የእለት ዜና

ስለ ፓርቲዎች የምርጫ አቤቱታ ሕጉ ምን ይላል?

Views: 73

ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም የተካሄደው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ተተብትቦ አልፏል፡፡
በተለይም ደግሞ ከአንድ መቶ ሥልሳ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው ቅሬታ እና አቤቱታዎች ለቦርዱ ትልቅ ተግዳሮት ሆነውበታል፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ምርጫ ላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያነሷቸው ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች በሕግ አግባብ እንዴት ይታያሉ? ሕጉስ ምን ይላል? ለሚሉትን ጥያቄዎች የምርጫ ቦርድን እና የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ምላሽ አካቶ የአዲስ ማለዳው ወንድማገኝ ኃይሉ ተመልክቶታል፡፡

ምርጫ ከበርካታ አማራጮች ወይም መፍትሄዎች መካከል አንዱን የመምረጥና ሌላውን የመተው ሂደት ወይም አንድን ቡድን ወይም ግለሰብ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲይዝ የማደረጊያ ሂደት ነው። በኢትዮጵያ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ፓርላሜንታዊ በመሆኑ (የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 45) እንደሌሎቹ በፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት ሥርዓት እንደሚተዳደሩ አገራት (ለምሳሌ አሜሪካ) ዜጎች መሪዎቻቸውን በቀጥታ አይመርጡም። ሕዝቡ ተወካዮቹን ወይም የምክር ቤት አባላቱን ከመረጠ በኋላ በሕዝቡ ድምፅ መሰረት መንግሥት የሚመሰርተው አሸናፊው የፖሊቲካ ድርጅት በፌደራል ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በክልሎች ደረጃ ደግሞ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮችን ይመርጣል።

የአስፈጻሚ አካሉም ቢሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩና በክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ሹመታቸው ይጸድቃል እንጂ ሕዝቡ በቀጥታ የሚመርጥበት ሥርዓት የለም። በአገራችን የምርጫ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከልም አንደኛው ይህ ምርጫ እንደሆነ በየጊዜው ሲነገር ይስተዋላል። ይህ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተካሄደበት አውድ በአገር ውስጥ የተደራረቡ ችግሮች የገጠሙበት እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ባሉበት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምርጫው እንዲተላለፍ አስገዳጅ በሆኑበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ምክንያት በእስር በሚገኙበት ወቅት መሆኑ ነው።

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድም ጠንካራ፣ ገለልተኛ እና ተዓማኒ የሆነ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ ለማድረግ ብዙ ሲሠራ እንደከረመም ይታወቃል። ይሁንና ታዲያ አሁን አሁን በተለይም በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ የተስተዋሉ ከአንድ መቶ ሥልሳ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች ለቦርዱ ትልቅ ተግዳሮት ሆነውበታል። መሠረታዊ የሆኑ የምርጫ መርሆዎች መረጋገጥና መከበር ለአንድ ምርጫ ስኬታማነት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መለኪያዎች ቀዳሚ መሆናቸውም እሙን ነው።

በአገራችን የሚከናወን ምርጫ እነዚህን መርሆዎች ማሟላት ያለበት መሆኑን በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 54 (1) እና በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 5 ላይ ማንኛውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛ፣ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት እና ያለምንም ልዩነት በሚደረግ ሕዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ ይሆናል በሚል ተደንግጓል። ይሁን እንጂ እነዚህን አንዳንድ ሕግ እና ሥርአቶችን በመተላለፍ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተካሂዶ እንዳለፈ ለአዲስ ማለዳ የሚናገሩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ዋና ጸኃፊ ገለታው ዘለቀ ናቸው።

ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለጸ ባይሆንም፣ በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ እንደነበር ገለታው አንስተዋል። የፓርቲው ዋና ጸኃፊ እንደገለጹት፣ በተለይም በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ ግድያ፣ ድብደባና የአካል ጉዳት ደርሷል። በአዲስ አበባ፣ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አከባቢ የጸጥታ ኃይሎች ታዛቢዎቻችንን የማስወጣት እና የማስፈራራት ተግባር እንዲሁም ዛቻ አዘል ድርጊት ፈጽመዋል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ፓርቲው ካሉት ቅሬታዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች የተከፈቱ ትርፍ የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው አግባብ እንዳልሆነ አንስተዋል።

ይህም በአገሪቱ የምርጫ ታሪክ የመጀመሪያ ሊያስብለው የሚችል ኢ- ፍትሃዊ እና ብልሹ አሰራር ሲሉም ገልጸውታል። በአገሪቱ የምርጫ ታሪክ ተጭበረበረ፣ የምርጫ ኮሮጆ ተዘረፈ ተብለው ከሚነሱ የተለመዱ ችገሮች በተለየ መልኩ ቦርዱ የማያውቃቸው የምርጫ ጣቢያዎች መከፈታቸው የሚያሳፍር ተግባር ነው። ይህ በየትም አገር ያልተለመደ ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው ሲሉ በምሬት ነግረውናል። አክለውም ትርፍ የምርጫ ጣቢያዎች መከፈታቸው ብቻ ሳይሆን የሚያስገርመው፣ የምርጫ ግብአቶች ከየት መጥተው እነዚያ ጣቢያዎች ላይ ደረሱ የሚለው ጥያቄን የሚፈጥር ነው ብለው። ይህም ሌላ ማጣራት እና ምርመራ የሚያስፈልገው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎቻቸው የሚገፉበትና ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው ሁናቴ እንደነበር አንስተዋል። አያይዘውም መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ወረቀት አልቋል ወይንም እጥረት አጋጥሟል የተባለበት ሁኔታ ምን እንደሆነ ሊገባን አልቻለም ብለዋል። ምክንያቱም አንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ የተመዘገቡትን የመራጮች ቁጥር ብቻ በመመልከት የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በተመዝጋቢው ቁጥር ልክ ምርጫ ቦርድ ማቅረብ ነበረበት ሲሉ አመልክተዋል። ምናልባትም በምርጫው ሂደት ላይ የወረቀት ብልሽት ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ ታዛቢዎቻችንን በማማከር የሚቀርብበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንጂ እጥረት አጋጥሞናል በማለት መራጩን ሕዝብ ማንገላታት እና የምርጫውን ሂደት ማስተጓጎል ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ለመራጩ ሕዝብ በምርጫው ወቅት ትክክለኛ እና አግባብ የሆነ ማብራሪያ (orientation) አልተሰጠም ብለዋል የጽህፈት ቤት ኃላፊው። አክለውም በዚህ ወቅት ምርጫ አስፈጻሚዎች ‹ይሄንን ፓርቲ ምረጡ፤ ያንን አትምረጡ› በማለት ተገቢ ያልሆነ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸው፣ ይሄንንም ከማስረጃ ጋር አስደግፈን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታችንን አቅርበናል ብለዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የምርጫ ቦርድን ምላሽ ተመልክቶ ተገቢው ምላሽ ካልተሰጠው ለምርጫ ተብሎ ወደ ተቋቋመው ፍርድ ቤት በመሄድ ሰላማዊውን ትግል መታገሉን ይቀጥላል ሲሉም ተደምጠዋል።

የእናት ፓርቲ ዋና ጸኃፊ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ምርጫ ተካሂዷል በተባሉ ቦታዎች የነበረው ይህ ምርጫ በማጭበርበር የተሞላ ነው ሲሉም በቅሬታ መልክ ሃሳባቸውን ነግረውናል። በየአከባቢዎቹ ያሉ ሚሊሻዎች እና ካድሬዎች በምርጫ ጣቢያዎች በመትመም ለማጭበርበር ሙከራ ሲያደርጉ እና ሲያስፈራሩ እንደነበር ታዛቢዎቻቸን ነግረውናል ብለዋል። በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ ላይ በምርጫው ዕለት ጸጥታ አስከባሪዎች መራጩን ሕዝብ በማስፈራራት ሲያስመርጡ እንደነበር ትዝብታቸውን ነግረውናል።
አያይዘውም በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም፣ አዊ እና ምዕራብ ጎጃም ዞን ላይ ሚሊሻዎች ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ እንደነበር አመልክተዋል።

በዚህ ኢ- ፍትሃዊ በሆነ ምርጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስህተቶች ታክለውበት ምርጫው ከተጠበቀው በታች እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል። አያይዘውም በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የእናት ፓርቲ ዕጩዎች ስም እና ፎቶግራፍ አንዳልነበረው ገልጸው፣ ታዛቢዎቻችን ቤተሰቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያነሷቸው ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች በሕግ አግባብ እንዴት ይታያሉ? ሕጉስ ምን ይላል? የሚለውን አዲስ ማለዳ የሕግ ባለሙያዎችን አነጋግራለች።

ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው፣ ምርጫ ለክርክር እና ለጭቅጭቅ በር ከፋች መሆኑን ተከትሎ በምርጫ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ቅሬታ አቅራቢዎች አሉን ያሉትን ማንኛውንም ቅሬታ እና አቤቱታ በጽሁፍ እና በማስረጃ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቅረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ቦርዱ የምርጫ ነክ ጉዳዮችን የማስተባበር እና የማስተዳደር ኃላፊነት ስላለበት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቤቱታ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሕብረተሰብ ምርጫው ላይ እንከን አለ ወይም በምርጫ ሕጉ መሰረት አልተፈጸመም በማለት እና ማስረጃ በማቅረብ ማመልከት እንደሚችል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ የዛቻ እና የኃይል ማስፈራሪያዎችን በማስረጃ ማቅረብ ካልተቻለ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጠቆም እና ቦርዱ ጉዳዩን በማጣራት ውጤቱን ለቅሬታ አቅራቢው በጽሁፍ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል። ነገር ግን፣ ይሄ በቦርዱ የማይፈታ ከሆነ እና በቦርዱ ምላሽ ቅር የተሰኘ ማንኛውም ፓርቲ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የምርጫ ጉዳይ ችሎት በይግባኝ ጉዳዩ ሊታይ እንደሚችል ጠቁመዋል። ፓርቲዎች በድምጽ ቆጠራም ሆነ ከድምጽ መስጫ ወረቀት ጋር በተገናኘ፣ እንዲሁም ከሰነድ ማጓጓዝ እና ከሎጂስቲክስ ጋር የተገናኘ ማናቸውም ጉዳዮችን ቀድመው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቅረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፓርቲዎች በምርጫ ክልሎች ላይ ያነሷቸው ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች ትክክለኛነታቸው ከተረጋገጠ እና ተጨባጭ ማስረጃ ካገኘ ምርጫውን የማስደገም እና ውጤቱን እስከመሰረዝ የሚያደርስ ሥልጣን እንዳለው አስረድተዋል።
አክለውም በምርጫ አዋጅ 1162/ 2011 ላይ በአንድ የምርጫ ክልል አስር እና ከዚያ በላይ ጣቢያዎች ላይ አጠራጣሪ ጉዳዮች ከገጠሙ የኹሉም የምርጫ ውጤት ተሰርዞ በድጋሚ ምርጫ ሊካሄድ እንደሚችል የሕግ ባለሙያው ጠቅሰዋል። ምርጫ ቦርድም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አክብሮ ቅሬታ በቀረበባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫውን በድጋሚ የማካሄድ ግዴታ እንዳለበት አብራርተዋል።

ለዚህ ሁሉ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የግል እጩ ተወዳዳሪዎች አሳማኝ እና ትክክለኛ ማስረጃዎችን ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው ባለሙያው አጽንኦት ሰጥቶበታል። ሌላኛው የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ በበኩሉ፣ በምርጫ አዋጁ ላይ በምርጫው ሂደት የሚኖሩ ክፍተቶች እና ጥፋቶች በምን አግባብ ሊታረሙ እንደሚችሉ በዝርዝር ተቀምጠዋል ይላል። ጉዳዩ በኹለት መልክ ሊታይ እንደሚችል ያነሳው ካፒታል፣ በምርጫው ሂደት ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ የወንጀል ተግባራት አንድም በምርጫ አዋጁ፣ አንድም በመደበኛ የወንጀል ሕግ ያስጠይቃሉ።

ለምሳሌ፣ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ የምርጫ ካርዶችን ማሳተም፣ ከቦርዱ እውቅና ውጪ የምርጫውን ሂደት ሊያዛቡ የሚችሉ ተግባራትን መፈጸም ወንጀል መሆናቸው በምርጫ አዋጁ አንቀጽ 156 ላይ ተቀምጧል። ለዚህም በመደበኛ የወንጀል አሰራር መሰረት አጥፊዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ የጠቀሰው የሕግ ባለሙያው፣ በልዩ ሁኔታ በምርጫ ሂደቱ ላይ የወንጀል ተግባር መፈጸሙን የሚያረጋግጥ አግባብ እና ትክክለኛ ማስረጃ ከተገኘ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፌዴራል ፖሊስ በወንጀል ሊጠይቁ እንደሚችሉም አስረድቷል።
አያይዞም፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ የተፈጸሙ ተግባራት ካሉ ቦርዱ ለሚመለከተው አካል አቅርቦ ጥፋተኞች ላይ እርምጃ የማስወሰድ ሥልጣን አለው ብሏል።

ከዚህ ባሻገር በምርጫ ሂደቱ ላይ በቀረቡት ዕጩዎች መካከል የሚነሱ ክርክሮችን ፍርድ ቤት ከማየቱ በፊት የምርጫ ጣቢያ ቅሬታ ሰሚ፣ የምርጫ ክልል ቅሬታ ሰሚ እና የቦርዱ ቅሬታ ሰሚ ተብሎ በተሳሰረው ሰንሰለት ሊታይ እንደሚገባ አስረድቷል።
ይሁን እንጂ ከቦርዱ አቅም በላይ ከሆነ ለምርጫ ተብሎ ወደ ተቋቋመው ፍርድ ቤት በማምራት ጉዳዩ የሚታይ ይሆናል። የተነሱት ቅሬታዎች ተመርምረው ትክክለኛነታቸው ከተረጋገጠም ምርጫውን እስከማስደገም የሚያደርስ ውሳኔ ፍርድ ቤቱ የመወሰን ስልጣን እንዳለው የሕግ ባለሙያው አብራርቷል።

አያይዞም፣ በምርጫው ሂደት ላይ የተስተዋሉ ችግሮች በምርጫ ቦርድ ስህተትም ሆነ አላስፈላጊ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ካለ ፓርቲዎች እና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ኹለቱንም አካላት ሊከሷቸው እንደሚችሉ አመልክቷል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርጫ በተካሄደባቸው በኹሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አካባቢዎች ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ያደረገውን ቅኝት አስመልክቶ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል በሚል ቀዳሚ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ቀዳሚ ሪፖርት ግድያ አና አካል ጉዳት፣ እስር፣ ማስፈራራትና ማስገደድ፣ የታዛቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት አባላትና የሚዲያ አካላትን ጥበቃ በሚመለከት፣ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የነበረው ተደራሽነት፣ የጸጥታ አካላት ሚና፣ የጸጥታ ሁኔታን በሚመለከት፣ ከምርጫ አስተዳደር ጋር የነበረው ሁኔታ በሚሉ ስምንት ነጥቦች ላይ ኮሚሽኑ የታዘበውን አትቷል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ እንዳመላከተው፣ በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላቶች እና ደጋፊዎች ላይ ግድያ፣ ድብደባና የአካል ጉዳት ደርሷል። ለአብነትም በምዕራብ አርሲ ዞን ሊበን አረሲ ወረዳ ለምርጫ ሥራ ከወረዳው ተመድበው የነበሩት የወረዳው ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ባልታወቁ ሰዎች ተገድለው ተገኝተዋል። በነቀምት ዲጋ ወረዳ በሬዳ በሶሮማ ቀበሌ ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ላይ የምርጫ ጣቢያ ሲጠብቁ የነበሩ 4 ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈፅሟል። በዚህም ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሦስቱ መቁሰላቸውንም ለማወቅ ተችሏል ብሏል። እንዲሁም በቡሌ ሆራ ዙሪያ ወረዳ ምርጫ ጣቢያ የዱግዳ ዳዋ ወረዳ ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የቀድሞ የሙረቲ ቀበሌ ሊቀመንበር ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ችያለሁ ሲል ኮሚሽኑ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቅሬታ እና የኮሚሽኑን ሪፖርት ይዛ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጠይቃለች። በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው አወል ሱልጣን እንደሚለው፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሌሎች ተቋማትና ፓርቲዎች ሪፖርቶችን ስላወጡ አልያም ስላላወጡ ሳይሆን፣ የተቋሙ ሥራ መሰል ጉዳዮችን ተከታትሎ በሕግ መዳኘት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥቷል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የትኛውም ተቋም ወይም ግለሰብ ሳይጠይቀው መደበኛው ሥራው እንደመሆኑ መጠን በወንጀል የተሳተፉትን ለሕግ እያቀረበ ነው ሲል ኃላፊው ተናግሯል። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ከቅድመ ምርጫው ወቅት አንስቶ በምርጫው ዕለትም የነበሩትን የኽግ ጥሰቶች አጣርቶ ለፍርድ ሂደት ማቅረቡ ነው። ፍርድ የተሰጣቸውም አሉ ሲል ይሞግታል። የምርጫ ቦርድም የቀረቡትን ቅሬታዎች አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።

በዚህም ረገድ ሰላሳ የሚሆኑ ፓርቲዎች በአንድ መቶ ስልሳ የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታ እና አቤቱታ ማቅረባቸውን ተነስቷል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርትኳን ሚዴቅሳ የቀረቡትን አቤቱታዎች በዝርዝር አስቀምጠዋል። ከነዚህም ውስጥ መምረጥ የማይችሉ ግለሰቦች እና መብት ሳይኖራቸው የመረጡ ስለመኖራቸው፣ በተለይም በብዛት ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎች ወይንም ታዛቢዎች ምርጫውን እንዳይታዘቡ ተከልክለዋል የሚለው አንዱ ነው። ከዚህ ባሻገር ዕጩዎች እና ታዛቢዎች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ተፈጽàል። ቆጠራ ሲካሄድ ሆን ተብሎ ወኪሎቻችን በሌሉበት ነው የተደረገው የሚሉ እና ዋጋ ያለው ድምጽ እንደተበላሸ ተቆጥሮ ተጥሏል የሚሉ በርካታ ቅሬታዎች ቀርበዋል ሲሉ አብራርተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ የመጨረሻ ውጤትን ሊያዘገየው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ የገለጹ ሲሆን፣ ቦርዱም ቅሬታዎቹን በፍጥነት መፍታት ይኖርበታል ብለዋል። በማጣራት ሂደቱም የምርጫውን ውጤት ሊለውጡ የሚችሉ ቅሬታዎች ካሉ በድጋሚ ምርጫ የምናካሂድባቸው ክልሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በሕጉ መሰረት እናውቃለን ነው ያሉት ዋና ሰብሳቢዋ። ነገር ግን፣ የሚቀርቡ አቤቱታዎች በማስረጃ እና እውነት ላይ የተመሰረቱ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል። ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም የተካሄደው የምርጫ ውጤት ገና ባይገለጽም፣ በበርካታ ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች ተተብትቧል። እነዚህ የቀረቡት አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ምርጫ ቦርድ እና ፍርድ ቤት ተመልክተው የሚያሳልፉት ውሳኔ ተጠባቂ ሆኗል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com