የእለት ዜና

‹‹ባንኮች በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትልቅ ችግር ይገጥማቸዋል››

Views: 155

ደስታ ባይሳ
የ MOSS ICT ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የኤም ብር ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹ኤም ብር› የመጀመሪያው ሞባይል መኒ ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 2010 ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነው። ኤም ብር ‹የሞባይል ኦፕሬቲንግ ሶፍትዌር ሲስተም› (MOSS ICT) እህት ኩባኒያ ሲሆን፣ ከ6 ብድርና ቁጠባ ተቋሟት ጋር እየሰራ የሚገኝ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰጪ ተቋም ነው። እነዚህ ተቋማት በአዲስ አበባ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በአማራ ክልል ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በትግራይ ክልል ከደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በደቡብ ከኦሞ ብድርና ቁጠባ ተቋም እንዲሁም ከፒስ ብድርና ቁጠባ ናቸው።

በአይርላንድ ደብሊን ዋና መሥሪያ ቤቱን ያደረገው MOSS ICT በኢትዮጵያ ኤም ብር የሚባል ሞባይል መኒ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ ነው። በኤም ብር የሞባይል መኒ ልዩ ልዩ አገልግሎት ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ የሞባይል የአየር ሰዓት መግዛት፣ገንዘብ ማስተላለፍ እና የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም ያስችላል። ኤም ብር በአሁኑ ሰዓት 19ሺህ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ 1.9 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት ችሏል። በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ እስከ 35 ቢሊየን ብር ድረስ የሚያስተላልፍ ድርጅት ሆኗል።

ደስታ ባይሳ የ MOSS ICT ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የኤም ብር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በኢኮኖሚክስ የማስተር ዲግሪ አግኝተዋል። በተጨማሪም የዩኤን ዲጂታል ፋይናንስ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ኮርስ የወሰዱ ሲሆን፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። የአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ ስለ ሞባይል መኒ እና አጠቃላይ ዲጂታል ፋይናንስ በተመለከተ ከደስታ ባይሳ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

የሞባይል መኒ በኢትዮጵያ በማስጀመር ፈርቀዳጅ የሆነው ኤም ብር እንዴት ተመሰረተ?
ኤም ብር በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሞባይል መኒ መሆኑ ይታወቃል። መስራቾቹ ወደ ኢትዮጵያ ይህን ሀሳብ ይዘው የመጡት በ2010 ሲሆን፣ በሰዓቱ ፊንቴክ (ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ) አቅርቦት ግንዛቤ አልነበረም። ስለዚህ ከተቆጣጣሪው አካል ፍቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸው ነበር። ይህ ቴክኖሎጂ እንዴት እና በምን መልኩ ይተግበር የሚለውን ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ ሲሠሩ ነበር። ለእንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂ መስፋፋት እና ጥቅም ላይ መዋል የቴሌኮም አገልግሎት አስፈላጊ ነበር። በመቀጠልም ይህን ሥራ መሥራት የሚያስችል መሰረተ ልማት ኢትዮ ቴሌኮም ማሟላት ነበረበት።

ከባንኮች ጀምሮ እስከ ማይክሮ ፋይናንስ ድረስ በምን መልኩ መሥራት እንዳለባቸው ሲወያዩ የቆዩ ቢሆንም፣ መስራቾቹ ቴክኖሎጂውን በመጀመሪያ ለገጠሩ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ፈልገው ነበር። ስለዚህ ይህን ለመተግበር የሚያስችል ደንብ ከብሔራዊ ባንክ እንዲወጣ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ መሥራት ብሎም፣ ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደደቢት፣ ኦሞ፣ ፒስ እና አዲስ አበባ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጋር ለመሥራት ቅድመ ሁኔታዎችን ሠርተው ነበር።

በመቀጠልም 2011 ላይ ከተጠቀሱት ተቋማት ጋር በኮንትራት እና በቋሚነት ስምምነት በመፈጸም ወደ ሥራ ገብተው ነበር። ነገር ግን ቴክኖሎጂው አዲስ እንደመሆኑ መጠን የአግልገሎቱ አሰጣጥ በተፈለገው መንገድ ለማስኬድ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተው ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ በይፋ ሥራ የጀመረው በ2015 ነው።

በኢትዮጵያ ስለሞባይል መኒ አገልግሎት ሕብረተሰቡ ጋር ብቻም ሳይሆን ባንኮችም ጋር ያለው ተቀባይነት ብዙ አይደለም። ባንኮች የራሳቸው ሞባይል መኒ ይፈጥራሉ እንጂ ለእንደናንተ አይነት ተቋም (ፊንቴክ) አይሰጡም። ለምንድን ነው?
ኬኒያ ላይ ሳፋሪኮም በ1970 የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ወቅት ባንኮች አልተነቃቁም ነበር። ባንክ ቅርንጫፍ ከፍቶ ሕዝቡ ጋር መድረስ እንጂ የቴክኖሎጂን እና የገንዘብን ግንኙነት አልተረዱትም ነበር። ኤም ፔሳ በሳፋሪኮም ስር ያለው የሞባይል ብር ማስተላለፊያ ትልቅ ለውጥ አምጥቶ በአሁኑ ሰዓት ከሱ ውጭ ሌላ የሌለ እስኪመስል ሰርጾ ገብቷል። በኛም አገር እየታየ ያለው ይህ ነው። ባንኮች ቅርንጫፎችን የማስፋት ምቾት ላይ ናቸው። ለምሳሌ ባንኮች የሚሰጡትን የኤ.ቲ.ኤም. አገልግሎት ማየት እንችላለን። ምን ያህል ባንኮች ናቸው ኤ.ቲ፣ኤማቸው ሰው በሚፈልገው መንገድ አገልግሎታቸው የሚሰራው ብንል የምናየው ሀቅ ነው።

ሞባይል ባንኪንግ ባንኮች ይሰጣሉ፤ ነገር ግን ደንበኞች ለማገልገል በጣም ሲቸገሩ ይታያል። ባንኮች በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትልቅ ችግር ይገጥማቸዋል። ምክንያቱም ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን እያሰፋ ነው። እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ትልቅ ውድድር ይፈጥራል። ኢትዮ ቴሌኮም ያቋቋመው ቴሌ ብር የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በሚሰፉበት ወቅት ባንኮች ደግሞ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚገደዱበት ሁኔታ ይፈጠራል።

ባንኮች ገንዘብ መሰብሰብ እንጂ ደንበኞች በቀላሉ የሚገለገሉበትን አማራጭ አያቀርቡም። ይህ ደግሞ ደንበኞች ሌላ አማራጭ እንዲጠቀሙ ያደርጋል። በዚህ ወቅት ምናልባት ባንኮች ነቅተው ሊሰሩ ይችላሉ። ለእንደኛ አይነት ቴክኖሎጂ አቅራቢዎችም ቢሆን ባንኮችን ይዞ ቴክኖሎጂውን ለማሳደግ መሞከር አስቸጋሪ ሲሆኑ ይስተዋላል። ፍጥነታቸውም ሆነ የሚያሳዩት ፍላጎት በጣም አነስተኛ ነው።

በብሔራዊ ባንክ የወጡ አዳዲስ መመሪያዎች ለፋይናንሻል ቴክኖሎጂ እድገት ምን አስተዋጽኦ አላቸው?
ባለፉት ኹለት ዓመት ብሔራዊ ባንክ ያደረጋቸው አዳዲስ የፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ሕጎችን ማሻሻል እና ማሳደግ ነበር። ይህ እንደ አገር ለዘርፉ ምን ያህል ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረት አንዱ ቴሌኮም ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ የሀይድሮ ፓወር ኢነርጂ ነው። ቴሌኮምን ለማሳደግ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ አስፈላጊነት ትልቅ ነው። የአባይ መገደብም ቢሆን ለዚህ አገልግሎት እድገት ወሳኝ ነው።

ፊንቴክ የሚባሉ እንደኛ ያሉ ተቋማት ለአገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆናቸው ይታወቃል። ይህ ሲባል ደግሞ ያለው የአገሪቱ ሕጎች ለእንደነዚህ አይነት ተቋማት መሥራት ባለባቸው ልክ እንዲሠሩ የማይፈቅዱ ብዙ ሕጎች ነበሩ፤አሁንም መቀየር የሚገባቸው አሉ።

ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው ሕጎች መካከል አንዱ ‹ናሽናል ስዊች› ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ባንኮች እና ፊንቴክ በጋራ እንዲሠሩ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በተቋማችን ለሚሠሩ የወደፊት ሥራዎች እንደበር ከፋች አድርገን እናየዋለን።

አሁን ያለንበት ወቅት የውድድር ነው። በዚህ ሁኔታ ወስጥ አገራችን የሚገኙ ባንኮች እርስ በርስ ተደጋግፈው መሥራት አይፈልጉም። ቴክኖሎጂ እና የተለያዩ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙትም ቢሆን ደካማ አገልግሎት በመስጠት ነው የሚታወቁት። ዓለም ደግሞ የተለያዩ መተግበሪያዎችን እያስተዋወቀች ክሬዲት ካርድ ሳይቀር እየተጠቀሙ ነው። አገራችን መቼ ነው እዛ ቴክኖሎጂ ላይ የምትደርሰው?
በአገራችን የሚገኙ ባንኮች ዓለም እየደረሰበት ያለው ፋይናንሻል ቴክኖሊጂ እድገት ላይ ደርሰዋል ለማለት ከባድ ነው። እንኳን ከዓለም ከቅርብ አፍሪካ አገራት ጋር መወዳደር አንችልም። ባንኮች የሚተዳደሩበት ሕግም ቢሆን ተጠቃሚው ላይ ጫና በመፍጠር የባንኮችን ትርፋማ መሆን ነው የሚፈልገው። ከዛ ውጭ ግን ወደፊት ባንኮች ለፍተው ደንበኛ ተጠቃሚ የሚያደርጉበት አስገዳጅ ሕግ እየወጣ ነው። ዓለም ላይ አንድ ሰው በአንድ ባንክ ያለውን ገንዘብ በሰከንድ ውስጥ ባለበት አገር ምንዛሬ ቀይሮ መጠቀም የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ተፈጥሯል።

ብሔራዊ ባንክ እያወጣቸው ያሉ መመሪያዎች የሚበረታቱ ቢሆንም፣ ከዚህ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ዶላር መላክ አንችልም። ስለዚህ ያለንን ተቀማጭ ገንዘብ ወደ ዶላር እንዲቀየር የሚያደርግ መመሪያ ያስፈልገናል። ከብር ወደ ዶላር ቀይሮ መጠቀም አለባት። ለእንደዚህ አይነት ሥራዎች ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ማስቻል የብሔራዊ ባንክ ሥራ ነው የሚሆነው። እንደ ፊንቴክ ተቋም ኹሉም ቴክኖሎጂ አለን። ክሬዲት ካርድ ሆነ ባንኮችን እርስ በርስ ተናበው እንዲሰሩ ማድረግ ቴክኖሎጂውን ማቅረብ ቀላል ነው፤ዝግጁም ነን።

እንደነዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሴኩሪቲ ያስፈልጋል። እንደ አገር ቴክኖሎጂን በደንብ የሚቆጣጠር የዳታ ሴኩሪቲ አቅም መገንባት አለበት። ሃክ ለመደረግ እና ለስርቆት የሚዳርጉ ችግሮችን ቀድሞ ማስተካከል ያስፈልጋል። በርግጥ የሴኩሪቲ ደረጃችንን እስከምናሳድግ ተብሎ ቴክኖሎጂው ሳይተገበር ደንበኛ መጉላላት የለበትም።

ኤም ብር ምን አዳዲስ አገልግሎት ይዞ እየመጣ ነው?
አንደኛው ብሎክቼይን ወደ ዋሌት መቀየር። ለምሳሌ የኤም ብር ዋሌት ውስጥ 500 ብር ቢኖረው በብሎክቼይን ውስጥ በወቅቱ የዶላር ምንዛሬ እኩል አድርጎ ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነትን ያለመቋቋም ችግርን ያጠፋል። አንድ ሰው ዋሌቱ ላይ ያለው ገንዘብ በቀጥታ ወደ ዶላር የሚቀየርለት ከሆነ ማንኛውም ከአገር ውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን መግዛት ይችላል። ገጠር ላሉ ሰዎች ደግሞ ከውጭ የሚላክላቸው በቀጥታ በዋሌታቸው ደርሷቸው መጠቀም ይችላሉ። ይህን አይነት ሥራዎች አብረናቸው እንድንሠራ የጠየቁን አጋር ድርጅቶች አሉ።

እንደዚህ አይነት የገንዘብ ዝውውር የሚጀመር ከሆነ፣ ሕገ-ወጥ የሆነ የገንዘብ ዝውውር ይቀንሳል። ደንበኛ እንደዚህ አይነት ሁኔታ የሚመቻችለት እና ባለበት ዘርፍ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኝ ከሆነ ዶላርን በሕገ-ወጥ መንገድ ማግኘት አይፈልግም። ኢንሹራንስን በተመለከተ ራሱ አርሶ አደሩን የሚጠቅም የለም። ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር እህሉ ባልታሰበ መንገድ የሚወድም ከሆነ ለዛ የሚሆን ካሳ የሚከፍል ድርጅት ያስፈልገዋል። ለዚህ ደሞ ኤም ብር አዲስ ቴክኖሎጂ ይዞ እየመጣ ነው።

እንደ አንድ ፊንቴክ ተቋም እየሠራን ያለነው ሌላ ሥራ የክሬዲት አገልግሎት ነው። ያለምንም ማስያዣ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል ሥራ እየሠራን ነው። የብድር አገልግሎትን ለመጠቀም የሚያስችል አዲስ ሲሰትም እየሠራን እንገኛለን። ይህ ሲስተም አሠራሩ ተግባራዊ የሚሆነው ሲስተሙ ከተዋቀረ በኋላ በዛ ሲስተም አማካይነት የተበዳሪውን የግል ዝርዝር መረጃ በመያዝ ነው። ሲስተሙ ዳታ ላይ የግለሰቡን ታሪክ (ሂስትሪ) ያጠናል ። ከተበደረ በኋላ የመክፈል አቅም አለው ወይ የሚለውን መረጃ በማግኘት የብድር አገልግሎቱን ከማንኛውም ባንክ ማግኘት የሚችልበትን ሲስተም ለመሥራት ታቅዷል።

ሰው ብድር የመክፈል አቅም አጥቶ ሳይሆን ብድር አግኝቶ የመጠቀም እድል ነው ያጣው። ስለዚህ የመበደር አማራጮችን የምናሰፋለት ከሆነ የኢንቨሰትመንት ፍሰት ይጨምራል። ኢኮኖሚውንም ያሳድጋል። 10ሺ ብር ባለማግኘት ብዙ ቢዝነስ የሚቋረጥበት ይኖራል። ያንን የሚደግፍ ‹ሪስክ ከቨር› የሚያደርግ ፓርትነር(አጋር) ይኖራል። እሱን ሲስተም ነው የምንገነባው።

እንደ ፊንቴክ ተቋም ምን ያህል ሠርተናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ፊንቴክ መሥራት ያለበትን ያህል ለመስራት ያሉትን መሰረተ ልማቶች መጠቀም አለበት። ለምሳሌ ኹሉም ሰው ስልክ ይጠቀማል፤ ስለዚህ በስልክ በመጠቀም ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን በማዳረስ ስንሠራ ቆይተናል። የአገራችን መሰረተ ልማት ችግር ቢኖርበትም፣ እንደ ግል ተቋም መድረስ የምንችለውን ለመድረስ ሞክረናል። በዚህም መንግሥት ያላሟላውን በራሳችን መንገድ ተጠቅመን ታች ያለውን ማኅበረሰብ መጥቀም ችለናል። መንግሥት ሕጉን በማሻሻል መንገድ የሚከፍትልን ከሆነ ደግሞ ብዙ ሥራ መሥራት እንችላለን። እኛ አገር አቅሙ ገንዘቡም እያለ ብዙ መሄድ አልተቻለም። ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች የማያሰሩ በመሆናቸው ነው። ኤም ብር የተፈለገበት ደረጃ ላለመድረሱ አንዱ ምክንያት የመንግሥት ፖሊሲዎች ክፍት አለመሆን ነው።

አሁን አዳዲስ ይዛችሁ ለመጣችሁት ቴክኖሎጂ የመንግሥት ፖሊሲ ማነቆ አይሆንባችሁም ?
እንደ ፊንቴክ ተቋም ትልቁ ችግራችን ቴክኖሎጂው ማምጣት ሳይሆን አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች መሻሻል የሚገባቸው አሉ። አንድ ተቋም በሞኖፖል ቴክኖሎጂ መያዝ የለበትም። በመንግሥትም ቢሆን በግሉም ቢሆን እኩል ሥራ እንዲሠራ ካልተደረገ በስተቀር ቴክኖሎጂ ማደግ አይችልም። በግሉም ዘርፍ ቢሆን ተወዳደሪ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ብሔራዊ ባንክ ሕጉን እንኳን ቢያወጣ በርካታ የግል ተቋማትን በሚያሳትፍ መልኩ መሆን አለበት ።

እንደ ኤም ብር በጋራ መሥራት እንፈልጋለን። ፊንቴኮች ከባንኮች ጋር፣ ከተቆጣጣሪው አካል ጋር የምንገናኝበት ነፃ ፎረም ያስፈልገናል። ዲጂታል ፋይናንስ ለማሳደግ የእያንዳንዱ ሚና ምንድነው? በሚል ነጻ የውይይት መድረክ በመፍጠር ዲጂታል ኢኮኖሚ ማሳደግ ይኖርብናል። አንድ ተቋም ኹሉንም አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ሳይሆን ኹሉም ድርጅቶች በአንድ ላይ ተግባብተው እንዲሰሩ የሚያደርግ ፖሊሲ ያስፈልገናል። ፊንቴክም ባንክም ከመሆን ባንክ ብቻ ሆነው ውጤታማ መሆን ይሻላቸዋል። ተቆጣጣሪው አካል የሚያወጣቸው መመሪያዎች ሁሉም የየራሱን ሚና እንዲጫወት ማድረግ የሚችሉ ሊሆኑ ይገባቸዋል። በአገር ደረጃም ቢሆን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። መንግሥት ያልደረሰበት ቦታ ቢዝነስ እንዲደርስ ማድረግ እና በብሔራዊ ባንክ የሚወጡ መመሪያዎች ላይ የኢኮኖሚ አማካሪዎች እንዲሳተፉ ማድረግ አለበት።

ባለፉት 10 ዓመታት የምንችለውን ያህል በሚጠበቅብን ልክ ባንሠራም፣ በብዙ ውጣውረድ እና ፈተናዎች ብናልፍም፣ የመጣንበት ሰዓት ኢትዮጵያ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር ሰዓቱ ያልነበረ ቢሆንም እንደ ፈርቀዳጅነታችን ለሕብረተሰቡ የዲጂታል ፋይናንስ አስተዋውቀናል። ወደፊት መንግሥት ጋርም ቢሆን እየተጋፈጥን በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ተዘጋጅተናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com