የእለት ዜና

የ2013 የ12ኛ ከፍል ተፈታኞች በ2014 ጥቅምት ወር ላይ እንደሚፈተኑ ተገለጸ

Views: 40

አገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ እንዳሳወቀው የ2013 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በ2014 ጥቅምት ላይ ሊሰጥ እቅድ መያዙን አስታውቋል፡፡
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በትግራይ ክልል ካሉ ተማሪዎች ውጪ 620 ሺሕ ተማሪዎች ተመዝግበው ፈተናውን በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ የኤጀንሲው መረጃ ያስረዳል።የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ኤጀንሲው በማንኛውም ሰዓት ፈተናውን መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የኢኮኖሚክስ ትምህርት ባለመሰጠቱ ፈተናው እንደማይሰጥ ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
የ2012፣ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደዚህ ዓመት ተሸጋግሮ ከየካቲት 29 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2/2013 ድረስ በመላው አገሪቱ የተሰጠ ሲሆን፣ ወደ ዩንቨርስቲ መግባት የቻሉ ተማሪዎች ወደየተመደቡባቸው ዩንቨርሲቲዎች በመግባት ላይ መሆናቸውን የኤጀንሲው መረጃ ይጠቁማል።
አገር አቀፍ ፈተናውን ከወሰዱ ከ250 ሺሕ በላይ ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ 55 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ከ350 በላይ አምጥተው ነበር። የዓመቱ ከፍተኛ ውጤትም 669 ሆኖ የተመዘገበበት የ2012 ፈተና ውጤቱ፣ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ 702 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት እንዳመጡ መገለጹ አይዘነጋም።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com