የእለት ዜና

በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ አርሶ አደሮች በተደራጁ ሽፍቶች ዘረፋ እየተፈጸመባቸው ነው

Views: 193

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ሸኮ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች በተደራጁ ሽፍቶች ዘረፋ እና ድብደባ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። የተደራጁ ሽፍቶች ናቸው የተባሉት አካላት ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 26/2013 ብቻ ከ10 በላይ ከሆኑ መኪኖች የተጫነ ዕቃ መዝረፋቸውን የዘረፋው ሰለባዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ዘረፋ የተፈጸመባቸው መኪኖች የጫኑት ዕቃ ወደ ገበያ የሚጓጓዝ አርሶ አድሮች ንብረት መሆኑ ተመላክቷል።

በሸኮ ዞን ከፍተኛ ዘረፋ የሚፈጸመው ሰንቃ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎች፣ የተደራጁ ሽፍቶች በአካባቢው እየተዘዋወሩ በሚፈጽሙት ዘረፋና ድብደባ አርሶ አድሩ ተንቀሳቅሶ የእርሻ ሥራ ለመከወን እንዲቸገር አድርጓል። የተደራጁ ሽፍቶች ናቸው የተባሉት አካላት በተለይ በሰንቃ ቀበሌ ያለማንም ከልካይ ቀን በቀን እየተንቀሳቀሱ በግልጽ ዘረፋ እየፈጸሙ ነውም ተብሏል።

የአካባቢውን አርሶ አደሮች ያስመረሩት የተደራጁ ሽፍቶች የተባሉት አካላት የሚፈፅሙት ዘረፋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንና መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ በተደጋጋሚ በጽሑፍና በቃል ነዋሪዎቹ ቢያሳውቁም፣ ጉዳዩን ተመልክቶ መፍትሔ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ የመንግሥት አካል እስካሁን እንደሌለ ተናግረዋል። ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ የአካባቢው አርሶ አደሮች እንደሚሉት ከሆነ ችግሩ በተደጋጋሚ የቀረበላቸው የወረዳና የዞን አመራሮች ቅሬታ ተቀብለው ለማስተናገድ እንኳን ፈቃደኛ አይደሉም።

በሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ በተለይም የሰንቃ ቀበሌ አርሶ አደሮች ለኹለት ዓመት የዘለቀ ከፍተኛ ችግር እንዳሳለፉ ጠቁመዋል። በኹለት ዓመት ውስጥ በነበረው የጸጥታ ችግር ሞት፣ ድብደባ፣ የቤትና ንብረት ቃጠሎ እንዲሁም መፈናቀሎች እንደነበሩ አርሶ አደሮቹ አስታውሰዋል። ይህንኑ ችግር ምክንያት በማድረግና በቀበሌው ከፍተኛ ችግር መኖሩን በመገንዘብ የክልል ልዩ ኃይልና መከላከያ በአካባቢው ጸጥታ ለማስከበር ተሰማርቶ እንደነበር ነው አርሶ አደሮች የሚገልጹት።

የነበረውን የጸጥታ ችግር መሰረት አድረጎ በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረው ጸጥታ አስከባሪ ልዩ ኃይልና መከላከያ ከግንቦት 2013 አጋማሽ በኋላ አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ዘረፋዎችና ድብደባዎች እንደተባባሱ ተነግሯል። በጸጥታ ኃይሉ መኖር ምክንያት ቆሞ የነበረውን የወንጀል ድርጊትን በማሰብ የጸጥታ አስከባሪው ከአከባቢው ከወጣ በኋላ ዘረፋዎችና ድብደባዎች እየተባባሱ መሆኑን ገልጸው፣ ጸጥታ አስከባሪ ወደ አከባቢው ተመልሶ እንዲገባ ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረው ጸጥታ አስከባሪ ልዩ ኃይልና መከላከያ መውጣቱን ተከትሎ በአርሶ አደሮች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘረፋና ደብደባ የዞኑ አስተዳደር እያወቀ ምላሽ መስጠት ተስኖታል ተብሏል። ይህንኑ ተከትሎ ከዚህ ቀደም ተፈጥሮ ኗሪዎቹን ለኹለት ዓመታት እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸው ግድያና መፈናቀል በድጋሚ እንዳይከሰት ስጋት አላቸው። አሁን ላይ የሚታዩት የዘረፋና የደብደባ ተግባራት አዝማሚያቸው ወደ ግድያና መፈናቀል እንዳያመሩ እየሰጋን ነው ብለዋል አርሶ አደሮቹ።

ችግሩ የተፈጠረበት አካባቢ የቡናና የበቆሎ ምርት በብዛት የሚመረትበት መሆኑን የጠቆሙት አርሶ አደሮቹ፣ አሁን ላይ ባለው የዘረፋና ድብደባ ተግባር ወደ ማሳ ተሰማርተው የግብርና ሥራቸውን መከወን እንዳልቻሉ ጠቁመዋል። በተለይ በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ ዋናውን የቡና ሥራ የሚሠራበት ጊዜ ቢሆንም፣ የተደራጁ ናቸው የተባሉ ሽፍቶች በቡና ጫካ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ በቡና ማሳ መሰማራት አልቻልንም ብለዋል።

በመሆኑም የዞኑም ይሁን የክልሉ መንግሥት ችግራቸውን ተረድቶ የጸጥታ አካላትን ወደ አካባቢው በማሰማራት የግብርና ሥራቸወን ከስጋት ነጻ ሆነው እንዲከውኑ ጠይቀዋል። ከዚህም በላይ ጉዳዩ ወደ ግጭትና መፈናቀል እንዳያድግ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸውና ጉዳዩም ትኩረት እንደሚሻ አርሶ አደሮቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com