የእለት ዜና

በመተከል የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፓስት አመራሮች በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የተሰባሰቡ ተፈናቃዮችን ጎበኙ

በመተከል የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፓስት አመራሮች  ፣ በግጭቱ ሳቢያ ከአካባቢያቸው ርቀው ተሰደው የነበሩና በመልሶ ማቋቋሙ በወረዳቸው አቅራቢያ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የተሰባሰቡ ተፈናቃዮችን ጎበኙ።

ከቤኒሻንጉል ክልል መተክል ዞን ማንዱራ ወረዳ ወደ አማራ ክልል አዊ ዞን ራንች የመጠለያ ጣቢያ ተሰደው የነበሩ የልዩ ልዩ ቀበሌ ነዋሪዎችን በመልሶ ማቋቋም ወደ ማንዱራ ፣ ዳንጉር ፣ ቡለን እና ድባጤ የተመረጡ የመጠለያ ጣቢያዎች እንዲሰፍሩ ተደርጓል።

በኮማንድ ፖስቱ ዋና ሰብሳቢ በሌተና ጀነራል አስራት ዴኔሮ የተመራ የልዑክ ቡድን ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውሮ የጎበኘ ሲሆን የጋራ ውይይትም አካሂዷል።

ተፈናቃዮቹ ፣ በውይይቱ በቀጣናው የተሰማራው የመከላከያ ኃይል አስተማማኝ ጥበቃ እያደረገላቸው መሆኑንና የደህንነት ስጋት ችግር እንደሌለባቸው ገልፀው ፤ ለሰራዊቱም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የእርዳታ እህል እየቀረበ ቢሆንም በልዩ ልዩ ምክንያት እህሉን ማግኘት ያልቻሉ ተፈናቃዮች መኖራቸውና ለችግር እየተጋለጡ እንደሆነም ገልፀዋል። የማብሰያ ቁሳቁሶች ፣ አልባሳት ፣ የልብስ ማጠቢያ ገንዳዋች እና ፍራሽ እጥረት መኖሩን ያነሱት ተፈናቃዮቹ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም መጠየቃቸው ተገልጿል።

“የጉምዝና የአማራ ህዝቦች ለዘመናት ተፋቅረንና ተቻችለን አብረን የኖረን ህዝቦች ነን ” ያሉት ተፈናቃዮቹ ፣ ከመጠለያ ወጥተው እንደ ቀደመ ግዚያቸው በሰላምና በፍቅር አብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ መንግስት እንዲያመቻችላቸውም ነው የጠየቁት። ከእርዳታ ጠባቂነት ይልቅ አርሰው ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸውም አሳስበዋል።

በጉብኝቱ የእርዳታ እህል ያገኙና ያላገኙ ተፈናቃዮችን የመለየት ስራ የተሰራ ሲሆን ላላገኙት ባስቸኳይ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች ሌተና ጀነራል አስራት ዴኔሮ ቃል ገብተውላቸዋል። በጋራ ለመኖር ላቀረቡት ጥያቄም በትኩረትና በፍጥነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የዞን እና የወረዳው አስተዳዳሪዎች በየበኩላቸው ፣ ከተፈናቃዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡ ገልፀው ፤ ራሳቸውን ለመቻል ላነሱት ጥያቄ መልስ የሚሆን 140 ሄክታር የእርሻ መሬት እና ፈጥኖ ለምርት የሚደርስ የአኩሪ አተር ዘር ማዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል።

ለጣቢያው ሁለት የጤና ኤክስቴሽን ሞያተኞች ተመድበው አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆኑ ፣ ሙያተኞቹ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንደ ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ቅድመ በሽታ መከላከል ላይ ትኩረት ተደርጎ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ምክረ ሀሳባቸውን ማቅረባቸውን ከኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com