ትዝብቶች በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ!

Views: 102

ሰኔ 14 የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ የተለያዩ አስተያየቶችን ያስተናገደ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለመደ ምልከታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሲያስተዋውቁ፣ አንዳንዶች ደግሞ አጠቃላይ መግለጫ እስከምንሰጥ ታገሱ ሲሉ ይደመጣሉ። ሕብረተሰቡና ፖለቲከኞች ስለ ምርጫው ያላቸውን አስተያየት መስማት የተለመደውን ያህል፣ ሂደቱን ስለሚያስፈጽሙት የምርጫ ቦርድ ሠራተኞችና አስተባባሪዎች ብዙም ሲባል አንሰማም፤ አልሰማንም።

ከመጋቢት ጀምሮ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ የምርጫ አስፈፃሚዎች በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ናቸው። ለመራጮች ምዝገባ 152 ሺሕ 700 አስፈጻሚዎች ተዘጋጅተው የነበረ ሲሆን፣ ለምርጫው ቀን ደግሞ 240 ሺሕ መዘጋጀታቸውን ምርጫ ቦርድ አሳውቆ ነበር። ድምፅ ይሰጥባቸዋል ከተባሉ 48 ሺህ ጣቢያዎች አኳያ ለአንዱ ቢያንስ 5 አስፈጻሚ ይኖራል ተብሎ ነበር። በዕለቱ ግን የተጠበቀው አልሆነም። አምስት አስፈጻሚዎች የተሟሉላቸው ጣቢያዎች በርካቶች ቢሆኑም፣ 4 ያላቸውና ሦስት አስፈጻሚዎች ብቻ የተገኙባቸውም ነበሩ።

ጭራሹኑ አስፈጻሚዎች ሳይገኙ፣ ምርጫ ጣቢያው ሳይከፈት፣ እስከምሽቱ 12 ሰዓት ሕዝብ ተሰልፎ እንዲጠበቅ የተገደደባቸው ጣቢያዎችም ነበሩ። አሰልጣኝ የነበሩ ምሽቱን ደርሰው ለሊቱን ምርጫው ሲካሄድ አድሯል። በአንድ ጣቢያ ከመካከላቸው ከሰዓታት በፊት ተነግሮት ያለምንም ስልጠና አብሮ መጥቶ ሲያግዝ የነበረ ግለሰብ እንደነበረ ማንነታቸው እንዲነገር ያልፈለጉ እማኝ አሳውቀውናል። በሌላ በኩል ምርጫው ከመካሄዱ ከቀናት በፊት ስልጠናውን በወሰደ ጓደኛ አማካይነት ተጠርቶ አስፈጻሚ ሆኖ ያገለገለ ሁኔታውን አስረድቶናል። ሌሎቹ አስፈጻሚዎች በሚነግሩት መሰረት በተቻለው ሥራውን በአግባቡ እንደፈጸመ የሚናገረው ይህ ግለሰብ፣ ሌሎች እንደሱ ስለመጠራታቸው ባያውቅም በቀረ ሰው ቦታ ተክተውት እንደሆነ ይናገራል።

የምርጫ አስፈጻሚዎች በየጣቢያው ቁጥራቸው 5 እንዲሆን ቢደረግም፣ ከሚፈለገው ኃላፊነት አንፃር አነስተኛ እንደነበረ የሚናገሩ አሉ። በተለይ ከከተማ ውጭ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች የሕዝቡ ግንዛቤ አነስተኛ ስለነበር ስለአመራረጡ ሂደት የሚያሳውቅ፣ መዝገብ የሚያጣራና ቀለም የሚቀባ፣ እንዲሁም ወረቀቱን ሰጥቶ ምን ያህል ሰው እንደሚመረጥ የሚያስረዳ፣ ሲመርጡ እገዛ የሚፈልጉ ከሆኑ የሚያግዝ፣ ኮሮጆውን አቀያይረው እንዳይከቱ የሚያጣራና ሲወጡ ሳኒታይዘር የሚያስጠቅም ለእያንዳንዳቸው ሰው እንደሚያስፈለግ ይነገራል። የአንድ ምርጫ ኃላፊ ምርጫው ከተጀመረ ከሰዓታት በኋላ የተላከላቸውን ሳኒታይዘር ሳይነኩት ካርቶኑ ውስጥ እንዳለ አግኝተናል። ለምን እንዳልተጠቀሙበት ስንጠይቃቸው የሚያስጠቅም ሰው አጥተው ግልጋሎት እንዲሰጥ ሳያደርጉ መቆየታቸውን ነግረውናል። ከብዙ ውይይት በኋላ ውጭ ወንበር ላይ አስቀምጠው ለተሰለፈው መራጭ መርጦ ሲወጣ ብቻ መጠቀም እንዲችል ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም ወዲያውኑ ተፈጻሚ ሊደረግ አልቻለም። ኃላፊው ውስጥና ውጭ እየሆኑ ሥልጠናውንና ቁጥጥሩን በአንድነት ከሌሎች ኃላፊነቶቻቸው ጋር ደርበው መስጠት እንደማይችሉ አሳውቀውናል።

ጮሌ በተባለች ከደብረ ብርሃን በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ የገጠር የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ የነበሩት ወንድማገኝ እንደነገሩን፣ ጣቢያው አርሶ አደሮችን ታሳቢ አድርጎ ቢቋቋምም ከተመደበላቸው የአስፈጻሚ ቁጥር አንጻር ሥራው አስቸጋሪ ሆኖባቸው እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የነበረው ሂደት ፈታኝ እንደነበር ያሳወቁን እኚህ ኃላፊ፣ በጣቢያው 3 አስፈጻሚዎች ብቻ ስለነበርን ሥራችን ላይ ክፍተት ፈጥሮብን ሂደቱ እንዲዘገይ አድርጎብን ነበር ብለዋል። አብዛኞቹ መራጮች አርሶ አደሮች በመሆናቸው የግንዛቤ እጥረት ስለነበረባቸው ተቸግረን ነው የዋልነው ያሉ ሲሆን፣ ማንንና ምንን መምረጥ እንደሚፈልጉ የማያውቁ ስለሚበዙ በተቻለን ለማገዝ ሞክረናል ብለዋል። ባለን ትንሽ የሰው ኃይል ግንዛቤ ለመፍጠር ስንሞክር ረጅም ሰልፍ ተፈጥሮብን ነበር። ይህ እንዳይሆን ፓርቲዎች አስቀድመው መሥራት የነበረባቸውን ባለማከናወናቸው ጫናው እኛ ላይ አርፏል ማለታቸውን ሰምተናል።

ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ስላልተሰጠ አብዛኞቹ ካርድ ስለወሰዱ ይመጣሉ እንጂ ማንን እነደሚመርጡ የማያውቁ ብዙ ነበሩ። አንዳንዶች ስም ይዘው ይመጣሉ ያሉት ወንድማገኝ፣ በነገሩን ስም መሰረት እኛ እገዛ አድርገንላቸዋል ሲሉ ስለውሏቸው አስረድተዋል። የሚመርጡትን ሰው ስምና ምልክት የሚያውቁትም ቢሆኑ፣ ምርጫ ወረቀቱ ላይ ለይተው ሳይዛነፍባቸው ቦታው ላይ ለማመልከት የሚቸግራቸው ነበሩ። እየነገሩን እኛ ምልክት እናደርግላቸዋለን ወይም ከመከለያው ወጥተን ብርሃን ወዳለበት ወስደን ታዛቢዎች ፊት እንዲጠቁሙ እያስደረግን አስመርጠናል ብለውናል።

በአጠቃላይ ወደ ምርጫ ጣቢያው መጥተው ድምፅ ከሰጡ 580 ገደማ አርሶ አደሮች 40 በመቶ የሚደርሱት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የእኛን እገዛ ይፈልጉ ነበር ያሉት እኚህ የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ፣ ከደብረብርሃን ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ጮሌ እንዲህ ከሆነ ከከተማ ይበልጥ በራቀና መገናኛ ብዙኃን በማይደርሱበት ገጠራማ አካባቢ ሁኔታው እንደሚብስ ነግረውናል።

በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ከተከሰቱ ችግሮች ሌላው የሥራ ሰዓቱ ጉዳይ ነው። ከምርጫ ዋዜማ ጀምረው እስከምሽት ሲሠሩ አድረው ለሊት መነሳት ግድ ሆኖባቸው ነበር። አንዳንዶች በምርጫ ጣቢያው አቅራቢያ በቀን 600 ብር ገደማ ለአልጋ እየተከፈለላቸው ቢያድሩም፣ በምርጫው ቀን ግን እዛው እጣቢያው ለማደር ተገደዋል። ሂደቱ ተጠናቆ የምርጫ ክልሉ እስኪረከባቸው ኃላፊነቱ የእነሱ ስለነበር ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ባገኙት አጋጣሚ ይናገራሉ። በክፍላተ-አገር ጣቢያዎች በየአቅራቢያው ባለ መኖሪያቸው ለመጓዝ ሌሊቱ አስፈሪ የሆነባቸው የምርጫ አስፈጻሚ እንስቶች ሳይቀሩ በመሸኛኘት ምርጫውን በተቻላቸው በሰላም እንዳከናወኑ ይናገራሉ።

ምግብ በየምርጫ ጣቢያዎች ቢዘጋጅም አዳር የምርጫ ውጤትን ሲቆጥሩ ላደሩት ግን በቂ እንዳልነበር ለመስማት ችለናል። ቁርስ ባይኖርም አልፎ አልፎ ቡናና ሻይ ይዘው የሚመጡ ሻጮች እንደጠቀሟቸው ይናገራሉ። ከውድቅት ጀምረው ያለ እረፍት ሲሠሩ ውለው በሌሊት ብርድ ሲሠሩ ያድሩ አስፈፃሚዎች፣ እንቅልፍ ሲያዳፋቸው ሥራውን አቋርጠው እዛው መሬት ላይ ለማደር ተገደው ነበር። የጸጥታ ኃይሎች ቅያሬ ኃይል እየተዘጋጀላቸው፣ አሊያም ፍራሽ ተዘጋጅቶላቸው እየተቀያየሩ ሲያድሩ፣ አስፈጻሚዎቹ ግን ካርቶን አንጥፈው ምንም ሳይለብሱ ለማደር ተገደዋል። በነበረው ውጥረት ታመው የሄዱና ታክመው የተመለሱም መኖራቸውን ሰምተናል።

የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ከወራት በፊት ጀምሮ ሥልጠና ሲወስዱ ቢቆዩም፣ የተለያዩ የብቃት ማነስ ጉዳዮች ሲስተዋሉባቸው ነበር። ተራ የሂሳብ ስህተት ሠርቶ የሌላን አስተያየት ለመቀበል ለረጅም ሰዓት ሲከራከር ከነበረ የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚ ጀምሮ፣ በቆጠራ ወቅት ተራ የሚባል የማስተዋል ችግር የነበረባቸውን ለማየት ችለናል። የምርጫ ሂደቱ ከቁሳቁስ አጠቃቀም አንስቶ የማስረዳቱ ሂደት አንዱ ከሌላው የተለያየ ነበር። በተለይ በውጤት ቆጠራ ወቅት በአንድ አዳራሽ የነበሩ 4 ምርጫ ጣቢያዎች በቅርብ ርቀት ሆነው ፍፁም የተለያየ የቆጠራ ሂደትን ሲከተሉ አስተውለናል። ለምሳሌ፣ ከቆጠራ በፊት ድምፅ መስጫ ወረቀቶቹ መሃተም እንዳላቸው የማረጋገጡን ተግባር ዘንግተው የነበሩትን አስፈጻሚዎችን ሥራቸውን እንዲያስተካክሉ በማስታወስ ብዙ ሳይሄዱ ለማረም ችለዋል። ይህ አይነት ልዩነትን አንድ ጋዜጠኛ የተለያዩ ሂደቶችን ስለሚታዘብ ሊያውቀው ቢችልም፣ አስተያየት ሲሰጥ ግን እየተዘዋወሩ ሲከታተሉ በነበሩ የብልጽግና ታዛቢ ድርጊቱን በበጎ አልታየም። “ምንም ቢሆን ጋዜጠኛ አስተያየት መስጠት አይችልም” ብለው ስህተት ሲፈጸምም ቢሆን ዝም ብሎ ማየት ብቻ እንዳለበት ተናግረዋል።

አንዳንድ አስፈጻሚዎች ላይ ከሚታይ የብቃት ማነስ ችግር በስተቀር፣ ከሞላ ጎደል አብዛኞቹ የታዘብናቸው ሥራቸውን በአግባቡ የተወጡ ናቸው። አንዳንድ አስፈጻሚዎች የምርጫ መመሪያውን ካለመረዳት የተነሳ ጋዜጠኞች መረጃ እንዳይወስዱ ይከለክሉ ነበር። በቆጠራው ምሽት ሞቅ ብሎት ሌሎች ባልደረቦቹንና ታዛቢዎችን እያዝናና ሲቆጥር የነበረንም ለማስተዋል ችለናል። ድንኳን ውስጥ ጋቢ እየለበሱ ሥራውን ከሚያስፈጽሙ ትጉኃን ሠራተኞች በተቃራኒ ከሥራ ገበታቸው ጥፍት የሚሉም ነበሩ።

በሌላ በኩል፣ በወሎ ተሁለደሬ የአንድ ምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎች ሳይደርሱ በሌሊት ሳጥን በመክፈታቸው ለእስር ከመብቃታቸው ሌላ ይሄ ነው የሚባል ወንጀል ሰርተዋል ሲባል አልተሰማም። ቆጠራውን በተመለከተ አዲስ አበባ ላይ እየተዘዋወርን ስንመለከት በአንድ ምርጫ ጣቢያ በምርጫው ማግስት 4 ሰዓት ገደማ ተገኝተን የታዘብነው ከሌሎች የተለየ ነበር። ፖሊሶች መግባት አይቻለም ብለው ለማገድ ቢሞክሩም ጋዜጠኛ ማለፍ እንደሚችል በማሳመን ወደ ውስጥ ገብተን ድምፅ ሲቆጠር አይተናል። ልዩ የሚያደርገው ታዛቢዎች እና አስፈጻሚዎች ተለይተው በማይታወቁበት ሁኔታ የሚካሄድ ቆጠራ መሆኑ ነው። ሁሉም አንድ ላይ ሆነው ሲቆጥሩ ከመቆየታቸው ባሻገር አስፈጻሚዎቹን ከታዛቢዎቹ ለመለየት አይቻልም ነበር። ይህ አይነቱ ሂደት የአንድ ፓርቲ ታዛቢ የሆነ ግለሰብ አሳስቶ ውጤት እንዲመዘግብ እድል ከመስጠቱ ባሻገር፣ የሌላውን እንዳይከታተል ሃሳቡን ይሰርቅበታል። ቆጥራችሁ አረጋግጡ እየተባሉ ታዛቢዎች ወደ አንዱ እንዲያተኩሩ የሚደረገው በዚህ ጣቢያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጭምር ነበር።

በየዋህነትና በመሰላቸት እንዲህ አይነት ያልተገቡ ተግባሮች እንዳይፈጸሙ ፓርቲዎችም ሆኑ ገለልተኛ ታዛቢዎችን የሚልኩ አካላት አስቀድመው ሊያስገነዝቡና ሊያስቡበት በተገባ ነበር። ሁነቶቹ ለቀጣይ ምርጫዎች ትምህርት ሊወሰድባቸው ስለሚገባ ምርጫ ቦርድም መመሪያውን የያዘ ሰነድ ለሁሉም አሰራጭቶ ሥራው በተመሳሳይ እንዲከናወን ማድረግ ይኖርበታል። አሁን ላይ የሰኔ 14ቱ ምርጫ ከነችግሮቹ የተቋጨ ሁነት በመሆኑ፣ ወደፊት የሚመጣው ቀጣይ ምርጫ በሁሉም ረገድ የተàላ ይሆን ዘንድ ካለፈው መማርና ማቀድ ያስፈልጋል። የፈሰሰ ውሃ ባይታፈስምና ድጋሚ የምንቀዳው በተመሳሳይ እንዳይፈስብን መጠንቀቅ ይገባናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com