የእለት ዜና

የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች ዓለማቀፍ የውኃ ፖለቲካና የኢትዮጵያ ሁኔታ

Views: 273

የዓባይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ በዓባይ የመጠቀም መብት ያላት ከመሆኑ በላይ የማንንም ጥቅም የማትነካ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ አገራት ኢትዮጵያ ይህን እንዳታደርግ ውጥረት ውስጥ ከመክተት አልታቀቡም። የድምበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም የተመለከተ ጉዳይ ሲነሳ አገራት ይህን ጉዳይ የሚያስተናግዱበት አካሄድ አላቸው። ለዚህ ሕግ ምንጭ የሆኑ አስተሳሰቦችም አሉ።
ሽመላሽ ወንዳለ ስለደምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም የሕግ ምንጭ የሆኑ አስተሳሰቦችን በማንሳት ኢትዮጵያ በድምበር ተሻጋሪ ወንዟ ዓባይ ምክንያት ከግብጽና ሱዳን ጋር የገባችበት ውዝግብ በየትኛው አስተሳሰብ ስር እንደሚወድቅ አመልክተዋል። የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም በሕግ ድንጋጌ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በአገሮች ፍላጎትም ላይ የተመሠረተ ነውና ኢትዮጵያም ይህንን ከግምት በማስገባት ጥቅሟን ማስጠበቅ ላይ ጠንክራ ልትሠራ ይገባል ባይ ናቸው።

በዓለም አቀፍ የውኃ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሚይዙ ጉዳዮች አንዱ የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ነው። የድምበር ተሻጋሪ ወንዞችን የውኃ አጠቃቀም በተመለከተ የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚራመዱ ሲሆን አስተሳሰቦቹ የሚተገበሩት እንደ አገሮቹ ጥቅም፣ ፍላጎትና አቅም ነው።

ይህም ማለት፤ አገሮች የራሳቸውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት አቅማቸው በፈቀደው ልክ ከአገራቸው የሚነሳ ወንዝን ይጠቀማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችም (lower riparian’s) በበኩላቸው ወደ እነሱ የሚፈሰውን ወንዝ የውኃ መጠንና ጥራት ለማስጠበቅ አቅማቸው በፈቀደ መጠን በውይይትና በድርድር ወይም በጉልበት እስከመጠቀም (ጦርነት እስከማወጅ) ሊደርሱ ይችላሉ።

አገሮች በድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ላይ ባለመግባባታቸውና በተደጋጋሚ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ግጭቶች በመፈጠራቸው፣ ጉዳዩን ሊገዙ የሚችሉ ዓለም አቀፍ የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕጎች በሥራ ላይ ውለዋል። ከእነዚህም መካከል እ.አ.አ. በ1966 የወጣው የሔልሲንኪ ስምምነት እንዲሁም እ.አ.አ. በ1997 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የድምበር ተሻጋሪ የውኃ አካላት ሕግ የሚጠቀሱ ናቸው።

ሆኖም ግን አገሮች ሕጉ የሚጠቅማቸው ሆኖ ሲገኝ ይጠቀሙበታል፤ የሚጎዳቸው ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ሊገዙበት ፍቃደኛ አይሆኑም። በዚህም ምክንያት የድምበር ተሻጋሪ ወንዞችን ዓለም አቀፍ ሕግን በሚጻረር መልኩ አገራት ሲጠቀሙባቸው በተደጋጋሚ ይታያሉ። እስከ አሁንም ለችግሩ መፍቻ የሚሆን ዘላቂ መፍትሄ አልተገኘም። ለዚህም አንዱ ምክንያት የዓለም አቀፍ ሕግ ባህሪ ሲሆን ይኸውም የዓለም አቀፍ ሕግን ለመተግበር አስገዳጅ የሆነ የሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ አካል አለመኖሩ ነው።

ለዓለም አቀፍ የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ ምንጭ የሆኑ አስተሳሰቦች (theories) ያሉ ሲሆን ከዚህ ቀጥሎ እንመከለታቸዋለን። አያይዘንም ኢትዮጵያ በድምበር ተሻጋሪ ወንዟ ዓባይ ምክንያት ከግብጽና ሱዳን ጋር የገባችበት ውዝግብ በየትኛው አስተሳሰብ ስር እንደሚወድቅ እንመለከታለን።

በርካታ አስተሳሰቦች ቢኖሩም ለዚህ ጽሑፍ ግን ዋና ዋና የሚባሉትን ሦስቱን እንዳስሳለን። ኹለቱ አስተሳሰቦች ጽንፍ ለጽንፍ (ተቃራኒ) ሲሆኑ ሦስተኛው ደግሞ የኹለቱን ተቃርኖ ለማስታረቅ አማካይ የሆነ አስተሳሰብ ነው።

1. ፍጹም የግዛት ሉዓላዊነት አስተሳሰብ (Absolute Territorial Sovereignty Theory)
ይህ አስተሳሰብ በሌላ ሥያሜው የሀርሞን አስተምህሮ (Harmon Doctrine) ይባላል። ምክንያቱም ሐሳቡ የጎለበተው ሀርሞን በተባለ አሜሪካዊ የሕግ ባለሙያ ነው። ቃሉም እንደሚያመለክተው አንዲት አገር በግዛት ክልሏ ውስጥ በሚመነጩ ድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ላይ ፍጹም የሆነ የግዛት ሉዓላዊነት እንዳላት የሚያብራራ አስተሳሰብ ነው። ሙሉ በሙሉም ወንዙ የሚመነጭባትን አገር የሚደግፍ ነው።

በዚህ አስተሳሰብ መሠረት ድምበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ የወንዙ ምንጭ የሆነችው አገር ከሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚመነጭን ወንዝ ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ከልካይነት፣ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ማማከር ሳያስፈልጋት፣ እንዲሁም የእነሱን ጥቅም መነካትንም ከግምት ውስጥ ሳታስገባ የወንዙን ተፈጥሯዊ አቅጣጫ እስከ ማስቀየር ድረስ መጠቀም ትችላለች ወይም መብት አላት። የወንዙ ምንጭ የሆነችው አገር ለራሷ ጥቅም ስትል የወንዙን ውኃ መጠንና ጥራት እስከመቀየር ፍጹም ሉዓላዊ ሥልጣን አላት።

ይህ አስተሳሰብ ብዙ ጊዜ ተግባር ላይ የሚውለው የወንዙ ምንጭ የሆነችው አገር ከተፋሰሱ የታችኞቹ አገራት (lower riparian’s) በኢኮኖሚና ወታደራዊ ጥንካሬ የበላይነት ሲኖራት ነው። እንደ ምሳሌም በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መካከል ያለውን ዘመናትን ያስቆጠረና እስካሁንም ያልተፈታ የድምበር ተሻጋሪ ወንዝ የውኃ አጠቃቀም ውዝግብ ማየት እንችላለን።

የኮሎራዶ ወንዝ ከአሜሪካ ተነስቶ ድምበር ተሻግሮ ወደ ሜክሲኮ የሚፈስና በመጨረሻም ወደ ኮርቴዝ ባሕር የሚቀላቀል ሲሆን፣ በአሁን ጊዜ ለጎረቤታሞቹ ለአሜሪካ እና ሜክሲኮ ያለመግባባት መንስኤ ነው። ምክንያቱም አሜሪካ ወንዙን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየተጠቀመችበት ስለሆነ ነው።

አሁን ባለው አጠቃቀም ምንም እንኳ ወንዙ በተፈጥሮ ድምበር ተሻጋሪ ቢሆንም፣ ነገር ግን አሜሪካ የዓለም አቀፍ የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግን በሚጻረርና የሜክሲኮን ጥቅም ፍጹም በሚጎዳ ሁኔታ እየተጠቀመችበት ትገኛለች። አሜሪካ በኹለቱ አገሮች ድምበር ላይ በገነባችው ግድብ ምክንያት ወንዙ ሜክሲኮ ሲደርስ ውኃው ከማነሱ የተነሳ የመድረቅ ያህል በሚባል መልኩ ሲፈስ አይታይም። አሁን የሚታይ ነገር ቢኖር በፊት ውኃ ይወርድበት የነበረው ቦይ (ሸጥ) ብቻ ነው።
አሜሪካ የኮሎራዶን ወንዝ በዚህ መልኩ ሆኖ የሚታይ አጠቃቀሟን ትክክለኛ የሚያደርግና የሚደግፋት የዓለማ አቀፍ ሕግ ኖሮ ሳይሆን በሜክሲኮ ላይ ያላትን የኢኮኖሚና ወታደራዊ ኃይል የበላይነት እንዲሁም ሌላ ማንም አገርና ድርጅት ምንም ተጽእኖ ሊያደርግባት እንደማይችል በመተማመን ነው።

ሆኖም ግን የፍጹም የግዛት ሉዓላዊነት አስተሳሰብ ምንጭና በተግባርም ተጠቃሚ የሆነችው አሜሪካ በአሁን ጊዜ ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለገባችበት ውዝግብ ለግብጽ በመወገንና ጣልቃ በመግባት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ የዓባይን ወንዝ የውኃ ፍሰት መጠንን በተመለከተ ግብጽ እና ሱዳን እንዳይጎዱ የዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት እንድትገነባ ስትልም በተደጋጋሚ ከማሳሰብ አልፋ ማዕቀብ በመጣል ኢትዮጵያን ልትቀጣ እንደምትችል ጭምር በማስፈራራት ላይ ትገኛለች።

ይሁን እንጂ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሆን ከላይ እንዳየነው ከግዛቷ የሚመነጭን ድምበር ተሻጋሪ ወንዝ እስከማድረቅ የደረሰ ለራስ ጥቅም ብቻ የማዋል ኢ-ፍትሐዊ አጠቃቀም ትከተላለች። ምክንያቱም ይህን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ስላላት ነው።
ይህ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ወንዙ የሚመነጭበትን አገር የሚደግፍ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለውና በዓለም አቀፍ የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች የውኃ አጠቃቀም ሕግም የማይደገፍ ነው።

2.ፍጹም የግዛት አንድነት አስተሳሰብ (Absolute Territorial Integrity Theory)
ይህ ሐሳብ ከላይ ከተመለከትነው ፍጹም የግዛት ሉዓላዊነት አስተሳሰብ ተቃራኒ ሲሆን ሙሉ በሙሉም የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው። በዚህ አስተሳሰብ መሠረት ወንዞች የተፈጥሮ ስጦታ ስለሆኑ ፍሰታቸውን፣ መጠናቸውን እና ጥራታቸውን መወሰን ያለባት ተፈጥሮ እንጂ ሰው አይደለም። ሰው ተፈጥሮን የመንካት ብሎም የማሻሻል መብት ወይም ሥልጣን የለውም። ይህም ማለት አንድ ወንዝ የሚመነጭባት አገር በምንም መልኩ፣ ለምንም ዓላማ ከግዛቷ የሚመነጭ ወንዝን የውኃ ፍሰት፣ ጥራትና መጠን ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ የሚችል ምንም ዓይነት ነገር፣ልማትም ቢሆን፣ መሥራት አትችልም። ይልቁንም ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ጥቅም ሲባል የተፈጥሮ ፍሰቱን የማመቻቸት የሕግና የሞራል ግዴታ አለባት።

በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ የሚገኙ ቃላትና ሐሳቦች ለትርጉም የተጋለጡ በመሆናቸው ለውዝግብና አለመግባባት ምክንያት የሚሆኑ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አንደኛው፣ ታሪካዊ መብት፣ ተፈጥሮአዊ መብት፣ ቅድሚያ መመካከር እና በሌሎች ላይ ጉዳት አለማድረስ የሚሉት ናቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ላይ ለታችኛው የተፋሰሱ አገራት ብቻ የሚጠቅም ሲሆን ብዙ ጊዜም የሚተገበረው የታችኛው ተፋሰስ አገር/ራት የወንዙ ምንጭ ከሆነችው አገር የኃይል የበላይነት ሲኖራት/ቸው ወይም አለኝ/ን ብለው ሲያምኑ ነው። ይህ ሲሆን የታችኛው ተፋሰስ አገር/ራት ከቃላት ማሳሰቢያና ማስፈራሪያ በማለፍ የወንዙ ምንጭ የሆነችው አገር ላይ በቀጥታ ጦርነት በማወጅ ሊወሩና ወንዙን ከነምንጩና ገባሮቹ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ ወይም በተለያየ መንገድ ሊሞክሩ ይችላሉ።
ለዚህ አስተሳሰብ ተጨባጭ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነውም የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ነው። ከግንባታው ጋር በተያያዘ ከግብጽና ሱዳን ጋር የምታደርገው ድርድር አልሰምር ሲል ኹለቱ አገራት በተለይም ግብጽ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ውል ሳትፈርም የግድቡን ግንባታና ሙሊት የምትቀጥል ከሆነ ወታደራዊ ኃይል በመጠቀም የግድቡን ግንባታና የውኃውን ሙሊት እስከማቆም ልትደርስ እንደምትችል በተደጋጋሚ መዛቷና ከሱዳን ጋርም ደጋግማ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓና ለማስፈራራት መሞከሯ የዚህ አስተሳሰብ ማሳያ ነው።
ግብጽና ሱዳን በተለይም ግብጽ በወንዙ አጠቃቀም ላይ ያላት ሐሳብና የምታራምደው አቋም ከዚህ አስተሳሰብ የመነጨ እንደሆነ በግልጽ መረዳት እንችላለን። ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሱትን አወዛጋቢ የመብት አጠቃቀሞች እንደ ታሪካዊና ተፈጥሮዋዊ መብት የምትወስዳቸው፣ ከወንዙ ሲደርሳት ከነበረው የውኃ መጠን አንዲትም ጠብታ እንዳይቀነስ የምትሻ፣ ብሎም ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ምንም ነገር ከማድረጓ በፊት በቅድሚያ ፍቃድ እንድትጠየቃት መፈለጓ፣ የግድቡ ግንባታ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስብኛል የመሳሰሉ ማሳሰቢያዎቿ እና ማስፈራሪያዎቿ በግልጽ ማንሳቷ ከዚህ አስተሳሰብ የመነጩ ናቸው።

ኹለተኛው ለትርጉም ተጋላጭ የሆነና ለውዝግብና አለመግባባት ምክንያት ከሆኑት መካከል፤ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም (Equitable and Reasonable Utilization) መርኆ ይገኛል። ፍትሐዊነትና ምክንያታዊነት የሚሉት ቃላት ትርጉማቸው ብዙ ጊዜ አንጻራዊ በመሆኑና እንደ አገሮቹ ፍላጎት ለተለያየ ትርጉም ስለሚጋለጡ ያለመግባባት ብሎም የግጭት ምንጭ ሲሆኑ ኖረዋል፤ አሁንም ናቸው። በሔልሲንኪ ስምምነትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት የድምበር ተሻጋሪ የውኃ አካላት ሕግ መሠረት ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም የሚለው ሐሳብ የሚከተሉትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ተደንግጓል፤
መልክዓ-ምድራዊ፣ የአየር ንብረትና ሌሎች ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች፤
የአገሮቹ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፤
በወንዙ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሕዝቦች ቁጥር (ብዛት)፤
የውኃው አሁናዊና የወደፊት የመጥቀም (የማልማት) አቅሙ፤
ውኃውን በአግባቡ የመንከባከብ፣ የመጠበቅና የማልማት ሁኔታ እና
ሌሎች አማራጮችን የመጠቀም እድል።
ስለሆነም አገሮች ድርድር ሲያደርጉ እነዚህን ነጥቦች ከግምት ውስጥ በማስገባትና በተጨባጭ በማስረዳት መሆን አለበት።

3.የተገደበ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አስተሳሰብ (Limited Territorial Integrity and Sovereignty Theory)
የዚህ አስተምህሮ ዓላማው ከላይ ያሉትን ኹለት ተቃራኒ ጽንፍ ላይ የተቀመጡት አስተሳሰቦችን የማስታረቅና የማመጣጠን ነው። ይህም ማለት ይህ አስተምህሮ ሉዓላዊነትና የተፈጥሮ መብቶችን የማጣጣም ዓላማ አለው።
በዚህ አስተሳሰብ መሠረት ፍጹም የተጠቃሚነት መብት የሚባል የለም። ይልቁንም የላይኛውም የታችኛውም ተፋሰስ አገራት ወንዙን በአግባቡ እና በፍትሐዊነት የመጠቀም ግዴታ አለባቸው። ለዚህ ይረዳ ዘንድም አገራት በመነጋገርና በትብብር እንዲሁም በቅንነት መንፈስ ሊሠሩ ይገባል። በዚህ መልኩም የግዛት ሉዓላዊነታቸውን፣ ተፈጥሮዓዊና ታሪካዊ የመጠቀም መብታቸውንና ጥቅማቸውን ማረጋገጥ ወይም ማጣጣም ይችላሉ።

በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ግልጽ ያልሆኑና ለትርጉም የተጋለጡ፣ አገራትም እንደየጥቅማቸውና ፍላጎታቸው የሚተረጉሟቸው፣ ለግጭት መንስኤ የሆኑ/የሚሆኑ ቃላት አሉ። ከእነዚህም የሚጠቀሱ፣ ምክንያታዊነት፣ ፍትሐዊነት፣ ምንም ጉዳት አለማድረስ፣ የመሳሰሉት ናቸው።
ለዚህ አስተሳሰብ ትግበራ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ህንድ እና ፓኪስታን ሲሆኑ ኹለቱ አገራት የኢንዱስ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ በተደጋጋሚ ስምምነት ከማድረጋቸውም በላይ ስለ ወንዙ አጠቃቀም ክትትል የሚያደርግና ችግር ሲኖር ወይም ንግግር ሲያስፈልግ ችግሩን እንዲፈታ ቋሚ የሆነ ኮሚሽን አቋቁመው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ኹለቱ አገሮች አሁንም ሰላማዊ በሆነና ኹለቱን አገሮች ወንዙን ባግባባ እንዲሁም ወደ ግጭት በማይከት መልኩ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

አገራችን ኢትዮጵያም በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር በምታደርገው ውይይትና ድርድር ላይ የምታነሳውና ወጥ የሆነ አቋሟም ከዚሁ የውኃ አጠቃቀም አስተሳሰብ የመነጨ ነው።
ይህ አስተሳሰብ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሕጎች፣ የዳኝነት አካላት ውሳኔዎች እና ስምምነቶች በሰፊው ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ ነው። በውስጡም የተካተቱት መርሆዎች ማለትም ምክንያታዊነት፣ ፍትሃዊነት፣ ምንም ጉዳት አለማድረስ የመሳሰሉት በ1966 በጸደቀው በሔልሲንኪ ስምምነት (አንቀጽ 4 እና 5)፤ ከዚያ በኋላም እ.አ.አ. በ1997 በጸደቀው የተባበሩት መንግሥታት የድምበር ተሻጋሪ የውኃ አካላት ሕግ (አንቀጽ 5-9) እና በሌሎችም የድምበር ተሻጋሪ የውኃ አካላት አጠቃቀም ስምምነቶች ውስጥ የተካተቱ ናቸው።
ሰለሆነም የዓለም አቀፍ የድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ከላይ እንዳየነው በዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በአገሮች ፍላጎትም ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ ኢትዮጵያም ይህንን ልማድ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥቅሟን ማስጠበቅ ላይ ጠንክራ ልትሠራ ይገባል።

በሌላ አገላለጽ፣ ኢትዮጵያ የዓባይንም ሆነ ሌሎች ድምበር ተሻጋሪ ወንዞቿን አጠቃቀም በተመለከተ የዓለም አቀፍ ሕግን እና የጋራ ተጠቃሚነትን ብቻ መሠረት አድርገው ለሚወያዩ አገሮች ሕግን አጣቅሳና የጋራ ጥቅምን ከግምት ውስጥ አስገብታ፣ በተቃራኒው ጥቅማቸውን ብቻ መሠረት አድርገው የሚመጡባት አገሮችን ደግሞ ጥቅሟን ባስቀደመ አግባብ ብቻ ልታስተናግዳቸው ይገባል።

ሽመላሽ ወንዳለ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ (LLB) እንዲሁም በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ የኹለተኛ ዲግሪ (MA) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በዚህ አድራሻ shiwondale@gmail.com ማግኘት ይቻላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com