የእለት ዜና

አለመምረጥ አማራጭ አይደለም! ( ምክር ለዜጎች፤ ኃላፊነት ለመሪዎች )

Views: 56

በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ‹‹መሪ›› የሚባሉ አካላት እጅግ በጣም በርካቶች ናቸው። መሪ የፓለቲካ ሰዎች እና ከቀበሌ እስከ የፌደራል ከፍተኛ የሥልጣን ርከን ላይ ያሉ የመንግሥት አመራር አካላት ብቻ አይደሉም። ጋዜጠኞችና የሚድያ አካላት ፣ በእያንዳንዱ የጥናት እና ምርምር ዘርፍ ውስጥ ያሉ ምሁራን ፣ ደራሲያን እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ፣ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ድረስ ያሉ መምህራን በጠቅላላ መሪዎች ናቸው። ከዚህ የተረፈው ሕዝብ ማሕበረሰብ ( ዜጋ ) በሚባል የወል ስም አቤት የሚል ፣ የራሳቸውን ኑሮ ኖረው የራሳቸውን ሞት ለመሞት በሚተጉ ግለሰቦች ጥርቅም የተሰላ ስብስብ ነው። ከዕለት ተዕለት ኑሮው ባሻገር ያለውን ማሕበረሰባዊ ዓለም አሻግሮ አይመለከትም።

ይሄንን ስብስብ ከፊት ሆነው የሚመሩት እና ዘመን የሚያሻግሩት እነዚህ ከላይ መሪ ብለን የጠራናቸው ብርሃናማ አካላት ናቸው። የዓለም ስርዓት በጠቅላላ ይሄንን የተከተለ ነው። የሰው ልጅ ከታችኛው የስልጣኔ ወለል ተነስቶ እዚህ እስኪደርስ ድረስ የመጣው በጥቂት ግለሰቦች መንገድ መሪነት ነው። እነዚህ መሪዎች ሕዝብን በአደራ ተቀብለዋል። በዘመናቸው አንድ ከፍታ ላይ ካደረሱት ፣ አንድ የሆነ ዘመን ካሻገሩት በኋላ ለተከታዩ ይሰጡታል። ማሕበረሰብ በዚህ የመሪዎች ቅብብል ሂደት ውስጥ ነው ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ ወደ ስልጣኔ ከፍታ የሚጓዘው።

የአንድን ማሕበረሰብ የስልጣኔ ደረጃ ከሚለኩት ነገሮች አንዱ ምርጫ መሆኑ ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል። የማንኛውም ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መገለጫ የሆነውን ምርጫ፣ ቀደም ብለው ከጀመሩት እና ባህላቸው ካደረጉት አገራት እኩል ባይሆንም፣ አገራችንም በየአምስት ዓመታቱ ልዩነት እያለፈችበት ትገኛለች። በዘንድሮው ዓመትም ይሄው ምርጫ ከተደረገ ጥቂት ቀናት አለፉት። በርግጥ ምርጫው ገና አልተጠናቀቀም። በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ ዜጎች አስደናቂ በሆነ ትዕግስት፣ በዝናብና ጨለማ መሀል መርጠው ተመልሰዋል። ምናልባት ግን አስቀድመው የምርጫ ካርድ ወስደው በልዩ ልዩ ምክንያቶች በወቅቱ መምረጥ ያልቻሉ እና ሳይመርጡ ግዜው ያለፈባቸው አካላት እንዳሉ ይነገራል።

ከነዚህ ባሻገር አስቀድሞም የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ እና የዘንድሮውን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ሳይጠቀሙበት የቀሩ ዜጎች ብዙ እንደሆኑ የሚናገሩ አሉ። በርካታ ዜጎች በአንድም ይሁን በሌላም ምክንያት በዘንድሮ አመት ምርጫ ይወክለናል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ሳይመርጡ ቀርተዋል። ሰሞኑን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ይወክለናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ሳይመርጡ የቀሩ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዜጎች ላለመምረጣቸው በርካታ ግላዊ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል። በርግጥ እያንዳንዱ ግለሰብ የየራሱ ግላዊ ሰበብ እና ምክንያት ያለው ቢሆንም ኃይማኖታዊ ሰበብ፣ አሁን አማራጭ ይዘው ከቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ይወክለናል የሚሉት የተሻለ የፖለቲካ ፓርቲ እና አማራጭ ማጣት፣ ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ግላዊ ኑሮ እና ህይወት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ማሰብና ቸልተኝነት ተደጋግመው የሚነገሩ እና የሚስተዋሉ ምክንያቶች ናቸው። አልፎ አልፎም ከዛሬ ነገ በሚል ቸልተኝነት ሳይመርጡ ወቅቱ ያለፈባቸው እና የምርጫ ጊዜው ካበቃ በኋላ ባለመምረጣቸው የተጸጸቱ ቢኖሩም፣ በመሰረታዊነት ግን ስለ ምርጫ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ እና አስተያየት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ይሄ የተሳሳተ ግንዛቤ ግን፣ ምርጫ ራሱን ችሎ ድብቅ እና ውስብስብ ትርጉም ያለው ቃል በመሆኑ የመጣ አይደለም።

ምርጫ ከቀረቡት በርካታ አማራጮች መካከል አንድ ግለሰብ የሚስማማውን ሃሳብ የያዘን ቡድን ወይ ግለሰብ መምረጥ ማለት እንደሆነ ለማንም የተሰወረ ትርጉም አልነበረም። ነገር ግን ከለውጡ በፊት በነበረው ሥርዓት ውስጥ የነበሩት ያለፉት አምስት የምርጫ ወቅቶች ባሳረፉባቸው ተጽዕኖ ምክንያት ለምርጫ ያላቸው ምልክታ ጤናማነቱ የተቃወሰባቸው ሰዎች በርካቶች ናቸው። ከዚህ በፊት በነበረው ሥርዓት ተካሂደው የነበሩት እና በብዙ ምሁራን ዘንድ እንደከሸፉ የሚቆጠሩት አምስቱ የምርጫ ወቅቶች ያሳረፉት ተጽዕኖ እጅግ አሳሳቢ እና ወደፊትም ጠንካራ ሥራ ተሠርቶበት ምርጫ ከዜጎች ህሊና ላይ ተስተካክሎ እንዲጻፍ ካልተደረገ ለመጻዒ የምርጫ ወቅቶችም አሳሳቢ ችግር መሆኑ የማይቀር ነው።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዜጎች ከሞላ ጎደል ዋና ምክንያታቸው፣ ‹‹ ሁልግዜም ቢሆን ሥልጣን ላይ ያለው የመንግሥት አካል ማሸነፉ አይቀርም›› የሚል ነው። ልክ ከአሁን በፊት እንደነበሩት ወቅቶች አሁን የተደረገውና ገና ያልተጠናቀቀው ምርጫም አሁን በሥልጣን ላይ ካለው አካል ውጭ እንደማይሆን ፍፁም ርግጠኛ በመሆን ምርጫ ለማድረግ ፈቃደኞች ሳይሆኑ መቅረታቸውን ለ አዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ከዚህኛው ቀጥሎ ተደጋግሞ የሚሰማው ድምፅ ከዚህ በፊት ከነገሥታቱ ዘመን ጀምሮ የነበረን የመንግሥት የሥልጣን ልውውጥ ባህላችን እንዳስለመደን የትኛውም መንግሥት በሰላምና በጸጥታ ወንበሩን ለተተኪው እንደማያስረክብ በዜጎች ልቦና ውስጥ ተደምድሟል።

አንዳንድ ጊዜም ሥልጣንን በምርጫ ተሸንፎ በፈቃደኝነት ለአሸናፊው አካል አስረክቦ መውረድ የሥልጣንም ሆነ የፖለቲካ ተፈጥሯዊ ባህርይ አይደለም እስከሚል ድምዳሜ በመድረስ። ‹‹ሰይፍ የመዘዘ በሰይፍ ይሞታል›› እንደሚባለው በጦርነት በትረ ሥልጣኑን የጨበጠ መንግሥት ወንበሩን የሚለቀውም በጦርነት ነው የሚል አስተሳሰብ ገዝፏል። አንዳንዶቹም ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለቀጣዮቹ የምርጫ ዘመናትም ቢሆን የመምረጥ ፈቃድ እንደሌላቸው አስረግጠው ይናገራሉ።

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው አንድን ማሕበረሰብ ዐይን እና ጆሮ ሆነው ሊመሩት፣ ሊያሻግሩት የሚችሉት ከላይ ‹‹መሪ›› ብለን የዘረዘርናቸው የማሕበረሰብ አካላት ናቸው። ማሕበረሰብ ባለመሰልጠኑ፣ ኋላ በመቅረቱ ፣ በመሳሳቱ ፣ በጥፋቱ ሁሉ ሊወቀስ አይችልም። ቢወቀስ እንኳን ትልቁን ኃላፊነት እነዚህ መሪ አካላት መውሰዳቸው አይቀሬ ነው።

ማሕበረሰባችን ስለ ምርጫ ያለው ግንዛቤ በአብዛኛው የተሳሳተ እና በተጽዕኖ ስር የወደቀ ነው። ይሄንን ማረም እና ማስተካከል የእነዚህ ኹሉ ተዋናዮች ትልቅ የቤት ሥራ ነውና አብዝተው ሊያስቡበትና ትልቅ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባቸዋል። ከሁሉም በላይ ግን መንግሥት ሊያስብበት ይገባል። ምናልባት ካለፉት የምርጫ ወቅቶች በተለየ መልኩ በዘንድሮው ዓመት የተደረገውና ገና ያልተጠናቀቀው ምርጫ ፍትሐዊ ፣ ሰላማዊ እና የዜጎችን ምርጫ አክብሮ እና አስከብሮ የሚያልፍ ከሆነ የቀጣይ የምርጫ ዘመናት ዕጣ ፋንታ ከዚህ አሁን ከተደረገውም ሆነ ከዚህ በፊት ከነበሩት ፍጹም የተለየ እና የተሻለ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አለመምረጥ አማራጭ ሆኖ የቀረበበት ግዜ የለም። ሰዎች ሁል ግዜም ከኹለት ትይዩ አማራጮች መካከል አንዱን በመምረጥ ውሳኔ ውስጥ ነው የመጡት። ይሄ ሊዛነፍ የማይችል የተፈጥሮ እና ማሕበረሰብ ሕግ ነው። በክፉና ደግ መካከል ፣ በማድረግና ባለማድረግ መካከል ፣ በመሆን እና ባለመሆን መካከል ፣ በመንታ መንገዶች መካከል ፣ በኹለት ግራና ቀኝ አማራጮች መካከል ምርጫ ማድረግ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው። ስለሆነም ዜጎቻችን ሊያስቡበት እና የሚመለከታቸው አካላትም ትኩረት ሰጥተው ትልቅ የግንዛቤ ሥራ ሊሠሩበት ይገባል። አሁን በአገራችን በምርጫ የተሳተፈው ሕዝብ ቁጥር ብዙ የሚባል አይደለም። ምናልባት ኹሉም ዜጋ በምርጫው ላይ የመሳተፍ ዕድሉን ቢጠቀምበት ኖሮ ውጤቱ አሁን ከሚሆነው የተለየ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም። ነገር ግን፣ ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን አሟልተው ባለመጠቀማቸው ምክንያት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በተወሰኑት ዜጎች ድምጽ ብቻ እንዲወሰን ግድ ሆኖበታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com