የእለት ዜና

አዲስ አበባ እንዴት መረጠች?

Views: 173

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበላይ መሪነት ስደስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ይካሄዳል በተባለበት ሰኔ14/2013 ተካሂዷል። በዚህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ከተደረገባቸው አካባቢዎች አዲስ አበባ አንዷ ነች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስደስተኛውን አጠቀላይ ምርጫ በአንድ ቀን ለማካሄድ አስቦ ሲሠራ ቢቆይም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በገጠሙ የጸጥታ ችግሮችና በፍርድ ቤት የተያዙ የምርጫ ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ ተገዷል። በዚህም የመጀመሪያ ዙር ምርጫ እንዲካሄድ በተያዘለት ጊዜ ሰኔ 14/2013 ተከናውኗል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገጠሙ ችግሮች አለመኖራቸውን ተከትሎ ቦርዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምርጫን በአንድ ዙር ማካሄድ ችሏል።
በአዲስ አበባ ሰኔ 14/2013 በተደረገው ምርጫ አዲስ ማለዳ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተግኝታ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ተመልክታለች። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በተመለከተቻቸው የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ታዝባለች። አዲስ ማለዳ ምርጫው በተካሄደበት ዕለት መልካምና የሚደነቁ ተግባራትን ተመልክታለች። በአንጻሩ በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የተመለከተቻቸው ችግሮችም ነበሩ።

በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ አዲስ ማለዳ ከታዘበችው መልካም ተግባር መካከል፣ በመራጩ ሕዝብ በኩል ያስተዋለችው ትዕግስትና ቁርጠኝነት በብዙዎች ዘንድ የተደነቀ ተግባር ሆኖ አልፏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 የተካሄደው ምርጫ ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ስዓት እንዲካሄድ አቅድ ነበር ምርጫው የተጀመረው። ይሁን እንጂ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተካሄደው ምርጫ በዕለቱ በገጠሙ ችግሮች በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ ቦርዱ የድምጽ መስጫ ስዓቱ እስከ ምሽቱ ሦስት ስዓት ድረስ እንዲራዘም ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጅ እስከ ምሽቱ ሦስት ስዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ድምጽ መሰጠት ሂደቱ አልተጠናቀቀም። የአዲስ አበባ ሕዝብ በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ዕለቱ የነበረውን ሰልፍ፣ ዝናብና ምሽት ተቋቁሞ ድምጹን ሰጥቷል። የአዲስ አበባን ሕዝብ እንድናደንቅ ከሚያደርጉን ጉዳዮች መካከል በዕለቱ ድምጹን ከሰጠው መራጪ መካከል ጨለማ ሳይበግረው፣ እንቅልፉን መስዋዕት አድርጎ እስከ ሌሊቱ ሰባት ስዓት ድረስ ጠብቆ ድምጹን የሰጠ በርካታ ነዋሪ የመኖሩ ጉዳይ ነው።

አዲስ አበባ በተካሄደው የድምጽ መስጠት ሂደት ባጋጠሙ መዘግየቶች ምክንያት መራጩ ሕዝብ ባለመሰላቸት እስከ ሌሊቱ ሰባት ስዓት ድረስ በምርጫ ጣቢያ ቆይቶ ድምጽ መስጠቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ናቸው ያረጋገጡት። በዚህም የአዲስ አበባ ሕዝብ ዝናቡ፣ ጨለማ፣ ብርድ፣ ረሃብና እንቅልፉን መስዋት አድርጎ ታሪካዊ ምርጫ በማካሄዱ አድናቆት ይገባዋል ብለዋል።

የሰኔ 14 ምርጫ የአዲስ አበባን በሌሎች አካባቢ ከተደረጉት ምርጫዎች ለየት የሚያደርገው በዕለቱ አዲስ አበባ ላይ እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ማምሽት በራሱ ቀላል ነገር አለመሆኑ ነወ። እንደሚታወቀው አዲስ አበባ በተወሰነም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ምሽት ላይ መንቀሳቀስ ቀላል አይደለም። ከሌሊቱ ሰባት ስዓት ማለት ከተማው ውስጥ አይደለም መደበኛ ትራንስፖርት የራይድ ትራንስፖርት አግልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች እንኳን የማይገኙበት ስዓት ነው። ታዲያ የአዲስ አበባ ሕዝብ ይህን ኹሉ ችግር ተቋቁሞና ድምጹ ዋጋ ያለው መሆኑን አውቆ ድምጹን ላመነበት ሰጥቷል።

አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ምርጫ የገጠሙ አንዳንድ ችግሮች መራጩን ሕዝብ ለእንግልት ቢዳርጉትም፣ ምርጫ ዋጋ እንዳለው በተግባር አሳይቷል። የዘንድሮው ምርጫ ገና ከሂደቱ ጀምሮ በአንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ “እስኪ ምርጫው ይለፍ” የሚሉ ድምጾች እንዲሰሙ ማድረጉ የሚዘነጋ አይደለም።

“እስኪ ምርጫው ይለፍ” የሚለው ሃሳብ እንዲነሳ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በአገሪቱ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ምርጫው የሚካሄድበት አውድ የገጠሙበት ሁነት ለተጨማሪ ስጋት የሚዳርግ መሆኑ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። እንደ ስጋት ታይቶ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ ሁኖ አዲስ አበባ ላይ እስካሁን ምንም አይነት የጸጥታ ችግር አልገጠመም።

በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ ሰኔ 14 በተካሄደው ምርጫ ላይ አዲስ ማለዳ የተመለከተቻቸው ክፍተቶች ነበሩ። አዲስ ማለዳ በዕለቱ በኹለት ክፍለ ከተሞች ተዘዋውራ ስምንት ምርጫ ጣቢያዎችን ተመልክታለች። በዕለቱ አዲስ ማለዳ ከተመለከተቻቸው ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የመጀመሪያው ክፍትት በምርጫ ጣቢያዎች ላይ የክልል ምክር ቤት ድምጽ መስጫ ወረቅት እጥረት ነበር። በዚህም ምርጫ ጣቢያዎች ሲቸገሩ አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዕለቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ክልሎችም ድምጽ መስጫ ወረቅት እጥረት እንደነበር ገልጿል። በአዲስ አበባም የገጠመው የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት ደምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ሌሊቱ ሰባት ስዓት ድረስ እንዲራዘም ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ሆኖ አልፏል።

ቦርዱ በመግለጫው እንዳስታወቀው ከሆነ ከማለዳው 12 ሰዓት መከፈት የነበረባቸው ምርጫ ጣቢያዎች በተያዘላቸው ስዓት ሳይከፈቱ ቀርተዋል። አዲስ ማለዳ ከዚህ ጋር ተያይዞ የታዘበችው ችግር፣ የምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ ካለመከፈታቸው በተጨማሪ በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች በቦርዱ የተሰየሙ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሳይገኙ መቅረታቸውን ነበር። አዲስ ማለዳ በአንድ የምርጫ ጣቢያ አምስት አስፈጻሚዎች ተመድበው አንዱ ምርጫ አስፈጻሚ በመቅረቱ በምርጫ ጣቢያው የአስፈጻሚ ክፍተት ተፈጥሮ እንደነበር ተመልክታለች።

በዚህም ምክንያት በምርጫ ጣቢያው ላይ የነበሩት አራት ምርጫ አስፈጻሚዎች ድምጽ የመስጠት ሂደቱን በሚገባ ለማሳለጥ ሲቸገሩ አዲስ ማለዳ ተመለክታለች። በሂደቱም መራጮች ላይ የሚታየውን የግንዛቤ ችግር ለማገዝ የሰው ኃይል አጥረት ችግር ሆኖ ነበር።
ምርጫ ቦርድ በምርጫው ዋዜማ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ የጠፋበት መራጭ ጉዳዩን ለምርጫ ጣቢያው በማስረዳት፣ የመራጩን ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ በማሳየት፣ እና በመራጭነት መዝገብ ላይ ስሙ ከተገኘ ጉዳዩ በቃለ ጉባኤ ተይዞ እንዲመርጥ ይደረጋል ይላል። ይሁን እንጅ አዲስ ማለዳ በተመለከተቻቸው ምርጫ ጣቢያዎች ከቦርዱ ትዕዛዝ ውጭ ሲፈጸሙ ነበር።

በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች የመራጭነት ካርድ የጠፋባቸውን መራጮች አስፈጻሚዎች ያለምንም ቃለ ጉባኤ ሲያስመርጡ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የመራጭነት ካርድ የጠፋባቸውን እንዳይመርጡ ሲመልሱና ካርድ ይዘው የመጡ መራጮች ከመረጡ በኋላ ስማቸውን አረጋግጠን እናስመርጣለን በሚል ሰበብ የሰጡትን ድምጽ ከድምጽ መስጫ ሳጥን ውጭ ሲያስቀምጡ ተስተውሏል።

አዲስ ማለዳ በተመለከተቻቸው ምርጫ ጣቢያዎች ከቅሬታ ሰሚ አካላት ያረጋገጠቸውና በቦታው ተግኝታ የተመለከተችው ሌላኛው ችግር የክልል ምክር ቤት ድምጽ መስጫ ወረቀትን አጣጥፎ መስጠት ሲሆን፣ በዚህም መራጮች ተጣጥፎ ከተሰጣቸው በኋላ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከላይ ያገኙትን በቀጥታ የመምረጥ ሁኔታ ሲተገብሩ ተስተውሏል። አዲስ ማለዳ ከቅሬታ ሰሚዎች እንደሰማችው ከሆነ፣ የችግሩን ቅሬታ ተቀብለው ማስተካከያ እንዲደረግ መወሰናቸውን ነው።

በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባው ምርጫ በዕለቱ ከታዩት ችግሮች መካከል የመራጮች ግንዛቤ ችግር ነው። ይህ ችግር በአብዛኛዎቹ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የታየ ክስተት ነበር። መራጮች ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያ በሚገቡበት ጊዜ እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው ሲቸገሩ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። በተለይ የክልል ምክር ቤት ድምጽ መስጫ ወረቅት ላይ የሰፈሩት እጩዎች በዛ ያሉ መሆናቸውን ተከትሎ መራጮች ሲወዛገቡ ነበር።

የመራጮች የግንዛቤ ችግር በምርጫ አስፈጻሚዎችም ላይ ያልተገባ የሥራ ጫና ሲፈጥር አዲስ ማለዳ ታዝባለች። ምርጫ አስፈጻሚዎች በመራጮች የግንዛቤ ችግር ሳቢያ ድምጽ እስከሚሰጥበት ድብቅ ቦታ ድረስ መራጮችን ተከትለው ሲገቡ ተስተውሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚለው ከሆነ፣ መራጮች ድምጽ ለመስጠት ብቻቸውን የሚገቡበት የተከለለ ቦታ ላይ ድጋፍ ከሚስፈልጋቸው ውጭ ማንም ሰው መግባት የለበትም። ይሁን እንጅ አዲስ ማለዳ በተመለከተቻቸው ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን ለማስረዳትም ይሁን ለሌላ ዓላማ ምርጫ አስፈጻሚዎች ከመራጮች ጋር በተደጋጋሚ ለድምጽ መስጫ ወደተከለለው ቦታ አብረው ሲገቡ ነበር።

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ የነበረው የምርጫ ሂደት ከላይ ከተጠቀሱት የተወሰኑ ችግሮች ውጪ አዲስ አበቤ “እስኪ ምርጫው ይለፍ” ብሎ እንደሰጋው ሳይሆን በሰላማዊ ሁኔታ ተካሂዷል። ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የአዲስ አበባ ሕዝብ በትዕግስትና በሥርዓት መምረጡ አድናቆት ተችሮታል። አዲስ አበባ ሰኔ 14 መርጣለች፤ የምርጫ ውጤቷንና የሚያስተዳድራትን አሸናፊ ለማወቅ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ እየተጠባበቀች ትገኛለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com