የእለት ዜና

የክብር ዶክተር አበበች ጎበና

ጊዜ ባለሥልጣን ነው። ሰው የተባለ ፍጥረት ሊቋቋመው የማይችለው ክንድ አለው፤ የሚሸነፍ አይመስልም። አንዳንድ ሰው ግን አለ፤ በጊዜ ላይ ይሠለጥንበታል። እንዴት ቢሉ በጊዜ ፊት ጊዜ የማያስረሳው፣ ዘመንም፣ ትውልድም ተሻጋሪ ሥራን ይሠራልና ነው። ብዙዎች ‹‹ማን ብለን እንሰይማት!› ብለው ተቸግረው በየፊናቸው የኮረኮራቸው ስሜት ባቀበላቸው የፍቅር ቃል የሚጠሯቸው የክብር ዶክተር አበበች ጎበና እንዲያ ካሉ ሰው መካከል ናቸው። ጊዜን ያሸነፉ፣ በጊዜ ላይ ንግሥት የሆኑበት ብርቱ እና ባለውለታ እናት። በእድሜ በምንሰፍረው ጊዜ፣ በየአንዳንዱ ሰዓትና ደቂቃ፣ ቀንና ወር፣ ወራትና ዓመት ውስጥ የወለዱን፣ ያሳደጉን፣ ማንም ሊያውቀው ይችል ያልነበረን የተተወ ትውልድ በለምለም ልባቸው ጸንሰው፣ በመልካም እናትነት አንስተው ያሳደጉ እናት ናቸው።

አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ አንድ ሰው ወደ አበበች ጎበና ቀርቦ በመሣሪያ አስፈራርቶ ሊዘርፋቸው ይሞክራል። ታድያ ብዙም ሳይቆይ ያ ሰው በተመሳሳይ በፈጸመው ሌላ ድርጊት ተይዞ ወደ እስር ቤት ይላካል። ይሄኔ ልጆቹ ያለአሳዳጊ ቀሩ። ጉዳያቸው ትውልድ፣ ልጆችና ሕጻናት ነበሩና አበበች የዚህን ሰው ልጅ ሊያሳድጉ ወደ ጉያቸው አስገቡ። በቃ! ልባቸው እንዲህ በቅዱስ መጽሐፍ አልያም በቅዱስ ቁርዓን ተመዝግቦ እንዳለ የጻድቅ ሰው ሥራ፣ በየጊዜው ለበጎነት የሚያተጋቸው ነው። አበበች ጎበና ምንም የሥጋ ልጅ ሳይኖራቸው፣ እናት ተብለዋል፤ ናቸውና። ብዙ ቤተሰብ የጠፋበትን ደስታ በእርሳቸው አግኝቷል። ከፈረሰ ቤተሰብ አውጥተው ‹የእኔ› የሚሉትን ቤት እንዲመሠርቱ ያገዟቸውና የአበበች ውለታ ያለባቸው ጥቂት አይደሉም። ያ ውለታና ድካማቸው፣ ቀናነትና እናትነታቸው በብዙዎች ልብና ሕይወት ታትሟል። በአካለ ስጋ አብረውን ባይሆኑም ትውልድ የሚቀባበለው መልካም ሥራቸው አረአያ ሆኖ ሲያስመሰግናቸው ይኖራል።

እናስታውስ!
አበበች ጎበና የተወለዱት ጥቅምት 10 ቀን 1928 ፍቼ ከተማ ነው። ጊዜው ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረችበት ነበርና ገና የአንድ ዓመት እድሜን በቅጡ ሳይዙ አባታቸውን በጣልያን ወታደሮች ጥይት ተነጠቁ። ልጅነታቸው አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ በአስራ አንድ ዓመታቸው በቤተሰብ ግፊት ወደ ትዳር ለመግባት ተገደዱ። ሆኖም ይህን ግዳጅ አልተቀበሉትም። ስለዚህም ከቤታቸው ጠፍተው እናታቸው ቤት አቀኑ። ነገር ግን ከእናታቸው በኩል ‹‹እንኳን መጣሽልኝ!›› የሚል አቀባበል አላገኙም። ይልቁንም ‹‹እንዴት ታዋርጅናለሽ!›› ተባሉ፤ ወደትዳራቸውና ባላቸው እንዲመለሱ ሆነ። ይህን ጊዜ ነገሩ ተባባሰ፤ በድጋሚ ቤት ጥለው እንዳይወጡ በጠባቂ በር ተዘጋባቸው። ያም አላገዳቸው፤ ለእለታት በአንዱ ቀን በእኩለ ሌሊት ያመልጣሉ።

ያኔ መንገድ ጀመሩ። ወደፊት። ሦስት ቀን በየደረሱበት እያረፉ ከተጓዙ በኋላ አንድ የጭነት መኪና አሽከርካሪ ይተባበራቸዋል፤ ወደ አዲስ አበባ ሊያደርሳቸው። ደረሱ፣ ግን የአሽከርካሪው ሁኔታው አላምር ብሏቸው ቆይቶ ነበርና ፒያሳ ላይ ተሸከርካሪው በቆመበት አጋጣሚ ወረዱ። ልብ በሉ! ገና የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ናቸው። በጊዜው አንድ የተከበሩ የተባሉ ሰው በዛ በፒያሳ ጊዮርጊስ መንገድ ሲያልፉ አጥሩ ጥግ የተቀመጠችውን ትንሽ አዳጊ ልጅ ተመለከቱ። አልፈው አልሄዱም፤ ጠጋ ብለው አነጋግረው ትንሿን ልጅ ወደ ቤታቸው ይዘው ሄዱ። እንደልጃቸው ቆጥረው አሳደጓት። በወቅቱ በነበረው የእጅ ሥራ ትምህርት ቤት ሳይቀር የመማር እድል እንድታገኝ አደረጉ።

የአበበች ጎበና ልጅነት እንዲህ ነው የተጻፈው። በኋላ ተቀጥረውም ሠርተዋል፤ በጊዜው የእህል ሰብል በሚባል ድርጅት ውስጥ። ሆኖም ሕይወታቸውን በምንኩስና የማሳለፍ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው። ወዳጅ ቤተሰቡ ግን ትዳር እንዲመሠርቱ አደረጓቸው። አገቡ። ከትዳሩ ግን ልጅ አልተገኘም። እንዲያም ሆኖ የተመቻቸ ኑሮን ይገፉ ነበር። ጊዜው ደረሰ። 1972 ነው። አበበች ጎበና የግሸን ማርያም በዓል ለማንገሥ በቀድሞ አጠራር ወሎ ክፍለ ሀገር አመሩ። በጉዞ መካከል በድርቅ ምክንያት እናታቸውን ያጡ፣ ነፍስ ያላወቁ ሕጻናትን ተመለከቱ። ሥራቸውን በዚህ ጀመሩ። ትንሽና ተራ ጉዳይ አላደረጉትም። ይልቁንም የሞቀ ቤታቸውን ትቶ ለመውጣት የማይሰስቱለት የሕይወት ግብና ዓላማቸው አደረጉት። ‹የእኔ› የሚለውን በአንድ አጥር ጊቢ፣ በአንድ ቤት፣ በደም የተሳሰረና በሥጋ የተዛመደ ብቻ አይደለም የሚል አቋም ሳይዙ አልቀሩም። ‹የእኔ›ን ከፍ አደረጉት፤ አገር ሆኑ፤ አገር አከሉ።

በአንድ ዓመት ውስጥ ኻያ ሕጻናትን ለማሳደግ ሰበሰቡ። ይህ ግን በቤተዘመዶቻቸው ዘንድ ‹‹አበበች አብዳለች››ን አስከተለባቸው። የበጎነታቸው ልቀቱ የቅርቤ ያሏቸው ሰዎች ጤናቸውን እስኪጠራጠሯቸው ነበር። እርሳቸው ግን ገፉበት። የሞቀውን ቤት ትተው፣ ከተተዉ፣ ብቻቸውን ከቀሩ ሕጻናት ጋር ተኮራምቶ፣ ችግራቸውን መካፈልና የእነዚህን ሕጻናት ነገ መሥራት ላይ አተኮሩ። በኢትዮጵያ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል የሕጻናት ማቆያ ድርጅት በአበበች ጎበና የመጀመሪያ ሆኖ ተመሠረተ።

ከብዙ ሀብት መካከል ጥቂት ፍራንክና ጌጣጌጦች ይዘው ከቤታቸው የወጡት አበበች ጎበና፣ ያንንም ለሕጻናቱ አዋሉት። ግን አላዘለቃቸውም። ስለዚህም በጊዜው በገበያው አዋጭ ነው ያሉትን ቆሎ አዘጋጅተው መሸጥን ተያያዙት። ልጆቼ ስላሏቸው ልጆቻቸው፣ ማንም ግዴታን ሳይጥልባቸው፣ እንደ ጻድቅ መልካምነትን በተጎናጸፈ ልባቸው ገፊነት የተነሳ መደብ ላይ ተኙ፣ የሚሞቅ አልጋ ግን ነበራቸው፤ ልብሳቸውን ቀድደው ለሕጻናት አለበሱ፣ ያለውን ቆርሰው ለልጆች አካፍለው ጾማቸውን አደሩ።

አላረፉም። ጥረታቸው ከተለያዩ የውጪ የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያገኙ አስቻላቸው። እርሳቸውም አልቦዘኑም፣ የቆሎ ንግዱ ላይ የተለያዩ ተጨማሪ ሥራዎችን አክለው ገቢ መሰብሰቡ ላይ በረቱ። ተሻገሩት። በልጅነት፣ በወጣትነትና በአዋቂነት ዘመን ሁሉ እንደየሁኔታው በጊዜው ውስጥ ተፈትነዋል። ጊዜ አላስቆማቸውም፣ አልተሸነፉለትም። እንደውም የነገ አዋቂ የሚሆኑ ጨቅላ ሕጻናት ላይ ሊሠለጥን የነበረን ጊዜ አስረጁት። በሥጋ ሳይሆን በነፍስ መመሪያና መርህ ኖረዋልና፣ የሥጋቸው መድከም አቅማቸውን ቢገታ ነፍሳቸውንና ለአገር ያጋቡትን መንፈስ አይረታም።

አበበች ጎበና ባይጠይቁም ለሰጡት አገልግሎት የምስጋናና የእውቅና ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል። ድርጅቱን ከመሠረቱ ጀምሮ ደመወዝ እንኳ ተቀብለው የማያውቁት አበበች ግን፣ የሚሰጣቸውን የገንዘብም ሆነ ጌጣጌጥና ልዩ ሽልማት ለራሳቸው ተጠቅመውት አያውቁም። ለልጆችና ሕጻናት ፈገግታ አውለውታል፣ በልጆችና ሕጻናት ፈገግታና ሕይወት ውስጥ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

ስለ አበበች ጎበና ፤ ከበጎ አድራጊዎች አንደበት
ስለ አበበች ጎበና ጥቂት ሐሳብና ቃል እንዲያካፍሉን ብለን እጅግ የተወሰኑ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራቾች ጋር ጥቂት ቆይታን አድርገናል። እነርሱም ደስ እያላቸው ከሐሳባቸው እንዲህ አካፍለውናል፤ የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ሲናገሩ፤ አበበች ጎበና ለአገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አረአያና ምሳሌ ናቸው አሉ። ‹‹በጣም ትልቅ መስዋዕትት የከፈሉ እናት ናቸው፣ አረአያ ናቸው። እድሜ ከሁላችን ተቀንሶ መስጠት ቢቻል፣ ለእርሳቸው ብንሰጥ ጥሩ ነበር።›› ሲሉ ተመኝተው ነበር፤ ከአንድ ወር በፊት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ። የተፈጥሮ ሕግና የሰው ሁሉ ፈጣሪ የሆነ አምላክ ፈቃድ ሆኖ ግን አበበች ጎበና ዛሬ አብረውን በስጋ የሉም።

‹‹ለሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩ ትልቁ ቁምነገር ለሌሎች መኖር ነው።›› ያሉት ሲስተር ዘቢደር፣ በሁሉም ሃይማኖት ፈጣሪ የሚጠይቀውም ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወት ያሳዩትን መልካምነት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ‹‹ለሌሎች እንደ መኖር የሚያስደስት ነገር የለም። አበበች ጎበና እንደ እናት ለሌላው ኖረው እኛንም አፍርተዋል።›› ሲሉም መስክረዋል።

ከወራት በፊት በአካለ ስጋ የተለዩን ሌላዋ ባለ ደግ ልብ የኒያ ፋውንዴሽን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ዘሚ የኑስ ነበሩ። ዘሚ ከእረፍታቸው ጥቂት ሳምንታት ቀድሞ ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገው ነበር። በዛም ስለ አበበች ጎበና ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፤
‹‹አበበች ጎበና እጅግ በጣም የማደንቃቸው፣ የምወዳቸው እናት ናቸው። የሚሠሩት ሥራ ትልቅ ነው፤ የታደለ ሰው ነው ይህን የሚሠራው። ለእኛም እንዲህ ያለ ልብ ይስጠን፣ እንዲህ እንድናገለግል ያድርገን። ከራስ አልፎ ለሌላ መትረፍ ቀላል ነገር አይደለም። ለእርሳቸው ብዙ ሥያሜ በመስጠት፣ በቁስ ወይም በንግግር መሸለም ሳይሆን ሥራቸውን በማስቀጠል ክብር መስጠት ይገባልም›› አዲስ ማለዳ አበበች ጎበናን በሚመለከት ካነጋገረቻቸው መካከል የአቤኔዘር የድጋፍና ልማት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አርጋው አየለ ይገኙበታል። በሐሳዋ ከተማ የሚገኙት አርጋው ማኅበሩን የመሠረቱት ከ15 ዓመታት ገደማ በፊት የአበበች ጎበናን ሥራና የልጆች ማሳደጊያ ከጎብኙ በኋላ እንደሆነ አውስተዋል። እናም ትልቅ አረአያቸው እንደሆኑና ታሪካቸውን ሲያስቡ እንደሚደነቁም ይናገራሉ።
‹‹ስለ ታላላቅ ሰዎች ካነበብነው የበለጠ እርሳቸው [አበበች ጎበና] በሕይወታቸው በተግባር ዐሳይተዋል። ምንም በሌለበት ትልቅ ሥራ ሠርተዋል። ትልቅ ክብር ይገባቸዋል። በሥማቸው ታቦት መሠራት ያለበት ሰው ናቸው። በየከተማውና በየቦታው መንገድ በሥማቸው ሊሰየም ይገባል። በእርሳቸው ሥም በተሰየመ መንገድ የሚራመዱ ሰዎች ሁሉ ደስ እያላቸው እንዲራመዱ፣ ደግሞም የአበበችን አረአያነቱ የማይነጥፍ ሥራን እያወሱና እያሰቡ እንዲጓዙ ያሻል።›› ብለዋል።

እንደ አገር ባለውለታና መልካም ሰው የነበሩትን አበበች ጎበና በስጋ ስላጣን አዲስ ማለዳ የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ትገልጻለች። ለልጆቻቸው፣ ለወዳጆቻቸው፣ እርሳቸውን በማጣት ለጎደለባቸውና ለጎደለብን ሁሉ መጽናናትን፣ ለእናታችን አበበች ጎበና የሠሩ፣ የደከሙና መልካሙን ሕይወት የኖሩ ናቸውና እውነተኛውን የነፍስ እረፍትን አምላክ እንዲሰጥልን ትመኛለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com