የእለት ዜና

በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውኃ ሃብት የክምችት መጠን ለማወቅ ጥናት መጀመሩ ተገለጸ

Views: 44

በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውኃ ሃብት የክምችት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ጥናት መጀመሩን የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ የከርሰ ምድር ውኃ ሃብት ክምችት መጠንን ለማወቅና ለይቶ የበለጠ ለመጠቀም በሚያስችልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ማካሄዱን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላች፡
በምክክሩ ላይ አማካሪ ኩባንያዎች ወደ ፊት በሚሠሩ ሠራዎች ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ከምርምር ተቋማት፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣኑ እንዳለው፣ ኢትዮጵያ ያላት የከርሰ ምድር ውኃ ሃብት በአግባቡ እየተጠቀመች አይደለም። ውኃ ይገኝባቸዋል ተብለው የተቆፈሩ ቦታዎችም በቂ ውሃ የማይሰጡበት ሁኔታ መፈጠሩን ባለሥልጣኑ ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውኃ ሃብቷን በአግባቡ መጠቀም ያልቻለችው በአግባቡ ጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራ ባለመሠራቱ ነው ተብሏል።
ችግሩን ለመፍታትም የእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ቃል በገባው መሰረትም በአፋር፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በሚገኙ በ53 ወረዳዎች የከርሰ ምድር ውኃ ሃብት ክምችት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ጥናት እንደሚሰራ ተመላክቷል።
ጥናቱ የትኛው አካባቢዎች ቅድሚያ ይሰጣቸው የሚለውን መሰረት በማድረግ በድርቅ የተጎዱና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ያረፈባቸውን በመለየት የሚካሄድ እንደሆነ ተጠቁሟል።
ለዚህም ሦስት አማካሪ ድርጅቶች ተመርጠው ከአንድ ወር በፊት ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመው፣ ጥናቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተረጋገጠ የውኃ ሃብት መኖሩን የሚታይበት መሆኑን ተነግሯል።
በደረቃማ አካባቢዎች ጤና ኬላዎች ተቋቁመው ውኃ ለማግኘት የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ዘበነ፣ ጥናቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት እና ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 17 ነጥብ 95 በመቶ የከርሰ ምድር ውኃ ሃብት መኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ቦታዎቹም በአድአ በቾ፣ አላይደጌ ብሌንስ፣ ቴሩ ጭፍራ፣ ቆቦ ጨፋ፣ ቆቦ ጊራና፣ ራያ፣ ቦረና እና ሽንሌ የመሳሰሉ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የእንግሊዝ መንግሥት 100 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ገንዘብ መድቦ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com