የእለት ዜና

አክብሩን ለማለት እንዳንፈራ የሚያስከብረንን እንሥራ!

Views: 30

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው እውቅናና ክብር እያደር እያሽቆለቆለ መምጣቱ ይነገራል። አገሪቱ ብቻ ሳትሆን ሕዝቦቿም በየሄዱበት የነበራቸው ተቀባይነት እየወረደ አሁን መጨረሻ ሊባል በሚችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና መንግሥቱም ሆነ ሕዝብ እንደተናቀ የሚያመላክቱ በርካታ ክስተቶች እየተስተዋሉ ይገኛል። በተለይ ከአፄ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ማብቂያ ጊዜ ጀምሮ በኃያላኑ ዐይን የነበረን እይታ እየሟሸሸ፣ የሚሰማንም ጆሮ እያጣን የኋልዮሽ እየተጓዝን እንገኛለን። ።

በአሁኑ ዘመን እንዳለው ዘመናዊ መገናኛ ሳይኖር፣ እንዲሁም የተደራጀ፣ በየአገራቱ የተሰራጨ ኤምባሲና ቆንስላ ሳይመሰረት፣ ደጃቸውንም ሳንጠና እዚሁ ባለንበት የምንፈልገውን ሰምተው በአንጻራዊነት ይመልሱልን ነበር። እንዳሁኑ በግላጭ ጠላት ብለን የፈረጅናቸውን ለመደገፍ ይቅርና ለመወደድና ከሌላው በተሸለ እንድናቀርባቸው አገራት ለዘመናት ይለማመጡንና ይማጸኑን የነበረው የሩቅ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።

ደርግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበሩት ምዕራባውያን ፊታቸውን ስላዞሩበት ወዳጅ ፍለጋ ወደ ምስራቁ ዓለም ለማማተር ተገዶ ነበር። የኮሚኒስቱ ጎራ አቅሙ እየተዳከመ፣ ድጋፉም እየቀነሰ ሲመጣ፣ ቀዝቃዛው ጦርነት በረዶ ሰርቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ያገኘው የነበረውን ድጋፍ አድርቆበታል። በዚህ ምክንያት ደርግ ሲመራው የነበረው መንግሥት እየተዳከመ፣ ምዕራባውያኑ የሚያስታጥቋቸው ሸማቂዎች ቀስ በቀስ መንግሥት ለመሆን በቅተዋል።

የምዕራባውያኑ የማደጎ ልጅ የነበረው ህወሓት ሥልጣን ተቆጣጥሮ በነበረበት ዘመን፣ ዝለል ሲባል እስከየት እያለ ድንበር አልፎ ሱማሊያ ገብቶ እስኪያርፍ ድረስ የእነሱን ጉዳይ ሲያስፈፅም ኖሯል። ቀስ በቀስ ግን ከአየር ንብረት መለወጥ ጋር በተገናኘ የአፍሪካ አገራትን አድናቆት እያገኘ ሲመጣ የልብ ልብ ተሰምቶት አድራጊ ፈጣሪዎቹን እያሳጣ በመምጣቱ ግንኙነቱ ሻክሮ ነበር። በተለይ የቴሌን ጨረታ የመሳሰሉ ግዙፍ የመንግሥት ወጪዎችን ለቻይና መስጠት ሲጀምር፣ በጥርጣሬ ያዩት የነበሩትን ትተው ሴራ መሸረብ መጀመራቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ይናገራሉ። በኋላም ‹‹ተቃዋሚ የለብኝም፤ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ›› ብሎ ጠላት እንደማያስነሱበት ተማምኖ ሲሳለቅ፣ መልምለው ያስቀመጧቸው በየቦታው እንዲነሱበት ማድረጋቸው ይነገራል። የሕዝብ አመፅም ሲበረታ የመረጡት ሰው ወደፊት እንዲመጣና ያልፈለጉት ሰው ስም እንዲደበዝዝ በአካል በመምጣት ጭምር ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንና ጥቁሮች ያላቸውን ንቀት በገሀድ አሳይተዋል። ለዚህ ሁሉ ክብር ማጣት የዳረገን ዋናው መከፋፈላችን እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ለውጥ መጣ ተብሎ የተለያዩ ነገሮች እንዲለወጡ ቢጠየቅም፣ መጀመሪያ ግን ምዕራባውያኑን ይገድቡ የነበሩ የቀድሞ ሕጎች ተሸረው ቅድሚያ እንዲስተካከሉ ተደረገ። ሕዝብ ተስማምቶ መታየቱ ስላላስደሰታቸው ግፍ ሲሰሩ የነበሩ የቀድሞ መሪዎች እንዳይያዙ ብዙ ጥረዋል። አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁም በኋላ በሕጋቸው በማይፈቀድ መልኩ የትም ተደርጎ የማያውቀውን ድርድር አድርጉ የሚል ሀሳብ ይዘው እጅ ሊጠመዝዙ ሲሞክሩ ቆይተዋል። መንግሥት አንዴ ከተጠመዘዘ ማስመለስ የማይችለውን ክብር ከማጣቱ በላይ፣ በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እንዲጠፋና ለበለጠ ታዛዥነት የሚያመቻቹበት ሂደት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል። ምዕራባውያኑ የእኛ መብት አለመከበር ወይም በአፍሪካውያን ላይ የሚደርስ ግፍ አሳስቧቸው እንደማያውቅ፣ የቱን ጉዳይ መርጠው የት የቱን እንደሚተዉት ማስተዋሉ በቂ ነው።

ኢትዮጵያ ከምዕራቡም ሆነ ምስራቁ ዓለም ጋር ወዳጅ የነበረችባቸው ጊዜያት ከሚለያዩበት ይልቅ የሚያመሳስላቸው እንደሚበዛ የሚናገሩ አሉ። ማንም አገር ለራሱ ጥቅም እንጂ የሚገብርለትን ሕዝብ ገንዘብ ለሌላ አገር ወስዶ ምንም ነገር የማድረግ ፍላጎት እንደሌለው ልንረዳ ይገባል። የኃያላን አገራት ወዳጅ መሆን አንዱ አንዱን የሚያጠቃበት መሳሪያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም። ሕዝብ ደግሞ እንደጥይት እየተተኮሰ ቀላሀ ሆኖ ከመውደቅ ወይም አረር ሆኖ ወንድሙን ከመግደል ያለፈ ሚና እንደማይኖረው መረዳት አለብን። መንግሥትም ቢሆን ጊዜያዊ ድልን ለማግኘት አሊያም ከሽንፈት ለመዳን ሲል ማንም ተቀናቃኝ የሆነ ኃይልን ወዳጅ ባያደርግ ይመረጣል። እንደ ስዊዘርላንድ ገለልተኛ ሆኖ መቆም ጽንፍ ላይ ሆኖ ለሚናጥ ዓለም ብቸኛው ረግቶ ከወጀቡ የማምለጫ መንገድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የማንንም ማስፈራሪያ ተከትሎም ሆነ ጥቅም ይገኝበታል በሚል ዘላቂ ጠላት ማፍራት እንደሌለብን፣ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈን መስጠት እንደማይገባን አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

ከዓባይ ግድብ ጋር በተገናኘ ታሪካዊ ጠላታችን እየተባለች ከልጅነታችን ጀምሮ የምትነገረን ግብጽ ጋር ምዕራባውያኑ የተለጠፉበት ምክንያት ሁሉም እንዲረዳው ማድረግ ያስፈልጋል። “እሾህን በእሾህ” እንደሚባለው በቅርብ ያለን ተቀናቃኝ ሩቅ ባለ ባላጋራ ድል ማድረግ ወይም ማስወገድ በሚለው መርህ እኛ ከምንጠቀመው ይልቅ የእኛን መፍረስ የሚፈልጉ አካላት አብረው ለመስራት ይቀላቸዋል። የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚባለው ዘመን አልፎ ኹለት ጠላቶቻቸውን እኩል የሚያስታጥቁበትና ለጦርነት የሚያሰልፉበት ዘመን ላይ ስለምንገኝ ቆም ብለን ማሰብ ይጠበቅብናል። በዳይን መቀያየር መበደላችንን ስለማያስቀረው፣ የተበደሉን በመቅረብ መረዳዳቱ እንደሚሻል ይታመናል። ግድቡን ገንብተን መጠቀማችን እንደማይቀር ሲረዱት ለማስፈራራትም ሆነ እጅን አዙሮ ለማሰር እንደማይችሉ የተገኘውን አጋጣሚ እየተጠቀምን ማሳወቅ እንዳለብን የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።

ዲፕሎማሲን በተመለከተ ዲፕሎማቶቻችንን ለእኛ እንዲሰሩልንና ሕዝባችንን በያለበት እንዲያገለግሉልን እንጂ አምባሳደርነት የባለሥልጣናት ጡረታ መውጫ ወይም ማግለያ መሆኑ መቆም አለበት። የሰው ኃይሉን መቀነሱም ሆነ ቁጥሩን ዝቅ ማድረጉ ከሚያስከትለው የወጪ ቅነሳ ይልቅ ትርፋማ ሊያረጉን የሚችሉበት ዕድል እንዲያገኙ ሊመቻች በተገባ ነበር። ቢያንስ የማይቀነሱት ለወደፊት የሚበጀንን ቀድመው መከወን እንደሚጠበቅባቸው አመላካች ደውል በመሆኑ፣ ካሁኑ የተላኩበትን ዓላማ ለማሳካት ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በዲፕሎማሲ ረገድ እንዲህ በተበለጥንበትና የጠላት ፕሮፓጋንዳቸው አንገት ባስደፋበት ወቅት ብቁ የሰው ኃይልን መጨመር ሲገባ መቀነሱ ላያስማማ ይችላል። ከመንግሥት የቀረበላቸውን የተመለሱ ጥሪ ባለመቀበል ይራዘምልን ያሉት ዲፕሎማቶቻችንን በደፈናው ጥያቄያችሁ ተቀባይነታ አላገኘም ከማለት ምክንያታቸውን ጠይቆ እንደልዩነታቸው ማስተናገድ ይገባ ነበር። ከብዛት ጥራት ተብሎ ያሉት በተገቢው መጠን ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ከተባለ እሰየው የሚያስብል ቢሆንም፣ ጥሩውን መጨመርም መዘንጋት የለበትም። ይልቁኑ ለሌላ የሚያገለግሉ፣ ያለአግባብ ቅንጡ ሕይወትን የሚመሩ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል።

ለሥራ ብለው ወደ አረብ አገራት የሄዱ ኢትዮጵያውያንም የመናቃችን መገለጫ የሆነ መከራ እየደረሰባቸው ይገኛል። “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንደሚባለው፣ የሌላ አገራት ሕገ-ወጥ ስደተኛ ሳይነኩ ኢትዮጵያውኑን ለይተው መቀመጫ አሳጥተዋቸዋል። እስር ቤታቸው ኢትዮጵያ በረሃ ውስጥ ያለ እስኪመስል ለይተው የፖለቲካ ቁማር መብያ ሊያደርጓቸው እንደዕቃ ቆጥረዋቸዋል። ሕፃን ልጅ ከተኳረፉት ጎረቤት ቤት እየሄደ እንደሚያሳጣው፣ ኢትዮጵያውያኑንም ችግር መከራውን እያስረሳቸው የሞት መንገድን አልፈው አሁንም ወደ ስደቱ ይተማሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ ወጪ እያወጣ ለመመለስና ክብራቸውን ለማስጠበቅ ደፋቀና ቢልም፣ አሁንም ከጉያው እያመለጡ የሚሄዱትን ሁኔታውን ለማሳወቅና ለማሳመን አልቻለም።

አገርም ሆነ ሰው አክብሩኝ ስላለ ብቻ አይከበርም። ሥራው ካላስከበረው በስተቀር ስለተናገረ ወይም እሱም በተራው ስለናቀና አጸፋውን ስለመለሰ ክብሩ አይመለስለትም። ክብር የሚገኘው እንዲያከብር የሚፈለገው አካል ቦታ የሚሰጠውን ነገር ሲይዙ ወይም ሲያደርጉ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይመሰክራሉ። ከሰው ሰው እንደአመለካከቱ ሐሳቡ ቢለያይም፣ ማክበር ያልፈለገን አካል ምንም ቢያደርጉ ከንቀቱ ስለማይወጣ እሱን መሥፈርት ከማድረግ ተላቆ ራስን ወደ ማክበር መሸጋገሩ ይበጃል። ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ማንም እንደማይቀበለው፣ መጀመሪያ እርስበርሳችን መከባበርና ለራሳችን ያለንን ግምት ከፍ ማድረግ እንዳለብን አዲስ ማለዳ ማስታወስ ትፈልጋለች። ቁጭ ብለን የሰቀልነው ቁመን ማውረድ እንዳይቸግረን፣ ከአወቅኩሽ ናቅኩሽ አስተሳሰብ ወጥተን ማክበር የሚገባንን ስናከብር እንደምንከበር ልንገነዘብ ይገባል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com