የእለት ዜና

አፍሪካ እንደምን ከረመች?

Views: 44

ወረርሽኝ መሆኑ ከታወጀ ዓመት ከመንፈቅ ያለፈው ኮቪድ 19፣ ስርጭቱ የጀመረ ሰሞን በአፍሪካ ከባድ ጥፋት ያደርሳል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ ነበር። በአንጻሩ ‹እንደውም ቫይረሱ ጥቁሮችን አይነካም!› የሚሉ ለቸልታ የሚጋብዙ መላምቶች ሲሰጡ ተሰምቷል።
ነገሩ ግን እንደ ስጋቱም ሆነ ቸልታው ጽንፍ የያዘ አልነበረም። እንደውም ከነበረው ስጋት አንጻር ቫይረሱ በአፍሪካ ያደረሰው ጉዳት ‹ደኅና› የሚባል እንደሆነ ሲነገር ተሰማ። አልፎም ቫይረሱን ለመከላከል ከተደረገ ጥረት ጀምሮ እስከ ክትባት ስርጭትና ማዳረስ ድረስ በአፍሪካ ምሳሌ የሚሆኑ የስኬት ታሪኮች እንደተገኙ ነው የተለያዩ ዘገባዎች የሚያስረዱት።

የአውሮፓ የጥናት ማዕከል (Institute for European Studies) ከወራት በፊት ይህን በሚመለከት አንድ ጽሑፍ አስነብቧል። ጽሑፉ አፍሪካ እንደ ኤች/አይ/ቪ ኤድስ፣ ማላሪያ እና ኢቦላ ያሉ እጅግ ገዳይ የሆኑ ቫይረሶች የከፋ ዱላ ያሳረፈበት ታሪክ እንዳላት በማውሳት ይጀምራል። የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ እንደጀመረም የዓለም ጤና ድርጅት ‹ከማንም በላይ ለአፍሪካ እሰጋላታለሁ› ማለቱን ያወሳል።

አክሎም የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ርዕሳቸው ምን እንደነበር ይጠቅሳል። ቢቢሲ ‹‹ኮሮና ቫይረስ፤ አፍሪካ ቀጣይ የወረርሽኙ መናኽሪያ ሳትሆን አትቀርም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አሳሰበ።›› ብሎ ነበር። ፍራንስ 24 ደግሞ ‹‹ከፍተኛ ተጋላጭ አኅጉር፤ አፍሪካና ኮሮና ቫይረስ›› ሲል አስነብቧል፤ ይላል ይኸው የአውሮፓ የጥናት ማዕከል ያወጣው ዘገባ። ሌሎችም ከዚህ በባሰ ስጋታቸውን ሲያንጸባርቁ እንደነበር ጠቅሶ፣ ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ የነበሩ ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች ትኩረት ሳይሰጣቸው እንደቆዩ ያነሳል።

ሆኖም ግን ብዙ ተስፋ ሰጪና ውጤታማ የሚባሉ ታሪኮች በአፍሪካ ምድር እንደተስተዋሉ ዘገባው ይመሰክራል። ከዚህም አንዱ ብሎ የጠቀሰው በጋምቢያ የታየውና ወረርሽኙ በምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቋቋም የተሰጠው ምላሽ ነው።
ይህም ልክ በኢትዮጵያ እንደታየው የመደጋገፍና የመረዳዳት ንቅናቄ ነው። ድጋፍና እርዳታን ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገንዘብ እንዲሁም ምግብና አስፈላጊ ግብዓቶችን መሰብሰብ በስፋት የተስተዋለ ተግባር ነበር። በዚህ ተግባር ወረርሽኙ በብዙዎች ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውንና ሊያሳድር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ ወይም ለመቋቋም ተችሏል።

የአውሮፓ የጥናት ማዕከል ያወጣው ዘገባ በምሳሌነት የጋምቢያን ሲያነሳ፣ በውጪ አገር የሚኖሩ የጋምቢያ ተወላጆች በተለያዩ ማኅበራዊ ገጾች በትብብር ድጋፍ ያሰባስቡ እንደነበር ይጠቅሳል። በተጓዳኝ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በየፊናቸው ለተቸገሩት በመድረስ፣ ቫይረሱ እጅ እንዲያጥራቸው ላደረገ ሁሉ አለን በማለት፣ የታመሙትን በማገዝና በማጽናናት ትልቅ ሥራን ሠርተዋል። ይህም በኢትዮጵያም ጭምር የታየ፣ ከወረርሽኙ አስከፊ ማዕበል መካከል የተገኘ የተስፋ መልክ ነበር።

ይኸው መነሻ ያደረግነው የአውሮፓ የጥናት ማዕከል ያስነበበው ጽሑፍ በጋምቢያ የነበረውን እንደማሳያ ያንሳ እንጂ የፈጠራ ሐሳብና ሥራ በመላው አፍሪካ ምን ያህል በውጤታማነት እንደታየ ሳይጠቅስ አልቀረም። ይሁንና የዓለም መገናኛ ብዙኀን በአፍሪካ ከተሠሩት የፈጠራ ሥራዎች፣ ከታዩት መረዳዳትና የአገር ፍቅር ስሜት መግለጫ በጎ ተግባራት ይልቅ ቫይረሱ ያስከተለው ጉዳትና ጫና ላይ ማተኮራቸውን ይጠቅሳል።

አሁን የቫይረሱ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ጉዳት ማሳረፍ የሚችለውን ያህል ዱላ አሳርፎ መረጋጋቱ ላይ የደረሰ ይመስላል። አጀንዳውም ተቀይሮ የክትባት ተደራሽነት ጉዳይ ርዕስ ሆኗል። ይህን በሚመለከት የዓለም ጤና ድርጅት ባስነበበው አንድ ዘገባ፣ እንደመጀመሪያው ጊዜ ‹ለአፍሪካ እሰጋላታለሁ› ከማለት ይልቅ እንደውም አፍሪካ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተግባርን ፈጽማለች ሲል አንስቷታል።

ከሳምንት በፊት ድርጅቱ በገጹ ባወጣው በዚህ ዘገባ፣ በአንጎላ ከታየው ምሳሌ የሚሆን ብዙኀንን የመከተብ እንቅስቃሴ ጀምሮ፣ በሩዋንዳ የተስተዋለው የተሳለጠ የክትባት ቁሳቁስ ስርጭት እንዲሁም በጋና እስከተሠራው በክትባቱ ላይ ያለን ጥርጣሬ የማጥፋት ዘመቻ ድረስ፣ አፍሪካ ስኬታማ ሥራን ሠርታለች ይላል። የዓለም ጤና ድርጅትም እነዚህን ጠቃሚ ትምህርቶች መዝግቦ እየያዘ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በድርጅቱ ክትባቱን በተመለከተ ግንዛቤ የመፍጠር ድርሻን የያዘው ቡድንም በአፍሪካ ክትባቱ በተለያየ ዙር የሚደርስ መሆኑን በማውሳት፣ በአኅጉሪቱ የሚገኙ አገራት በመጀመሪያ ተግባራዊ ያደረጓቸውንና ስኬታማ የሆኑ ልምዶችን እርስ በእርስ እንዲጋሩ እንደሚደረግ ይገልጻል። የዓለም ጤና ድርጅትም ከስር ከስር ልምዶችን መመዝገቡ ለልምድ ልውውጡ ትልቅ ግብዓት እንደሆነ በቡድኑ ታምኖበታል።

ይኸው ቡድን እንደውም የአፍሪካ አገራት የጤና ሚኒስትሮች፣ ስኬታማ የሆነም ይሁን ያልሆነ ልምዳቸውን እርስ በእርስ እንዲለዋወጡ ሲል አደራ ብሏል። ምክንያቱም ለምን ነው ቢባል ይህን ይላል፤ ‹‹የሁሉም የመጨረሻ ግብ የአፍሪካዊያንን ሕይወት መታደግ ነውና።››
ዶክተር መሠረት ሺበሺ በዓለም ጤና ድርጅት የክትባት ጉዳዮች ዘርፍ መኮንን (Immunization Officer) ናቸው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በጅማ የጤና ሳይንስ ተቋም ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ዙሪያ ነው።

ምንም እንኳ ክትባቱን በሚመለከት አፍሪካ ውጤታማ የተባሉ ምሳሌም የሆኑ ሥራዎችን ብትተገብርም፣ አሁንም ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች እንዳሉ ተናግረዋል። ባለሞያዋ ለሚሠሩበት የዓለም ጤና ድርጅት በሰጡት ቃለመጠይቅ እንደውም ስጋት ላይ ናቸው የተባለ የሕዝባቸውን ክፍል የከተቡ አገራት የተረፈውን ክትባት በእጅጉ ለሚያስፈልጋቸው አገራት እንዲያካፍሉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

‹‹ብዙ የአፍሪካ አገራት አሁንም ከባድ ትግል ውስጥ ናቸው። ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ስጋት ላይ ያሉ ዜጎችን ለመከተብ እስከ 2022 መጨረሻ መጠበቅ አያዋጣንም። ዓለማችን የእርስ በእርስ የተሳሰረች ናት። እናም አፍሪካ ወደኋላ ቀረች የሚለው ጉዳይ ለቀሪው የዓለም አገራት የሚልከው መልዕክት ያለ መሆኑን እናስታውስ።›› ሲሉ ተናግረዋል።

የክትባት እጥረት እንዲሁም በተገቢው በጊዜ ያለመሠራጨቱ ‹ልውጥ› ሆኖ እንደአዲስ የሚሰራጨውን ቫይረስ አስጊ እንደሚያደርገውም አሳስበዋል። እንደውም እንኳና ከላይ የተጠቀሱት ተስፋ ሰጪ የተባሉ ተግባራት ሊስተዋሉ ቀርቶ ‹‹ኮቫክስ ባይኖር ኖሮኮ አፍሪካውያን እስከ አሁን ያገኙትን ጥቂት ቁጥር ያለው ክትባትም ቢሆን አያገኙም ነበር።›› ብለዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት እለት ድረስ ‹ወርልዶሜትር› ላይ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ በአፍሪካ በጠቅላላው 5 ሚሊዮን 829 ሺሕ 961 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ 149 ሺሕ 186 ሰዎች ሕይወት አልፏል። 5 ሚሊዮን 41 ሺሕ 611 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል። 4 ሺሕ 614 ሰዎች ደግሞ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።ለአፍሪካ ከባዱ ጊዜ ቅርብ ነው ሲል ድርጅቱ ስጋቱን ገለጸ

የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ የኮቪድ 19 ሦስተኛ ማዕበል ከባድ እንደሚሆንና ለአፍሪካ ወረርሽኙ የሚያስከትለው የከፋው ክስተት እየቀረበ ነው ሲል ስጋቱን ገልጿል።
በድርጅቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ማትሺድሶ ሞቲ እንደተናገሩት፣ በአፍሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየ18 ቀኑ በእጥፍ እየጨመረ ይገኛል። ይህም ከሳምንት በፊት በየ21 ቀኑ ይታይ የነበረ ነው። ከሰኔ 21 እስከ 27 በነበረው ሳምንት 251 ሺሕ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፣ ይህም ቀድሞ ከነበረው ሳምንታዊ አሃዝ በ20 በመቶ የጨመረ ነው ብለዋል።
ዳይሬክተሯ 16 የአፍሪካ አገራት አሁን ላይ ቫይረሱ እንደ አዲስ እያገረሸባቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም በዐስሩ ‹ዴልታ› የተባለው አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ መገኘቱን ጠቁመዋል። ደቡብ አፍሪካም በዚህ ክፉኛ ከተጎዱ መካከል ናት ብለዋል።
አያይዘውም በአፍሪካ የክትባት ስርጭትና አቅርቦት እንዲስፋፋ ጥሪ ማቅረባቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ እንዲሁም ፍራንስ 24 ላይ ያገኘነው ዘገባ ያመለክታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com