የሕወሓት አኩራፊዎች፦ አዳዲሶቹ የትግራይ ተቃዋሚዎች ምን ይዘው መጡ?

0
981
  • የትግራይ ሪፐብሊክ
  • ታላቋ ትግራይ
  • ኤርትራና ትግራይን ማቀራረብ

ሕወሓት በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ውስጥ ያለውን ተፅዕኖ በሕዝባዊ ተቃውሞ እና በኢሕአዴግ የውስጥ ለውስጥ ፖለቲካ ከተነጠቀ በኋላ አመራሮቹ በክልሉ ፖለቲካ ተወስነው መቆየታቸው ይስተዋላል። ይህ በእንዲህ እያለ ኹለት የፖለቲካ ድርጅቶች ምሥረታ ላይ መሆናቸውን አሳውቀዋል። ኤፍሬም ተፈራ የፓርቲዎቹን መሥራቾች በማግኘት ዓላማቸውን እና ከሕወሓት የሚለዩበት አቋም ምን እንደሆነ በመጠየቅ ዝርዝሩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል።

በትግራይ የተቃውሞ ፖለቲካ ረድፍ ለረዥም ጊዜ ከሚታወቀው ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ (ዓረና) በተጨማሪ፣ ሌሎች አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በመግለጫቸው ካሳወቁ ኹለት ሳምንታት አልፏቸዋል። ኹለቱ አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የፓርቲ ምሥረታ መጀመራቸውን አሳውቀው፥ ለሒደቱ ድጋፍ ደብዳቤ ከቦርዱ ወስደዋል።

ይሁን እንጂ የአዲሶቹ ፓርቲዎች መነሻ አሳብና በመግለጫቸው የሚተነትኗቸው ርዕሰ ጉዳዮች፣ ከህውሓት ፕሮግራምና ዓላማ ብዙም ልዩነት የሌላቸው ናቸው የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዘርባቸው ይደመጣል። የ“ታላቋ ትግራይ”ን ግብ በማንገብና በማቀንቀን በኩል፣ እንዲሁም ትግራይን የሥልጣኔ መነሻና ምንጭ አድርጎ በማየቱ ዙሪያ ያላቸው አመለካከትና እምነት አንድ መሆን፣ በአንዳንድ ፖለቲከኞች ዘንድ “ሕወሓት የፈጠራቸው” የሚል ሥም ሲያሰጣቸው፥ በሌሎች ደግሞ “ታላቋን ትግራይ” ለመገንጠል የመጡ የሚል ሥም ተሰጥቷቸዋል። ከኤርትራ ጋር ዳግም እንዲፈጠር የሚፈልጉት ግንኙነትና በምሥራቅ አፍሪካ የትግርኛ ተናጋሪዎችን መስተጋብር ለማጠናከር ለመሥራት ማሰባቸውም ይነገራል፤ ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡንም ወደነሱ ጎራ ብለን በሚነሱት ጥያቄዎች ዙሪያና በሌሎችም አጀንዳዎች ላይ አዲስ ማለዳ አነጋግራቸዋለች።

የፓርቲዎቹ መመሥረት እንደምታ
ለአራት ዓመታት ያኽል ውስጥ ለውስጥ ሲደራጅና ራሱን የቻለ ኃይል ሆኖ ለመውጣት የተመቻቸ ጊዜ ሲጠብቅ የነበረው “ሣልሳይ ወያነ ትግራይ” የወጣት ምሁራን ስብስብ መሆኑን ከፓርቲው መሥራቾች አንዱ ከሆኑት ኀይሉ ከበደ ሰምተናል። በትግራይ ክልል በቅርቡ የተመሠረተው ፓርቲው፣ በመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫው ተፎካካሪ ፓርቲው ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም እንደሚሠራ አመላክቷል። ፓርቲው ሶሻል ዴሞክራሲ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተልም በመግለጫው አንስቷል።
ሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ይዞ የሚንቀሳቀስ ብሔረተኛ ፓርቲ እንደሚሆን የገለጸው ሣልሳይ ወያነ ትግራይ፣ በትግራይ ጠንካራ መንግሥት ለመመሥረት እታገላለሁ የሚል አቋም ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ታውቋል። ሣልሳይ ወያነ ትግራይ ሚያዝያ 14/2011 ባወጣው የመጀመርያ መግለጫው፣ “የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት አድርጎታል” የሚለውን ትግልና የተጎናፀፈውን ድል ይጠቅሳል።

ፓርቲው፣ በ1930ዎቹ አጋማሽ በትግራይ የነበረው ‘ቀዳማይ ወያነ’ በሚል የሚታወቀው፥ አርሶ አደሮች በዐፄው ስርዓት ላይ ያደረጉት ተቃውሞ፣ እንዲሁም ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በትግራይ በሕወሓትና ሌሎች ያልተደራጁ እንቅስቃሴዎች ተጋድሎ ተቀጥያ መሆኑን ያወሳል።

ሣልሳይ ወያነ የፖለቲካ ድርጅት በሒደት የተፈጠሩ የፖለቲካ ችግሮችን በመጥቀስ “ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ የግድ ያስፈልጋል” ብሎ እንደሚያምን ኀይሉ ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል። በዋናነትም በትግራይ ክልል ትኩረት ያደረገ ፖለቲካል ኢኮኖሚን መርሕ አድርገው ይንቀሳቀሳሉ። በማኅበራዊ ጉዳይም ትምህርትን መሠረታዊና ቁልፍ የመፍትሔ አቅጣጫ አድርጎ እንደሚሠራና ትምህርትን በፍትሐዊነት ተደራሽ የማድረግ ዕቅድም እንዳለው ያወሳሉ።

ከ“ሣልሳይ ወያነ ትግራይ” ምሥረታ በኋላ፣ በሳምንታት ልዩነት ብቅ ያለው ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)፣ በቀድሞ የዓረና አመራሮችና አባላት፣ ምሁራን፣ እንዲሁም ሌሎች የትግራይ ተወላጆች የተመሠረተ መሆኑ ተነግሯል። ትግራይ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆንዋን የሚገልጸው የፖለቲካ ድርጅቱ፣ ከዚህ በመነሳት ሁሉን ዐቀፍ ለውጥ የሚፈጥር የድርጅት ስትራቴጂ በመያዝ ለመንቀሳቀስ ወደ ፖለቲካ ትግሉ መግባቱን የፓርቲው መሥራች መካከል አንዱ የሆኑት ኪዳኔ የማነ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል። “ባይቶና” ማለት የውስጥ ዴሞክራሲ ማለት እንደሆነም ይናገራሉ።

“ታላቅዋን ትግራይ በተባበረ የተጋሩ ትግል እንገነባለን!” በሚል ወደ መድረክ የመጣው ባይቶና፥ ኢትዮጵያ በከባድ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ እየተናጠች እንደሆነ ይጠቅሳል። በዚህ ሒደት በርካታ ምስቅልቅሎች የተከሰቱ ሲሆን፣ ገሚሶቹ መልካም ገጽታ ያላቸው፣ የተቀሩትና አብዛኞቹ ደግሞ በአገራችን ታሪክ አዲስ አሉታዊ ገጽታ እየፈጠሩ ኢትዮጵያ ወደማትወጣው ጥልቅ አዘቅት ይዘዋት እየነጎዱ መሆኑን ኪዳኔ አስታውቀዋል። በሕወሓት ሥምና ሰበብ በትግራይ ተወላጆች ላይ ሲደርስ የቆየና እየደረሰ ያለው ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጦርነት፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ መገለልና መድልዖ ግምባር ቀደም የፖለቲካው አዘቅቶች መሆናቸውን የገለጹት የባይቶና መሥራች አባል ኪዳኔ፥ “እነዚህ ችግሮች እየከፉ ከመሔዳቸው በፊት ለትግራይ ሕዝብ ልንቆምለት መጥተናል” ብለዋል።

የኢሕአዴግ አመራር በውስጥ የፖለቲካ ውሳኔ መሠረት የትግራይን ሕዝብ የማግለልና የማጥቃት ሥራ ተቋማዊና መደበኛ ሥራው አድርጎ መሔድ ከጀመረ ሰንብቷል የሚሉት ኀይሉ በበኩላቸው፥ የዚህ ማሳያም በኢሕአዴግ ውስጥ ከአግላይነቱ በላይ በጥላቻ የተሰባሰበና ኀይለኛ የሥልጣን ጥማት የተጠናወተው ኀይል በሕዝባችን ላይ የፈጠረው ጠባሳ ታሪክ አይረሳውም ሲሉ ስለ አስከፊነቱ ያወራሉ።

እነዚህ አድልዎ፣ ቂም በቀልና ቀቢፀ ተስፋ የወለዳቸው በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠሩ መንግሥታዊ እርምጃዎችና ውሳኔዎችን ለመቀልበስ ድርጅታቸው ባይቶና ከትግራይ ሕዝብ፣ የትግራይ ሕዝብን ከሚያከብሩ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸውንና ድርጅቶች እንዲሁም ከመላው የዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን አበክሮ በፅናት ለመታገል መምጣቱን ኪዳኔ ያብራራሉ።

በሚያዝያ/2011 መጨረሻ አካባቢ ወደ ፖለቲካ ትግሉ የመቀላቀል ሒደት ላይ እንዳለ የገለጸው ፓርቲው፣ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ በየዘመናቱ ያጋጠሙት ችግሮች፣ ያካሔዳቸውን ትግሎችና ያስመዘገባቸውን ወርቃማ ድሎችን በመዘርዘር፣ የትግራይ ሕዝብ ለኅብረ ብሔራዊ ሐሳብ ዕውቅና የሚሰጥ፣ አገራዊ ግንባታ እንዲኖር የሚፈልግ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ገዢዎች በአንፃሩ፣ ማንነቱንና ክብሩን በመነጠል የአገር ግንባታ ለማካሔድ በመፈለጋቸው የተነሳ፣ የጥቃት ዒላማ መሆኑን፣ መሬቱ በተለያየ ቦታ እንዲቆራረስና ትግርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ወደ ኹለት እንዲከፈል መደረጉን ኀይሉ ያትታል። በፓርቲ ፖለቲካ የመምጣታቸው ምክንያት ይህ መሆኑን በመጠቆም።

በሕወሓት የተመራው የኹለተኛው ወያነ ትግል የትግራይን ሕዝብ በአንድነት ያሰለፈ እንደነበር፣ በዚህም ምክንያት ፋሽስታዊው የደርግ ስርዓትን ብቻ ሳይሆን፣ ጨቋኙን የአሃዳዊ አስተሳሰብ ስርዓትን አብሮ ከሥሩ መንቀሉን፣ ይህን ተከትሎ ደግሞ፣ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያረጋገጠ ሕገ መንግሥት መፅደቁን ሣልሳይ ወያነ ይገልጻል።

የትግራይ ሕዝብ ከድል በኋላ ሥር ነቀል የሆነ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት፣ ጥንታዊ ሥልጣኔውን ለመመለስ፣ ባሕላዊና ኢኮኖሚያዊ አብዮት ለማካሔድ ጉጉትና ፍላጎት የነበረው ቢሆንም፥ “ከደርግ ውድቀት በኋላ በሚያሳዝንና በሚገርም ሁኔታ በትግራይ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ፣ ትግራይ ካላት አቅም ተነስቶ ፕሮግራምና ፖሊሲ ቀርፆ የሚንቀሳቀስና የሚያንቀሳቅስ ብሔራዊ መንግሥትና ድርጅት አላገኘም” የሚል እምነት ያለው ፓርቲው፥ የትግራይ ሕዝብ በፌደራል መንግሥቱ ሳይቀር ጫና እየደረሰበት መሆኑን በመግለጽ፥ የትግራይ ሕዝብ ትግል ወደሌላ ከፍተኛ ምዕራፍ መሸጋገር ሲገባው ተመልሶ ሕልውናን ወደ ማስጠበቅ መውረዱን፣ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደገና ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ኀይሉ ያብራራል።

የትግራይን ሪፐብሊክ መመሥረት
መገንጠልን እንደ ፖለቲካ ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደሉም። ሕወሓትም ቢሆን በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የትግራይ ሪፐብሊክን የመመሥረት ውጥኑን እንደ አጀንዳ ይዞ መነሳቱ ይታወሳል። በቅርቡ ደግሞ አንዳንድ የድርጅቱ ደጋፊዎች በቀድሞ የሕወሓት አመራሮች (ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ) መታሰራቸውና ለእስር መፈለጋቸው ደረሰብን ላሉት ጥቃት አፀፋ መገንጠል አማራጭ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በእርግጥ ሐሳቡ የግለሰቦቹ እንጂ የፓርቲው ወይም የሕዝቡ መሆኑን በዚህ ማወቅ አይቻልም። ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) “ተከባብረን እንኖራለን፣ ወይም ኢትዮጵያ ትበታተናለች” በማለት መናገራቸውም የሚታወስ ነው።

የአዲሶቹን ፓርቲዎች መምጣት ተከትሎና የሚሰጡትን መግለጫዎች አድምጦ፣ “እነዚህ ፓርቲዎች ትግራይን የመገንጠል ዓላማ አላቸው” የሚሉ አስተያየቶችን የሚሰነዝሩ አካላት መበራከታቸውን ተከትሎ አዲስ ማለዳ ጥያቄ ሰንዝራላቸው ነበር። ኪዳኔ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይ፣ “ባይቶና አንድ ሁኑም ተገንጠሉም ብሎ መመሪያ አይሰጥም፤ እንደ አማራጭም አያቀርብም። ነገር ግን ሕዝቡ ራሱ የመወሰን መብት አለው፤ ሕዝቡ የወሰነውን ባይቶና ያከብራል። ሕዝቡ እገነጠላለሁም ይሁን አልገነጠልም ካለ መብት አለው” ብለዋል።

ኀይሌ “እኛ ከኢትዮጵያ የመነጠል ዓላማ አንግበን አይደለም የተነሳነው፤ የትግራይን ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር እንጂ። በቀጠናውም ሆነ በኢትዮጵያ የትግራይ ሕዝብ ጥቅሞች አሉ። ያንን ሊሸከምለት የሚችል ብሔራዊ ድርጅት ያስፈልገዋል ብለን ነው የተነሳነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። “የትግራይ ሕዝብ ጥቅሞች በኢትዮጵያ ውስጥም መከበር ይችላሉ ብለን እናምናለን” በማለት በመገንጠል አስፈላጊነት እንደማያምኑ የሚናገሩት የሣልሳይ ወያነው ኀይለ፥ “የትግራይ ሕዝብ መብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መከበር የማይችሉ ከሆነ ግን የትግራይ ሕዝብ የራሱን ውሳኔ የመወሰን መብት አለው” ሲሉ ይናገራሉ።

ዓረና ከኹለቱም ፓርቲዎች የተለየ አቋም ነው ያለው፤ “እኛ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን፣ የአገር አንድነት ማምጣት እንደሚገባንና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲቆም ሁሉም ሕዝብ እንደ አንድ ሕዝብ በጋራ እንዲታገል መጣር አለብን ነው የምንለው” ሲል መገንጠልን እንደአማራጭ ማቅረብን እንደማይቀበለው ይናገራል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ፣ የኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል ከሚያሳስባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ትብብር በመፍጠር፣ አንድ ላይ መሥራት እንዳለባቸው እንደሚያምኑና በትግራይ አካባቢ ሕዝብን ፖለቲካ ማስተማርና ማደረጃት እንደሚገባ፣ ከምንም በላይ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ እንዳለብን አቅጣጫ አስቀምጠናል ይላሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አንዶም ገብረሚካኤል።

“ይሔ ሕገ መንግሥቱ የሰጠው መብት ነው። ውሳኔው የትግራይ ሕዝብ ነው። መገንጠልም፣ መነጠልም በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጠው ጉዳይ ነው” ሲሉ የአንዶምን ሐሳብ የሚቃወሙት ኀይሌ፣ የትግራይ ሕዝብ መገንጠል ከፈለገ ውሳኔውን እናከብርለታለን። በኢትዮጵያዊነቱ መቀጠል ከፈለገም እናከብርለታለን። የትግራይ ሕዝብ በየትኛውም አገር ጥቅሞቹ ሊከበሩለት ይገባል ነው የምንለው በማለት ከባይቶናው ኪዳኔ ጋር ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ትግራይ የኢትዮጵያ መሠረት ነው ብለን ነው የምናስበው” የሚሉት አንዶም በበኩላቸው፣ ትግራይ ከሚለው ሥም በፊት ኢትዮጵያ ብሎ የትግራይ ሕዝብ እንደሚያምን በማንሳት፣ “ይሔ ሐሳብ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚደርሱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች የተነሳ የመጣ መሆኑንና ተገፋሁ የሚል አካል ይሔን ማንሳቱ የሚገርም ባይሆንም፣ ጊዜያዊ ስሜት መሆኑ ግን አያጠያይቅም” ሲሉ በትግራይ የሚነሱት የመገንጠል ጥያቄዎች ከጥቃትና ከመገፋት የመጣ መሆኑን ያነሳሉ። “የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊ አንድነቱ ፅኑ መሠረት አለው” የሚሉት አንዶም፣ “ወደ መገንጠል ወይም ሌላ አማራጭ የሚሔድ አይደለም። ይሄ ሐሳብ የመከፋት ስሜት መኖሩን የሚጠቁም እንጂ፣ የትግራይ ሕዝብን አቋም የሚገልጽ አይደለም። የእኛም እምነት የኢትዮጵያ አንድነት ነው። አጀንዳችንም የኢትዮጵያን አንድነት ማምጣት ነው” ሲሉ አቋማቸውን ይገልጻሉ።

ሣልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦችም ተመሳሳይ የመብት ጥያቄ አንግበው ይታገሉ ስለ ነበር፥ የትግራይ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማረጋገጥ አልሞ ያካሔደው ትግልና የተጎናፀፈውን ድል መጋራታቸውን በማስታወስ፣ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት የሚያጎናፅፋቸውን ውስጣዊ ነጻነት ያላቸው ክልላዊ መንግሥታትና በጋራ አስተዳደር የሚመራ ፌዴራላዊ መንግሥት ለማቋቋም የሚያስችል ሕገ መንግሥት መፅደቁንና፣ ውስጣዊ ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት በዘላቂነት ለመጠቀም፣ ለማጎልበትና ለመጠበቅ ዋስትና የሚሰጥ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት እና ሕገ መንግሥታዊ አሠራር እንደተቀመጠለት በማውሳት በዛ ሕገ መንግሥታዊ አሠራር መሠረት እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።

“የትግራይ ሕዝብ በመራራ ትግሉ እና መስዋዕትነቱ ያረጋገጣቸው እንደ ሕዝብ ማንነቱ ጠብቆ የመቀጠልና ያለ መቀጠል ወሳኝ የሆኑ ውስጣዊ ሉዓላዊነት፣ ግዛታዊ አንድነት እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶች ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም” የሚለው ኀይሉ፣ “ሣልሳይ ወያነ ትግራይ የትግራይ ሕዝብ በትግሉ ያረጋገጣቸው ዓላማዎች ለመጠበቅና እንዲሁም ቀሪዎቹን ከግብ ለማድረስ በፅናትና በቁርጠኝነት ይታገላል፤ ሕገ መንግሥቱ እና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በማፍረስ ፌደሬሽኑን ለመበተን የሚንቀሳቀሱ ኀይሎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳስባል” ብለዋል።

“አሁን የብሔር ፖለቲካው የበላይነቱን ስለያዘ፣ ለጊዜው ሕዝብን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እየሰበክን ነው መንቀሳቀስ የምንፈልገው” የሚሉት የዓረና ተወካይ ናቸው። አንዶም “አጀንዳው በብሔር ፖለቲካ ውስጥ ከባድ ቢሆንብንም በኢትዮጵያ አንድነት ተስፋ አለን። በሕዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው ችግርም የገዥዎች የአፈና ውጤት ነው ብለን እናምናለን። ይሔ አፈና ሲቆም የሕዝቦች ግንኙነት ይጠናከራል የሚል እምነት አለን፤ ስለዚህ መገንጠል እንደ አማራጭ መቅረብ የለበትም” ይላሉ።

‘ታላቋን ትግራይ’ የመገንባት ጥሪ
“ሣልሳይ ወያነ ትግራይ” የትግራይ ታላቅነት አለ ብሎ እንደሚያምን ኀይሉ ተናግረዋል፤ “ያ ማለት የአክሱማይት ሥልጣኔ ዳግም በክልሉ እንዲመጣ እንፈልጋለን ብለን በመግለጫችንም አስቀምጠናል” ይላሉ። በዘመኑ የአክሱም ሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሱ ማኅበረሰቦችና መንግሥታት መካከል አንዱ እንደነበር የሚያወሱት ኀይሉ፣ ይሄ የልኂቃኖች፣ የመንግሥታቶች፣ የኅብረተሰቡ ድምር ውጤት ነው ብለው እንደሚያምኑና፣ ይሄንን ድምር ውጤት የሚያመጣ አመራር፣ መንግሥት፣ በዘመናችንም ትልቅ ደረጃ የሚደርስ ማኅበረሰብ እንገነባለን ነው እያልን ያለነው ሲሉ ታላቋን ትግራይ ስለመገንባት ያላቸውን ዓላማ ያስረዳሉ።

ኪዳኔ ፓርቲያቸውን ወክለው እንዳወሱን፣ “ታላቋ ትግራይ” ብለው ሲነሱ ብዙ ሰው በተሳሳተ መንገድ እንደሚገነዘበው ገልጸው፣ የመገንጠል ሐሳብ ይዘው፣ ወይም ደግሞ ከሌሎች ሕዝቦችና ክልሎች ትግራይን ከፍ አድርጎ ለማመልከት ሳይሆን፣ ጥንታዊቷን “የአክሱም መንግሥት” ኃያልነት በማስታወስና ያንን ለመመለስ የታሰበ መሆኑን ይናገራሉ። በትግራይ ክልል ይሄንን የሚያሳዩ በርካታ የሥልጣኔ ምልክቶች መኖራቸውን በማስታወስ።

“ታላቋ ትግራይ’ ስንል የግዛት ማስፋፋት አይደለም፤ በአንድ ወቅት ላይ ሕዝቡ ታላቅ ነበር። አሁን ያንን የሚያስታውሰው (ሪቫይዝ) የሚያደርግለት ይፈልጋል። በዚህ መንገድ ነው በቀጣይ የትግራይን ሕዝብ ሁለመና ጥቅም ለማስከበር የምንሠራው” ሲሉም በፓርቲያቸው ዓላማ ውስጥ “ታላቋ ትግራይ” በሚል ስለተቀመጠው ርዕሰ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከኤርትራ ጋር ታሪክን ማደስ
የኹለቱን አገሮች የቅርብ ጊዜውን ቅራኔ ስንመለከት፥ እ.ኤ.አ. ከ1961 እስከ 1991 የኤርትራ የተለያዩ ኀይሎች የነጻነት/የመገንጠል ጦርነት ማካሔድና ይህም ጦርነት በኤርትራ አሸናፊነት መጠናቀቁ፣ ከ1991 እስከ 1997 በኹለቱ ሃገሮች መሃል የኢኮኖሚ ውድድር መፈጠሩና ውጥረት ማምጣቱ፣ ከ1998 እስከ 2000 በኹለቱም ወገን ወደ 500 ሺሕ ሰው ያሳተፈ የድንበር ጦርነት መደረጉ፣ ከ2000 እስከ 2015 ቀጥተኛ ጦርነት ባይኖርም በመቶ ሺሕ የሚገመት ሠራዊት በያንዳንዱ በኩል ጎራ ለይቶ አንዱ አንዱን እንዳይወረው እየተጠባበቀ ይገኝ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በ2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሰጡት ትኩረት የኹለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ከ19 ዓመት በኋላ ዳግመኛ መገናኘት መጀመራቸውና፣ በኹለቱ አገራት መካከልም ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግንኙነት በአዲስ መልክ መጀመሩ የሚታወቅ ነው። ይህንንም ተከትሎ በአንዳንድ ወገኖች ዕይታ “የትግራይንና የኤርትራን ሕዝብ ለመለያየት የሚደረግ ጥረት አለ”። ይህንን ጥረት “ለማክሸፍ” የትግራይ ክልል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ ጀምሯልም ይባላል። አዲስ የመጡትም ፓርቲዎች በኹለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ማኅበራዊና ባሕላዊ ግንኙነት ለማደስ ዕቅድ መያዛቸውን ይናገራሉ።

ባይቶና “በአፍሪካ ቀንድ ለትግርኛ ተናጋሪዎች መቀራረብ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ” ኪዳኔ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። “በሆነ ሰዓት ላይ የኤርትራ ሕዝብና የትግራይ ሕዝብ እንዲለያይ ተደርጓል” የሚሉት ኪዳኔ፣ ይህ የፖለቲካ ሴራ እንደነበር ገልጸው “የኹለቱ ሕዝብ አንድነት ያለውን ጠቀሜታና ሕዝባዊ አንድነት ስለምንረዳ እንደሌሎቹ ፓርቲዎች ወደብ እናመጣለን ከማለታችን በፊት፥ የሕዝቡን አንድነት አስቀድመን ለማምጣት እንሠራለን” ሲሉ በምሥራቅ አፍሪካ የትግርኛ ተናጋሪዎችን የማቀራረብ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ያወሳሉ።

ሣልሳይ በበኩሉ “የኤርትራ ሕዝብ በተለይ ከትግራይ ሕዝብ ጋር በቋንቋ፣ በታሪክ የተሳሰረ ሕዝብ ነው፤ ከትግራይ ሕዝብ ለመነጠልም የሚያስቸግር አንድ ዓይነት ሕዝብ ነው። ለዓመታት የነጻነት ትግል በጋራ አካሒዷል። ነጻ አገር መሥርቷል፤ ይሄንንም እናከብራለን። በዚህ ቀጠና ውስጥ አብረን እስካለን ድረስ ግን እኛም እዛ ጥቅሞች አሉን። እነርሱም እዚህ ጥቅሞች አሏቸው። ስለዚህ ይሄንን አቻችለን፣ አብረን መቀጠል እንችላለን። ቀጠናውን የሰላም፣ የብልፅግናና የመስተጋብሮች ድምር ማድረግ ይቻላል” በሚል የኹለቱን ሕዝቦች መቀራረብ ትኩረት ሰጥቶበት እንደሚሠራ ኀይሌ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
“ቀጠናውን ከማሥፋፋት አንፃር ብዙ መሥራት እንችላለን” የሚሉት ኀይሌ፣ “በተለይ በትግራይና በኤርትራ ሕዝብ መካከል ያለውን ወንድማማችነት ተጠቅመን ኹለታችንም ጥቅማችንን የምናስከብርበትን ሁኔታ መፍጠር ይኖርብናል ብለን እናምናለን” ይላሉ። “በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም፣ በዲፕሎማሲም፣ በጋራ መሠረተ ልማትም ቢሆን ብዙ ነገሮችን አብሮ በማቀድ መሥራት ይቻላል፤ ስለዚህ የኤርትራን ሁኔታ በተለየ ሁኔታ ነው የምናየው” ሲሉም ያክላሉ።

ሕውሓትና አዲሶቹ ፓርቲዎች ምን ለያቸው?
ባይቶና ሚያዝያ 29/2011 የፌደራል መንግሥቱን ባስጠነቀቀበት መግለጫው መዝጊያ ላይ “ዘለኣለማዊ ክብር ለሰማእታት!” የሚል መፈክር ሰፍሮ ይገኛል። “ሣልሳይ ወያነ ትግራይ” በበኩሉ መግለጫውን ሲጨርስ “ዘለኣለማዊ ክብር ለትግራይ ሰማእታት!” የሚል መፈክር ያሰማል።

ኹለቱም ፓርቲዎች የትግራይ ሕዝብ ፋሽስቱን የደርግ ስርዓት ለመገርሰስ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተደራጅቶ በንቃት እየተዋደቀ ተኪ የሌለው አስተዋፅዖ ማበርከቱ የማይታበል ጥሬ ሐቅ ነው በማለት የሕውሓትን የትግል እንቅስቃሴ ይደግፋሉ፤ ያበረታታሉ።

ሕወሓት በኢሕአዴግ የግንባሩ ማዕቀፍ ውስጥ በአሉታም ሆነ በአወንታ የሚወሳ ሥራ ከሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች ጋር አብሮ የድርሻውን በመወጣት ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ አገሪትዋን በኢሕአዴግ መሥመር በመምራት ሒደት ላይ የራሱ ሚና እንደነበረው አሌ የማይባል ሐቅ ነው ሲሉም ይከራከራሉ። ባለፉት 27 ዓመታት ለጠፉትም የኢሕአደግ ጥፋት የራሱ የግንባሩ እንጂ የሕውሓት ብቻ አለመሆኑን አበክረው ሲናገሩም ይደመጣል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡን ኪዳኔ ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር የዓላማ አንድነት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ “ከሁሉም የትግራይ ፓርቲዎች ጋር የሐሳብ ልዩነት አለን፤ ወደ አንድነት ለመምጣት ደግሞ የዓላማ አንድነት ያስፈልጋል፤ ያ ማለት ግን ለክልሉ በጋራ በሚያቆሙን ነገሮች ዙሪያ በጋራ አንቆምም ማለት አይደለም፣ በሚያግባቡን ነገሮች ላይ በጋራ እንሠራለን” ሲሉ በትግራይ ክልል ካሉ ሁሉም ፓርቲዎች የፕሮግራም ልዩነት እንዳላቸው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በፓርቲዎቹና በነርሱ መካከል ያለውን ልዩነት በዝርዝር ለመናገር መጀመሪያ ፓርቲውን ማጠናከርና ጠቅላላ ጉባዔውን መጥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኀይሌ በበኩላቸው “ሣልሳይ ወያነ የፌደራል ስርዓቱን ከሚቀበሉና ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው ከሚሠሩ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ ብንሆንም የአይዲኦሎጂ ልዩነት ስላለን አብሮ መሥራቱ ላይ እንቸገራለን” ብለዋል። “ለምሳሌ ዓረና ሊበራል እንደመሆኑ ከኛ ጋር የርዕዮተ ዓለም ልዩነት አለው” ያሉን ኀይሌ፣ “እኛ የፌደራሉን ሕገ መንግሥት እንደ ቅድመ ሁኔታ እናስቀምጣለን” ብለዋል። ከሕውሓት ጋር መሠረታዊ ልዩነት እንዳላቸው የሚያወሱት ኀይሌ፣ ሕውሓት ለትግራይ ሕዝብ ትኩረት ሰጥቶ፣ አጀንዳ ቀርፆና መሠረተ ልማቶችን ዘርግቶ የሠራው ሥራ አለመኖሩን በመናገር፣ ፓርቲያቸው ከሕዝቡ ጎን ቆሞ እስከዛሬ ድረስ በሕውሓትና በማዕከላዊው መንግሥት የደረሰበትን በደል በማደስ እንደሚሠራም አስረድተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here