የእለት ዜና

የሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን ምርጫዎች ባህሪ!

Views: 62

የህወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ከተመሰረተ ወዲህ የአሁኑን ጨምሮ ስድስት ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ይካሄዱ የነበሩት ምርጫዎች ለይስሙላ ዲሞክራሲ እየተገነባ ነው ለማስባል እንጂ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት እንዳልሆነ የ1997ቱ ምርጫ ምስክር ነው፡፡ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ሕዝብ እንዲያምን የሚደረጉ ቅስቀሳዎች እስካሁን መልካቸውን ሳይቀይሩ ቀጥለዋል፡፡ በተለይ በምርጫ ሰሞን ሕዝብም ሆነ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲያነሱ “ዲሞክራሲ በአንዴ አይገነባም” የምትል የማደንዘዣ መልዕክት በባለ ሥልጣናቱና ካድሬዎች እንደሚስተጋባ የሚናገሩት ግዛቸው አበበ ያላቸውን ምልከታ እንዲህ አስፍረውታል፡፡

ከመንግሥት እና ከውጭ መንግሥታት የበርካታ ቢሊዮን ብሮች በጀት በተሟላለት፣ አንዳንድ የምርጫ ሰነዶቹን በዓረብ አገር ባሳተመው፣ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ወጣ ገባ የሚሉ ፈረንጆች ስለበዙበት የውጭ አገር ኤምባሲ ይመስላል በተባለለት፣ ለበርካታ ዋና ዋና ሠራተኞቹ በመቶ ሽሕ የሚቆጠር ደሞዝ ስለሚከፍል ቅጥረኛነትና አድርባይነት በሚያጠቃቸው ሰዎች እየተመራ እንዳይሆን በተሰጋለት፣ ለበርካታ የምርጫ ጣቢያዎቹና የምርጫ ክልል ሠራተኞች አበል አልከፈለም በሚል ሰበብ ብዙ የሥራ ሰዓታት ወይም በርካታ የሥራ ቀናት በተስተጓጎሉበት፣ በኦሮምያ ክልል ብልጽግና ብቻውን ሩጦ ብቻውን አሸናፊ ለመባል የተበተበውን ሴራ በዝምታ ተመልክቷል በሚል በታማበት፣ እና ሠላም የለም በሚል ምክንያት በብዙ ቦታወች ምርጫ እንዳይካሄድ ባገደው ምርጫ ቦርድ የተመራው ምርጫ-2013 ተካሂዷል። ከወዲሁ የሚፈነጥዙና የሚያማርሩ ወገኖች በየፊናቸው ዕየታዩም ቢሆን የምርጫው ውጤት በመጠበቅ ላይ ነው።

ዲሞክራሲ በአንድ ቀን አዳር አይገነባም፤ ዲሞክራሲ በቀላሉ አንስተህ እንደ ቆብ የምትጭነው ጉዳይ አይደለም፤ ዲሞክራሲ መቶና ኹለት መቶ ዓመታት ዕድሜን በሚጠይቅ ሂደት የሚገነባ ሥርዓት መሆኑን ከአሜሪካ መማር ይገባል፣ወዘተ. የሚሉ አባባሎች ምርጫዎች በመጡ ቁጥር ከህወሓት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናትና ካድሬወች፣ ከአድር ባይ ምሁራን፣ በሥርዓቱ ህልውና ጥቅማቸው ከሚከበርላቸው ባለጸጋወችና ታዋቂ ሰዎች አንደበት መሰማታቸው የተለመደ ነገር ነው። ልማታዊ አርቲስቶችና ልማታዊ ጋዜጠኞችም ይህንኑ ሲያስተጋቡ መሰማታቸው እንግዳ ነገር አይደለም። እርግጥ ነው ዲሞክራሲ እየዋለ የሚያብብ፤ እያደረ ፍሬውን የሚያፈራ፣ እየከራረመ ሰፊ አቃፊነትንና ምሉዕነትን እየተጎናጸፈ የሚሄድ፣ መሆኑን መካድ ተገቢ አይደለም። ነገር ግን ‘በኢትዮጵያችን እየታየ ያለው ነገር እንደዚህ ነውን?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ‘የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት ዲሞክራሲን እንደ ጠላት የሚመለከት ሥርዓት አይደለምን?’ ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው።

የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት ከላይ እስከ ታች የተሰማሩ ፖለቲከኞቹና ካድሬወቹ የየግል ጥቅማቸውን፣ በሕጋዊ ይሁን በሕገወጥ መንገድ ያገኙትን ጥቅማ ጥቅምና ሃብትና ንብረት፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች ያገኟቸውን ማዕረጎች ይዘው ለመቀጠል የሚችሉት ይህ ሕጋዊ ውንብድናን፣ ሕጋዊ ቀማኛነትን፣ ሕጋዊ አጭበርባሪነትንና ሕጋዊ ጸረ-ሕዝብነትን ያሰፈነ ሥርዓት እስካለና ዕድሜውም እስከተራዘመ ብቻ መሆኑን በሚያምኑ ግሰለቦች የተሞላ ነው። ስለዚህም ምርጫ በመጣ ቁጥር የነዚህ ሰዎች ቁልፍ ሥራ የሚሆነው የሥርዓቱን ዕድሜ በማራዘም ነገሮች ኹሉ ባሉበት እንዲቀጥሉላቸው በየወረዳውና በየምርጫ ጣቢያው ጥረት ማድረግ ነው። ለዚህ ነው በ2007 ዓ.ም. ሥርዓቱን ራሱን ያስደነገጠ መቶ-በ-መቶ ያስደፈነ ምርጫ የተካሄደው። በምርጫ 1997 አቶ በረከት ስምዖንን፣ አባዱላ ገመዳንና ጁነዲን ሳዶን የመሳሰሉ ከፍተኛ ሹማምንት ጭምር የሚገኙባቸው በርካታ ኢሕአዴጋውያን ‘የተሸነፍነው ምርጫው ተጭበርብሮ ነው’ ብለው እነሱ በተወዳደሩበት የምርጫ ክልል በድጋሜ ምርጫ እንዲካሄድ አድርገው አሸነፉ መባሉ አይረሳም። ይህን መሰሉ የአውራ ካድሬዎች አካሄድ በቀጣዮቹ ምርጫዎች የመንደርና የሰፈር ካድሬዎችም ጭምር ምርጫ በመጣ ቁጥር አፍራሽ ሚናዎችን እንዲጫወቱ በር ከፍቷል። የእያንዳንዱ ኢሕአዴጋዊ ዋና ሥራ ዲሞክራሲ እንዲያብብ መትጋት ሳይሆን ሥርዓቱ ወድቆ የእነሱ የግል ብልጽግናና የምቾት ዘመን እንዳያከትም ሴራወችን መተብተብና አስመሳይ የምርጫ ጨዋታዎችን መጫወት ከሆነ ሰነባብቷል። ይህን የመሰለ ጸረ-ዲሞክራሲና ጸረ-ምርጫ ዘመቻ ሆነ ብለው እያካሄዱ ዲሞክራሲ በአንድ ቀን አዳር አይገነባም እያሉ መቀለድ ተገቢ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ ለዘላለሙ እንዳይገነባ ጥረት እየተደረገ ነውና።

በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን በከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በወረዳዎች፣ በትንንሽ ከተሞች ወይም በገጠር መንደሮች ውስጥ ሳይቀር ዘርፈው የከበሩ፣ ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው ሰውን ያሰሩና የደበደቡ፣ የገደሉና ብዙዎችን ከመኖሪያቸው እንዲሰደዱ ያደረጉ በርካታ ግለሰቦች ምርጫዎች በመጡ ቁጥር ሕዝብ መረጣቸው እየተባሉ በትንንሹና በትልልቁ ሥልጣን ላይ እንደተኮፈሱ ኖረዋል። ለውጥ መጣ ተብሎ ሕዝብ መዋቅሮች እንዲስተካከሉ፣ ግፈኞች ከአመራርነት እንዲነሱ ጥያቄ ሲያቀርብ የተሰማው ለዚህ ነው። የሕዝብ ጥያቄ አድማጭ ስላጣ የብልጽግና ዘመን ሰው እንደ ዋዛ የሚገደልበት፣ የሰው ሃብትና ንብረት እንደ ዱር ፍሬ በተመኘው ኹሉ የሚዘረፍበት፣ የምስኪኖች ቤት እንደ ማገዶ የሚነድበት፣ መጤ የተባሉ ኢትዮጵያውያን እንደ ባዕዳን ተቆጥረው ውጡልን የሚባሉበት ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ግድ ሆኗል። በምርጫ-2013 ከነዚህ ግፈኞች ስንቶቹ ይሆኑ ለምርጫ በዕጩነት የቀረቡት?

ምርጫዎች በመጡ ቁጥር በየምርጫ ጣቢያው የሚፈጸሙ መራጮችን የማስፈራራት እና ተመራጮችን (ዕጩዎችን) የማጥቃት ዘመቻዎች፣ ታዛቢዎችን የማባረር ተግባራት፣ መራጮችን እያስገደዱ ለገዥው ቡድን ድምጽ እንዲሰጡ የማድረግ ድርቅናዎች፣ መራጮችን እያደራጁ በቡድን ተመሳሳይ ድምጽ እንዲሰጡ የማድረግ ጠርናፊ አካሄዶችና የመሳሰሉት ተግባራት አገዛዙ እያወቀ የሚፈጸሙ የህወሓት/ኢሕአዴግ ጸረ-ዲሞክራሲና ጸረ-ምርጫ ወንጀሎች ናቸው። አስፈሪው ነገር እነዚህን ወንጀሎች የሚፈጽሙትና የሚያስፈጽሙት ኢሕአዴጋውያን በሕዝብ ተገምግመው በምርጫ ጣቢያወች ድርሽ እንዳይሉ ስለመደረጋቸው ምንም የተነገረ ነገር ሳይኖር ነው ምርጫ 2013 የተካሄደው።

ብዙ ሰዎች የ1997ቱን ምርጫ እያስታወሱ የሥርዓቱ ዲሞክራሲያዊነት ከፍ ብሎ እንደነበረና ከዚያም እንደገና ዲሞከራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው እያሽቆቆለ መሄዱን ሲናገሩ ይሰማሉ። ነገር ግን፣ ህወሓት/ኢሕአዴጋውያን በ1997 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 17 ምሽት ዲሞክራሲያዊ መስለው የታዩት የተሞኘልንን አሳምነን፣ የሚደናበረውን አደናብረንና፣ የሚሸወደውን ሸውደን፣ ዲሞክራሲያዊ ገጽታ ገንብተናልና በምርጫው የብዙውን ሕዝብ ድምጽ እናገኛለን ብለው በተሳሳተ ምክንያታዊነት ላይ ተመርኩዘው ያንን የመሰለ የምርጫ ክርክርና የምርጫ ሂደት እንዲኖር መፍቀዳቸውን በመጥቀስ የሚሞግቱም ብዙዎች ናቸው። ምርጫው ሊካሄድ ኹለት ቀናት ሲቀሩት አቶ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚወች ጥቂት ወንበሮችን እንደሚያገኙና ሥራቸውም ወንበሩን ከማሞቅ የዘለለ እንደማይሆን በሙሉ እርግጠኝነት መናገራቸው የሚረሳ አይደለም።

ግንቦት 7/1997 ዓም በህወሓት/ኢሕአዴግ መንደር ድንጋጤ የተፈጠረው ከቀኑ ዘጠኝና ዓስር ሰዓት አካባቢ መሆኑን ከህወሓት መንደር የተናፈሱ ወሬወች ያሳያሉ። በዚያ ቀን በመላ አገሪቱ በሚባል ደረጃ ብዙዎች ለምርጫ በተሰለፉበት ቦታ፣ ድምጽ ሰጥተው ሲወጡና በሌላም አጋጣሚ የቅንጅትን የጣት ምልክት እያሳዩ ሃሳብ መለዋወጣቸውና ሰላምታ መስጠታው፣ ድምጽ ሰጥተው የምርጫ ጣቢያውን በመልቀቅ ላይ እያሉ አለቀ ደቀቀ የሚል ምልክት የሚያሳዩ ወይም የህወሓት/ኢሕአዴግን ሥርዓት ቀበርነው እያሉ በይፋ የሚናገሩና የመሳሰሉ ስሜትን ገላጭ ነገሮችን ማሳየታቸው፣ አንዳንዶችም የምን የምስጢር ድምጽ መስጫ ነው እያሉ በአስመራጮችና በታዛቢወች ፊት ከቅንጅት የምርጫ ትይዩ ምልክት እያኖሩ የምርጫ ወረቀቱን ወደ ኮረጆ መጨመራቸውና የመሳሉት ድርጊቶች በብዛት ሪፖርት በመደረጋቸው በህወሓት/ኢሕአዴግ ካምፕ ሽብርን ማንገሱ የውስጥ አዋቂዎች ይናገሩ ነበረ። ምርጫውን አስቀድመው ያጠናቀቁ የምርጫ ጣቢያዎች ቆጠራ እንዲያካሂዱና ውጤቱን የኢሕአዴግ ሰዎች ወደ በላይ አካል ሪፖርት እንዲደርጉ መደረጉንም እነነዚሁ የውስጥ አዋቂዎች ተናግረዋል። ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባው ምርጫ ለአዲስ አበባ ጥሩ ነገር ሠርተዋልና እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በእሳቸው ሥራ ሌሎች ኢሕአዴጋውያን ይመረጡ ዘንድ ይረዳሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው የአቶ አርከበ ዕቁባይ በምርጫው መሸነፍ ወደ መቐለው የህወሓት ጽሕፈት ቤት ሪፖርት የተደረገው የግንቦት 7 ፀሐይ ሳትጠልቅ መሆኑን በወቅቱ በመቐለ የነበሩ ሰዎች ተረድተውታል። ወሬው እንደ ሰደድ እሳት ነበረ በፍጥነት በመላ ከተማዋ የተዛመተው። ይህን መሰሉ ነገር ተደማምሮ ነው ግንቦት 7 ከምሽቱ ኹለት ሰዓት ላይ አቶ መለስ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ላይ ቀርበው የአገሪቱ ታጣቂ ኃይል በሙሉ በእሳቸው ትዕዛዝ ስር መግባቱን፣ መሰብሰብና መሰለፍ ብቻ ሳይሆን በጣት የቅንጅትን የምርጫ ምልክት ማሳየት ለቅጣት እንደሚዳርግ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ ያደረጋቸው። ከዚህ በኋላ ምርጫን በተፈለገው መንገድ ማጭበርበር፣ የመራጭን እጅ መጠምዘዝና ማምታታት ካልሆነም በጠራራ ጸሐይ ኮሮጆ መገልበጥ ለተራው ካድሬ ሁሉ በይፋ የተሠጠ መብት የሆነ መሰለ።

በምርጫ 1997 የታዩትን ክስተቶች ተከትሎ በህወሓት/ኢሕአዴግ ሰፈር የሰፈነ አንድ አመለካከት አለ። ጥቂትም ይሁኑ ብዙ የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት አባላት ምርጫ 1997 እስኪመጣ የሕዝብን ፈቃድ ያገኘ አካል አገሪቱን መምራት እንደሚገባው እምነት ነበራቸው፡፡ ምርጫ 1997 እውነተኛ ምርጫ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ተቋም እንጅ ለህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት አዋጭ አለመሆኑን ካሳየ በኋላ ግን ሁሉም በሚባል መጠን የህወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎችና ተራ አባላት ሁሉ ድርጅታው በማንኛውም መንገድ ምርጫዎችን እንደ ሽፋን እየተጠቀመ፣ ምርጫዎችን በማንኛውም ዘዴ እያጭበረበረ፣ ሕዝብ መረጠኝ እያለ የሥርዓታቸውን ሕልውና ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን አምነውበታል ማለት ይቻላል። ምርጫን በስጋት ዐይን ማየትና በምርጫወች ወቅት የተፈለገው ወንጀልና አፈና ተፈጽሞ ሥርዓቱ እንዲቀጥል ማድረግ ተገቢ መሆኑን አምነውበታል ማለትም ይቻላል። ይህ አቋም ወደ ተግባር ተተርጉሞም በምርጫ 2002 አንድ ተቃዋሚ ብቻ፣ በምርጫ 2007 ደግሞ ምንም ተቃዋሚ የሌለበት ፓርላማ ሠርተው በአገሪቱ ላይ ፈንጭተዋል፤ በመጠነ ሰፊ አፈናና ዝርፊያ እየበለጸጉ ለመኖር ሞክረዋል።

በምርጫ 2002 ዋዜማ በአንድ አካባቢ በተደረገ የሥርዓቱ ካድሬዎች ስብሰባ ላይ የስብሰባው መሪ የሰጠውን ምክር መለሰ ብሎ ማየት ኢሕአዴጋውያኑ እውነተኛ ምርጫዎችን ለምን እንደሚፈሩና ምርጫዎችን ማምታታትን ለምን እንደ ጠቃሚ ነገር አድርገው እንደሚያዩ በግልጽ ለመረዳት ያስችላል። ሰብሳቢው የሰነዘረው ማስጠንቀቂያ መሰል ማሳሰቢያ ህወሓት/ኢሕአዴጋውያኑ የትዳር ጓደኞቻቸውንና ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ቤተዘመዶቻውንና ጎረቤቶቻቸውን ኹሉ ለሥርዓቱ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው የሚናገር ነበረ። ይህን ማድረግ ካልታቻለ በትልልቅ ስልጣንና ሥራወች ላይ ያሉ ብዙ ኢሕአዴጋውን ወደ መሀይምነታቸውና ወደ ተራ ሥራዎቻቸው እንደሚመለሱ ሰብሳቢው ሲናገር ተሰምቷል። ሰብሳቢው ይህን የተናገረው በምርጫ 1997 ቅስቀሳ ወቅት የቅንጅት መሪዎች በፎርጅድ (በሀሰተኛ)የትምህርት ማስረጃዎች፣ በሥራ ላይ ካሉ የአገርቤትና የውጭ የትምህርት ተቋማት በገንዘብ በተገዙ የትምህርት ማስረጃወች ሽፋን ምሁር ተብለው በየሥልጣን ቦታውና በየሥራ መስኩ የተሰገሰጉ ግለሰቦችን እንመነጥራለን ብለው የተናገሩትን በማስታወስ ነው። ስለዚህ ለዚህ ካድሬ ምርጫ ማለት በየአምስት ዓመቱ የሚመጣ ምቀኛና እንደምን ተደርጎ ተጭበርብሮ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን የምሁርነት ማዕረግ ለማስቀጠል ድራማ ሊሰራ የሚገባበት አጋጣሚ ነው ማለት ይሆናል። ባለ ዲፕሎማ፣ ባለ ዲግሪ፣ ባለ ማስተርና ባለ ፒኤች ዲ ካድሬዎች ምርጫውን እንዲህ በስጋት የሚያዩትና ለማጭበርበሩ እንዲህ በመንጋ የሚዘምቱበት ከሆነ ሥርዓቱ ሚሊዮነርና ቢሊዮነር ያደረጋቸው ፖለቲከኞች፣ ካድሬዎች፣ ልማታዊ ባለሃብቶች፣ ልማታዊ አርቲስቶችና ልማታዊ ጋዜጠኞች፣ወዘተ. ስለምርጫ ምን እንደሚያስቡና ምን እንደሚደርጉበት መገመቱ ከባድ አይሆንም። በዚህ ዓይነቱ የተጣመመ አመለካከት ላይ የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት የሚያራምደው ዘር ተኮር ፖለቲካና ጠባብ ክልላዊ ወገንተኝነት ሲጨመርበት ምርጫ ግለሰባዊ ጥቅም የሚያስከብረውን ሥርዓት ዕድሜ ከማራዘም አልፎ አገርንና ሕዝብን የሚጠቅም ፍሬ ለማፍራት የማይችል ይሆናል።

የሚገርመው ነገር እነዚህ ሁሉ እንዲህ በተናጠልና በመንጋ በጸረ-ዲሞክራሲ ዘመቻ ተሰልፈው እየታዩ ነው ልማታዊ ምሁራን ምርጫ በመጣ ቁጥር ዲሞክራሲ በአንድ ቀን አዳር እንደማይገነባና ኢሕአዴግ የዲሞክራሲ ግንባተውን ተያይዞታል እያሉ ሲነግሩን የከረሙት።
በቁጥር ኹለት ኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ የተለመደውን የግል ጥቅማ ጥቅምንና ዘረኝትን መሰረት አድርጎ በምርጫ ከመሳተፉ በተጨማሪ ኃይማኖትን መሰረት አድርጎ ለመመረጥና ለመምረጥ መሮጥ በጉልህ እየታየ የቆየ ጉዳይ ነው። በምርጫ 2013 ሦስት የፖለቲካ ቡድኖች ኃይማኖታዊ መስመሮችን ተከትለው ለመመረጥ ውስጥ ውስጡን መሥራታቸው ሕዝብን በሰፊው እያነጋገረ የነበረ ጉዳይ ነው። በእምነት ተቋማት ውስጥ የተካሄዱና ሰዎች የትኛውን የፖለቲካ ድርጅት መምረጥ እንደሚገባቸው በመስበክ ኃይማታዊ ጫና የሚሳድሩ ቅስቀሳዎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች መሰራጨታቸው፣ ድርጅቶቹ ለምርጫ ያሰለፏቸው ዕጩወች የአንድ እምነት ተከታዮች መሆናቸውና የመሳሉት ነገሮች ሃቁን የሚያጋልጡ ቢሆኑም፣ የፖለቲካ ድርጅቶቹ አመራሮች መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ጉዳዩን የሚመለከት ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲክዱ፣ ሲቆጡና ሰዎችን ሲዘልፉ ተስውለዋል።

ቀድሞም ይሁን አሁን በዘመነ ኢሕአዴግ ምርጫዎች ጠባብ አጀንዳዎችን ተንተርሰው እንዲካሄዱ ስለሚደረግ አንድን ወይም እንዲትን በሙያው/በሙያዋ አንቱ የተባለ/የተባለች ዶክተር እዚህ ግባ የሚባል ሙያና ዕወቅና የሌለው/የሌላት ግለሰብ አሸነፈው/አሸነፈችው የሚል ወሬን መስማት የተለመደ የኢሕአዴግ ዘመን ምርጫዎች ገጠመኝ ነው። ሰዎች ፈጽሞ የማያውቁትን ሰው የገዥው ቡድን ዕጩ ስለሆነ ብቻ መምረጣቸውም የተለመደ ነገር ነው። በተሰማራበት ሥራ ወይም በተሰጠው ሹመት እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ባይከውንም፣ የገዥው ቡድን ዕጩ በመሆኑ ብቻ ይመረጣል። ይህን መሰሉ አካሄድ ሥርዓቱ በአንድ አምባገነን ፈላጭና ቆራጭነት የሚዘወር መሆኑን ከማሳየት አልፎ ሌሎች ባለሥልጣናትና ተመራጮች ኹሉ የሚመራቸውን ወይም የሚጎትታቸውን ፈረስ ከመከተል ውጭ ሌላ ሚና የሌላቸው የበድን ጋሪነት ሚና ብቻ ያላቸው መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

በመላው ዓለም በሚባል ሁኔታ በስፖርት ውድድሮች ተመልካቾች ወደ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራወች እንዳይገቡ ተደርጓል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ይህን አሰራር ተከትሎ በፌዴሬሽኑ ስር በሚመሩ ውድድሮች አንድ ቡድን ከዐስር ያልበለጡ ደጋፊወቹን ብቻ ይዞ ወደ ስቴዲዮሞች እንዲገባ የፈቀደው የ2013 ዓ.ም. የውድድር ዘመን ተጠናቋል። ነገር ግን ፖለቲካዊ ስብሰባወች፣ ለብልጽግና ቡድን ገጽታ ማሳመሪያና ድጋፍ ማሳያ ተብለው የሚደረጉ ሰልፎችና የስፖርት እንቅስቃሴዎች፣ ከሰፈሮች እስከ ክፍላተ ከተሞች በተደራጀ ሁኔታ የሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮች፣ወዘተ. የሕዝብ ብዛትና የኮቪድ-19 ጥንቃቄዎች ቁጥጥርና ክትትል ሳይደረግባቸው እየተካሄዱ ነው ቆዩት። ስቴዲዮሞች፣ አደባባዮች፣ አዳራሾች፣ ጎዳናዎችና የመሳሰሉት ቦታዎች ሕዝብ በብዛት ተሰባስቦ እንዲውል የተደረገባቸውን አጋጣሚዎች መቁጠር በጣም ያዳግታል። ይህ ሁሉ የሚደረገው ለብልጽግና ቡድንን ፕሮፓጋንዳ ከመሥራት ጀምሮ የአንድን ወይም የአንዲትን የብልጽግና ፖለቲከኛ ገጽታ ለማሳመርና የሚሊዮኖች የጤና ሁኔታና ሕይወት ችላ ተብሎ ነው። ይህን የመሰለው ፖለቲካዊ ጥቅምን ያስቀደመና የሕዝብን ደኅንነት ችላ ያለ ግርግር በሰፊው የተካሄደው በዋናነት የጤና ሚኒስትሯንና የአዲሰ አበባ ምክትል ከንቲባን ደንታቢስነት ተመርኩዞ ነው። እነዚህ ግለሰቦች በምርጫው ዕጩ ሆነው ቀርበዋል። ይህን አሳፋሪና አሳዛኝ የሆነ፣ ሥልጣንን አስቀድሞ የሕዝብ ጤንነትን ችላ ያለ ሥራ የመሩና በዝምታ የተመለከቱ ሰዎች በዕጩነት የቀረቡት ብልጽግና ቡድን የአባቱን የኢሕዴግን የምርጫ ሂደት መከተሉ አይቀሬ በመሆኑ ነው። ለነገሩማ እነዚህን የመሳሰሉ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው ሰዎች በዕጩነት መቅረባቸውን እያወሳ የገመገመ መገናኛ ብዙኃን፣ እነሱን በግል እየተቸ እኔ እሻላለሁና ምረጡኝ እያለ የቀሰቀሰ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ዕጩም አልነበረም።

ስለተቃዋሚዎች ከተነሳ አይቀር አንድ ነገር ማለት ተገቢ ነው። በስደቱ ዓለም ይኖሩ የነበሩ ተቃዋሚዎች ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ በእስር ቤት የነበሩ ተቃዋሚወችም ነጻ ናችሁ ተብለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ በቅተው ነበረ። ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ ወደ ስደቱ ዓለም የተመለሱና ወደ እስር ቤት የተወረወሩ ተቃዋሚወች ቁጥር ቀላል አይደለም። ይህን የመሰለ ነገር በታየበት ወቅት የተካሄደውን ምርጫ የተበላ ቁማር ነው የሚሉ ብዙዎች ነበሩ። አሁን አሁን ብዙዎች በምርጫው ማን አሸነፈ ብለው ውጤት ከመጠባበቅ ይልቅ በአደባባይ፣ በጎዳናዎችና በስቴዲዮሞች ወጣቱ ትውልድ ጉሮ ወሸባዬ እያለና እያጨበጨበ ከተቀበለቸው ተቃዋሚወች ውስጥ እነማን ድምጻቸውን አጥፍተው ወደ መጡበት ውጭ አገር ይመለሳሉ የሚለው ጥያቄ የሚብላላ ሆኗል።

ግዛቸው አበበ በኢሜል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.comማግኘት ይችላሉ፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com