የእለት ዜና

የፖለቲካ ፓርቲዎችና 6ኛው አገራዊ ምርጫ

Views: 128

ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ የተወሰኑት ኢ-ዴሞክራሲያዊ እና ኢ- ፍትሐዊ ነው ሲሉ፣ ገሚሱ ደግሞ በአንጻራዊነት ዴሞክራሲያዊ ነበር በማለት ኹለት አይነት መልክ ሰጥተውታል፡፡ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በምርጫው ላይ በነበራቸው ትዝብት ወዝ አልባ የሆነ እና ፍትሃዊ ያልሆነ ምርጫ በማለት ሞግተዋል፡፡ አዲስ ማለዳም ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ትዝብት ምን መልክ ይዞ አልፏል የሚለውን ወንድማገኝ ኃይሉ በሀተታ ዘማለዳ ተመልክቶታል፡፡

ምርጫ የአንድ አገር ሕዝብ በማንኛዉም ሁኔታ ልዩነት ሳይደረግበት የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብቱን የሚጎናፀፍበት፣ በቀጥታ፣ በነጻነትና በሚስጥር ተወካዮቹን የሚመርጥበት ነው። ነዋሪዎች በመረጡት ተወካይ አማካይነት ራሳቸዉን በራሳቸዉ ለማስተዳደር ይችሉ ዘንድ ፍቃዳቸውን የሰጧቸው ተወካዮቻቸው ብቻ እንዲመሯቸው እድል የሚያገኙበት ዴሞክራሲያዊ አሠራር እና ሂደት ነው።

ተወዳዳሪ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲሁም ለነጻና ፍትሐዊ ምርጫ አፈጻጸም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያካተቱ አዋጆችን በማውጣትና ምርጫውን የሚያስፈጽም ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ በማቋቋም፣ ከአድልዎ የጸዳ ምርጫ ማካሄድ እንደሚችሉም እሙን ነው።

ሃሳብን በነጻነት መግለጽ እና በየጊዜው የሚከናወን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የዴሞክራሲ መገለጫ ተብለው ከሚጠቀሱት ቀዳሚ መመዘኛዎች ውስጥ ይካተታሉ። ምርጫ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝብን በመወከል ውሳኔ የሚያሳልፉ ወኪሎችን የመምረጥ ሂደትን የሚመለክት ጉዳይ ነው ምርጫ ከሚፈልገው አንድ ዋና ጉዳይ ተመራጭ መኖሩ ነው። የፈለገውን ያህል ጥሩ የምርጫ ድግስና ዘመቻ ቢኖር ሕዝብ ልቡ የሚያርፍበት አማራጭ ከሌለ የምርጫን ትርጉም ከመሰረቱ ያበላሻል። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ያለባት ዘርፈ ብዙ ችግር በጣም የገዘፈ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካው ስሪት ራሱ ዜጎች የፓርቲ መዓት እንዲቀፈቅፉ ያደርጋል።

ለምርጫ የሚሰጠው ዋጋ ከዚህ ቀደም የነበሩትን እንደማሳያነት ብናነሳ በበርካታ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እና እውነተኛ ምርጫ ተካሂዷል ለማለት የሚያስችል እንዳልነበር ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል። ከዚህ ቀደም የተደረጉ አገራዊ ምርጫዎች ኢህአዴግ መንበረ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ምርጫ ተካሂዷል የሚለውን መስፈርት ለማሟላት እንጂ፣ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚኖርበት የምርጫ ሜዳ እንዳልነበረው ይታወቃል። የዘንድሮው ማለትም ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በብዙኃኑ ማሕበረሰብ ዘንድ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተከናወነ እንደሆነም በርካቶች ሲመሰክሩ ይስተዋላል።

ይህ ብዙ ተስፋ የተጣለበትን ምርጫ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወክለኛል ያለውን ጨለማ፣ ብርድ፣ ዝናብ እና ጸሀይ ሳይበግረው ለረጅም ሰዓት በመጠበቅ ምርጫ በተካሄደባቸው አከባቢዎች ድምጹን ሳያባክን ለሚፈልገው አካል መስጠቱን አዲስ ማለዳ በተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራት ተመልክታለች። ይህ የሕዝብ ንቅናቄ ሕዝቡ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር እና ለአንድነቱ ቅድሚያ መስጠቱን ያሳየ ነው ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገልጸዋል። የእናት ፓርቲ ዋና ጸኃፊ ጌትነት ወርቁ፣ ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ እና የውጭ ጫናዎች አቅሟን እየፈተኗት ባለበት በዚህ ወቅት ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ መቻሏ የሚያስደንቅ ተግባር ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በኹለት እግሩ መቆም ያልቻለ መንግሥት አገሪቷን ሲመራ እንደነበር የገለጹት ዋና ጽኃፊዋ፣ አሁን ሲመረጥ ራሱን ችሎ የሚቆም ተጠያቂ መንግሥት ሊኖር እንደሚችል ነው ያነሱት። ከዚህ ቀደም ከባድ የሚባሉ ኹነቶች አልፈውብናል ያሉ ሲሆን፣ በተለይም ከሰላም እና ጸጥታ አንጻር ተገቢውን መንግሥታዊ ተግባር መፈጸም ያልተቻለበት፣ ከቀድሞ አገዛዝ በመወራረስ የመጣ እና በኹለት ልብ የተከፈለ መንግሥት እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ግን አንድ የታወቀ፣ በሕዝብ ሊወቀስ እና ሊከሰስ የሚችል ራሱን የቻለ መንግሥት ሊኖር እንደሚችል በሙሉ ተስፋ ሳይናገሩ አላለፉም።

ይሁን እና ባለፈው ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ነው ብሎ ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለማሰብ ያዳግታል በማለት ወዝ አልባ ምርጫ ነው ሲሉም ተደምጠዋል። አዲስ ማለዳም የፓርቲው ዋና ጸኃፊ ስለጉዳዩ እንዲያብራሩ በጠየቀችበት ወቅት የመለሱት ‹‹በኦሮሚያ ክልል ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ብቸውን ሮጦ፣ ብቻውን ተወዳድሮ ያሸነፈበት፣ ማንም ተቀናቃኝ እና ተወዳዳሪ ያልነበረበት ምርጫ ነው›› ሲሉም በሀሳብ ሞግተዋል። እንዲሁም፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተደረገው ምርጫም ቢሆን ከኦሮሚያ ክልል እምብዛም ልዩነት የሌለው ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አማራ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች ላይ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የተወሰኑ ቦታዎች ተደርጓል የተባለው ምርጫ በማጭበርበር የተሞላ ነው ሲሉም በቅሬታ መልክ ሃሳባቸውን ነግረውናል። በየአካባቢዎቹ ያሉ ሚሊሻዎች እና ካድሬዎች ሙሉ ሥራቸውን እና ውሎአቸውን በምርጫ ጣቢያዎች በማድረግ ለማጭበርበር ሙከራ ሲያደርጉ እና ሲያስፈራሩ እንደነበር ታዛቢዎቻቸን ነግረውናል ብለዋል። የምርጫ ቦርድም በተለይም ለደቡብ ክልል መንግሥት ዛሬ ሥራ የለም እና በቤታችሁ ተቀመጡ ብሎ መልዕክት ማስተላለፉን በማንሳት የጉዳዩን አሳሳቢነት ታዝበናል በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል።

እናት ፓርቲ በደቡብ ክልል ሆሳእና ከተማ ላይ ተወዳድሮ የማሸነፍ ሰፊ እድል ሊኖረው ይችል እንደነበር የገለጹት ጌትነት፣ በምርጫው ዕለት መርማሪ ፖሊስ (inspector) መንገድ ላይ እየጠበቀ መራጩን ሕዝብ በማስፈራራት ነው ሲያስመርጥ የዋለው ሲሉ ትዝብታቸውን ተናግረዋል። አያይዘውም በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም፣ አዊ እና ምዕራብ ጎጃም ዞን ላይ ሚሊሻዎች ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ ማንም ሀይ ያላቸው እንደሌለም አመልክተዋል። በዚህ ኢ- ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ስህተቶች ታክለውበት ምርጫው ወዝ አልባ እንዲሆን አደርጎታል ብለዋል።

ለዚህም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ከተሁለደሬ ምርጫ ክልል አንድ እና ኹለት፣ የምርጫ ወረቀቱን በመውሰድ በዞኑ ዋርዛ ወረዳ ላይ ድምጽ ሲሰጥበት እንደዋለ አንስተዋል። በደቡብ ወሎም በሳይንት አንድ እና ኹለት የምርጫ ክልል ላይ የሚወዳደረውን አካል ከአንደኛው ምርጫ ክልል ወደ ኹለተኛው በማዘዋወር ድምጽ ሲሰጥበት ነበር ነው ያሉት። አያይዘውም በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የእናት ፓርቲ ዕጩዎች ስም እና ፎቶ ግራፍ አንዳልነበረው ገልጸው የታዛቢያችንን እናት ፖሊሶች ሲያስፈራሯቸው እንደነበር ደርሰንበታል ሲሉ ጠቁመዋል።

በዚህም ረገድ የሰኔ 14 ምርጫውን ያስፈጸመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሳይሆን በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ ካድሬዎች ናቸው ብለዋል። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ድርጊቶች እየተፈጸሙ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዷል ብሎ ማሰብ ያስተዛዝባል። መንግስትም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምን ማለት እንደሆነ የገባው አልመሰለኝም ሲሉ አመልክተዋል። በአዲስ አበባ እና አንዳንድ የክልል ከተሞች ላይ በአንጻራዊነት የተሻለ ምርጫ ሂደት የነበረ ቢሆንም፣ በገጠር አከባቢዎች ላይ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ምርጫ ተካሂዷል ነው ያሉት ጌትነት።

ምንም እንኳ በአንጻራዊነት ካለፉት አምስት ምርጫዎች የተወሰኑ ለውጦች ቢኖሩም፣ የተነሱ ችግሮችን በቀጣዩ ምርጫ እንዲስተካከል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የእናት ፓርቲ ዋና ጸኃፊ የሆኑት ጌትነት ወርቁ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው የምርጫውን ሁኔታ በኹለት ከፍለው ማየታቸውን ያስረዳሉ። በአገራችን ሰላማዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለን የተንቀሳቀስንበት እና ጊዜያችንንም በዚሁ መስመር ላይ መስዋዕት አድርገን ተሳክቶልናል ያሉት ፕሮፌሰሩ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ መጠነኛ አለመረጋጋቶች እንደነበሩ አስተውለናል ብለዋል።

ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅመኛል፣ ነገ በደንብ ይመራኛል ብሎ ላመነበት ፓርቲ ወይንም ግለሰብ ድምጽ ለመስጠት በነቂስ ወጥቶ እና ተሰልፎ፣ እንዲሁም በትዕግስት ብዙ ሰዓታት ተሰልፎ መምረጡ አስደሳች ነው ብለውታል።
ይህም ለወደፊት ብሩህ ተስፋ እና ፍሰሃ የሚፈነጥቅ መሆኑን የገለጹት የፓርቲው ሊቀመንበር የአገራችንን ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ማማ ላይ በማስቀመጡ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው በአስተያየታቸው አንስተዋል። ሊቀመንበሩ በሌላ በኩል አያይዘው እንደገለጹት ከከተሞች አንስቶ ታች ቀበሌ ድረስ ባደረግናቸው ቅኝት እና እንቅስቃሴዎች በአርሶ አደሩ መካከል በደቡብ፣ በምዕራብ አረሲ ዞን፣ ጅማ ዞን እና ድሬዳዋ የተሻለ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ይህ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን ገዢውን ብልጽግና ፓርቲ ጨምሮ አንድ አይነት አቋም እንደነበራቸው ጠቅሰው፣ እንመርጣለን እናስመርጣለን የሚሉ የጥፋት ኃይሎች እኩይ ተግባራትን ለመፈጸም ዓላማ በማንገብ የምርጫውን ሂደት ለማደናቀፍ ሙከራ ማድረጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ አሳዝኖናል፤ ሕዝቡንም አስከፍተዋል ብለዋል ሊቀመንበሩ። በአጠቃላይ ኹለት አይነት መልክ የነበረው ምርጫ ነው ሲሉም የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ስለ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ አስተያየታቸውን እና ትዝብታቸውን አስቀምጠዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ፕሬዚደንት ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፣ የሰኔ 14ቱ ምርጫ በአንጻራዊነት ሰላም የሰፈነበት እና የጎላ ችግር ያልተስተዋለበት እንደነበር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ የአገሪቱ ክፍል በተለይም በገጠር አከባቢዎች ላይ የመኢአድ ታዛቢዎች በተመደቡበት ቦታ ላይ ተገኝተው የምርጫውን ሂደት እንዳይታዘቡ የተከለከሉበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል። በተለይም ይህ ኢ- ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ በደቡብ ክልል እና ከፊል አማራ ክልል ላይ እንደተስተዋለ ነው ማሙሸት የገለጹት።
በተቻለ መጠን ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሐዊ እንዲሆን ከቅድመ ምርጫ ወቅት ጀምሮ ብዙ ሲሠራበት ቢቆይም፣ በየአከባቢው የሚገኙ አንዳንድ ካድሬዎች በመጠኑም ቢሆን የምርጫውን መልክ ለመቀየር ሞክረዋል ብለዋል።

በሌላም በኩል ምንም እንኳን ከሰላም እና ጸጥታ ጋር በተያያዘ እንደተፈራው የጎላ ችግር ባያጋጥመንም በደቡብ ክልል ወላይታ፣ በጎንደር፣ በአዳማ እና በአምቦ አከባቢዎች መጠነኛ አለመረጋጋት መስተዋሉ በጸጥታ አካላት በኩል ክፍተቶች መስተዋላቸውንም አመልክተዋል።
በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟን ካጣች አመታት ተቆጥረዋል ያሉት ማሙሸት፣ በዚህም በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ እየተገደለ፣ ከቤት ንብረቱ እየተፈናቀለ አገር እንደ አገር እንዳትቀጥል በብዙ ችግሮች እና ተግዳሮቶች የተተበተበችበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ምርጫ ቦርድም እነዚህን እኩይ ተግባራትን ለማስቆም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ጥረት ማድረጉን እና ምርጫውን ፍትሐዊ ለማድረግ የሄደበት እርቀት የሚያስደንቅ መሆኑነም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ለዚህም ማሳያነት የሚሆነው በምርጫው ወቅት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረብናቸው አቤቱታዎች እና ቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ ያገኙ መሆናቸው ነው ሲሉ ሌለኛውን የምርጫውን በጎ ጎን አንስተዋል። ስለዚህም፣ ከምንም በላይ የአገር እና የሕዝብ ሰላም ይበልጣል እና ከዚህም በኋላ በሚኖረው ምርጫም ቅድሚያ ለሰላም በመስጠት ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ አንዲሆን በሚገባ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። የጸጥታ አካላት ከገዢው መንግሥት ጥገኝነት በመላቀቅ ለአገር እና ለሕዝብ ታማኝ በመሆን አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተመለከቱትን እና የታዘቡትን አዎንታዊ እና አሉታዊ እይታቸውን አስቀምጠዋል። ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለጸ ባይሆንም፣ በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ እንደነበር ኢዜማ ባወጠው መግለጫ ጠቅሷል። ለዚህ ምርጫ ሰላማዊነትና የአገሪቱን የነገን ቀጣይነት በምርጫ ለማረጋገጥ፣ ዜጎች በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ኢዜማ የበኩሉን ድርሻ በኃላፊነት ተወጥቷል የሚል የጸና እምነት እንዳለው አመላክቷል።

የተደረገው የ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት እስከሚገለጽ ፓርቲው እንደሚጠብቅ ገልጾ፣ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትንና በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቃቸው በርካታ ተግዳሮቶችን በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካላት ይዞ የሚሄድበትን ሁኔታ ቀድሞ ለሕዝብ የሚያሳውቅ ይሆናል ተብሏል። ኢዜማ የምርጫ 2013 አጠቃላይ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ የሚያስተባብር የምርጫ ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ኮሚቴ ከዓመት በፊት አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ አንስቷል።

በምርጫው ሒደት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በሕግ አግባብ ፓርቲው እንደሚጠይቅ ገልጾ፣ ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የድርጅቱን መዋቅር ይበልጥ በማጠናከር ወደ ሥራ እንደሚገባም አስታውቋል። ከዚህ አንጻር የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በምርጫ ሂደት የተገኘውን ውጤት፣ ልምድ፣ የሰው ኃይል፣ ልዩ ልዩ ግብዓቶች እና ወዘተ. የመሳሰሉትን ፓርቲውን ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀምና ድርጅቱን በጥንካሬ ለመምራት በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ ብርቱ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና በቀጣይ ለሚያጋጥሙ አገራዊ ጉዳዮችና ሰላማዊ ለሆኑ የትግል እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁም ጥሪ አቅርቧል። በምርጫው ላይ ከሰላም እና ጸጥታ ችግሮች ጋር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በርካታ ቅሬታዎችን ሲያነሱ አዲስ ማለዳ አስተውላለች።
ይሁን እንጂ የፌደራልና የክልል የደህንነትና ጸጥታ ተቋማት በበኩላቸው፣ አገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻና ገለልተኛ ሆነው የሕዝብን ሰላምና የአገርን ደህንነት እንዲያስከብሩ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምንና ሉዓላዊነትን እንዲያረጋግጡ የተቀመጠው አቅጣጫና የተሠራው ሥራ በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ፍሬ አፍርቷል በማለት መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል።

ተቋማቱ ኹሉንም የምርጫው ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች በገለልተኝነት መርህ እኩል በማገልገላቸው የምርጫው ሂደት የጎላ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የምርጫውን ሂደት ከታዘቡ አካላት፣ እንዲሁም ሕብረተሰቡ ከሰጣቸው ግብረመልሶች መረጋገጡን በመግለጫው ተመላክቷል።

6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ እንዲቻል የጸረ-ሰላምና አሸባሪ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ትርጉም ያለው ተጽዕኖ እንዳይኖራቸው በማድረግ ረገድ በቅድመ ዝግጀት ወቅት የተከናወነው ሥራ ውጤት አስገኝቷል ተብሏል። በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሚመራው የብሔራዊ ምርጫ ደህንነት ስትራቴጂ ማዘዣ አማካይነት የሰው ኃይልንና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት ከምርጫው ሂደት ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ክስተቶች ዙሪያ ከአንድ ማዕከል ኹለገብ ክትትልና ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተጨባጭ አቅም መፍጠሩ ተጠቁሟል።

ሂደቱ የፌደራልና የክልል የደህንነትና ጸጥታ ተቋማቱ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ተሞክሮ ያገኙበት በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጫው ጠቁሟል። ከመንግሥት በኩል ስለ ምርጫው ይህን መሰል መግለጫዎች እና ሪፖርቶች እየወጡ ቢሆንም፣ የተለያዩ ፓርቲዎች ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ አይደለም ከማለት ጀምሮ፣ ምርጫው ድጋሚ ይካሄድ እስከሚል አቋም ይዘዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com