የእለት ዜና

የዓባይን ልጅ ጨለማ እንዳይውጠው!

Views: 40

በሳምንቱ መነጋገሪያና የኢትዮጵያውያን የደስታ ምንጭ የሆነው በዓባይ ወንዝ ላይ ስለሚገነባው ግድብ በጸጥታው ምክር ቤት የተሰማው ብስራት ነው። የግድቡ መገንባት ከተጀመረ ጀምሮ በበጎ ለማየት የተሳናት ግብጽ አንዴ ያዙኝ ልቀቁኝ ስትል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስትለማመጥ ቆይታለች። የኃያላኑን በር እያንኳኳች ጫና እንዲፈጥሩ ገንዘብም እንዳያበድሩ ስታደርግ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በተጠየቀች ቁጥር ለውይይትም ሆነ ድርድር አሻፈረኝ ሳትል እስከተቻላት እየተገኘች አቋሟን አሳውቃለች። አንዴ በአረብ ሊግ፣ ሌላ ጊዜ በአሜሪካ ማስፈራሪያ ከግንባታዋ እንድትታቀብ ትዕዛዝ አዘል ማስጠንቀቂያ ቢሰነዘርባትም፣ ማናቸውንም ሳትፈራ ግንባታውን ቀጥላ ኹለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ሰሞኑን ለመጀመር በቅታለች።

ኹለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት መጀመሯን፣ እንደመጀመሪው ዙር እስኪሞላ ሳትጠብቅ፣ ያለምክንያት ለሚሰጉት ግብጽና ሱዳን በማሳወቅ ጀምራለች። የግብጽ ባለስልጣናትና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ሲያካሂዱት የኖሩት የማስፈራራትና የማስገለል ዛቻ እንዳልሰራ ሲያውቁ ሌላ አማራጭ ወደ መፈለጉ አዘንብለዋል። በተደጋጋሚ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ቢያቀርቡትም ሊሳካላቸው አልቻለም ነበር። ከእኛ ጥረት ባሻገር የራሺያ፣ የቻይና የኬንያና የሌሎች ጥቂት አገራት ድጋፍ ግድቡን ለማስቆም ለሚፈልጉት አካላት እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር።

ሐሙስ ሌሊት የተካሄደው የምክርቤቱ ጉባኤ ከእስከዛሬው የተለየ ውጤት የተገኘበት ነበር። የአፍሪካውያንን ችግር (ግድቡ ችግር ባይሆንም) አፍሪካውያን ይፍቱ የሚለው አባባል ስር ሰዶ በዓለም አቀፍ መድረክ ተቀባይነት ያገኘበት ዕለት ነበር። ብዙ ኢትዮጵያውያን እንቅልፋቸውን አጥተው ሲከታተሉት ያደሩት ጉባኤ ብዙዎችን ያስደሰተ፣ ልዑካን ቡድኑን ያስመሰገነ፣ እንዲሁም እርስ በርስ እንኳን ደስ ያላችሁ ያባባለ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሁሉም ሳይከራከር ወገን ሳይዝ ያደነቀው ሂደት እንደነበር ለመታዘብ ይቻላል።

በምክር ቤቱ ታሪክ የውኃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ሲገኝ የመጀመሪያ ነው ብለው በቦታው ተገኝተው ከሚጠበቀው በላይ አንጀት በሚያርስ መልኩ ያብራሩት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር / ኢንጅነር) በየማኅበራዊ ሚዲያው ሲሞካሹና ሲንቆለጳጰሱ ነበር። የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው የሚባለውን ተረት እስኪገባቸው በቃላትም ሸንቁጠዋቸዋል። የዓባይን ልጅ ጨለማ ዋጠው ሳይባል በፊት ጉዳዩን ማየት ወደሚገባው አፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በእሳቸው ንግግርም የፀጥታው ምክር ቤት ጸጥ እንዲል አድርገዋል ተብሏል። የተለያዩ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸው ቢያስመሰግናቸውም የዲፕሎማቶቻችንን ያህል ያስደሰተ የለም። ደስታው የጋራችን ቢሆንም በሌሎቹ ላይ የተሸናፊነት መንፈስ ፈጥሮ ለሌላ ዙር ሙግት እንዳይዳርግ ቀዝቀዝ ማድረጉ ይሻላል የሚሉ አሉ። በአንጻሩ ልዑካኑ ከአትሌቶቻችን ያላነሰ አቀባበል ሊደረግላቸው የሚገባቸው ብሔራዊ ጀግኖቻችን ናቸው የሚሉ ቢኖሩም፣ ሁሉም ነገር በልኩ ቢሆን መልካም ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com