የእለት ዜና

“ከኤርትራ ጋር ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ነው ያስታረቀን”

Views: 39

ሻምበል ኤልያስ ሥፋቱ ይባላሉ። ሲዳማ ተወልደው ዕድሜያቸው ሲደርስ የውትድርናውን ዓለም ተቀላቅለው፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ውስጥ ሠራዊቱ እስኪበተን ድረስ አገልግለዋል። አብዛኛውን የውትድርና አገልግሎታቸውን ወሳኝ በሚባሉ ጊዜያት ትግራይ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራት ፈጽመዋል።
የቀድሞው ጦር ሠራዊት ከትግራይ የወጣበት መንገድና አሁን መከላከያ ክልሉን የለቀቀበትን ልዩነትና መመሳሰል ከቆዩበት ልምዳቸው በመነሳት አስተያየት ይሰጣሉ። ስለህወሓት ባሕሪ እንዲሁም ስለሚረዷቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሚያውቁትንና የታሪክ መማሪያ ይሆናል ብለው ያሉትን አካፍለዋል።

ስለራስዎ ትንሽ ቢነግሩን?
ስሜ ሻምበል ኤልያስ ሥፋቱ ይባላል። ከ1974 እስከ 1983 ድረስ ጦርነት ውስጥ ነበርኩ። በ8ቱም የትግራይ አውራጃዎች እየተዘዋወርኩ ውጊያ ውስጥ ነው የኖርኩት። በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች እየተዘዋወርኩ ስለቆየሁ ስለትግራይ በሚገባ አውቃለሁ። በዘመኑ ብዙ ችግሮች እንደነበሩ ተመልክቻለሁ። የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት እንጓጓ የነበረ ቢሆንም፣ ሁኔታዎች የተመቻቹ ስላልነበሩ ሳንችል ቀርተናል። በፊትም ሆነ አሁን በዚህች አገር ላይ የሚሰራው ደባ ከፍተኛ ስለሆነ ጥረታችን ሳይሳካ ቆይቷል።

እኔ ከትግራይ የወጣሁት በ1981 ሽሬ ሲደመሰስ ነው። ከአክሱም፣ አድዋና ሰለኽላካ ቀጥሎ በሽሬ ጦሩ ሲደመሰስ መቀሌ ተለቀቀ። ቀጥሎ አዲግራትም ተለቀቀ። እኔ ከዛ ጊዜ በኋላ ለ3 ወር ያህል ሽሬ በረሃ ለበረሃ ቆይቻለሁ። ሽራሮም አካባቢ ያለ ስንቅ ስንከራተት ነበር ጊዜውን ያሳለፍኩት። የትግራይ ሕዝብና ወያኔ በጣም የተለያዩ ነበሩ። ያን ያህል ጊዜ ስቆይ እያበሉ መንገድም እየመሩ ይተባበሩኝ ነበር። ያንን ኹሉ አልፌ በአስመራ በኩል አድርጌ ተመልሼ ነው የመጣሁት። ዞሬ ወሎ ገብቼ ጦርነቱ እስኪያልቅ እዛ ቆይቼ በኋላ ወደ አፋር ወርጃለሁ። ከአባት አያቶቼና ከአብዲሳ አጋ የተማርኩት ስላለ እጅ መስጠት አልወድም ነበር። አፋሮች ኢትዮጵያን የሚወዱ ስለሆኑ መንግስቱ ኃይለማሪያም ከአገር ከወጣ በኋላም እዛ ቆይቻለሁ። እያበሉ ካኖሩኝ በኋላ ተመልሼ እጄን አልሰጥም ብዬ ተቀምጫለሁ። ከዛ በኋላም ሆነ በፊት ወያኔዎች ሰዎች ሳይሆኑ አውሬዎች እንደሆኑ አውቃለሁ።

የትግራይ ሕዝብ ያሳዝን ነበር። እኛ በ1977 ድርቅ በተከሰተ ጊዜ ሠራዊታችንን አስተባብረን ረድተን ነበር። ውቅሮ አካባቢ እርዳታ እንዲመጣ አድርገን አከፋፍለን ነበር። 1ሺሕ 200 የሚሆኑትን በአማካይ 4 ሕፃናትን የታቀፉትን ተቀብለን ነበር። ገና በልጅነታቸው ብዙ የወለዱ ይበዛሉ። በመጀመሪያ እየመጡ እህል ስንሰጣቸው ሊወስዱ ሲሉ በራፍ ላይ ወያኔዎች እየጠበቁ አስፈራርተው ይነጥቋቸው ነበር። በኋላ ላይ አንሄድም ስላሉን መጠለያ ሠርተን ልናቆያቸው ችለን ነበር። በዛ አይነት መንገድ ብዙ ችግር አሳልፈን ቆይተናል። አብዛኞቹ ባለቤታችሁስ የት ናቸው? ሲባሉ ሄዱ ይሉናል። የት? ስንላቸው ሁመራ። ማን ወሰዳቸው? ስንል ዞቢ እያሉ የሚጠሯቸውን ወያኔዎች መሆናቸውን ይነግሩናል። የትግራይ ወጣቶች ማስወለድ እንጂ ማሳደግ አይፈልጉም ነበር። በዚህ ጉዳይ ጥናት አስጠንተን ወጣትና ጎልማሶች በከተማ እንደማይታዩ አውቀን ነበር። ሽማግሌዎቹን ስንጠይቅ የሚሉን የወያኔ ሚሊሻ እየመጣ እንደሚያስረግዛቸውና ልጆቹ አባቶቻቸውን እንደማያውቁ ነው። አልፈልግም ያለች ሴት ሕፃንም ብትሆን ትደፈር እንደነበር እንሰማ ነበር።

በቀድሞ ዘመን ወታደሩ ትግራይን ለቆ የወጣው በሽንፈት ነበር?
ሽንፈት ነው ሊባል ይችላል። ምክንያቱም በመደዳ አክሱም፣ አድዋ፣ ሰለኽላካ፣ ሽሬ እንዲመታ የተደረገው በሳቦታጅ(ሻጥር) ስለነበር ነው። የተፈጸመው ሴራ ከፍተኛ ስለነበር መንግሥት ማድረግ የነበረበት ማስወጣት ነው። አሁን ወያኔ የጠበቀው እንደዛ ይሆናል ብሎ ነበር። ያኔ መቀሌ ከተለቀቀ በኋላ ኢህዴን የሚባለው የጎንደርን ሕዝብ እያስተባበረለት እየጨፈሩ ነው የገቡት። የበፊቱ እና የአሁኑ ሠፊ ልዩነት ነው ያለው። ያኔ ሻዕቢያ በላይ በኩል፣ ወያኔ ከመሀል፣ ከታች ደግሞ አርበኞችም ነበሩ። ሌላው በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚባሉትን የውጭ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን፣ “ግብረ ሰይጣን” ነው የምላቸው፣ እነሱ፣ ግብጽና ሱዳን አብረው ሆነው ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነበር። አሁን እያደረጉ እንዳሉት በፊትም እያሰለጠኑ ይልኩብን ነበር። አካባቢው ተራራማ ስለሆነ የመንግሥት መዋቅርም ከተማ ብቻ ስለሆነ መቆጣጠር አይቻልም ነበር።

ሳቦታጅ (ሻጥር)ያሉኝ ከውስጥ ሆነው ለእነሱ ይሠሩ የነበረው ሁኔታ አሁንም አለ?
ውስጥ ሰግስጎ ለማስገባት አሁንም ይጥራሉ። ኹሌም ውስጥ ይጠፋሉ ብለን አንገምትም። ይህ ቢሆንም የትግራይን ሕዝብና ወያኔን መለየት መቻል አለብን። ወያኔዎች እንደፈለጉ እንዲሆኑ እያደረጉ ያሉት በአሜሪካና አውሮፓ የሚመሩት ግብረ ሠናይ የሚባሉት ተቋማት ናቸው። ከነሱ በመቀጠል አረብ አገሮችና ግብጽ ናቸው የሚረዷቸው። ይህን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ አለበት።

የትግራይ ሕዝብ አብዛኛው ህወሓትን እንደሚደግፍ ሠሞኑን መነገሩን እንዴት ያዩታል?
ሕዝቡ እንደሚደግፋቸው የተነገረው ትክክል ነው። እዚህ ጋር መለየት ያለብን አሁን ያለው ትውልድ ወያኔ ጫካ ውስጥ እያለ ጀምሮ የተወለደ ነው። አሁን ብቻ ሳይሆን በፊትም ከቦታ ቦታ ስንንቀሳቀስ መረጃ የሚያቀብሏቸው እነሱ ናቸው። ሠራዊቱ እያወቀ እንዳይመታቸው ሰላማዊ መስለው ነው ያሉት። በዚህ መንገድ ነው ሕዝቡንና ሠራዊቱን ለማጋጨት የሚሞክሩት። በተቃራኒው እነሱ ስለሚበድሏቸው ኩናማ፣ ቋሂር፣ ኢሮብና ተንቤን የሚያወራ የለም። ተንቤኖችን “ልበ እባብ” ይሏቸዋል፤ አጋሜዎችን “ኩንቲ ለቃሚ” ይሏቸዋል። እንዲህ አይነቱን ነገር ለማስቆም መንግስት ስርዓት ማስያዝ አለበት።

አሁን የትግራይ ሕዝብ ህወሓትን የሚደግፈው ክልሉ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥም ሆነው በተለያየ መንገድ የሚደግፏቸውም አሉ። በሕዝቡ ላይ በደል ሳይፈጸም ደጋፊዎቻቸው መለየት አለባቸው። አሁን በ15 ቀንና በወር ውስጥ የሚለዩ ነገሮች አሉ። በትግራይ ከወረዳ ከተሞች በታች የመንግሥት ሰው ስለሌለ ከዚህም ቢሆን በየገጠሩ ላሉት እንዲልኩ ተመቻችቶላቸዋል። እዛው የሚሰጣቸውንም እየወሰዱ የሚሰጡ እንዳሉ አሁን ብቻ ሳይሆን በፊትም ይታወቅ ነበር። ትልቁ ነገር “ግብረ ሰይጣን” የምላቸው ተቋማት የሚፈጽሙት ተግባር ነው። የዛሬ 37 አመት ደርግ ሰደድን ሲመሰርት ወያኔ ማሌልትን መስርቶ ነበር። ከዛን ጊዜ ጀምረው የራሳቸውን ወንድሞች በመግደል የሚታወቁ ናቸው።

ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ነን የሚሉት ያኔም እርዳታ ማድረስ አቃተን ብለው ደርግን ወጥረው ይዘውት ነበር። እኛ በዚያን ጊዜ ዓቢ ዓዲን ይዘን ነበር። ወርቅ አምባ አካባቢ እርዳታውን ካላደረስን ብለው ተፈቅዶላቸው ነበር። እህሉ ውስጥ ጥይት፣ ቦንብና ክላሽ ተፈታቶ ለቀናት እንዲሰራጭላቸው አድርገው ነበር። አዛውንቶች የሆነውን አይተው እየመጡ ይነግሩን ነበር። ድጋፉን የሚያደርገው መንግሥት ይመስላቸው እንደነበር እናውቃለን። “ደርግ እንዲህ መርዳት ከፈለገ በቀጥታ በመኪና ለምን አያመጣም?” ይሉናል። በሕዝቡ ስም እየተለመነ የሚደረገው ይህ አይነት ተግባር አሁንም እንደቀጠለ ነው። ያለፈው ነገር አሁንም እንዳይደገም መንግሥት ማሰብ አለበት። ሰሞኑን ምዕራባውያን እያደረጉ ያሉት በግልጽ እየታየ ስለሆነ ሚዲያውም ቢሆን ይፈጽሙት የነበረው አይነት ነገር እንዳይደገም ሕዝቡን ማሳወቅ አለበት።

ከጦር ሠራዊቱ ሞራል አኳያ በቀድሞ ጊዜ ከትግራይ ሲወጣ የነበረውን ሂደት ካሁኑ ጋር እያነፃጸሩ የሚናገሩ አሉ። የሕዝቡን አቀባበልስ እንዴት ያስተያዩታል?
የበፊቱ ሰራዊት ተበድሏል። ልመና እስኪገባ ድረስ ዞር ብሎ ያየው የለም። የተጠላበት ምክንያት ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ስለያዘ ነው። የአሁኑ ሠራዊት ውስጥ እነሱ ያደራጇቸው ነበሩ። እነሱ አሁን ወጥተዋል። ሪፎርም ተብሎ ውስጡ ቢፈተሸም ጠንካራ ሆኖ መውጣት ይጠበቅበታል።

ትልልቅ ከተሞች ከፖሊስና ደንቦች በስተቀር መኖር የለባቸውም። ሠራዊት መኖር ያለበት ድንበር ላይ ነው። ህወሓቶች ሐሳባቸውን በቅርብ ጊዜ ካልቀየሩ አሁን ያለው ሁኔታ ባለበት ይቆያል። አሁን እንደበፊቱ ምግብም ሆነ ሌላ ነገር ከዚህም ከዚያም እናገኛለን የሚሉበት ጊዜ አይደለም። የሚደረግላቸው ድጋፍ እየጎደለ የሚመጣበት ጊዜ ይኖራል። ሕዝቡም ቢሆን በነበረበት መልኩ ድጋፉን አይቀጥልም። ገበሬውን ስለሚዘርፉትም ቀስ በቀስ ወደየአካባቢው አያስጠጋቸውም።

ያኔ በደርግ ጊዜ እንደሚደርጉት አሁንም የወታደሩን ዩኒፎርም እያስለበሱ ሴቶችን ይደፍራሉ፤ ግፍ ይፈፅማሉ፤ ሀብትና ንብረትም ይዘርፋሉ። የእነሱን ተንኮልና ሴራ ለመመከት ሕዝቡ በየወረዳው ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይኖርበታል። አንድም፣ ኹለትም፣ ስምንትም ዓመት ይፍጅ ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነቱን አምኖ እንዲመጣ መደረግ አለበት።

ትግራይ አብዛኛው ደረቅ ነው። ከሽራሮና ማይጨው በስተቀር አረንጓዴ የሚታይበት የለም። ችግር ያለበትን የሕብረተሰብ ክፍል ማስተማር ያስፈልጋል። መሀል ከተማ ያሉት አስተሳሰባቸውን ማስተካከል አለባቸው። አቋማቸውን ካላስተካከሉ ኤርትራውያኖች ላይ እንደሆነው እነሱም ላይ ሊደርስባቸው ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉበት ቦታ የለም። ኹላችንም ተረባርበን ህወሓትን ከሕዝቡ የመለየት ሥራ መሥራት አለብን።

ከ8 ወር በፊት ወደነበረው ልመልሶትና መከላከያ ላይ ጥቃት ተፈጸመ ሲባልና በኹለት ሳምንት ተሸንፈው ይለቃሉ ብለው ገምተው ነበር?
ለሆነው ኹሉ ፈጣሪን ነው የማመሰግነው። ተጣልተን የነበርነውን እኛንና ኤርትራውያንን አስቀድሞ በማስታረቁ ሊመሰገን ይገባል። ከኤርትራ ጋር ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ነው ያስታረቀን። ህወሓቶች አጣልተውን ስለነበር ስንታረቅ ጠቅሞናል። ቀድመን ባንታረቅ ኑሮ ከፍተኛ አደጋ ይደርስ ነበር። በጊዜው አሸነፍን ሲባል እንባዬ እስኪመጣ ድረስ ነው ደስ ያለኝ። በእኛ ጊዜ ሰለኽላካና ሽሬ ላይ የተደረገው ነገር ነው አሁን መከላከያ ላይ የተፈጸመው።

እኔ ትግራይ ሰለኽላካ ውስጥ እነደምሴ ቡልቶ የጠሩት ስብሰባ ላይ የተፈጠረውን አልረሳውም። መርዕድ ንጉሴ ከመከላከያ፣ ቁምላቸው ደጀኔን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተው ነበር። የስብሰባው ዓላማ ሰለኽላካን የኢንዱስትሪ መንደር እናደርጋለን የሚል ነበር። አክሱምና አድዋ መንገድ ተዘግቶ ስለነበር እሱን እናስከፍታለንም ሲሉ ነበር። በዚህን ጊዜ አንድ ምክትል መቶ አለቃ እጁን አውጥቶ ተናገረ። በመድፍና በጀት ምቱልን ስንል እኛ እንመታለን፤ ከኋላችንም ታስመቱናላችሁ፤ ጀነራል የሚመታው መቼ ነው? ሲል ደምሴ ቡልቶ በንዴት መልሰውለታል። ቁምላቸው ደጀኔ ደግሞ፣ “አንተ ጀነራል ስትሆን ነው” ብሎት ነበር። ይህ በ1981 ከተፈጠረ በኋላ መንገዱን አስከፍቱ ተብሎ ሠራዊቱ ከካንፕ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ከጀርባው እንዲመታ ተደርጎ ነበር።

ሌላው ስህተት በእያንዳንዱ ወረዳ 300 ወጣቶች አካባቢቸውን ይጠብቁ ተብለው በእኛ እንዲሰለጥኑ መደረጉ ነው። ለሚሊሻ ተብሎ ሲመለመል እነሱ የሚልኳቸውን እየተቀበልን ነበር የምናሰለጥንላቸው። ጥናት ሳይደረግ እጃቸውን የሰጡ እየተባሉም እንዲቀላቀሉ ይደረግ ነበር። በእንዲህ አይነት መንገዶች ውስጣችን እየገቡ ሲሰልሉ ቆይተው ድንገት ሆ ብለው ይነሱና ጉዳት ያደርሳሉ። በዚህ መንገድ ነው አሁንም ሠራዊቱ ላይ ጥቃት የፈጸሙት። አሁንም ውስጣቸው ስለማይታመን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

መከላከያ ሰሞኑን ከትግራይ የወጣበት ጊዜ ከችግሩ አንጻር ቆይቷል ወይስ ፈጥኗል ነው የሚሉት?
የወጣበት ጊዜ ሁኔታው ስላስገደደ ተገቢ ነው ብዬ ነው የማስበው። አገርን እየጠበቀ ያለ ሠራዊት ላይ ሕዝብን አነሳስተው እንዲያ አይነት አሳዛኝ ተግባር ሲፈጽሙ መቆየት አልነበረበትም። የቆየበት ጊዜ ማንነታቸውን ለመለየት በቂ ስለነበር ከ8 ወር በኋላ መውጣቱ ጥሩ ነው። በፊት የተፈጸመው ነገር እንዳይደገም ግን መጣር ይኖርበታል። አወጣጡ አልዘገየምም አልፈጠነምም።

መከላከያ መውጣቱን ተከትሎ ወደ መሀል አገር መግባቱን የሚተቹና ዳር ድንበር ላይ መጠበቅ ነበረበት የሚሉ አሉ። እዚህ ላይ አስተያየቶ ምንድን ነው?
የተከዜን ድንበር ይዞ እስከ አፋር ድረስ መስፈር ነበረበት። ከላይ ያለውን የኤርትራ ድንበር ራሳቸው ኤርትራውያኑ ይጠብቃሉ። እነሱ ራያንና ወልቃይትን መልሰን እንቆጣጠራለን እያሉ ነው። የሕዝቡ ፍላጎት እስኪረጋገጥ ድረስ መከላከያ መራቅ የለበትም። በአጠቃላይ መከላከያ ክልሉን አጥሮ ነው መቀመጥ ያለበት። አሁን በኦነግ ሸኔም ይሁን በሌላ በየቦታው ሕዝብ እያለቀ ነው። በመላው አገሪቱ ውስጥ የሚፈጸመውን ወንጀልና ግፍ ለማስቆም ፖሊስ ብቻውን የሚወጣው አይደለም።

ሱዳን ድንበር ዘልቃ መግባቷንስ እንዴት ያዩታል?
ሱዳን 40 ኪሎ ሜትር ድንበራችንን አልፋ የእርሻ መሬትን ይዛለች። ይህ የሆነው ከእሷ ጋር ጦርነት ስንገጥም ህወሓቶች አጋጣሚውን ለመጠቀም ነው። ያኔ በሱማሊያ ወረራ ጊዜ እንደተደረገው አሁንም ለመድገም አስበው ነበር። ያኔ ሱማሊያ የኔ ነው እያለች ስትወር አሜሪካ ነበረች ከኋላ ሆና ስትደግፍና አይዞሽ ስትል የነበረችው። ወቅቱ የአብዮት ጊዜ ስለነበር እንዲበጠበጥ አደረጉት። አሁንም ለውጡን ለማስቀረትና አገሪቱን ለመበጥበጥ ሱዳን እንድትወር አድርገዋል። ዓላማቸው ስላልተሳካላቸው ነገ ራሳቸው ለቀው ይወጣሉ። እንደእኔ በዛ ግንባር ጦርነት መከፈት የለበትም። አልፈው የሚመጡ ከሆነ ግን ዝም መባል የለባቸውም። ወያኔዎች 30 ሺሕ ጦር ሱዳን ውስጥ እንዳላቸው ስለተናገሩ ጉዳዩን ቀለል እድርጎ ማየት አያስፈልግም። አሁንም ወስደው እያሰለጠኑ ስለሆነ ሁኔታውን መቆጣጠር ያስፈልጋል።

የአማራ ክልል ታጣቂዎች ወደ ትግራይ ድንበር መከላከያን ተክተው እንዲጠጉ መደረጉ ጉዳዩን የሁለቱ ክልል እንዳያደርገው ብለው ስጋታቸውን ስለሚገልጹ ሰዎች ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
ኹለቱን ወገኖች ለማጣላት ከፈርዖኖች ዘመን ጀምሮ ግብጾች ሲጥሩ ነበር። የሁለቱንም ፖለቲከኞች በመጠቀም ሕዝቡን ለማጋጨት እየሞከሩ ነው። የአማራ ፖለቲከኞች ከዚህ ጉዳይ እጃቸውን ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። የትግራይም ሆነ የአማራ ድንበርተኞች ኹለቱም ከተከዜ ወንዝ በጋራ ሲጠቀሙ የኖሩ ናቸው። እርስ በርሱ ያልተጋባና ያልተዋለደ የለም።

እኔ ክልል የሚባለውን ስሙንም መጥራት አልፈልግም። ኤርትራንም ቢሆን እንደወንድም ክፍለ አገር ነው የማየው። በቅርብ ዘመናት የሆነውን ሕዝብ ማወቅ አለበት፤ እኛም ማስተማር አለብን። በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ተከፋፍለው እንዲባሉ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችን ሴራ መረዳትና ዓላማቸው እንዳይሳካላቸው መተጋገዝ አለብን።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com