ዕፅ፣ ዴሞክራሲ እና ደኅንነት

0
806

የኔዘርላንድ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ተቋም (NIMD) “Drugs, Democracy and Security” በሚል ርዕስ የተደራጁ ወንጀሎች በላቲን አሜሪካ የፖለቲካ ስርዓት ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ የሚዳስስ ጥናታዊ መጽሐፍ እ.ኤ.አ. በ2011 አሳትሟል። በመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተዳሰሰው የተደራጁ ወንጀሎች እንዴት እንዳደጉ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅፋት እንደሆኑ ነው። መጀመሪያ ወታደራዊ መንግሥታት ቦታቸውን ለሲቪሎች ለቀቁ። በመቀጠል የተደራጁ ወንጀለኞች ለአገረ መንግሥታቱ አደገኛ የደኅንነት ሥጋት ሆኑ። እነዚህ የተደራጁ ወንጀለኞች ደግሞ የዕፅ ጦርነት (drug wars) አስከትለው ከመንግሥታቱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ አካባቢዎች ተፈጠሩ።

ጥናቱ እንደሚያሳየው በኮሎምቢያ፣ በፔሩ እና በቦሊቪያ የዕፅ አምራችነት በጨመረ ቁጥር ሕዝባዊ አመፅም በተመሳሳይ ይጨምራል። በነዚህ አገራት የሕገ ወጥ ገንዘብ ምንዛሬ፣ የሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውውር እና የፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ ሙስና፣ ተጠያቂነት ማጣት እና አመፅ እንዲበራከት አድርጓል። በዚህም ምክንያት የዴሞክራሲያዊ መርሖዎችን መተግባርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማቋቋም አልተቻለም።

በኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናት አልተደረገም እንጂ የዕፅ ተጠቃሚነት እና ዝውውር እንዲሁም የተደራጀ ወንጀል መጠን መጨመሩ ይነገራል። እነዚህ ችግሮች ሥር ሳይሰዱ መፍትሔ ካልተበጀላቸው በስተቀር በላቲን አሜሪካ እንደሆነው ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋትም ይሁን የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ፈተና መሆናቸው የማይቀር ነገር ነው። ሆኖም የመፍትሔ እርምጃዎቹም በራሳቸው ለዴሞክራሲ ስርዓት ጠንቅ ሊሆኑ ይችላል። አንዳንድ አገሮች በዕፅ ተጠቃሚነት ላይ ያወጁት ጦርነት (war on drugs) የዜጎችን መብቶች የሚገፍፉ ጨቋኝ የወታደራዊ እርምጃዎች ላይ የተመሠረቱ መሆኑን ሌሎች ጥናቶች ያመላክታሉ።

ዕፅ ተጠቃሚነት ምርታማውን የማኅበረሰብ ክፍል ከማሽመድመዱም በተጨማሪ ለሕገ ወጥ ግብይት እና ለግጭት መንገድ ይከፍታል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ለዜጎቻቸው ደኅንነት እና ምርታማነት ቦታ የሚሰጡ ናቸው።

የዕፅ አምራችነት፣ ተጠቃሚነት፣ ዝውውር እና መሰል ድርጊቶችን መከላከል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና ባሕል ከመገንባት ጋር ተያይዞ የሚታይ ነገር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ስለሆነም ችግሩን ከሥሩ መንቀል ጊዜ የማይሰጠው የቤት ሥራ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here