የእለት ዜና

አሁናዊ የኮቪድ ስርጭት በኢትዮጵያ

Views: 60

ለአለማችን ሆነ ለአህጉራችን አፍሪካ ትልቅ የራስ ምታት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ወይንም በሳይንሳዊ መጠሪያው ኮቪድ 19 የበርካታ አገራት ዜጎችን ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል፤ ምጣኔ ሀብታዊ ድቀትንም አስከትሏል። የዓለምን ትኩረት የሳበውና የወትሮ የኹሉንም ክፍላተ ዓለም እንቅስቃሴ ለጊዜው አቅጣጫ ያስቀየረው ኮቪድ 19 ዛሬም መልኩን እየቀያየረ የኹሉንም ቤት እያንኳኳ ይገኛል። በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ግብረ-ኃይል ምላሽ ዳይሬክተር ዶ/ር መብርሀቱ ማሴቦ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በሽታው ልክ እንደ ሰደድ እሳት ነው።

በትንሿ አንዲት አካባቢ ታይቶ ውስጥ ውስጡን ተቀጣጥሎ ድንገት ሰፊ አካባቢን የሚሸፍን አደገኛ ተላላፊ በሽታ ነው ብለዋል። በዚህም የመተላለፊያ መንገዱም ሆነ የሚጎዳው የአካል ክፍል በመበርከቱ ለህክምና ባለሙያዎች ሌላ የቤት ሥራ እንደሆነም ቀጥሏል ብለዋል።
የተሃዋሲው ምንነት ተጠንቶ ሳያበቃ፣ የሚጎዳው የአካል ክፍልም አይነቱ እየበረከተ፣ መያዣው በጠፋበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የታማሚዎች ቁጥር በትንሹ ጀምሮ ከፍ እያለ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው የህክምና ባለሙያው ያነሱት። ይህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ እየተስፋፋ የመጣው በየዕለቱ እጅግ ብዙዎችን በሚያስተናግዱ ባቡርን ጨምሮ የአውቶብስ እና የታክሲ ትራንስፖርቶች ላይ በሚፈጠረው መተፋፈግ እና ንክኪ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአገሪቱ ለጥቂት ወራት በነበረው የኮቪድ 19 ንቅናቄ እና በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የተወሰኑ ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ ከዛ ወዲህ የሕዝቡ መዘናጋት ቫይረሱ እንዲያገረሽ አድርጎታል ብለዋል። ከኹሉም በላይ ደግሞ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚያወጡት ዕለታዊ ሪፖርት መዘናጋቶች እንዳሉ አስተውለናል ብለዋል። ለዚህም የላቦራቶሪ ምርመራ ከሚያደርጉት አምስት ሺህ ዜጎች መካከለል ከአንድ መቶ የማይበልጡ ብቻ ቫይረሱ እንዳለባቸው የሚያመላክት ሪፖርት በመመልከት የቫይረሱ ስርጭት ቀንሷል የሚል የበዛ መዘናጋት በመላ አገሪቱ እንዳለ ደርሰንበታል ሲሉ ነው ያብራሩት ዶ/ር መብርሀቱ።

እስካለፉት ጥቂት ጊዜያት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ከማሻቀቡ የተነሳ በርካታ የሚሆኑት ታማሚዎች በጽኑ ህክምና ክፍል ውስጥ ይገኙ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር መብርሀቱ፣ የሟቾችም ቁጥር አስጊ እንደነበር አንስተዋል። ይህም ባሉት የህክምና መሳሪያዎች እጥረት ላይ ተጨምሮ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎት እንደቆየም ጠቅሰዋል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር የቀነሰው የቫይረሱ ስርጭት ጋብ ስላለ ሳይሆን፣ አሁን ላይ የላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገላቸው ያሉ ግለሰቦች ተጓዳኝ ህመም ኖሮባቸው በህክምና ተቋማት ላይ ክትትል እያደረጉ ያሉ ብቻ በመሆናቸው ነው ብለዋል።

የላብራቶሪ ወይንም የኮቪድ ምርመራ አሁን ላይ እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ ሕብረተሰቡ ውስጥ በመግባት ምርመራ እየተካሄደ አለመሆኑንን የገለጹት ዶ/ር መብርሀቱ፣ እየተመዘገ ያለውን ጥቂት የተጠቂዎች ቁጥር በመመልከት ብቻ ሕብረተሰቡ መዘናጋት እንደሌለበት አመልክተዋል። በመዘናጋት እና እራስን ከቫይረሱ በመጠበቅ ውስጥ ሊኖር የሚችለው ልዩነት ለመላው ሕብረተሰብ የሚታይ ቢሆንም፣ አሁን አሁን የቫይረሱ ሥርጭት ቀንሷል በሚል መዘናጋት ወረርሽኙ ስር እየሰደደ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ባሻገርም ተጥለው የነበሩት ገደቦች በተነሱበት ወቅት በትላልቅ የገበያ ስፍራዎች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አከባቢዎች እርቀትን ሳይጠብቁ በሚፈጠሩ ንክኪዎች የሥርጭት አድማሱ ሊስፋፋ እንደቻለ አስረድተውናል።

ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ ላይ የተስተዋለ ችግር መሆኑንም አንስተዋል። የዓለም መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡትና መላው ዓለምን በየዕለቱ ማነጋገሩ የቀጠለው አዲሱ የኮሮና ተሃዋሲ ስጋት ደቅኗል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታዩ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ጭራሽ ሰዎች ስለበሽታው ግንዛቤ ያላቸው እንደማይመስል በየማኅበራዊ መገናኛዎች የሚሰራጩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች ያሳያሉ። ይሁንና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ምርመራ የተደረገላቸው ከ2 ሚሊዮን 866 በላይ ሲሆኑ፣ በቫይረሱ ተይዘው የህክምና ክትትል የሚደረግላቸው 11ሺሕ 413 መሆናቸውም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

አጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው 276 ሺሕ 037 ሲሆኑ፣ ከቫይረሱ ያገገሙት ከ260 ሺሕ በላይ ናቸው። 4ሺሕ 320 ዜጎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል። የታማሚዎችን ስብጥር በተመለከተም በአዲስ አበባ የተገኙት ቁጥር ከፍያለ ሲሆን፣ በመቀጠል ሶማሌ ክልል፣ እንዲሁም ኦሮሚያና ትግራይ ክልል መሆናቸው ተገልጿል። ይህ ቁጥር በአንድ ጀንበር አልነበረም ከዚህ የደረሰው። 32ሺሕ ዜጎቿን በሚያስደንቅ ፍጥነት በአንድ ጀንበር ያጣችው ጣሊያንም ሆነች ከኋላዋ ተነስታ በሦስት እጥፍ በልጣ 90 ሺሕ ዜጎቿን በአንድ ቀን ውስጥ የቀበረችው ዩናይትድ ስቴትስ ተሐዋሲውን የቻይና፣ የሚጎዳውም ቻይናን ግፋ ቢል እሲያን ነው የሚል መዘናጋት እንደነበረባቸው ዛሬ በቁጭት ይነገራል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች ባለው መዘናጋት ምክንያት ስርጭቱ እየተስፋፋ ሲሆን፣ ኹሉንም የጥንቃቄ መንገዶችን ያለመዘናጋት መተግበር ያስፈልጋል። አሁንም ቢሆን አስገዳጅ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ቤት ውስጥ መቆየት፣ አካላዊ እርቀትን በአግባቡ መጠበቅ እና ያንንም ተግባራዊ ማድረግ፣ በየትኛውም ሁኔታ እና እንቅስቃሴ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መጠቀም፣ እጅን በአግባቡ በንጹህ ውኃ እና ሳሙና መታጠብ አማራጭ የሌላቸው መፍትሄዎች መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በጤናው ዘርፍ 500 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የክረምት መርሃ ግብር ተጀመረ
የጤና ዘርፍ የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በአለርት ሆስፒታል ተካሄዷል፡፡
በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት የጤና ዘርፍ የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በአለርት ሆስፒታል መካሄዱን ጤና ሚኒስቴር አሳውቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ ማኅበራት እና አባላት የተገኙ ሲሆን፣ አገልግሎቱ 500 ሺሕ የሚሆኑ ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል። በዚህም የጤና ተቋማትን ለማገዝና ለማስፋፋት፣ መገልገያ መሳሪያዎችን ለመጠገን፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለባለሙያዎች ለመስጠት ታቅዷል ተብሏል።የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለም ፀሀይ ጳውሎስ የጤናው ዘርፍ የበጎ ፈቃድ ስራ የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኮቪድ 19 ከገባ በኋላ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ 20 ያህል የጤና ማኅበራት ጥምረቶች ወደ 11 በሚጠጉ የጤና ተቋማትና ሌሎች አካባቢዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአለርት ሆስፒታል የነበረው የመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ችግኝ በመትከል መጀመሩን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com