የእለት ዜና

የተለመደው የዋጋ ግሽበት እና የግብይት ሰንሠለት

Views: 78

አገራችን አሁን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ከገጠሟት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የዋጋ ግሽበትን ተከትሎ የተፈጠረውና ሕዝቡን እያስመረረ ያለው የኑሮ ውድነት ነው። በመዲናችን አዲስ አበባ እና በመላ አገሪቱ ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት በርካታ ምክንያቶች አሉ። በዋነኛነት የገበያ መረጃ እጥረት፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ፣ ለአምራቹ የሚደረግ ድጋፍ አለመኖር፣ ምርት መደበቅ፣ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ዋጋ መናር እና በግብርና ምርት አምራቾችና በሸማቾች መካከል ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር አለመኖር ይጠቀሳሉ።

ካሳለፍነው ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በግብርና ምርቶች (በምግብ ሰብሎች) ላይ በተለይ በጤፍ፣ በበቆሎ፣ በአትክልት፣ ጥራጥሬ እና ሌሎች ሰብሎች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ አዝማሚያዎችን ማስተዋል ይቻላል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላና አሁን የተፈጠረውን የዋጋ ማሻቀብ ለማርገብ አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት ኹለቱንም ተጠቃሚ ለማድረግ የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በርካታ ሥራ መሥራቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ኡስማን ሱሩር ይናገራሉ። ኤጀንሲው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምርት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በወሰደው እርምጃ የ500 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እንዲያገኙ አመቻችቷል። የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማሕበረሰቡን ከተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የመጠበቅ ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የመንግሥት እገዛ እንደሚሹ ታምኖበት እርምጃው መወሰዱን ኡስማን ጠቁመዋል።

ኡስማን እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የምግብ ሰብሎች፣ አትክልቶች፣ ጥራጥሬዎችና ቅመማ ቅመሞች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ሲሆን የእነዚህ ምርቶች እጥረት በአገር አቀፍ ደረጃ ፈጽሞ እንደሌለ ተናግረዋል። የዋጋ ጭማሪው ዋነኛ ምክንያት በአምራቹ እና ሸማቹ መካከል ያለው የግብይት ሰንሠለት መርዘም ነው ብለዋል። የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ፣ የከተማው የሥራ ኃላፊዎች እና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙበት፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚስተዋለውን ያልተገባ የዋጋ ንረት መሰረታዊ ችግሮችና ሊወሰዱ የሚገቡ ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ለመምከር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።

ያልተፈለገ የዋጋ ንረትን በሚመለከት የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጁት መድረክ ላይ ምክንያተ ብዙ በሆነው የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል። ዋጋ የሚንርባቸውን ምክንያቶች ለመቀነስ እና አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ ለማገናኘት ኤጀንሲው በሚሠራቸው ሥራዎች ይታወቃል። የኑሮ ውድነት በአገራችን ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው ሕዝብ በቁጥር ብዛቱ ያለው በመሆኑ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት ያስፈልጋል።
አንዳንድ ጊዜ ጤናማ የሚባል የዋጋ ጭማሪ እንደሚታይ የሚነገር ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ገበሬው የሚያጋጥመው የመሰረተ ልማት እጥረት ምክንያት ነው ሲሉ ኡስማን ገልጸዋል። የግብርና ግብዓቶች አንደ ኬሚካል፣ ማዳበሪያ እና ትራክተሮች ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ከሆነ ጤናማ የማይባለውን የኑሮ ውድነት መከላከል ይቻላል ሲሉ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአሁኑ ሰዓት ገበሬው የምርት እጥረት አጋጥሞት አያውቅም፤ ይልቁንም ያመረተውን ምርት የሚገዛው አጥቶ ምርቱ ለብልሽት እየተዳረገበት ነው ይላሉ የግብርና ባለሙያዎች። የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ እንደዚህ አይነት የምርት ብክነት እንዳያጋጥም ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ሥራ እንደሚሠራ ይናገራል። በተጨማሪም የፋይናንስ ማነቆን ለመፍታት በአነስተኛ የብድር ወለድ የብድር ድጋፍ ማመቻቸት እና የመክፈያ ጊዜን ማራዘም አስፈላጊ መሆኑም ይነሳል። እነዚህ ችግሮች እንደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ባሉ ተቋማት በኩል የሚፈቱ ቢሆንም፣ መንግሥት ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ስለዚህ ‹‹እገዛ ይደረግልን። እኛ ከገበሬው ተቀብለን ሰንሠለቱን በማሳጠር በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ለሕብረተሰቡ እናቀርባለን›› ሲሉ ከኦሮሚያ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበር ኤጀንሲ የተገኙ አካላት ገልጸዋል።

ይህ ክረምት አልፎ የሚመጣው መስከረም አዳዲስ ምርት የሚመጣበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን ሰው ሰራሽ የምርት መወደድ ሊገጥም ይችላል ብለዋል። ሰው ሰራሽ የምርት መወደድ ከሚያስከትሉት ጉዳዮች መካከል በአገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩት ግጭቶች እና በገበያ ሥርዓቱ ሂደት ምርት ከተጠቃሚው ጋር ከመድረሱ በፊት የሚሳተፉ ደላሎች መብዛት ይጠቀሳሉ። በመዲናችንና በአገራችን የግብርና ምርቶች ላይ እየታየ ያለውን የዋጋ መጨመር አዝማሚያ መረዳትና የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ሚና መረዳት እንዲሁም በየደረጃው ተገቢውን የአመራር ድጋፍ ማድረግ ነው መፍትሄው ተብሏል። በሂደቱም ከዚህ ቀደም ያሉትን ልምዶች አሟጦ በመጠቀም፣ የአምራች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብይት ትስስሮችን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ አሁን በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን የግብርና ምርቶች የዋጋ ንረት አዝማሚያ መግታትና መከላከል ይቻላል። አመራሩ ያካበተውን የድጋፍ ማዕቀፍ በመተግበርም አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በአጭር ግብይት ሰንሠለት ምርቶቻቸውን በማቅረብ የሸማቹን ሕብረተሰብ እርካታ ማረጋገጥ ነው ዓላማው።

ለዚህ ደግሞ ጤናማ የገበያ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው። አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘት ሰንሠለቱ ማጠር ይገባዋል።ይህን ያሉት በውይይቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በነበራቸው የፓርላማ ቆይታ ምርት ከገበሬው ጀምሮ ተጠቃሚ ጋር የሚደርስበትን በጣም ረጅም ሰንሠለት በኹሉም የባለድርሻ አካላት ርብርብ ማሳጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ያለውን ችግር ለመቅረፍ የግብይት ሰንሠለቱን በማጥበብ አርሶ አምራቹም ሆነ ተጠቃሚው የሚገናኝበትን አጭር መንገድ ለመፍጠር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተግባር ወሳኝ ነው ሲሉ አዳነች አበቤ ገልጸዋል። አዳነች አበቤ፣ አዲስ አበባ ላይ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በመንግሥት በኩል አምራቹ እና ተጠቃሚውን በማገናኘት ረገድ ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መኮንን አባይ እንደሚሉት፣ አምራቹ ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂን መጠቀም ይኖርበታል። ይህ ማደግ የሚገባው ቴክኖሎጂ፣ ከተማ ያለውን አምራች ገጠር ካለው አርሶ አደር ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክር መሆን እንደሚገባው አንስተዋል። ያደጉ አገራት የሚባሉት አሜሪካ እና ቻይና ባላቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚሰሩት ሥራ ኢኮኖሚያቸውን እንዳረጋጋ የጠቀሱት መኮንን፣ በአገራችንም ማኅበራጹ በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ታግዘው የንግዱን ሥርዓት ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ሳኚ ደሺ ከጨፌ ወጣቶች ማኅበር የመጡ ሲሆኑ፣ በተለያየ አካባቢ የሚገኘውን የአርሶ አደሩን ምርት ወደ ከተማ ማስገባት ፈተና ሆኖብናል ሲሉ ያለውን ችግር ገልጸዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ኃላፊነት ወስዶ ምርትን ወደ ከተማ ከማስገባት ይልቅ ኃላፊነትን ለሌሎች ማስተላለፍ ይስተዋላል ብለዋል። ከ10ሺሕ አባላት በላይ ያሉት ጨፌ ወጣቶች ማኅበር የተለያዩ ምርቶችን ወደ ከተማ በማስገባት በርካሽ የሚሸጥ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ምርት በሱፐርማርኬቶች እና በንግድ ሥፍራዎች በእጥፍ ሲሸጡ ይስተዋላል። እንደዚህ አይነት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ሲኖር ሊቆጣጠር የሚችል ተቋም እንደሚያስፈልግ ሳኚ ጠቅሰዋል። ይህን በተመለከተ የገጠማቸውን ችግር በጥቂቱ ያነሱት ሳኚ 7መኪና ሽንኩርት ይዘው ወደ ከተማ ገብተው የማረፊያ እና የማከፋፈያ ቦታ በማጣት የተንገላቱበት ሁኔታ አስታውሰዋል። ‹‹የግብርና ምርትን ከአርሶ አደሩ ተቀብሎ በስፋት ለከተማው ሕብረተሰብ የማከፋፈል አቅም ቢኖረንም፣ እገዛ የሚያደርግልን ባለመኖሩ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት አልተቻለም›› ብለዋል።

በነዳጅ፣ በስንዴ፣ እና በዘይት ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየት ከጀመረ ሰነባብቷል። የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመመጣጠን የአገሪቱን የኑሮ ውድነት ካናሩት ነገሮች መካከል አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገውን ምግብነክ ነገሮች ማምረት በሚጠበቅብን ልክ እያመረትን አይደለም። ከሰኔ 2012 ጀምሮ የስንዴ ግዢ በመቋረጡ ያንን ክፍተት በተፈለገው ደረጃ መሙላት አለመቻላችን ትልቅ ተጽእኖ ማሳደሩን ምሁራን ያነሳሉ። በተለያዩ ክልሎች የሚፈጠሩ ግጭቶች የተሳለጠ የምርት ልውውጥ እንዳይኖር በማድረግ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠራቸውም የሚታይ ሀቅ ነው።የነዋሪዎች ገቢና ወጪ አለመመጣጠን ደግሞ የኑሮ ውድነት ጎልቶ ትኩረት እንዲሰጠው ያደረገ ምክንያት ነው። የኑሮ ውድነት ትንሽ፣ ትልቅ፣ አዛውንት እና ወጣት ሳይል እያስመረረና ግራ እያጋባ የሚገኝ ጉዳይ ነው።

ለምን እና እንዴት የሚሉትን ጥያቄዎች ሕብረተሰቡም ሆነ መንግሥት የሚጠይቁት እና መፍትሄ ብለው ያሰቡትን የሚወያዩበት ሁኔታ ቢኖርም እስካሁን የኑሮ ውድነቱ አልተረጋጋም። ኢትዮጵያውያን ያለን ባህል ተሳስቦ እና ተረዳድቶ መኖር ቢሆንም፣ ኹሉም በየዘርፉ በስግብግብነት ምርት በመደበቅ እና አላስፈላጊ ዋጋ በመጨመር ያለአግባብ ለመበልጸግ ሲሞክር ይስተዋላል። በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ በአቅራቢያው በተቋቋሙት የመጀመሪያ ደረጃ ግብይት ማዕከላት አማካይነት ተጠቃሚነቱ እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ ከተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በግብይት ሰንሠለቱ እሴት የማይጨምሩ የሕገወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች በርካታ ናቸው። የጥራጥሬ የግብይት ሰንሠለትን ለአብነት ያህል ብንመለከት፣ አምራቾችን ጨምሮ የምርት ሰብሳቢ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የጅምላ ነጋዴዎችና የችርቻሮ ሸማቾች የሚሳተፉበት ነው። በተራዘመው የግብይት ቅብብሎሽ ሂደት ምክንያት በምርት ዋጋ፣ ጥራትና አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ ደላሎች ገበያውን እያዛቡት ይገኛሉ።

የገበያ ሥርዓት ውጤታማ እና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ከአርሶ አደሩ እስከ የውጭ አገር ምርት ተቀባዩ ድረስ ያለውን ትስስር በማጠናከር፣ በባለድርሻ አካላት መካከል ቅንጅት በመፍጠር፣ የብድርና የክትትል ድጋፍ በማድረግና በጠንካራ የቢዝነስ ሥርዓትና ፖሊሲ በመመራት ውጤትን ማረጋገጥ ይገባል ተብሏል። የላኪዎችንና የግብርና ምርት ገዢ ኩባንያዎችን ትስስር ለማጠናከርና የገበያ ድርሻ ለማሳደግ የላኪዎችን ወቅታዊ የግብርና ምርት መረጃ ለማጠናከር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብዙ ሥራዎች እንደሚጠበቅም ተነግሯል።
የግብርና ምርት ግብይት በአገር ውስጥ የተጀመረው በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ የአርኪሎጂ ጥናቶች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ በአንድ አካባቢ የተመረተውን የግብርና ምርት ወደ ገበያ በማውጣት ከሌላ አካባቢ በተገኘው ምርት ልውውጥ በማድረግ የግብርና ምርት ግብይት ሥርዓቱ ይከናወን እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com