የእለት ዜና

ፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ማግስት

Views: 54

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ለማካሄድ መወሰኑን ተከትሎ ባሳለፍነው ሰኔ 14/2013 የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ አካሂዷል። የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ውጤትም በቦርዱ በኩል እየተገለጸ ይገኛል። በምርጫው ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችም በመጀመሪያው ዙር በተሳተፉባቸው አከባቢዎች ያገኙትን ውጤት በማወቅ ላይ ናቸው።

ሰኔ 14 በምርጫው የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ ያላቸውን ቅሬታና ትችት ከማቅረብ ባለፈ ወደፊት ስለሚከተሏቸው አቅጣጫቸው ጥቆማዎችን እየሰጡ ነው። በመጀመሪያው ዙር ምርጫ በርከት ያሉ ቅሬታዎች ያቀረቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምርጫው ችግሮች የተሞሉበት ነው የማለታቸውን ያህል በአንፃሩ ምርጫው በጥሩ ሁኔታ የተካሄደ የተሳካለት ምርጫ እንደነበር የሚገልጹም ፓርቲዎች አሉ።
በመጀመሪያው ዙር ምርጫ በርካታ ቅሬታዎች ካቀረቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) አንዱ ነው።

ኢዜማ ምርጫውን በተመለከት በሰጠው መግለጫ ሰኔ 14/2013 የተደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ ይፋ ባይሆንም፣ በብዙ ግልጽ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን ገልጿል። ኢዜማ በምርጫው ላይ ከ400 በላይ ቅሬታዎች እንዳሉት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ዕለት በርካታ እንቅፋቶች እንደገጠሙት አንስቷል።

ኢዜማ በገጠሙት ችግሮች መነሻነት በምርጫው ማግስት ለቀጣይ የኢዜማ መዋቅር አደረጃጀት ለፓርቲው ደጋፊዎች፣ አባላትና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ዋና ዋና ያላቸውን አቅጣጫዎች አሳውቋል። ከነዚህም መካከል በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትና በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቃቸው በርካታ ተግዳሮቶችን ቦርዱ በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት እንደሚወስደው መግለጹ የሚታወስ ነው።

በምርጫ 2013 አጠቃላይ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ የሚያስተባብር የምርጫ ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ኮሚቴ ከዓመት በፊት አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ኢዜማ ጠቁሟል። በዚህም ኮሚቴ በኩል አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ከሚዘጋጀው የግምገማ አጠቃላይ ሪፖርት እና በድርጅት በኩል፣ በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተቋቋመ ቡድንና ከፓርቲው ውጪ በተመረጡ ገለልተኛ አካላት ከሚቀርበው ግምገማ ተነስቶ አጠቃላይ ሁኔታውን አገልጻለሁ ብሏል።

ኢዜማ በምርጫው የገጠሙትን ችግሮች እልባት ከማሰጠት ባሻገር በምርጫው ማግስት የወደፊት አቅጣጫውንም የጠቆመ ሀሳብ በመግለጨው ላይ አካቷል። “ኢትዮጵያ በታሪኳ በተለያየ የመንግሥት ቅርጽና የፖለቲካ ፍልስፍና በየጊዜው ሥልጣን ላይ በወጡ ኃይሎች ስትመራ መቆየቷ ይታወቃል። ላለፉት 30 ዓመታት እስከ 6ኛው ዙር ምርጫ ድረስ በምርጫ ብቻ ሥልጣን ለመያዝ የተሞከረው ሂደት ተስፋ ሰጪ ባይሆንም ዜጎች የምርጫ ተሳትፎ ማድረጋቸው አንድ ጥሩ እርምጃ ነው ሊባል ይችላል” ብሏል ፓርቲው።

ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ያለውና ከምርጫ በኋላም ቢሆን ሊኖር የሚገባው ነው ያለው ኢዜማ፣ በምርጫው ሂደት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በሕግ አግባብ እየጠየቀ ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የድርጅቱን መዋቅር ይበልጥ ለማጠናከር ወደ ሥራ መገባቱን አሳውቋል። የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በምርጫ ሂደት የተገኘውን ውጤት፣ ልምድ፣ የሰው ኃይል፣ ልዩ ልዩ ግብዓቶች እና ወዘተ. የመሳሰሉትን ጉዳዮች ፓርቲውን ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀምና ድርጅቱን በጥንካሬ ለመምራት በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ብርቱ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና በቀጣይ ለሚያጋጥሙ አገራዊ ጉዳዮችና ሰላማዊ ለሆኑ የትግል እንቅስቃሴዎች እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል።

ሌላኛው፣ ገና በቅድመ ምርጫ ወቅት ምርጫው ከደረጃ በታች እንደሆና ሂደቱ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ሲገልጽ የቆየው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ዳልደራስ) ነው። ባልደራስ በምርጫው ጉዳይ ላይ ሰኔ 29/2013 ባወጣው መግለጫ በሰኔ 14/2013 የተደረገው 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተመለከተ መረጃዎችን በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የምርጫ ክልሎች በሙሉ በማሰባሰብ አጠናክሮ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። በተጨማሪም፣ በድምጽ አሰጣጡ እና ቆጠራው የነበሩ ችግሮችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል።

ባልደራስ በምርጫው ማግስት በድምጽ መስጫ ቀን አጋጠሙኝ ካላቸው ችግሮች በተጨማሪ፣ በድምጽ ውጤት መዘግየት ቅሬታ እንዳለው ገልጿል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/11 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤትን ይፋ ከማድረጉ በፊት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ውጤቱን ከመግለጽ እንዲቆጠቡ የሚከለክል ሕጋዊ ክልከላ ጥሏል።

የአዲስ አበባ ከተማን ውጤት አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ለሕዝብ ይፋ ሳያደርግ ጊዜ እየወሰደ ነው ያለው ባልደራስ፣ በፓርቲዎች የቀረቡ ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው፣ ቦርዱ ውጤቱን ያፋ ሳያደርግ በተድበሰበሰ ሁኔታ መቆየቱ አላስፈላጊ ለሆኑ እንቅስቃሴዎች በር የሚከፍት እንደሆነ ጠቁሟል። በመሆኑም “ብርቱካን ሚደቅሳ የአዲስ አበባን ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ለመራጩ ሕዝብ ይፋ ያድርጉ” ሲል ጥሪውን አቀርባል።

ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ ጊዜ አሁንም መውሰዱን የሚቀጥል ከሆነ፣ ባልደራስ በእጁ ያለውን የጥናት ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እና በቀጣይ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት የሚገደድ ይሆናል። ፓርቲው በምርጫ ማግስት የወደፊት አቅጣጫውን በሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደሚቀጥል ጠቁሟል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሰኔ 28/2013 ባወጣው መግለጫ፣ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በምርጫው ሂደት የተፈጸሙትን አበይት የምርጫ ጥሰቶች በማሰባሰብና በዝርዝር ቅሬታዎችን በመሰነድ በሕግ አግባብ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቅረቡን አስታውቋል።

ፓርቲው የምርጫ ቦርድ ከተጣለበት ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት፣ከሰው ኃይል፣ ከፋይናንስ፣ ከተሞክሮና ከሎጂስቲክ አቅም አኳያ ውሱንነት ቢታይበትም በአጠቃላይ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ አንጻራዊ አዎንታዊነት እንዳሳየ እናምናለን ብሏል። በቦርዱ የበላይ አመራር የታየው የገለልተኝነት፣ ግልጽነትና ፍትሐዊነት መንፈስ እንደ ተቋም የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም አብን ገልጿል።

በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተግዳሮቶች እንደገጠሙት የገለጸው አብን፣ ሰኔ 14/2013 በተካሄደው የምርጫ ሂደት የታዩ ክፍተቶችን ከምርጫ ውጤት አኳያ የሚመዘኑ ከሆነ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የሃሳብ ብዝኀነት የማያመለክት መሆኑን ጠቁሟል።

አብን እንደ ድርጅት በምርጫ በመሳተፉ አንዳንድ ተስፋ ሰጪሁኔታዎችን መገንዘቡን የጠቆመ ሲሆን፣ የሕዝብ እውነተኛ ወኪል መሆኑን መራጩ ሕዝብ የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁሞ በሰጠው የመተማመኛ ድምጽ በቂ ማረጋገጫ እንዳገኘ ጠቁሟል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የምርጫው ሂደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረለትም አመላክቷል።

በመሆኑም በቀጣይም ከሂደቱ ያገኛቸውን ተመክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካችን ሁነኛ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል አብን አረጋግጧል። የመራጩ ድምጽ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ሕጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የመራጩን ሕዝብ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል አብን በምርጫው ማግስት ያለውን አቋም አመላክቷል።

እስካሁን ድረስ በምርጫ ማግስት ሀሳብ የሰጡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥውን ፓርቲ ብልጽግናን ጨምሮ የምርጫውን ውጤት ተቀብለው ቀጣይ ሰላማዊ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com