የእለት ዜና

ትግራይ በአዲስ መንታ መንገድ ላይ!

Views: 138

በህወሓት ላይ በፌደራል መንግሥት ለስምንት ወራት የተካሄደው “ሕግ የማስከበር እርምጃ” የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር የተናጠል የተኩስ አቁም ሥምምንት እንዲደረግ የፌደራል መንግሥቱን ጠየቀ መባሉን ተከትሎ፣ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ፣ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ፣ የተናጠል የተኩስ አቁም ከሰኔ 21/2013 ጀምሮ በፌደራል መንግሥት ታውጇል።

የመንግሥትን ውሳኔ ተከትሎ በትግራይ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቆ ወጥቷል። ሠራዊቱን ከትግራይ ለቆ እንደወጣም በትግራይ ክልል የሚገኙ የሕክምና ተቋማት እየተዘረፉ እንደሆነ ዓለም አቀፉ ድንብር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታውቋል። ሰዎች ህመም ላይ መሆናቸውን የገለጸው ቡድኑ፣ ብዙዎች እየተሰቃዩ ነው ብሏል። አዳዲስ የህክምና ግብዓት አቅርቦት በቅርቡ ያገኙ አንዳንድ የጤና ተቋማት እንደገና ተዘርፈዋል ሲል ቡድኑ በቲውተር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ አሳውቋል። በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ጉዳይ እስካሁንም ድረስ በወላጆች በኩል ስጋት እንደፈጠረ ነው። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ እየመከርኩ ነው ቢልም እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በክልሉ ከስምንት ወራት በኋላ የፌደራል መንግሥት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ ትግራይ በአዲስ መንገድ ላይ ናት። በጉዳዩ ላይ ከጅምሩ አንስቶ አሁን እስከተፈጠረው አዲስ መንገድ ድረስ የነበሩ ሁኔታዎችን እንዲሁም ሰሞነኛውን ውሳኔ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የሐተታ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገ የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ ክስተት ነበር። ህወሓት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሥልጣን መምጣት ከጅምሩ የተቀበለዉ ቢመስልም፣ የኋላኋላ ግን እያፈገፈገ መጣ። ህወሓት እንዲያፈገፍግ ካደረጉት መነሻዎች አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥተዳደር ከተለመደዉ የተለየ አካሄድ መከተሉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በፈጠሩት አዲስ የመነቃቃት ወኔ፣ መላዉ አገሪቷን እየተዘዋወሩ ከሕዝብ ጋር እየተወያዩና አዲስ መንገድ እያስተዋወቁ በነበረበት ጊዜ መቀሌ ላይ ጥሩ የሚባል አቀባበል አግኝተዉ ነበር። ይሁን እንጅ የጠቅላይ ሚኒስተሩ አስተዳደር የሚያደርጋቸዉ የተቋማትና የአመራር ለዉጦች በህወሓት በኩል ቅሬታን የፈጠሩ ነበሩ።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተፈጠረዉ የፖለቲካና አስተዳደር ልዩነት ከመሰረቱ ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ መጣ። በኹለቱ ኃይሎች መካከል የታየዉ የልዮነት ጎራ ጉልቶ እንዲታይ የሚደርጉ ሁነቶችም ተከሰቱ። የህወሓት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በልዩነት እየተጓተቱ የመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ እንዲደርሱ ያደረጉ ዋና ዋና ክስተቶችን አንዱ፣ ትግራይ ዉስጥ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ማዕከል እንዲንቀሳቀስ የፌደራል መንግስቱ ፍላጓት ቢኖርም ከህወሓት በኩል ጦሩ ከትግራይ እንዳይወጣ ክልከላ ተደርጎበት ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ጦር ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ከነበረባቸው ከተሞች አንዳያልፍ ሲታገድ እንደነበር የሚታወስ ነዉ።

አዲሱ አስተዳደር ተቋማት ላይ የሚያደርገዉ ለዉጥም ህወሓትን ያስኮረፈ ነበር። በተለይ የቀድሞዉ ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ አመራሮች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ መያዛቸዉ፣ ህወሓት የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ዉንጀላ ነዉ በማለት የልዩነት ጎራውን አሰፋው። የልዩነት ጉራዉ እያደገ በመጣበት ሁኔታ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥተዳደር የኢትዮጽያን ፖለቲካ በቀዳሚነት የሚዘዉሩትን ድርጅቶች አክስሞ ወደ አንድ ለማምጣት ዉጥን በያዘበት ጊዜ ህወሓት ዉህደቱን አልተቀበለም ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ውህድ ፓርቲ የመመስረት ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ። ኢህአዴግን ከመሰረቱት እና የአድራጊ ፈጣሪ ሚናውን ከፊት ሆኖ ለ27 ዓመታት ሲዘውር የቆየው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ብልጽግና የተባለውን ውህድ ፓርቲ ሳይቀላቀል ቀረ። ከውህድ ፓርቲነት እራሱን ያገለለው ህወሓት ተቃዋሚ በመሆን ጉዞውን ጀመረ። ይህ ምናልባትም በውህድ ፓርቲው ብልጽግና እና በተቃዋሚው ህወሓት መካካል ትልቅ ልዩነት የፈጠረ ክስተት እንደሆነ ይታመናል።

ኹለቱ ሃይሎች ወደ አልተፈለገ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ካደረጋቸው ዋና ምክንያቶች አንዱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መክሰምና የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ ይገኝበታል። ኢሕአዲግን አክስሞ አዲስ ፓርቲ መመስረቱ ለሦስቱ ነባር አውራ ፓርቲዎች ማለትም ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ)፣ ለኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደኢህዴን) እና ሌሎች ከዚህ በፊት አጋር ተብለው አብረው ለሚሰሩ ድርጅቶች ቀላል ቢሆንም፣ ለህዝበ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ግን ቀላል የነበረ ጉዳይ አልነበረም።

የኢሕአዴግ ክስመትና የብልጽግና ውልደት ህወሓትን ከቀደሙት ጊዜያት በላይ ወደ መቐለ እንዲከትም እና የተናጠል ሀሳብ እንዲያራምድ እንዳደረገው ይታመናል። ህዳር 11/2012 ከህወሓት ውጪ በተደረገ የያኔው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ምክር ቤቱ ውህደቱን በሙሉ ድምፅ ያጸደቀ ሲሆን፣ ህዳር 21 ውህደቱን የተቀበሉት ፓርቲዎች ተፈራርመው ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሰረተ። ህዳር 24 ፓርቲው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ጥያቄ አቅርቦ ቦርዱ ታህሳስ 15/2012 ለብልጽግና ፓርቲ እውቅና መሰጠቱ ይታወሳል።
የቀድሞዋ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሒም ሚያዚያ 22/2010 የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እስከለቀቁበት ሰኔ 1/2012 ዕለት ድረስ በኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። የኬሪያ ከአፈ-ጉባኤነት ለቀው ወደ መቐለ መሄድ የህወሓት ወደ መቐለ የመክተቱ መገለጫ ተደርጎ ተወስዶ ነበር።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የሥራ አስፈጻሚ አባልና የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ከኃላፊነት የመልቀቃቸውን ውሳኔ መቐለ በመገኘት ነበር በትግራይ ቴሌቪዥን የተናገሩት። ኬሪያ በወቅቱ ሥልጣናቸውን የለቀቁት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ አንደማይችል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ፣ ምርጫውን ለማራዘም በወቅቱ የተቀመጠውን አማራጭ የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥ ውሳኔ እና ትርጉም ለመሥጠት እየተሄደበት ያለውን መንገድ ባለመደገፋቸው መሆኑን አብራርተው ነበር።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የህወሓትና የፌደራል መንግሥቱ የልዩነት ጎራ ከነበረበት ደረጃ ከፍ እንድል የሚደርግ ሌላ ክስተት ተፈጠረ። ይሄውም ዓለምን ያሸበረው ኮቪድ-19 ሲሆን፣ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስትኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት ላይ ነበር። በዚህም በሽታው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጠየቁን ተከትሎ ነበር ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው። የሕገ-መንግሥት ትርጉምን እና ምርጫ መራዘምን በወቅቱ አምርሮ የተቃወመው ህወሓት፣ የራሱን ክልላዊ የተናጠል አካሄድ መከተል ጀምሮ ነበር። ይሄውም ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ኮቪድ-19 እያለም በመደበኛ ጊዜው አካሂዳለሁ በማለት የክልሉን ምርጫ አስፈጻሚ አዋቅሮ ዝግጅት ጀመረ።
እንዲህ አንዲህ እያለ የልዩነት ደረጃው እያደገና በሀሳብ ልዩነት ላይ የተመሠረተው ፍትጊያ ወደ ተግባር መቀየር ጀመረ። ህወሓት በፌደራሉ መንግሥት ሕገ-ወጥ ነው የተባለውን ምርጫ ጳጉሜ 4/2012 በይፋ በማካሄድ ማሽነፉን አበሰረ። ማሽነፉን ተከትሎ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትግራይ ክልል መንግሥት ሆኖ እንደሚቆይ በይፋ አወጀ። ከመስከረም 25/2012 በኃላም የፌደራል መንግሥቱ ሕጋዊ እውቅና ውክልና እንደሌለው በመግለጽ ለማዕከላዊው መንግሥት ተገዢ እንደማይሆን አስታወቀ።

በዚህ ሂደት የፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ክልል ሕገ-ወጥ የተባለውን ምርጫ በማካሄዱ ሕገ-ወጥ ቡድን እንደሆነ በማወጅ ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን በጄት በወረዳዎችና በክፍላተ-ከተሞች ደረጃ እንደሚያሰራጭ አስታወቀ። ውሳኔው ህወሓትን ያስደነገጠ ነበር። በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት እያደገ ሂዶ አንዱ ሌላውን ሕገ-ወጥ ቡድን በሚል ሲካሰሱ ቀናቶች ተቆጠሩ። ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን በጄት ለክልሉ ሕገ-ወጥ መዋቅር እንደማይሰጥ ከወሰነበት ቀን ጀምሮ፣ ህወሓት የፌደራል መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት አንዳወጀ እንቆጥረዋለን በማለት ከውይይት ይልቅ ወደ ጦርነት የሚመሩ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሲያወጣ ነበር።

ህወሓት ጳጉሜ 4/2012 ባካሄደው ክልላዊ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዝዳንት የሆኑት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ሰኞ ጥቅምት 23/2013 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፌደራል መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ በደል መፈጸሙን በመግለጽ አሁን ላይ ያለው የመጨረሻ አማራጭ እንደ ሕዝብ መዋጋት መሆኑን በይፋ ተናግረው ነበር። ደብረጽዮን በመግለጫቸው ከመንገዳችን የሚያደናቅፈንን ኃይል ውጊያ እንገጥማለን በማለት የተፈራውን ጦርነት ለመቀስቀስ ጉትጎታ አድርገዋል። “የምንገጥመው ውጊያ የሕዝብ ውጊያ ነው የሚሆነው። ድሉ የኛ ነው፤ ድሮም የኛ ነበር፤ አሁንም አሽናፊዎች እኛ ነን” ሲሉም የጦርነት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠው ነበር። ፕሬዝዳንቱ አክለውም “የፈለገው መሳሪያ አያሸንፈንም፤ እንደ ትግራይ ተዘጋጅተናል፤ እንገጠማለን።” ሲሉ የጦርነት ነጋሪቱን ጎስመዋል።

ይህ በሆነ በማግስቱ ማክሰኞ ጥቅምት 24/2013 ሌሊት ላይ በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው መቐለ ላይ ያልታሰበ እና መላ ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ ድርጊት ተፈጽሞ ማደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 25/2013 በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ብለው አረዱ። በማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማው ዜና “ህወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል” የሚል ነበር። ህወሓት ያልተፈለገ ጦርነት መጀመሩን ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያ በአካባቢው ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሰራ ትዕዛዝ መሰጠቱን ገልጸው ነበር። በቃላት ጦርነት የገነገነው የኹለቱ ኃይሎች ልዩነት በጥቅምት 24 ሌሊት ጀምሮ ወደ ጠብመንጃ ኃይል ተቀይሯል።

የስምንት ወራቱ “የሕግ ማስከበር እርምጃ”
በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል የኃይል ፍልሚያው በግልጽ ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 አንስቶ እስከ ሰኔ 20/2013 ድረስ አንዳንድ ጊዜ እየሞቀ አንዳንድ ጊዜ እየቀዘቀዘ አሁን ላይ ደርሷል። ህወሓት ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለውን ተቃርኖ ከቃላት ጦርነት ወደ ኃይል ከቀየረ ከወራት በኋላ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን በአሸባሪነት ፈርጆ ነበር። ለስምነት ወራት ሲካሄድ የቆየው የህወሓት እና የመከላከያ ፍልሚያ ከሰው ሕይወት ህልፈት፣ አካል ጉዳትና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ እስከ ከፍተኛ የሀብት ብክነት ያስከተለ እንደሆነ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ፣ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የገባው ሕግ ለማስከበር መሆኑን አስታውሰዋል። በዚህም የተሳካ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል። የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን “ሕግ የማስከበር እርምጃ” ህዳር ወር ላይ እንደተጠናቀቀ መገለጹ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጅ በትግራይ በህወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል የሚደረገው የተኩስ ልውውጥ እንዳላቆመ በሚዲያዎችና በውጭ አገራት በኩል ይሰማ ነበር። የፌደራል መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራ ካጠናቀቀ በኋላ የትግራይ ሕዝብን ከጉዳት ለመካላከል መጠነ ሰፊ የመልሶ ማቋቋምና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ዐቢይ ጠቁመዋል። የመንግሥት ባለሙያዎች መስዋዕትነት እየከፈሉም ጭምር በትግራይ መሠረተ ልማትን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አክለው ጠቁመዋል።

የፌደራል መንግሥት ባለፉት ስምንት ወራት ከወታደራዊ ወጪ ውጭ ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና ቀለብ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ከክልሉ አጠቃላይ ዓመታዊ በጀት የ13 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል። የፌደራሉ መንግሥት ለክልሉ ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ቢሆንም፣ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት “የችግሩ ምንጭ ተደርጎ በተሳሳተ መረጃ ዘመቻ ሲደረግበት ቆይቷል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚነስትሩ አሁን ላይ ሠራዊቱ የተለየ ነገር እንዳጋጠመው ተናግረዋል። ሠራዊቱ የክልሉን ነዋሪ ለመጠበቅ በሚያደርገው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ፊት ለፊት የሚገጥመው የታጠቀ ኃይል እንደሌለ ጠቁመው፣ ነገር ግን በሚጠብቀው ማኅበረሰብ ውስጥ ከጀርባ እየተወጋ መሆኑን አብራርተዋል።

አያይዘውም ሕዝቡ በመንግሥት ከሚደረግለት የምግብ ድጋፍ በመቀነስ ለሽብርተኛው ቡድን እየመገበ መሆኑንም አንስተዋል። ከኢትዮጵያ ሕዝብና ከሠራዊቱ ተቀንሶ ለክልሉ ሕዝብ የሚሰጠው ውኃም ጭምር ለሽብርተኛው እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ማኅበር ፕሬዝዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በትግራይ ክልል ለስምንት ወራት የተካሄደው ጦርነት የሕግ ማስከበር እርምጃ መሆኑን በማውሳት፣ ጉዳቱ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ገልጸዋል። የተኩስ ልውውጥ የተደረገበት “የሕግ ማስከበር እርምጃም ወይም ይሁን ጦርነት” በሰው ሕይወት፣ በሰው አካልና በንብረት ላይ ቀላል የማይባል ኪሳራ እንደሚያስከትል ጠቁመዋል። ላለፉት ስምንት ወራት በተካሄደው “የሕግ ማስከበር እርምጃ” የተኩስ ልውውጥ በተደረገበት አካባቢ የሚኖር ማኅበረሰብ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በስምንት ወራት ውስጥ የተካሄደው የተኩስ ልውውጥ በመከላከያ ሠራዊት አባላትና ምናልባትም በሲቪል ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አስከትሎ ያለፈ ነው ማለት እንደሚቻል ጠቁመዋል። በጥቅሉ የተኩስ ልውውጥ ያለበት ሁኔታ በማንኛውም መንገድ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ነው ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ የጠቆሙት።

ትግራይ በአዲስ መንገድ
ባለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ክልል በህወሓትና በክልሉ በተሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ሲደረግ የነበረው “የሕግ ማስከበር እርምጃ” ካሳለፍነው ሰኔ 21/2013 ጀምሮ በፌደራል መንግሥት በታወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቆም ተደርጓል።

የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይም ነው ተብሏል። ኹሉም የፌዴራልና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት ይሄን የተኩስ አቁም እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። የታወጀወን የተኩስ አቁም አዋጅ ዕድል ለክፉ የሚጠቀሙ ወገኖች ካጋጠሙ ግን አስፈላጊው ሕግን የማስከበር ተግባር እንደ አግባቡ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።

የፈደራል መንግሥት ይህን ውሳኔ የወሰነው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር በክልሉ የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ሲሆን፣ መንግሥት የጊዜያዊ አሥተዳደረሩን ጥያቄ የተቀበለው ሕዝቡ በተረጋጋ ሁኔታ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን እና የጥሞና ጊዜ መስጠት በማስፈለጉ ነው ተብሏል።

በውሳኔው መሰረት መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱ ከሰሞኑ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ እና ግራ ያጋባ ውሳኔ መሆኑ ይገልጽ ነበር። በጉዳዩ ላይ መንግሥት ማብራሪያ እንደዲሰጥ ሲጠየቅም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ማክሰኞ ምሽት በጉዳዩ ላይ ለጋዜጠኞች ገለጻ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው፣”አሸባሪው ህወሓት በምንም መልኩ ለአገር ህልውና አስጊ ባለመሆኑ ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ተደርጓል፤ የክልሉ ሕዝብም የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ የተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት በሚጠብቀው ማኅበረሰብ ከጀርባ እየተወጋ መሆኑን ገልጸዋል። ሁኔታው በሠራዊቱ ውስጥ መጥፎ ስሜት እየፈጠረ በመሆኑ እና በሂደቱም በኢትዮጵያ ታሪክ ላይም ጥቁር ጠባሳ አስቀምጦ የሚያልፍ ታሪክ እንዳይከሰት በማሰብ ሠራዊቱ እንዲወጣ መደረጉንም ገልጸዋል።

በሕዝቡ በኩል በመንግሥት ከሚደረግለት የምግብ ድጋፍ በመቀነስ ለሽብርተኛው ቡድን እየመገበ መሆኑንም የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕዝቡም የሚበጀውን እንዲለይ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ሠራዊቱ መውጣቱ አስፈላጊ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። “ሠራዊቱ ውኃ እንዳያገኝ እየተከለከለም ጭምር ለክልሉ ሕዝብ ሠላም ዋጋ ከፍሏል። ይህን ሁኔታ በጥልቅ ከመረመርን በኋላ ክልሉን ለቆ እንዲወጣ ወስነናል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት “ሠራዊቱን ይሆናል ባልነው ቦታ እንዲቀመጥ አድርገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰራዊቱን ለማጥቃት የሚሞክር ኃይል ካለ ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድበትም አረጋግጠዋል። ሰራዊቱ እንዲወጣ የተደረገበት ውሳኔም ከኢትዮጵያ ጥቅም አንጻር ተተንትኖ መሆኑንም አብራርተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና መከላከያ ሰራዊት በጉዳዩ ላይ ባሳለፍነው ሰኔ 23/2013 በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ከዚህ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለሚከሰት ችግር የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠያቂ እንደማይሆን አስታውቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን በሰጡት መግለጫ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመቐለ ለቆ በመውጣቱ፣ የፌዴራል መንግስት ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል ዙሪያ ለሚኖር ችግር ተጠያቂ እንደማይሆን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማትም ከዚህ በኋላ ዕርዳታ ደረሰ አልደረሰ ብለው የፌዴራል መንግስትን ሊጠይቁ እንደማይገባ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፣ የትግራይ ክልልን በተመለከተ ሙሉ ኃላፊነቱን አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት እንደሚወሰድም ገልጸዋል።
የፈደራል መንግሥት ትግራይን ለቆ ከወጣ ብኋላ፣ በክልሉ የሕክምና ተቋማት ላይ ዝርፊያ እየተፈጸመ መሆኑን ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ገልጿል። ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል በወጣ በማግስቱ የህክምና ቁሳቁሶች መዘረፋቸውን ተከትሎ፣ ሕዝቡ በችግር ውስጥ እንደሆነ ጠቁሟል።

በሌላ በኩል፣ መከላከያ ድንገት ትግራይ ክልልን ለቆ በመውጣቱ በትግራይ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችና ሠራተኞች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል። በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ልጆቻቸውን ልከው የሚያስተምሩ ወላጆች ሙሉ በሙሉ የስልክ ግንኙነት በመቋረጡ ልጆቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጸዋል። በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎችን በተመለከተ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት እና የተቋማት አመራሮች ጋር እየመከረ መሆኑን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ባሳለፍነው ሳምንት የተማሪ ወላጆች በሰጠው ምላሽ ተማሪዎቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል። ይሁን እንጅ በወላጆች በኩል መከላከያ ከክልሉ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በተማሪዎቹ ድህነት ላይ አስተማማኝ ነገር አስተማማኝ ማስረጃ እንዳላገኙ ገልጸዋል።
ልጆቻቸውን በትግራይ ክልል ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ልከው የሚያስተምሩ ወላጆች፣ ሰኔ 24/2012 “ልጆቻችን ያሉበትን ሁኔታ መንግሥት ያሳውቀን” በማለት ቅሬታቸውን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቅርበዋል። በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ በሆነው ራያ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ከ200 በላይ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን ሲጠብቀው የነበረው መከላከያ ለቆ በመውጣቱ ለድህነነታቸው በመስጋት ለቀው እንደወጡ ተገልጿል። ግቢውን ለቀው የወጡ ተማሪዎች ወልዲያ ከተማ እንደሚገኙም አሳውቀዋል። ተማሪዎቹ ወልዲያ የደረሱት ግማሽ መንገድ በእግራቸው ተጉዘው መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በእግር በመጓዝ ላይ እያሉ ውኃ ለመጠጣት ብለው የቀሩ ተማሪዎች መታገታቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ከስምንት ወራት በኃላ ከፌደራል መንግሥት በኩል የመጣው አዲስ መንገድ፣ በሕዝቡና በህወሓት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥራት የአገር መከላከያ ክልሉን ለቆ መውጣቱ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ያምናሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት “ማንም የማይክደው ሀቅ የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን ይወዳል” በማለት ነው። በመሆኑም ሠራዊቱን ከክልሉ አውጥቶ ጉዳዩን ማጥራት አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ሰራዊቱ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሆኖ ከኋላ እየተወጋ ልዩነቱን ማጥራት አይቻልም ብለዋል።

በሠራዊቱ ላይ በሕዝቡ ትብብር የደረሱበትን የተለያዩ ጥቃቶችና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲደርሱ የነበሩ ግድያና አፈናዎችን ለማጥራት የሠራዊቱ ለቆ መውጣት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑም አክለው ገልጸዋል። እንደ ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ገለጻ ከሆነ፣ በክልሉ የሚደረገው ትግል ለውጥ ካላመጣ በሠራዊቱ በኩል የሚከፈለው መስዋዕትነት አስፈላጊ አይደለም ብለዋል።

በሌላ በኩል በውጭ አገራት በኩል በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚደርሰውን የዲፕሎማሲ ጫና ለመቋቋም ዕድል እንደሚፈጥር የጠቆሙት ሃምሳ አለቃ፣ የጦሩ መውጣት ተገቢ ቢሆንም፣ አካባቢውን በንቃት መከታተል ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል። የፌደራሉ መንግሥት ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ መንግሥትን ላይ ጫና ሊፈጥር የሚችል ኃይል እንዳይፈጠር ትኩር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የውስጥ ሠላም ለማወክ የሚፈልጉ የውጭ አካላት ትግራይ ከፌደራል መንግሥት ነጻ መሆኑን ተከትሎ ከህወሓት ጋር የመደራጀት እድል እንዳያገኙ የመረጃና ደህንነት ሰዎች በጥብቅ የክትትል ሥራቸውን መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። ደርግ ከህወሓት ጋር ባደረገው ውጊያ በትግራይ ክልል በተሳተፉበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሱት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ደርግ ከፊት ለፊት ሲዋጋ ከጀርባ የሚገዳደረው አካል እንደነበር አስታውሰዋል። ዛሬም መሰል ተግዳሮቶች እንዳያጋጥሙ በትኩረት መከታተል አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com