የእለት ዜና

የኢትዮጵያውያን መከራ በሳዑዲ አረቢያ

Views: 44

በኢትዮጵያውያን ወደ አረብ አገራት የሚደረገው ጉዞ በብዙ ችግሮች እና ውጣ ውረዶች የተተበተበ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ብዙኃኑ ተሰዳጆች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግለሰባዊ የምጣኔ ሀብት ጫናን ለመቋቋም፣ ህልውና ለማስቀጠል የተሳሳተ የጉዞ መንገድን ሲመርጡም ይስተዋላል፡፡ ታዲያ ዓላማቸውን አንግበው ከአሰቡበት ለመድረስ በሚያደርጉት ሕገ-ወጥ ጉዞ የበረሀ ሲሳይ ሆኑ መባልን ማድመጥ ከተጀመረም አያሌ አመታት ነጉደዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሕጋዊ መንገድ ሄደውም ያሰቡትን ሳያሳኩ ቀርተው ለዓመታት በእስር ቆይተው ለእንግልት ሲዳረጉም ተስተውሏል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዚሁ ችግር ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ የአዲስ ማለዳው ወንድማገኝ ኃይሉ የችግሩን አሳሳቢነት በተመለከተ ስደተኞችን እና የሚመለከታቸውን ተቋማት አነጋግሮ በሀተታ ዘማለዳ በስፋት ተመልክቶታል፡፡

ኢትዮጵያውያን የመካከለኛው ምስራቅ አገራትን ጨምሮ በመላው ዓለም ተሰደው ይኖራሉ።ስደቱ አሁንም በሕጋዊ እና በሕገ ወጥ መንገድ ቀጥሏል። በተለይ በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች ለበርካታ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸው በየጊዜው እየተነገረ ቢሆንም ስደቱ ግን አሁንም አልቀነሰም። በተለይ ድንበር ተሻግሮ ወደ ተለያዩ አገራት የሚደረግ ፍልሰት መንገዱ እጅግ አደገኛ እና የሞት ጥላ ያጠላበት መሆኑ ቢነገርም፣ ብዙዎች ደፍረው እየተጓዙበትና ሕይወታቸውን እያጡበት እንደሆነ በየዜናዎቹ በየጊዜው እየሰማን ነው። የአገሪቱ ፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ሥራ አጥነት፣ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጨው የተዛባ መረጃ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ አገራት የሰው ኢኮኖሚያዊ አቅም ቶሎ ይለወጣል የሚለው አስተሳሰብብ የዜጎች መሰደድ እንዳይቆም የራሱን ሚና ተጫውቷል። ከዚህ ባሻገር ለስደት በዋናነት ከሚነሱ ምክንያቶች አንዱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ዕድገት ቢያሳይም፣ ከዚሁ ጋር የተመጣጠነ የሥራ ዕድል ፈጠራው እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ነው። በሌላም በኩል ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት በአደገኛ መንገድ የሚሰደዱ ወጣቶች፣ ከሥራ እጦት በተጨማሪ፣ በአገራቸው እንደ ኹለተኛ ዜጋ የመቆጠራቸው ሁነት ለስደት ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ። ወጣቶቹ በተሠማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ፍትሐዊ ውድድር አለመኖርም ከሚነሱ በርካታ የስደት ምክንያቶች ተጠቃሽ ነው።

አገር ለቀው በሚሄዱ ስደተኞች ላይ የሚደርሱ ኢ-ሰብዓዊ ጥቃቶችና ለጆሮ ሰቅጣጭ ዜናዎች መደመጥ ከጀመሩም ሰነባብቷል። የድረሱልን ጥሪ በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዘንድም በተደጋጋሚ ይሰማል። በተለይም ወጣት ኢትዮጵያውያን በሕገ-ወጥ መንገድ በሚደረግ የሰው ዝውውር በውኃ ጥም፣ በርሃብ፣ በአውሬ በመበላት፣ ኢ-ሰብዓዊ በሆኑ ሕገ-ወጥ የድንበር አሻጋሪዎች እጅ በመውደቅና በመደፈር፣ በሰው መገደል እና የሰውነት አካላት ሽያጪ በተሰማሩ ደላሎች፣ እንዲሁም በሌሎችም ወንጀለኞች እጅ በመውደቅ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸውም ይገኛል። በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ የአካል ጉድለት፣ ለአእምሮ መታወክ፣ ባስ ሲልም አንገታቸውን እስከመቀላት ደርሰዋል።

በርካታ ስደተኞች በመንገድ በሚያጋጥማቸው ፍጹም ኢ-ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ካሰቡበት ቦታ ሳይደርሱ ቀርተዋል። በተለይም ደግሞ በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰው ስቃይ እና ፈተና እጅጉን ይበረታል። በሕገ-ወጥ መንገድ ተጉዘው አረብ አገራትን መኖሪያቸው ያደረጉ ሴቶች እያሳለፉ ያሉትን ሁኔታ ሲናገሩ ሁሌም እንባቸው ይቀድማል። ምክንያቱም ቃላት ከሚገልጸው በለይ ዘግናኝ የሆነ መከራ እና ስቃይ ስለሚያሳልፉ ነው። ይህ በአንዲህ እንዳለ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት፣ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለአስከፊ ችግር ተጋልጠዋል።

ሰርቼ ያልፍልኛል፣ ከእኔም ተርፎ አቅመ ደካማ ቤተሰቦቼን እደግፋለሁ የሚል ተስፋን ሰንቀው በብዙ ውጣ ውረድ ወደሚመኙት አገር ቢደርሱም፣ የሚደርስባቸው የጉልበት ብዝበዛ ከሚያገኙት ጥሪት ጋር እንደማይነጻጸር አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻት በሳዑዲ አረቢያ የምትሠራ እና ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች ስደተኛ ተናግራለች። በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚፈልሱ ስደተኞች ሥራ ከጀመሩ በኋላ በአሰሪዎቻቸው አስገድዶ መደፈርና ግድያ ይፈጸምባቸዋል። ክብርን በሚነካ እና ሰብዕናቸውን በሚጎዳ ሁኔታ የጥቃት ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ እኔ የዐይን ምስክር ነኝ በማለት እንባ እየተናነቃት አስረድታናለች።

በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ ሳዑዲ የገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከአንድ ዓመት በላይ ወደ እስር ቤት በማቆየት፣ እህል እና ውኃ እንኳን በቅጡ ማግኘት ባለመቻላቸው ለአስከፊ ችግር ተዳርገዋል ብላናለች። ሳዑዲ አረቢያ ከተመለሱት መካከል ወጣት ተመስገን ታንቱ በበኩሉ በሪያድ የአንድ ዓመት ተኩል ቆይታ ዝርፊያ፣ እስር፣ ድብደባ እና ስቃይ ገጥሞታል። ከዚህ መከራ እና ስቃይ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ደርሶ ስለታደጋቸው ደስተኛ መሆኑን የገለጸው ወጣቱ፣ መንግሥት በዚያ በስቃይ ላይ የሚገኙ ሌሎች ዜጎችን እንዲመልስ ጠይቋል። በሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ደረጄ ታዬ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ የሄዱ ስደተኞችን የአገሪቱ መንግሥት እያስወጣ መሆኑን ነው።
ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ሳዑዲ አረቢያ ለግብጽ ወግና በመቆሟ ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ሳውዲ ግፍ፣ በደል፣ ስቃይ እና እንግልት እያደረሰች ያለችው ሲሉ ተደምጠዋል።በዚህ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ሁኔታ፣ በሕጋዊ መንገድ የሄዱትን እና የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውንም ጨምሮ ፈቃዳቸውን በመሰረዝ እና ውላቸውን በማቋረጥ፣ ሳዑዲ ዜጎቻችንን እያስወጣች እንደሆነም ደርሰንበታል ብለዋል ዳይሬክተሩ። ሕጋዊ ከሆኑት ውጪ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑት ተመላሾች በሕገ-ወጥ መንገድ ተሰደው የተመለሱ እነደሆኑ ገልጸዋል።

አክለውም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከሀምሳ ሺሕ በላይ ዜጎችን በሕጋዊ መንገድ ወደተለያዩ የአረብ አገራት አሰማርተናል ብለዋል። በተለይም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው መሰረት ማንኛው ዜጋ ወደ ተለያዩ አረብ አገራት ሂዶ መሥራት የሚፈልግ ከሆነ ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቀ፣ የቤት ሥራዎችን እንዴት መሥራት እንዳለበት በውል የሚያውቅ፣ ለዚህም ሥልጠና እና የተግባር ተኮር ፈተና ወስዶ ያለፈ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ከዚህ ውጪ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ሰዎች የበረሃ ሲሳይ ከመሆን ባለፈ በዚህ ፈታኝ ጉዞ ውስጥ እንደወጡ ይቀራሉ። ከሞት የተረፉትም ለዘረፋና ለብዝበዛ ይጋለጣሉ፤ ሴቶችና ሕጻናት ይደፈራሉ፤ ለወሲብ ንግድም ይጋለጣሉ፤ ሲሉ ዳይሬክተሩ የሕገ ወጥ ስደት አስከፊነትን ይገልጻሉ። ታዲያ የመንገዱን መከራ እንኳን ቢያለፉ በደረሱበት አገር ደግሞ ሌላ መከራ ይጠብቃቸዋል። ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የላቸውም፤ ለማግኘትም መንገዱ በጣም ጠባብ ይሆንባቸዋል ነው ያሉት። አሁን ላይ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት የመጡትን ጨምሮ፣ በተለይም የሳዑዲ ተመላሾችን ወደ ሥራ ለማሠማራት እንዲቻል የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ያተካተቱበት ቡድን ተቋቁሟል። በዚሁ መሰረት ግብረ-ኃይሉ ተመላሾች የመጡበትን አከባቢ ከክልሎች ጋር በመነጋር ከመለየት ጀምሮ የሥራ እድል እንዲያገኙ ሁኔታዎች የሚመቻች መሆኑን አስረድተዋል። ተመላሾቹ ራሳቸውን ከመለወጥ ባለፈ፣ ለአገር የሚጠቅም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት እንደሚሠራም አብራርተዋል። ተመላሾቹ ወደ ማሕበረሰባቸው እስኪመለሱ ድረስ ጊዜያዊ ድጋፍ ለማድረግ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል። ችግሩን ከመሰረቱ ለመግታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር እየሠራ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። አያይዘውም የሳዑዲን የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ሕግጋትን ተላልፈው በመገኘታቸው በስደተኞች ማቆያ ጣብያዎች ከአንድ ዓመት በላይ በእስር የቆዩ ዜጎች አሉ ብለዋል።

እነዚህ እስረኞች በሙሉ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከሳዑዲ የሚመለከተው ወገን ጋር በመነጋገር ብዛት ባላቸው በረራዎች ዜጎችን የመመለስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ደረጄ አብራርተዋል። 40 ሺሕ ዜጎችን ለመመለስ ከታቀደው ውስጥ ይህ ጽሁፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 19 ሺሕ ዜጎች ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከነዚህ ውስጥ 16 ሺሕ 631 የሚሆኑት ወንዶች፣3 ሺሕ 69 የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን አንስተዋል። ከፍተኛ ችግር ያሉባቸው፣ ማለትም የሥነ ልቦና፣ የአካል ጉዳት እና ሌሎች ችግሮች የገጠàቸው ካሉ ተለይተው፣ በአጋር ኢትዮጵያ በኩል እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል። ተመላሾችን ወደ ሥራ ለማሠማራት በየክልሉ ከሚገኙ የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ጋር በመተባበር እንደሚሠራም አመልክተዋል። ይህን ከማድረግ ባሻገር ወደየአካባቢዎቻቸው ሲመለሱ የትራንስፖርት እና የኪስ ገንዘብ እንደሚመቻችላቸው አንስተዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በርካታ ዜጎች በአገሪቱ እንደመኖራቸው፣ ኢትዮጵያውያን ላይ እንግልት እና ስቃይ እያደረሰባቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በአገሪቱ በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ ገብተው እየሠሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ከአገሪቱ እያስወጣ መሆኑንም ነው ያነሱት። በጉዳዩ ላይ ቃል አቀባዩ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዚህም ረገድ በጅዳ እና ሪያድ ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶች ተገኝቶ የሚሠራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሊፈጠር ከሚችለው ችግር ዜጎችን ለመታደግ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ወደ አገር የመመለስ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ነው የጠቆሙት። በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንግልት እና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ መንግሥት ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ ነው ብለዋል። የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በአገሪቷ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን እያስወጣ ያለው ከሕዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ ለግብጽ ውግንና ይዞ ነው ሲሉ ሌሎች ከላይ ያሚያነሱትን ምክንያት እንደሚጋሩ አምባሳደር ዲና አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዜጎቹ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሰነድ ማሳደስ ካልቻሉ ያላቸው ዕድል አገር መልቀቅ መሆኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ ወደ አገር ቤት ለመመለስም ከኤምባሲዎች የይለፍ ደብዳቤ ማግኘት አለባቸው ብለዋል። በዚያው የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን ፓስፖርትና ሌሎች ሰነዶችን እያደሰና የይለፍ ደብዳቤ በመስጠት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።ሆኖም በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን በአቅራቢያቸው የሚገኘውን ኤምባሲና የቆንፅላ ጽህፈት ቤት የሚያገኙት ችግር ሲያጋጥማቸው ብቻ በመሆኑ ለዜጎች ትክክለኛውን ጥበቃና ክትትል ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኗል ነው ያሉት።

በተለይም በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከየአካባቢው ማሕበረሰቦች ጋር በመሆን ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ መሥራቱን እንደሚቀጥል አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል። በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት የመመለስ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም አግባብነት ያላቸው የፌዴራል ተቋማት የተሳተፉበት ኮሚቴ ከተለያዩ አገራት የሚመለሱ በርካታ ዜጎችንም የመመለስ ሥራ እየሠሩ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም። በዚህም ረገድ፣ በሳዑዲ የሚገኙ ቀሪ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚቻልበት መንገድ ላይ በልዩ ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ተፈላጊው ሂደት ተጠናቆም እነዚህ ችግሮች በቅርቡ መፍትሄ የሚያገኙ ይሆናል ብለዋል። አምባሳደሩ በችግር ላይ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንና ጉዳዩን የሚያስተባብር ግብረ ኃይል በሳዑዲ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እስካሁን ወደ አገራቸው ከተመለሱት ዜጎች በተጨማሪ በየቀኑ ኹለት ሺሕ ዜጎችን ለመመለስ ውጥን መኖሩንም ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ የስደት ድርጅት (IOM) በሥሩ በተደራጀው የልማት ፈንድ (IOM Development Fund) በሚታገዘውና በኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን አስተዳደር ለማጠናከር እየተካሄደ ባለው ፕሮጀክት አማካይነት፣ ከኢትዮጵያ የሚደረግን ፍልሰት ሕጋዊነት እና ሥርዓት ባለው መንገድ ለመምራት፣ አሠራሩን ለመወሰንና ኢ- መደበኛ በሆነ መልኩ ወደ ሌሎች አገራት፣ በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ የሚደረጉ ፍልሰቶችን ለመግታት የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው። የዚህ ተግባር ግብ የመንግሥትንና በውጭ አገር ሥራ ስምሪት ጉዳይ አስተዳደር ውስጥ የተሰማሩ ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት አቅም ለመገንባት ያለመ ነው። ይህ ግብ ከሚሳካባቸው ስልቶች መካከል አንዱ በውጭ አገር ሥራ ስምሪት አመራር ላይ በፌደራልና በክልል መንግስታት አካላት ውስጥ ለሚሰሩ የተመረጡ ባለሙያዎች ሰፊ የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ነው ተብሏል። የስደተኞች ፍልሰት ጉዳይ ሲነሳ በተለይ በሳዑዲ አረቢያ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንደተስተዋለው አሊያም በሰሐራ በረሃ እንደተፈጠረው አይነት አንዳች ችግር ሲፈጠር መንግሥት ይተቻል፤ ይወቀሳል። መንግሥትም ትኩሳቱ ሲበረታ ችግሩን እፈታለሁ፤ ጥናት ሰርቻለሁ፤ ሕገ-ወጥ ደላሎችን እቀጣለሁ ሲል ቃል ይገባል። ይሁን እንጂ ይህን የሚያክል አገራዊ አጀንዳ ከምንጩ ማድረቅ የተሳነው ይመስላል። ይህ ሥር የሰደደው ችግርም እንዲህ በቀላሉ መንግሥት እየሰጠ ባለው ምላሽ ብቻ የሚፈታ አይመስልም። ይፈታ እንደሆነም የጊዜ ሚዛን ያሳየናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com