የእለት ዜና

የሰኔ 14ቱ ምርጫ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች

Views: 46

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው ቀን እና በድኅረ ምርጫ የሰብዓዊ መብቶችን ሁኔታ ክትትል ሲያከናውን ቆይቶ የመጀመሪያ ዙር በድምጽ መስጫ ቀን የነበሩ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ኮሚሽኑ በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን በተመለከተ እና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ እንዲሁም ምርጫው የአካል ጉዳተኞችን እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ያሳተፈና ለእነሱ ተደራሽ የሆነ በማድረግ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን በሪፖርቱ ገልጿል። በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 16/2013 ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው በኹሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የክትትል ቡድን በማሰማራት ክትትል ማድረጉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ሰኔ 14/2013 በተመለከታቸው አካባቢዎች አገራዊ ምርጫን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከስቷል ብሏል። በዕለቱ ከተከሰቱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ እስር፣ ማስፈራራት እና ማስገደድ ይገኙበታል ብሏል።

ግድያ አና አካል ጉዳት
በተፎካካሪ ፓርቲ አባላቶች እና ደጋፊዎች ላይ ግድያ፣ ድብደባ እና የአካል ጉዳት ደርሷል ያለው ከሚሽኑ፣ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባላቶች ላይ፣ በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙት ባሶ ሊበን፣ ጎንቻ እና ደምበጫ ዙሪያ ወረዳ ገሊላ ቀበሌ ላይ ድብደባ መድረሱን ኮሚሽኑ ሰምቻለሁ ብሏል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በኮንሶ ዞን፣ ጃርሶ ቀበሌ የሚኖር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ደጋፊ የቀበሌው ኹለት ሚሊሻዎች ሰኔ 12/2013 ይዘውት ድብደባ ከፈጸሙበት በኋላ በቀበሌው ግቢ ውስጥ ጥለውት መሄዳቸውን እና በዚያው ማደሩን፤ በማግስቱ ሰዎች አንስተው ወደ ጤና ተቋም እንደወሰዱት ተረድቻለሁ ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት አስተዳደር አካላት እና በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ የታጠቁ ቡድኖች ግድያ እና የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ኮሚሽኑ መረዳቱን በሪፖርቱ አሳውቋል። በምዕራብ አርሲ ዞን ሊበን አረሲ ወረዳ ለምርጫ ስራ ከወረዳው ተመድበው የነበሩት የወረዳው ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰኔ 9/2013 ባልታወቁ ሰዎች ተገድለው ተገኝተዋል ብሏል። በነቀምት ዲጋ ወረዳ በሬዳ ሶሮማ ቀበሌ ሰኔ 12/2013 ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ላይ የምርጫ ጣቢያ ሲጠብቁ የነበሩ አራት ሰዎች ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሦስቱ መቁሰላቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሷል። እንዲሁም በቡሌ ሆራ ዙሪያ ወረዳ ምርጫ ጣቢያ የዱግዳ ዳዋ ወረዳ ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የቀድሞ የሙረቲ ቀበሌ ሊቀመንበር ሰኔ 11/2013 በታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን አውቃለው ነው ያለው ኢሰማኮ።

በቤኒንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ተቀማጭ እና ተንቀሳቃሽ ወኪሎች እና የፓርቲውን አመራሮች ጨምሮ 72 ሰዎች ታስረው እንደነበረ ገልጿል። የክልሉ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ከክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስለጉዳዩ ባደረገው ንግግር ኹሉም ሰኔ 13/2013 ምሽት ጀምሮ ባለው ጊዜ ከእስር መለቀቃቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን፣ ኢሰመኮ በፖሊስ ጣቢያ ተገኝቶ ያነጋገራቸው 17 የኢዜማ ደጋፊዎች እና አባላት፣ ሰኔ 6/2013 በካማሌ ቀበሌ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገው ሲመለሱ በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል። ፖሊስ ለፍርድ ቤት ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎ በገንዘብ ዋስትና እንዲፈቱ ቢወስንም አለመፈታታቸውን ተከትሎ፣ ኮሚሽኑ ባደረገው አፋጣኝ ክትትል ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የቆዩት ግለሰቦች ሰኔ 14/2013 ከእስር ተለቀዋል ተብሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ 25 ሰዎች፣ በባቱ ከተማ 3 ግለሰቦች፣ በነገሌ ከተማ 2 ሰዎች፣ በቶኬ ኩታዬ ወረዳ 9 ሰዎች፣ በነቀምት ዲጋ ወረዳ 20 ሰዎች፣ በአምቦ ከተማ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች፣ በጅማ ዞን 2 ሰዎች፣ በጭሮ ከተማ 75 ሰዎች፣ በጭሮ ወረዳ 28 ሰዎች፣ በገመቺስ ወረዳ 9 ሰዎች፣ በሂርና 40 ሰዎች፣ በጡሎ ወረዳ 120 ሰዎች ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ታስረው የነበሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ መመልከቱን ገልጿል። በአዳማ ከተማ በአባ ገዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የነበሩ 28 የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትና ታዳጊዎች 20 ሲሆኑ፣ ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ መለቀቃቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በማስፈራራት እና ማስገደድ
በተወሰኑ በተለይም የገጠር አካባቢዎች መራጮች ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ጥቆማዎች እንደደረሱት ጠቁሟል። በደቡብ ክልል አለታ ወንዶ በጎርድአማ፣ ቢቾ እና አጋራ የገጠር ቀበሌዎች ሕብረተሰቡን “ብልጽግናን ካልመረጣችሁ ፓርቲው ካሸነፈ በኋላ ምንም መብት አይኖራችሁም” በሚል ማስፈራራት እና ዛቻ እንደደረሰባቸው ቅሬታቸውን ኮሚሽኑ ተቀብያለሁ ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ጭሮ ከተማ በገጠራማው ቀበሌዎች የሚገኙ የተወሰኑ ሰዎች፣ ለኢሰመኮ እንዳስረዱት በምርጫው የማይሳተፉ ወይም የምርጫ ካርድ ያላወጡ ሰዎች በቀበሌ ሚሊሻ እና ፖሊስ ለእስር እና እንግልት እንደተዳረጉና፣ በምርጫው የተሳተፉት በተፈጠረባቸው ጫናና ባደረባቸው ፍርኃት መሆኑን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን ከተማ እና አካባቢው የምርጫ ክልል፣ በቀበሌ 06 የምርጫ ጣቢያ 03-1-ሀ ላይ የምርጫ ቦርድ ፍቃድ ከተሰጣቸው ሰዎች ውጪ የአካባቢው የመንግሥት አመራሮች የራሳቸውን ሰዎች መድበው “አስተባባሪ” ነን በሚል ስም በምርጫ ጣቢያው ውስጥና አካባቢ ሲንቀሳቀሱ፣ መራጮችን ሲያሰልፉ እና ሲያስፈትሹ እንደነበር ኮሚሽኑ ተመልክቷል።

እነዚሁ አመራሮችም በተለይ በእድሜ የገፉ መራጮችን “እናግዛችሁ” በሚል ተከትለው እስከ ምስጢር ድምጽ መስጫው ቦታ ድረስ አብረዋቸው ይገቡ የነበረ መሆኑን እና አንድ የቀበሌ አመራርም እስከ 15 የሚደርሱ አዛውንትና አካል ጉዳተኞችን “ደግፎ” በመያዝ የምስጢር ድምጽ መስጫ ቦታ ውስጥ ድረስ ሲገባ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች መመልከታቸው ተመላክቷል።

በቡታጀራ እና በአፋር ክልል ሰመራ፣ አሳዒታ፣ ሎጊያ እና ዱፍቲ በነበሩ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ አስፈጻሚዎች የምስጢር ስፍራው ድረስ በመግባት እገዛ ሲያደርጉ እንደነበረ እና በቡሌ ሆራ በኤጀርስ ፎራ ቀበሌ 02 ሀ ምርጫ ጣቢያ “በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች” በሚል የተሰባሰቡ ሰዎች መካከል አንደኛው በምርጫ ጣቢያ የምስጢር ድምጽ መስጫ ቦታ በመግባት ለመራጮች ካርዳቸውን ሲሞላ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ተመልክተዋል። በቢሻን ጉራቻ (ጥቁር ውሃ) ምርጫ ጣቢያዎች መራጮች በቡድን በመምጣት በአንድ ላይ ሆነው ወደ ምስጢር ድምጽ መስጫ ቦታ ሲገቡና የምርጫ አስተባባሪዎች እና የገዥው ፓርቲ ተወካዮች በምስጢር ድምጽ መስጫው ቦታ ከመራጮች ጋር አብረው መታየታቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አካቷል።

በቡታጅራ ከተማ የኢሰመኮ ክትትል ቡድን በተገኘባቸው 5 የምርጫ ጣቢያዎች የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እና አባላት የምርጫ ቦርድ ከሰጠው ካርድ (ባጅ) ውጪ የራሳቸውን ካርድ አዘጋጅተው ባልተፈቀደላቸው ስፍራ፣ በመራጮች ሰልፍ ላይ፣ በምርጫ ጣቢያ ውስጥና በዙሪያው በመገኘት መራጮችን አዋክበዋል ተብሏል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ከተለያዩ ወገኖች ጫና እንደነበረ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በደቡብ ክልል ከኮንሶ ምርጫ ክልል አስተባባሪ በተገኘው መረጃ መሰረት የምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ዛቻ እና ማስፈራራያ መፈጸሙን ጠቁሟል።
በይርጋ ጨፌ ምርጫ ጣቢያ 02 ከምርጫ ቦርድ ውጪ ሌላ ካርድ (ባጅ) የነበራቸው ተዘዋዋሪ ታዛቢዎች የምርጫ አስፈጻሚዎችን ሥራ ላይ ጣልቃ በመግባት ሲያስችግሯቸው እንደነበር ከምርጫ ክልል ኃላፊዎች ገለጻ እና ከምልከታ ኮሚሽኑ ተረድቻለሁ ነው ያለው።

ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የነበረው ተደራሽነት
ምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች፣ ለነፍሰጡሮች፣ ለአረጋውያን መራጮች እና ለአቅመ ደካሞች ያላቸውን ተደራሽነት በሚመለከት ኮሚሽኑ ክትትል ካደረገባቸው 404 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል 82 ወይም 20 በመቶ ያክሉ አካላዊ ተደራሽነት አልነበራቸውም ተብሏል። ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የምልክት ቋንቋ መግለጫ አገልግሎት እንዳልነበር ገልጿል።

የኮንሶ ዞን ምርጫ ክልል አስተባባሪ በሰጡት መረጃ በኮንሶ ዞን ለነበሩ “ተፈናቃዮቹ ወደ መደበኛ መኖሪያ ቀበሌዎቻቸው ስለሚመለሱ ምርጫ ጣቢያ ማቋቋም አያስፈልግም” በሚል ምክንያት ባለመቋቋሙ በመመሪያው መሰረት ምርጫው እንዳልተካሄደ ነው ኮሚሽኑ የጠቆመው። በዚህም ምክንያት ለምሳሌ የሰገን ገነት ቀበሌ ተንቀሳቃሽ ምርጫ ጣቢያ 02 ላይ 58 መራጮች ብቻ በመመዝገባቸው የነበረው የመራጭ ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ከምርጫ አስተዳደር ጋር የነበረው ሁኔታ
ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በምርጫ አስተባባሪዎች በኩል መራጩን ዜጋ ለማስተናገድ በተደረገው ሁኔታ ጥቂት በማይባሉ ስፍራዎች መራጮችን ለበርካታ ሰዓታት ያስጠበቁ ረዥም ሰልፎች ስለነበሩ፣ በተወሰኑ ቦታዎች መራጮች በድካምና መሰላቸት ምርጫውን ትተው ሲመለሱ ኮሚሽኑ መታዘቡን ጠቁሟል። የድምጽ መስጫ ሰዓት ስለመራዘሙ ያላወቁ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘጋታቸው እና የድምጽ መስጫ ሳጥኖቹን በመቆለፋቸው፣ የተመለሱ መራጮች እንደነበሩ ኮሚሽኑ መመለክቱን አብራርቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com