የእለት ዜና

በሰበታ ከተማ ከባለይዞታዎች መሬት የገዙ ሰዎች በተደራጁ አካላት ለእንግልት እየተዳረጉ ነው

ጉዳዩ ለሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል ተብሏል

በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ ከባለይዞታዎች መሬት የገዙ ሰዎች በተደራጁ አካላት ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ እየተገደዱ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። በሰበታ ከተማ ከግል ባለይዞታዎች በሕጋዊ አካሄድ ቦታ የሚገዙ ሰዎች በከተማው በተደራጁ አካላት ለተጨማሪ ክፍያና እንግልት እየተዳረጉ ቢሆንም ችግሩን የሚያስቆም አካል እንዳላገኙ ጠቁመዋል። በሕጋዊ መንገድ ከባለይዞታዎች ቦታ የገዙ ግለሰቦች “በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጁና የታጠቁ ” ናቸው ያሏቸው አካላት፣ ቤት ለመሥራትና ለማጠር ሲንቀሳቀሱ “ብር ካልከፈላችሁን ቤት አትሠሩም” በማለት አስገድደው ብር እያስከፈሉን ነው ብለዋል።

ጉዳዩን ለአዲስ ማለዳ ያስረዱ ቅሬታ አቅራቢዎች እንዳሉት ከሆነ፣ ከባለይዞታ ቦታ ሲገዙ የሰበታ ከተማ አሥተዳደር ጉዳዩን የሚያውቅ ቢሆንም፣ በተደራጁ አካላት ብር እንዲከፍሉ እንደሚገደዱና ማስፈራሪያ ጭምር እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ቢገልጹም ችግሩ ሊቀረፍ አለመቻሉን ነው።

በሰበታ ከተማ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ኗሪዎች፣ “በሰበታ ከተማ መንግሥት ማን እንደሆነ አይታወቅም። በከተማዋ ኗሪዎች ላይ የሚፈጸመው ተግባር ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱት አካላት መንግሥት እንዲመስሉ አድርጓል” ሲሉ ገልጸዋል። የከተማዋ ኗሪዎች ከባለይዞታዎች መንግሥት በሚያውቀው ሕጋዊ ውል ቦታ ከገዙ በኋላ ነው የተደራጁ ናቸው የተባሉት አካላት ሕጋዊ አይደላችሁም፣ብር ካልከፈላችሁን ቤት መሥራት አትችሉም በማለት ክፍያ እንዲከፈል የሚያደርጉት ተብሏል።

ለተደራጁት አካላት ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀው የማይከፍሉ ገዥዎች ካሉ ድብደባና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ተግልጿል። አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሰማችው፣ በዚሁ ጉዳይ የሰዎች ሕይወት እየጠፋ እንደሆነ ነው። ለአብነትም ባሳለፍነው ሰኔ 28/2013 በሰበታ ከተማ ቀበሌ ሦስት ዲያስፖራ በሚባል አካባቢ ከግለሰቦች የቤት መሥሪያ ቦታ የገዙ ሰዎች፣ ቤት ለመሥራት ሲንቀሳቀሱ የተደራጁ አካላት ድብደባና እንግልት መፈጸማቸው ተሰምቷል። በዕለቱ በግዥ የራሳቸው ባደረጉት ቦታ ላይ ቤት ለመሥራት ሲንቀሳቀሱ የተደራጁ ናቸው በተባሉት ቡድኖች ድብደባና እንግልት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አለማየሁ ቱሳ የተባሉ ግለሰብ ከነባለቤታቸው ይገኙበታል።

ግለሰቡ የተጠየቁትን ብር አልከፍልም በማለታቸው የተደራጁት አካላት ያለ ማንም ከልካይ ድብደባና እንግልት ሲያደርሱባቸው የተመለከተው የ18 ዓመት ልጇቸው በብስጭት ውኃ ውስጥ ገብቶ መሞቱ ነው የተገለጸው። àቹ ወጣት ሄኖክ አለማየሁ ሲባል በቅርቡ የ8ኛ ክፍል ፈተና አጠናቆ ወደሚቀጥለው የትምህርት ክፍል ለመሸጋጋር ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ነበር።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ኗሪዎች እንደሚሉት፣ በሰበታ ከተማ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በ2012 ስምንት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። እንደ ኗሪዎቹ አገላለጽ ችግሩን ለከተማ አሥተዳደሩ በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም እስካሁን መፍትሔ ባለማግኘቱ ለብዙዎች አሳሳቢ ሆኗል። በከተማዋ በሕገወጥ መንገድ ተደራጅው ኗሪዎችን የሚያስቸግሩ አካላት፣ ከንብረት ኪሳራ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የደረሰ ጉዳት እያስከተሉ በመሆኑ፣ ኗሪዎቹ ጉዳዩን ወደ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ለማድረስ እንደሚፈልጉ ተመላክቷል።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ከቅሬታ አቅራቢዎች ከሰማች በኋላ ከሰበታ ከተማ አሥተዳደር ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ብትሞክርም ሊሳካ አልቻለም።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!