የእለት ዜና

በአኮርዲዮን የሚገፋ ሕይወት “በወር ለሽንት 100 ብር እየከፈልን ነው የምንጠቀመው”

አለባቸው ካሳ ይባላሉ፤ በደብረ ብርሃን መኖር ከጀመሩ ግማሽ ምዕተ አመት አስቆጥረዋል። ከልጅነታቸው በለመዱት የአኮርዲዮን አጨዋወት ከባለቤታቸው ጋር በመሆን እየተዘዋወሩ በመሥራት ሕይወታቸውን ሲገፉ ቆይተዋል። ባለቤታቸው በእድሜያቸው መግፋት ሳቢያ በሽታ ተደራርቦባቸው አብረው ባያንጎራጉሩም ሁሌ አብረዋቸው ይዞራሉ። ባለቤታቸው እድሜያቸው ስለገፋ በጨዋታቸው መካከል እንዲያርፉ ለማድረግና ብቻቸውንም ላለማምሸት ሚሪንዳ እየጠጡ ይጠብቋቸዋል። አዲስ ማለዳ የሚሰሩበት

ግሮሰሪ ባመራችበት ወቅት ባልና ሚስት ጎን ለጎን ሆነው አኮርዲዮናቸውን እንደታቀፉ እረፍት ላይ ሆነው ነው ያገኘቻቸው። በመካከላቸው ያለው ፍቅር የሚያስቀና ነው። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ነው በደንበኞች ጥያቄ ተነስተው ማዜም የጀመሩት። በዘመናችን የማይታይ እርጋታ የሚታይባቸው ጋሽ አለባቸው፣ ግጥም እየተቀበሉ ታዳሚውን በአኮርዲዮናቸው እያዝናኑ እስኪደክማቸውና ባለቤታቸው እስኪጠሯቸው ቆይተው መድረኩን ሲጠብቅ ለነበረ ወጣት ባለማሲንቆ አስረክበው ተቀምጡ። እኛም እድሉን አግኝተን በመቅረብ ለበነጋታው ተቀጣጥረን አግኝተናቸዋል። ምሽቱን ይዘውት የነበረውን ትልቅ እድሜ ጠገብ አኮርዲዮን በማምጣት የሕይወት ውጣውረዳቸውን እንዲህ አጫውተውናል።

ስለእርስዎ ቢያስተዋውቁን?
አለባቸው ካሳ ከልካይ እባላለሁ። ተወልጄ ያደግሁት ቦረና ሳይንት፣ ደብረሲና መካነ-ሠላም ነው። እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬ ከወንድሜ ጋር ወደ አዲስ አበባ መጣን። እዛ አኮርዲዮን መጫወት ተምሬ እየተዟዟርኩ ከሠራሁ በኋላ፣ ሸዋ ክፍለ-አገር ደብረብርሃን መጥቼ እየኖርኩ ነው። አሁን እድሜዬ 78 ነው።

አኮርዲዮን መጫወትን እንዴት ለመዱ? ምን ያህል ዓመት ተጫወቱ?
አኮርዲዮን መጫaወት የለመድኩት በወንድሜ ተመስገን ካሳ አማካኝነት ነው። እሱ ሲጫወት ዐይቼ በጣም ሙዚቃ ስለምወድ እኔም አዲስ አበባ ተማርኩ። እሱም ሙዚቃ ስለሚወድ ከሰው ነው የተማረው። መቼ እንደሆነ ዘመኑ ትዝ ባይለኝም በኃይለሥላሴ ዘመን መሆኑን አውቃለሁ።

የት የት ተጫውተዋል?
አዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ጅማና አምቦ፣ እንዲሁም አሰብ በ1957 ኑሬያለሁ። ከኹሉም የቆየሁት አዲስ አበባ ነው። ምን ያህል እንደቆየሁ ባላውቅም ለተወሰኑ ዓመታት መርካቶ 32 ቀበሌ፣ 4ተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ስሠራ ቆይቻለሁ። የነበርኩበትን ወቅት ስላልመዘገብኩት በዚህ ጊዜ ነበር ብዬ መናገር አልችልም።

በግል ብቻ ነው ወይስ ኦርኬስትራ ውስጥ ሠርተዋል?
ኦርኬስትራ ውስጥ ልሠራ ነበር ትቼው ነው ወደዚህ የመጣሁት። በዚህ የሸዋ አውራጃ ውስጥ በነበረ ኪነት ውስጥ ሠርቻለሁ። በዚህ ደብረብርሃን አውራጃ ውስጥ እየተዘዋወርን ብዙ ቦታ ሠርተናል።

አኮርዲዮኑን በስንት ብር ነበር የገዙት?
በጊዜው ከ700 እና 800 አይበልጥም ነበር። ዛሬ ግን ገበያ ላይ አይገኝም። እኔ ከገዛሁ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። ከኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሬ ተጫውቻለሁ። ነገር ግን በደርግ ጊዜ ግጥምና መልዕክቱ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልገ ነበር።

ሥራዎን በካሴት ለማሳተም ሞክረው ነበር?
ሥራዬ በካሴት አልታተመም። ዝም ብዬ ምሽት ክበቦች ነው ስሠራ የኖርኩት። ሌላ ምንም ገቢ ስለሌለን ቤተሰቤን በዚሁ እየሠራሁ ስለማሥተዳድር ጊዜ አልነበረኝም።

ስለቤተሰቦ እስኪ ይንገሩን?
በዚሁ በአኮርዲዮን እየተጫወትኩ በሙያዬ ነው ቤተሰቤን የማሥተዳድረው። ደሳሳ የቀበሌ ቤት እየኖርን፣ የተወሰነውን ክፍል ለልጃችን እንድትሠራበት ሰጥተን በመሰላል የሚወጣበት የቆጥ ክፍል ውስጥ በስተርጅና እየኖርን እንገኛለን። ቀበሌ ለምን ሰጥታችሁ ታሠራላችሁ ብለው እኛን ከቤታችን ለመንቀል ብዙ ሞክረው በስንት ችግር ትተውናል። ከስድስት ልጆቼ አንዱ ሞቷል። ከቀሩት ኹለቱ አብረውን እየኖሩ ይገኛሉ። አንደኛዋ ልጄ ለሥራ አሁን ወልድያ ነው ያለችው።

ባለቤትዎ አብረዎት እያገዙ ሲያመሹ አይተናል። ምን ያህል ጊዜ በትዳር ቆይታችኋል?
አዲስ አበባ ነው የተገናኘነውና የተጋባነው። አብረን መኖር ከጀመርን ብዙ ዓመት ይሆነናል። ደብረ-ብርሃን ከመጣን 50 አመት የሚያልፈን ይመስለኛል። ኃይለሥላሴ ደብረ-ብርሃን ብርድ ልብስ ፋብሪካን ሊያስመርቁ ሲመጡ እኛ እዚህ እየኖርን ነበር።

በዛ ጊዜ የነበረውና አሁን ያለው የአኮርዲዮን ተቀባይነት ልዩነቱ ምን ያህል ነው?
በጣም ትልቅ ልዩነት ነው ያለው። አሁን ያለው ሥራ የተሻለ ቢሆንም ፕሮግራምና ስርዓት ግን የለውም። ብዙ ቦታዎች ስርዓት የሌለው ነገር ስለሚበዛ አልሠራም ብዬ እምቢ ያልኳቸው አሉ። ለመናገር እስኪቸግር ድረስ ምሽት ላይ ባለጌው ብዙ ነው። አስነዋሪ ነገር ስለማይ እንደዚ አይነት ቤቶች መገኘት አልወድም። እኔ ከክርስቲያናዊ ሥነምግባር የራቀ ቦታ ላይ መገኘት አልፈልግም ( ሴተኛ አዳሪዎች ያሉበት ቤቶችን እንደሆነ ከጎናቸው የማይለዩት ባለቤታቸው መናገር እየከበዳቸው አሳውቀውናል)።

ከባለቤትዎ ጋር ሁሌ አብራችሁ ነው የምትሰሩት?
አዎ ሁሌ አብረን ነው የምንሰራው። አንለያይም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እሷ በጣም ስለሚያማት እንደድሮው አብራኝ አታንጎራጉርም። በቀን 11 ኪኒን ነው የምትውጠው። ብዙ በሽታ ነው ያለባት። ኩላሊት፣ ግፊትና ስኳር ያስቸግራታል። ትንሽ መንገድ ስትሄድ ያማታል።

በቀን ምን ያህል ገቢ ያገኛሉ?
በምሠራባቸው ቀናት እስከመቶ ብር ላገኝ እችላለሁ። በአብዛኛው 50፣60ና 70 ብር ነው የማገኘው። አሁን ሰው አቅሙ ስለደከመ እንደበፊቱ አይሰጥም። እንደው በወረት ካልሆነ በስተቀር ያን ያህል ገቢ የለውም። በዚህ እድሜዬ ብዙ ነገር አይቻለሁ። ችግርንም በደንብ ስለማውቀው አሳልፈዋለሁ። የራሴን ችግር መቋቋም ችዬ ነው የኖርኩት። ከዚህ ሥራ የምናገኘው ገቢ በቂ ስላልሆነ ቤታችን ውስጥ እየከፈለን የሚኖርን ሰው አስገብተናል።

ከመዝናኛ ቤቶች ውጭ ሌላ ሠርግና ክርስትናን የመሳሰሉ ፕሮግራሞች ላይ ይሰራሉ?
በፊት አንዳንድ ጓደኞቼ እየጠሩኝ ምርቃትም እሠራ ነበር። አሁን አሁን ግን ማንም የሚጠራኝ የለም። የእኩዮቻችን የጡረታ ሽኝት ፕርግራም ላይም እንጠራ ነበር። አሁን ግን እንዲህ አይነት ጥሪ የለም። ብንጠራም ባለቤቴ ረጅም ሰዓት መሥራት አትችልም። እኔም ቆሞ መቆየቱ ይከብደኛል። ባለቤቴ ጋር አዲስ አበባ ከተገናኘን ጀምሮ አብረን ነበር የምንሠራው። እኔ የሙዚቃ መሳሪያውን እጫወታለሁ እሷ ታንጎራጉራለች። አሁን በእድሜ መግፋት ሳቢያ እኔ ብቻዬን የቻልኩትን ያህል እጫወታለሁ።

ከልጆችዎ የእናንተን ሙያ የተከተለ የለም?
የሞተው ልጄ ነበር ፍላጎቱ የነበረውና መጫወት የሚችለው። ሌሎቹ ያን ያህል አይደሉም። ያሉትን ተማሩ ብላቸው እምቢ አሉ። ስሜትና ፍላጎት ያለው ካልሆነ መሥራት አይችልም።

ከሙዚቀኞች ማንን ያደንቃሉ? ማንንስ አግኝተው ያውቃሉ?
አሰፋ አባተን፣ ጥላሁን ገሠሠን፣ ተፈራ ካሳን፣ አለማየሁ እሸቴን፣ ብዙነሽ በቀለን፣ ሂሩት በቀለን፣ ተዘራ ኃይለ ሚካኤልን እንዲሁም ሌሎች አንጋፋዎቹን አደንቃለሁ። ካገኘኋቸውና አብረን ከሠራነው መካከል ማሪቱ ለገሠ ዋናዋ ጓደኛዬም የነበረች ናት። ሌላው አብረን የመሥራት ዕድል ያገኘሁት ነፍሱን ይማረውና ከከተማ መኮንን ጋር ነበር።

በሥራ ወደ ውጭ የመሄድ ዕድል አግኝተው ያውቃሉ?
አይ አግኝቼም አላውቅ። መጀመሪያ እኮ አስተዋዋቂ ሰው ሲኖር እኮ ነው ዕድል የሚኖረው። እኛ የመሄድ እድል ባናገኝም ሥራችንን እየቀዱ ጣሊያንና አሜሪካን እየወሰዱ ተጠቅመውበታል። በእኛ ሥራ የተጠቀሙ ምንም አላደረጉልንም። እኛ በዕድላችን ከማዘን ውጭ ምንም ማድረግ አልቻልንም። እኛ ያለንበትን ክፍል ለሰው ለማሳየት እናፍራለን። ልጃችን ሊያድስ ጀምሮ ያልጨረሰው ቤት ውስጥ ነው ያለነው።

በሥራ ላይ ያጋጠሞት የተለየ ክስተት ነበር?
በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ድምጻችንን ቀድተው ወስደው፣ “አልፋችኋል ኑ ካሴት ይሠራላችኋል” ብለው ጠርተውን ነበር። ካሴቱን ከሚሠራው አለቤ ከተባለ ባለቤት ጋር ተገናኝተን ከጨረስን በኋላ በአሻጥር የእኛ እንዲቀር ተደረገ። እኛ አሸንፈን ዕድሉን ለሌላ ሰጡብን። የብርቱካን ዱባለ ባል የባለቤቴ ወንድም ነው። ፋንታሁን ደበስ ይባላል። እሱ በሕይወት እያለ እንድንሻሻል ብዙ ነገር ያደርግልን ነበር። ሌላም ሰው ቢጥርልንም ፈጣሪ ስላላለ ሳይሆን ቀረ።

ማታ ማታ እስከ ስንት ሰዓት ታመሻላችሁ?
እስከ 4 ሰዓት ብቻ ነው የምንቆየው። አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ጀምረን እያረፍን እንሠራለን። ስንቱን ግሳንግስ ችለን ነው የምንሠራው። የሰመያዊ ሕንፃ ባለቤት መቶ አለቃ፣ ጥሩ ሰው ስለሆኑ፣ እየፈቀዱልን እሳቸው ቤት አልፎ አልፎ እንሠራለን። እሳቸው ጋር እየሠራን የተነሳነው ፎቶ ከነስማችን ደብረ ብርሃን ምክር ቤት ተለጥፎልናል። ቅርስ ነው ብለው ምስላችንን አስቀመጡ እንጂ እኛን ከፍ የሚያደርግ ነገር አላደረጉልንም። እኛ የሽንት ቤት ቦታ እንኳን ቸግሮን በወር ለሽንት 100 ብር እየከፈልን ነው የምንጠቀመው። በጣም ብዙ ችግር ነው ያለብን። ከዚህ በላይ ለመንገር ይከብዳል።

ምን ቢደረግ ጥሩ ነው ይላሉ?
የእኔ መልዕክት ሽንት ቤት ያለው ቤት እንድናገኝ ነው። እያረጀን ስለሆነ ቢያንስ የሽንት ቦታ አጠገባችን እንዲሰጠን እንፈልጋለን። ቤታችን በጅምር የቀረ ስለሆነ የሚያድስልን ብናገኝ ደስ ይለናል። ጆሲ የሚባለው እኛን አይነት ሰዎችን የሚረዳው ጋር የሚያገናኘን ብናገኝ ጥሩ ነበር። ቤታችንን አይቶ የሚሆነውን ያደርግልናል። የድሃን ቤት የሚያድስ ጥሩ ሰው ነው። ደብረ ብርሃን ስለማይመጣ እኛም አዲስ አበባ ሄደን ያላገኘነው እንደሆነ ብለን እስካሁን አልሞከርንም።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com