የእለት ዜና

መገንጠልን የሚፈቅደው ሕግ ዘላቂነት

Views: 67

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ብሎ እስከመገንጠልን የሚፈቅደው የሕግ ጽንሰ ሐሳብ በአገራችን ሕገ-መንግሥት ቦታ ካገኘ ሩብ ምዕተ ዓመት አልፎታል። ይህን የመሰለ አገርን ለመበታተን የሚዳርግ ሕግ በሌሎች አገራት አለመኖሩን በርካታ ምሁራን ይናገራሉ። የሚያስከትለውን መዘዝም በመጠቆም እንዲቀር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቆይቷል። አንቀጽ 39 እየተባለ በሚታወቀው በዚህ ሕግ መሠረት ኤርትራ መገንጠሏን የሚያነሱ አካላት፣ ለአገር የማይጠቅም እንደሆነ በተለያየ አጋጣሚ በማስታወስ እንዲሻር ሲጠይቁ ኖረዋል። ህወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ሕጉ አይቀየርም በማለት ሕገ-መንግሥቱም የሚሻሻል እንዳልሆነ ትክክለኛነቱን በመጥቀስ ሲሟገትለት ኖሯል።

የህወሓት ዘመን አብቅቶ አጋሮቹ የነበሩት ሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ሕዝቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች አንቀጹ እንዲቀየር፣ ሕገ-መንግሥቱም እንዲሻሻል በተደጋጋሚ ፍላጎታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ይህ ቢሆንም ቅሉ ከመንግሥት በኩል ይጠበቅ የነበረው ተግባር በመዘግየቱ ቅሬታ አስነስቶ ነበር። በሕጋዊ መንገድ እንዲሻሻል ጥያቄ ስለመቅረቡ ባይታወቅም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የማሕበረሰብ አንቂዎች አንድ ሰሞን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተውት ጥያቄው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጭምር ምላሽ አግኝቶ ነበር። ምላሻቸው ግን የተጠበቀው ሳይሆን በመቅረቱ የብዙዎችን እንጥል ዱብ ያደረገና ደጋፊዎቻቸውን ጭምር ኩም ያደረገ ነበር። ከሠንደቅ ዓላማ መቀየር ጋር በተገናኘ ‹ለአንድ ክልል ብለን ሕገ-መንግሥት አናሻሽልም› የሚል ይዘት ያለው ንግግራቸው፣ የብዙዎች ተስፋ ላይ ውሃ ቸልሶበት ድጋፋቸው እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ሆኖ ነበር የሚሉ አሉ።

ምርጫ ተደርጎ አሸናፊ የሆነ አካል ካልሆነ ሕገ-መንግሥቱንም ሆነ ሌሎች ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ማድረግ አይቻልም እየተባለ 10ኛ ክልል ቢመሰረትም፣ ሕገ-መንግሥቱን በተመለከተ ምንም የተቀየረ ነገር አልነበረም። የኢሕአዴግ አወቃቀር ሲቀየር ፣ ሌሎች አዋጆችና ደንቦች ሲሻሻሉና ሲቀየሩ ሕዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲጠይቁ የነበረው የሕገ-መንግሥቱ ጉዳይ ግን ተዘንግቶም ይሁን ጊዜ እየተጠበቀለት እስካሁን እንዲቆይ ተደርጓል።

የተለያዩ ጽንፍ የያዙ አካላት አሉ በማለት፤ አንዱ ቡድን ሕገ-መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቀየር ይሻል፤ ሌላው ደግሞ ፍፁም እንዳይነካበት ይፈልጋል፤ የተወሰነው ደግሞ በሕዝብ ይሁንታ የተወሰነው ክፍል ይሻሻል የሚል ፍላጎት አለው በማለት፣ እስከቅርብ ጊዜ መንግሥት ሁሉንም አስታራቂ የሆነ አማራጭን ነው የሚፈልገው እየተባለ በደፈናው ሲመለስ ነበር።

ሕገ-መንግሥቱን ሥልጣን ላይ ከወጣን እናሻሽላለን ሲሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ ቢሆኑም፣ የማሸነፍና መንግሥት የመመስረት እድላቸው እየተመናመነ ሲመጣ የማሻሻሉ ወሬም እየተዘነጋ መጥቷል። አሁንም ቢሆን ሕዝብን በዘር የሚከፋፍልና የሚነጣጥል የሕገ-መንግሥቱ ክፍል እንዲሻሻል የሚጠይቁ አልጠፉም። በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫው ከተሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉበት አጋጣሚ ላይ፣ ተመሳሳይ ሕገ-መንግሥቱ አይሻሻልም ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ሕገ-መንግሥቱን በተመለከተ በቀረበው ጥያቄ ደስተኛ እንዳልነበሩ ለሚዲያ ዝግ በነበረው ጉባዔ ላይ የተገኙ ማንነታቸው እንዳይነገር የፈለጉ ተሳታፊ አሳውቀውናል። ስለምርጫው ሂደት ለመወያየት በተጠራው ስብሰባ ስለሕገ-መንግሥት መሻሻል ሲጠየቁ ደስተኛ ባይሆኑም፣ የመለሱት ግን ያልተጠበቀ እንደነበር አስተያየታቸውን ሰጥተውናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ-መንግሥቱ እንዲሻሻል እሳቸውም እንደሚፈልጉ በማሳወቅ፣ መሻሻሉ ግን ምርጫውን ስለምናሸንፍ ብቻ አይሆንም ብለው እንዴት መሆን እንዳለበት ዕምነታቸውን አሳውቀዋል። ምርጫውን ማሸነፉ ብቻ ሳይሆን እንደከዚህ በፊቱ “የሕዝብ ቅቡልነት የለውም፤ ሕብረተሰቡ ሳይሳተፍበት የተደረገ ነው” እንዳይባል በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። ሕዝበ ውሳኔ የሚፈልገው ተለይቶ፣ እንዲሁ ማሻሻል የሚቻለውም ላይ ሕዝብ ተወያይቶበት እንጂ ስላሸነፍን ተብሎ የሚደረግ ብቻ መሆን የለበትም ማለታቸውን ሰምተናል። ሲሻሻል ታዲያ ውስጡ ያሉ በጎ ነገሮች ሳይነኩ እንዲቀሩ ይደረጋል ቢሉም፣ በደፈናው በመናገራቸው የቱ ተሻሽሎ የቱ እንደሚቀር ፍንጭ አልሰጡም። ዝርዝር ጉዳዩ ላይ እንዲሁም ሂደቱ መቼ እንደሚጀመርም ሆነ፣ ለዚሁ ሥራ ተብሎ የተቋቋመ አካል ስለመኖሩም ምንም አላሉም።

ንግግራቸውን እንደሰሙት ተሳታፊ ከሆነ፣ መሻሻሉ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ፍላጎታቸው መሆኑን ለማወቅ ችለዋል። በመልሳቸው ተሳታፊው ደስተኛ ስለነበር በጉዳዩ ላይም ተጨማሪ ማብራሪም ሆነ ማረጋገጫ አልጠየቁም። ሀሳባቸውን ዝግ በሆነ ውይይት ወቅት በመናገራቸው ሕዝቡ ሊያውቀው እንዳልቻለ የጠቆሙን ሲሆን፣ የምርጫው ውጤት በይፋ ሲነገር አሸናፊ ከሆኑ የሚያሳውቁት እንደሆነ ግምታቸውን ነግረውናል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎትና ዕምነት ይህ ነው ቢባልም፣ በተቃራኒው የሕዝብን ምኞት መልሶ የሚያደበዝዝ ጉዳይ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ተሰምቷል። ባሳለፍነው ሳምንት ምክር ቤቱ የተቋቋመበት አዋጅ እንዲሻሻል የሚያደርጉ ኹለት አዋጆችን ለማሻሻል ረቂቅ አዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ነበር። ለአዋጆቹ መሻሻል መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች ቢያስቀምጥም፣ አንዳንድ ሕዝብ እንዲቀየሩ ሲጠይቃቸው የነበሩ ጉዳዮች በአዲሱ ረቂቅ ላይ እንዲካተቱ ማድረጉ ግራ አጋብቷል። የመገንጠል መብትን የሚፈቅደውን የሕገመንግስቱን አንቀፅ 39 የሚ,ያስፈጽምበት አንቀፅ በአዲሱ ማሻሻያ ላይ ማካተቱ ሕገ-መንግሥቱ አይሻሻልም ለሚሉት ግብዓት ሆኗል። ሕገ-መንግሥቱ ላይ ያለው አንቀፅ ሳይሻር ማስፈጸሚያ አዋጁ ሊቀር ባይችልም፣ እንዳለ አቆይቶ የሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ባለመጠበቁና የምክር ቤቱን አዋጅ በዚህ ሁኔታ ለማሻሻል መቸኮሉ ግራ አጋብቷል።

ከሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ጋር በተገናኘ የተለያዩ አካላት ይሻሻል የሚሉት የሕጉ ክፍል ቢለያይም፣ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ጠንሳሹ በስተቀር መሻሻል እንዳለበት ሁሉም ፓርቲዎች ማለት እስኪቻል ድረስ ይስማማሉ። ፓርቲዎች ይሻሻል የሚሉትን ክፍል ለይተው ለውይይት እንዲያቀርቡ ከዚህ በፊት ሐሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ሂደቱ አሁን ምን ላይ እንዳለ አይታወቅም። ያም ሆነ ይህ፣ አሁን በምርጫው የሚያሸንፍ አካል የማሻሻል መብቱም ሆነ ግዴታው ስለሆነ ውስጡ ያሉ አንቀፆች መዘዝ ሳያስከትሉ በቶሎ ለውጡ ወይም መሻሻሉ እንዲካሄድ የብዙዎች ፍላጎት ነው። በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየከረረ የመጣው ፅንፍ የረገጠ አመለካከት፣ ትውልዱ ሊወስነው የማይገባውን ግዙፍ ውሳኔ በእልህ ወስኖ፣ ለትውልዶች የሚተርፍ መከራ ከማስከተሉ በፊት በቶሎ እንዲስተካከል የሚወተውቱ አሉ። በሱማሌ ክልል ሊፈጸም የነበረን ተመሳሳይ የችኮላ እርምጃ አስቀርቶ በሕጋዊ መንገድ ሕዝብ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ለመሄድ ከመቻሉ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን አሁንም መማር እንዳለብን የሚናገሩ አሉ።

ስለሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ጉዳይ እንዲሁም፣ መገንጠልን ስለሚፈቅደው አንቀፅ 39 አጠቃላይ ሁኔታ አዲስ ማለዳ የሕግ ባለሙያና ጠበቃ የሆኑትን ካፒታል ክብሬን አነጋግራ ነበር። እንደሳቸው አመለካከት ሕገ-መንግሥቱ እንደሚሻሻል የተለያዩ ፍንጮች እየተነገሩ ቢሆንም፣ ማረጋገጫ የሚሆን የተጀመረ ተጨባጭ ነገር የለም። ከመንግሥት የሚሰማው መረጃ ፍላጎትን የሚያሳይ ቢሆንም ሕገ- መንግሥትን ለማሻሻል መታለፍ ያለባቸው ሂደቶች አሉ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ያዘጋጀው ማሻሻያ ረቂቅ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ፈጽሟል ሊያስብል የሚችል ባይሆንም፣ ወቅታዊነቱ ግን ያጠያይቃል። ጉዳዩን እንዲያስፈጽም ሥልጣን የተሰጠው አካል መሆኑ በግልጽ ቢደነገግም፣ ይሻሻላል የሚል ፍንጭ እንደኛ መስማታቸው ስለማይቀር ቢታገሱ መልካም እንደነበር አስተያየታቸውን ሰጥተውናል። በመርህ ደረጃ ሕግ ቶሎ ቶሎ መሻሻል የለበትም። ለረጅም ጊዜ ጸንቶ የመቆቱ ነገር አንዱ የጥሩነቱ መመዘኛ ስለሆነ፣ ሊሻሻል ከሚችል ጉዳይ ጋር የተገናኘን ቀድሞ አንስቶ ማሻሻሉ በቅርብ ጊዜ መልሶ እንዲሻሻል ያደርገዋል። ይሕ የሕግ ዘላቂነትን የሚቀንስ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት የመንግስት አካላት ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል። በአጭር ጊዜ ሊተኩ የሚችሉ ሕጎችን ማሻሻሉ ለአላስፈላጊ ወጪም እንደሚዳርግ የሕግ ባለሙያው ጠቅሰዋል።

ሕገ-መንግሥቱን ከማሻሻል አኳያ ኹለት መንገዶች አሉ ያሉን ሲሆን፣ አንደኛው የተወሰኑ አንቀፆችን ለማሻሻል ሲፈለግ የኹሉንም ክልሎች ይሁንታ የሚጠይቀው ነው። ሌላኛው ደግሞ በሕጉ የተጠቀሰው ኹለት ሦስተኛ ያህል የተወካዮች ምክርቤትና የፌደሬሽን ምክርቤት ድምፅ ከተገኘ የሚሻሻልበት አሰራር ነው። በዚህ መሠረት ከአንቀፅ 13 እስከ 44 ያሉት ምዕራፍ 3 ላይ የተጠቀሱትን የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አንቀፆች ለማሻሻል የኹሉም የክልል ምክር ቤቶች ይሁንታ ያስፈልጋል። ይህ ማለት የመገንጠል መብት የሚሰጠውን አንቀፅ 39 ለማሻሻል ግድ የኹሉም ክልሎች ይሁንታ ያስፈልጋል። በዚህ ምክንያት ይህን የመሳሰሉትን አንቀፆች ማሻሻልን በቀጣይ ዓመት መንግሥት የሚመሰርት ፓርቲ ሊያከናውነው አይችልም። ምክንያቱም በትግራይ ምርጫው ስላልተደረገ የክልሉን ምክር ቤት ይሁንታ ማግኘት አለመቻሉን የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል።

በተለያዩ ባለሥልጣናት ሕገ-መንግሥቱ እንደሚሻሻል ሲነገር ቢሰማም በሕጉ መሰረት ቢያንስ በቅርብ ጊዜ ሊሆን የማይችል ሀሳብ ነው። ክልሎች የተመሰረቱበትን አንቀፆች ማሻሻል ቢቻልም፣ ብዙዎች እንዲሻሻሉ የሚፈልጓቸውን አንቀፆች ለመንካት ግድ ትግራይ ምርጫ ተደርጎ አሸናፊው መታወቅና ምክር ቤቱ ይሁንታ መስጠት ይኖርበታል። ይህም ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ለማሻሻል የኹሉንም ምክር ቤት ይሁንታ የሚጠይቀውን ራሱን አንቀፅ 105ንም ለማሻሻልም፣ የኹሉም ክልሎችን ይሁንታ ስለሚፈልግና እርስ በርሱ ስለተቆላለፈ ማስተካከል ይከብዳል የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል በሕጉ መሰረት ለማሻሻል የማይቻል ከሆነ፣ ዋናው በዘላቂነት እስኪጸድቅ ለጊዜው አምሳያው መሸጋገሪያ ተዘጋጅቶ ነባሩን ማገድ ይቻላል የሚሉም አሉ። በአጠቃላይ የሕገ-መንግሥት መሻሻል ጉዳይ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com